Saturday, 30 April 2016 11:33

የታመመ ብቸኝነት

Written by  ተሾመ ገብረሥላሴ
Rate this item
(17 votes)

     ጐልማሳነቱ ላይመለስ ርቋል፡፡ በጊዜ ፈረስ ሸምጬ ጉልምስናውን ላፍታ ስቤ ሳበቃ “እንካ የዘመን ክፍተቶችህን ሙላ! እንባህን አብስ! የለም አታልቅስ!” አልልው ነገር የቸገረ፡፡
የመከራ ስለት የላላ ልቡን እየበጣ! ፀፀቱ ገደብ ጥሶ፤ ከሟሟው ሽንሽን በእንባ ሲለበለብ… ላየ፣ ለታዘበ፤ ሰው ለሆነ ፍጡር ይኼስ ያምማ። ነጭ ሃጫ ጢሙ ተንጨባሮ፣ በብልዝ ጥርሶቹ ከንፈሩን ነክሶ፣ በቀኖቹ ማምሻ ማዶ ማዶውን እያየ፣ በቀጥቃጣ ድምፁ ‘ሀቅ!‘ ሲል ሆድ ያላውሳል፤ ስሜት ይንጣል፡፡
መንፈሴ ታውኳል፡፡ “አታልቅስ!” ብዬ ምኑን እሰጠዋለሁ? “ለምን አላለስቅ?” ቢለኝ ምን እለዋለሁ? ብቸኝነት መልክ አለው፡፡ ቀለም አለው፡፡ ፅሞና ነው፡፡ ከወፈ-ሰማይ ጋር ሲንጫጫ ከርሞ ከራሱ የተጣጣ፣ ራሱን የሚያዳምጥበት፤ ሌሎችን መስማት የኑሮው ቀንበር የሆነበት ከእስራቱ ተፈትቶ የማያቋርጠው የፈጣሪ ድምፅ ‘ሚሰማበት፡፡ ብቸኝነት አንዳንዴ ጠበል ነው - ተጠምቀው ‘ሚነፁበት፡፡
በብቸኝነት ጥላ ውስጥ ነፋስን፣ ዛፎችን፣ ተራሮችን፣ ደመናትን፣ ዝናባትን፣… ለማድመጥ የሚያስችል አቅም አለ፡፡ በጫጫታ ተሸፍነው የኖሩትን የእውነት ድምፆች አጥርቶ ለመስማት፣ ሰምቶም ለመመለስ አንዳንዴ ብቸኝነት ፍቱን መላ ነው፡፡
ይህ ሽማግሌ ግን በታመመ ብቸኝነት ሲሰቃይ ኖሯል፡፡ የታመመ ብቸኝነት እስር ቤት ነው - ቅጣት፡፡ የእሳት ለበቅ፡፡ የታመመ ብቸኝነት ጫጫታ አለው - የነፍስን ጆሮ ‘ሚገዘግዝ፡፡
በተንጣለለው ቪላ የሰገነት ያህል ከፍ ካለ በረንዳ ላይ ተቀምጦ የግቢውን በር በር ያያል። ለዓመታት በዚህ በር በኩል አልፎ ወደ ቤቱ የዘለቀ የለም፡፡ ዳዋ የበላውን ሰፊ ቅጥር እያየ ሲተክዝ ይውላል፡፡
ስምንት ልጆቾ የት እንዳሉ አያውቅም። ምናልባት የልጅ ልጆችም ሳይኖሩት አይቀርም። ትናንሽ ልጆቹ ይህን መስክ በደስታ አልቦረቁበትም፡፡ አባታችን መጣ ብለው በሃሴት እየዘለሉ በእቅፉ ሊያርፉ አልተራኮቱም፡፡ ይልቁኑ ጂፕ መኪናው አቧሯ እያስነሳች መጥታ አጥር በር ላይ ጥሩንባዋን ስታንጣርር፣ ከአራት እናቶች የሚወለዱ ስምንት ልጆቹ መግቢያ መውጫው ይጠፋቸዋል፡፡ አንዳንዶቹም በቁማቸው ሽንታቸውን  ያዘራሉ፡፡ እርሱ ወደ ሰፈሩ ሲዘልቅ ምድሪቱ ትንቀጠቀጣለች። ከመንገድ ዳር ቆመው የሚያወጉ አረጋውያን በፍርሃት አካባቢውን ይለቅቃሉ፡፡
በሙሉ የጦር ሠራዊት የደንብ ልብስና ትጥቅ የተንቆጠቆጡ አጃቢዎቹ፤ ቦርሳውን ተሸክመው ከፊትና ኋላ ሆነው ወደ ቪላው ያዘልቁታል፡፡ አራቱ ሴት የቤት ሠራተኞቹ ማእድ ሊያቀርቡ በሰልፍ ይራኮታሉ፡፡ ሦስቱ ወንዶች ልጆቹ ቴትሮን ሙሉ ልብስ እንደለበሱ ከተለመደው የመመገቢያ ስፍራቸው ላይ አንገታቸውን ደፍተው ይቀመጣሉ፡፡
በሌሎች ክፍሎች ውስጥ ያሉ ሁለት ሴቶችና ሁለት ወንዶች ልጆቹ አዳፋ እንደለበሱ ከማአድ ቤት አንገታቸውን ደፍተው የተሰጣቸውን በፀጥታ ይመገባሉ፡፡ እነዚህን አራቱን የወለዳቸው ከተለያዩ የቤት ሠራተኞቹ ነው። በቁንጅና መስፈርት እየተመረጡ የሚቀጠሩ የቤት ሠራተኞቹ የሚስትነትም ሚና ነበራቸው። ከአራት የተለያዩ ሚስቶቹ ከሚወለዱ ልጆቹ መካከል አንዷ ለብቻዋ መኝታ ቤቷ ተቀምጣ ከሳሎኑ የሚወረወረውን የመብረቃማ ድምፅ አቅጣጫ ትከታተላለች፡፡ ሴት ስለሆነች ወደ ማእድ ሳሎራ እንድትቀርብ አይፈቀድላትም። ከሳሎን እንዲስተናገዱ የተወሰነባቸው ወንዶችዋ፤ ከአባታቸው ጋር የሚያሳልፉት የምግብ ቆይታ ጊዜ ከሲኣለ እንደሚረዝምባቸው ስለምታውቅ አብራ አለመቀመጧን እንደ እድል ትቆጥረዋለች፡፡
ልጆቹ የት እንዳሉ አያውቅም፡፡ ከልጆቹ መካከል አንዱ አድጐና ጐርምሶ በከተማው ነፍሰ ገዳይና ወንበዴ ሆነ ቢሉት፣ ራሱ ወታደራዊ ፖሊስ አዘምቶና መርቆ ያደፈጠበትን ስፍራ በመክበብ በጥይት አስደብድቦ በማስገደሉ ‘እውነተኛ ሃገር ወዳድ’ ተብሎ በምስጢር ተሸልሟል፡፡
ዛሬ በግቢው ፍርሃት የሚያንቀጠቅጠው ፍጡር የለም፡፡ ሁሉም ወጥተው እንደ ጨው ዘር ተበትነዋል፡፡ ምናልባትም በብቸኝነትና በፀፀት የሚንቀጠቀጠው እርሱ ብቻ ነው። በዳዋ ተከባ ሳር በቅሎባት አጥር ጥግር ላይ የተተወችው አረንጓዴ ጂፕ መኪና አስደንጋጭ ጥሩምባዋ ከከሰመ ዓመታት አልፈዋል፡፡
አይጦች ከወለል ሳንቃና ከችፑድ ኮርኒስ ላይ እየፈሰሱ ሲቦርቁ ውለው ሲዳሩ ያነጋሉ፡፡ ከሳሎን የእሳት ማቀጣጠያ ምድጃ ላይ እንደተቀመጠ ዓመታትን ባስቆጠረው የማዕረግ ልብሱ ላይ የአይጦች በጠጥ ተከምሯል፡፡ ዛሬም የገረዶቹና የአጃቢዎቹ የሹክሹክታ ድምፅ በኮርዶሮቹ መካከል ይሰማዋል፡፡ የልጆቹን ትንፋሽ ሲሰማ ጆሮውን ሊቀስር ይዳዳዋል፡፡ ልጆቹ ነፋሱ ላይ የቀረና ዓመታትን የሚሻገር ትንፋሽ መች ኖሯቸው ያውቃል?
ከብዙ ፍለጋ በኋላ የተጠቀምኩትን ቤት ያገኘሁ ስለመሰለኝ ኩበት ከአመድ ጋር እየቀላቀለች የምትጠፈጥፍ ሴት አግኝቼ፡- “የኮሎኔል በሱፈቃድ ቤት ይሄ የሆን እንዴ?” ስል ጠየቅሁ - በቆርቆሮ የታጠረውን ትልቅ ግቢ እያመለከትኩ፡፡
“አንተ ማነህ?” አለችኝ በጥርጣሬና በጥላቻ ድምፀት፡፡
“ፀሃፊ ነኝ መፅሃፍ እፅፋለሁ፤ በአንዳንድ የታሪክ ጉዳዮች ላናግራቸው ፈልጌ ነበር” አልኳት፡፡
“ወይ ጉድ! ይሄ አረመኔ ዛሬም ጥርሱ አልረገፈም? ያውልህ ክፍት ነው ግፋና ግባ፡፡” አለችኝ” እንዳለችኝም በቀላሉ ገፋ አድርጌ ወደ ውስጥ ዘለቅሁ፡፡ ግቢውን ሰንበሌጥና ሙጃ ውጦታል፡፡ ሽማግሌው ከቪላው በረንዳው አሮጌ ሶፋ ላይ ተቀምጦ ወደኔ አቅጣጫ አትኩሯል፡፡
“አንተ ማነህ?” አለኝ፡፡
“ፀሃፊ ነኝ! ለመፅሐፌ ማጠናከሪያ የሚሆን ታሪክ እንዳሎት ሰው ነግሮኝ ነው” አልኩት፡፡ አልሰማኝም!
“…አብዮት፣ መስከረም፣ አበባ፣ ልደት፣ ምሥራቅ፣…” ስምንቱንም ልጆቹን ጠራቸው፡፡
“አይደለሁም ደራሲ ነኝ” ፈቃደኛ ከሆኑ በአንዳንድ ያለፉ ታሪኮች ላይ ላናግሮት ነበር፡፡”
ስለ እርሱና ጓደኞቹ የጦር ሜዳ ውሎና ገድል እንዲተርክልኝ ቀጠሮ ለመያዝ ነበር አመጣጤ፡፡”
“ተወው እርሱን!” አለኝ አረጋዊው ኮሎኔሉ፡፡
“በብዙ የጦር አውድማዎች አሸንፈናል። የሃገራችንን ዳር ድንበር አስከብረናል፡፡ ጓዶቻችንን ሰውተን ክብራችንን አስጠብቀናል። በሰላሙም ቀን የሃገራችን ተከብራ ስለምትቆይበት ስልት ነድፈናል ግን ሃገር በጦር ስልት አትመራም፡፡ ቤተሰብ በማርሽ አጀብ አይፀናም፡፡”
እስከ እለተ ሞቱ ያፀና ነው፡፡ የታሉ ልጆቹ? የታሉ የልጅ ልጆቹ? የታሉ ጓዶቹ? የሃገሩን ድንበር በእሳት እያጠረ መሃሉን የሚያፈርስ እንደምን ጀግና ይባላል? የገዛ ልጄን አፈረስኩት። አፍርሼው ሳበቃ የጀግኖች ጀግና ተባልኩ። እዚያ ስገነባ እዚህ ሳፈርስ፣ እዚያ ከጠላት ጋር ስተናነቅ፣ እዚህም ከወገን ጋር ስተናነቅ እድሜዬን ፈጀሁ፡፡ በእድሜዬ ማምሻ ብነቃ ሁሉም ነገር መፍረሱን አየሁ፡፡”
“ሰው በፈለግሁ ጊዜ ቀና ብል ሰው አጣሁ። ለካ ሰውም ተክለህ የምታለመልመው ዘርተህ የምታበቅለው በረከት ነው፡፡ ወልዶ ልጅ በማብዛትና የወለዱትን የራስ፣ የራሱ፣ የሃገርና በጠቅላላው የምድሪቱ በማድረግ መካከል ልዩነት አለና? ማለት ይኼም አነጣጥሮ መምታትን ይጠይቃል? ልጆቹ የታሉ? እንደ እቃ እየቀጠቀጥኩ ካባረርኳቸው የልጆቼ እናቶች መካከል አንዷ እንኳን አጠገቤ የለችም። ለምንስ እፈልጋቸዋለሁ? ያልዘራሁትን የፍቅር ዘር እንዲሰጡኝ ለምን እሻለሁ? አየህ ዛሬም ራስ ወዳድ ነኝ፡፡”
አምርሮ አለቀሰ፡፡ የዛሉ እጆቹን ከጭኖቹ መካከል አስገብቶ አቀረቀረ፡፡ እንደ ህፃን ሲንሰቀሰቅ ሳይ እንባዬ መጣ፡፡ ሽማግሌው ለቅሶው ረጅም ቢሆንም እንባው ግን የጠብታ ያህል ነበረች፡፡ ያረጋዊ እንባ ደረቅ ጅማትን እየበጣ፣ የከረሩ ጡንቻዎችን እየሰነጠቀ ስለሚወጣ የሌለ ያህል ነው፡፡ ግን ደግሞ በጣም ያምማል፡፡ ይለበልባል፡፡ ያቃጥላል፡፡ ይፋጃ። ባለቀሰ ቁጥር ምንኛ እየተቃጠለ ስለመሆኑ የሰውነቱ መንቀጥቀጥ ይናገር ነበር፡፡
“…ደራሲው! ልጆቹን ካገኘሃቸው ንገራቸው። ከሰባቱ ልጆቹ ከአራቱ የልጆቹ እናቶች እዚህ ከጐኔ ሆነው በኔ ሲንቀጠቀጡ ከኖሩ ጐረቤቶቼ መካከል አንድ እንኳን ይቅርታ የሚያደርግልኝ ቢኖር በምድር ላይ እኔን መሳይ እድለኛ ፍጡር አይኖርም ማለት ነው፡፡ እባክህ ንገራቸው - አደራ፡፡” ተሰናብቼው ግቢውን ስለቅ ደግሞ ደጋግሞ ይህንኑ ያሳስበኝ ነበር፡
የቅጥረ ግቢውን የብረት በር እየገፋሁ መለስ ብዬ ላፍታ ዓይኖቼን ወደ በረንዳው ወረወርኩ። የተመሰቃቀለ ነጭ ፂሙን እየሞዥቀ ሰማይ ሰማዩን ያያል፡፡ ፊቱ ላይ አንዳች እንግዳ ነገር አየሁ ልበል? - ጠብታ ፈገግታ!
በኮሎኔል በሱፈቃድ (ለገመናቸው ሲባል ስማቸው የተለወጠ)
(ከባልታሰሩ ክንፎች መፅሐፍ የተወሰደ)




Read 5153 times