Saturday, 30 April 2016 11:40

ተናዳፊ ግጥም

Written by 
Rate this item
(3 votes)

እንግዳ ነፍስ አዝላ
የበረከት በላይነህ “ተቃርኖ”
ምርጫና ሂስ ፥ ዕዝራ አብደላ

  በረከት በላይነህ  ከወጣት ብዕሮች በመነጠል በሶስት ዘርፍ -የሬድዮ ድራማ፥ ተውኔትና ሥነግጥም- የግሉን ፈር ቀዷል።  ለረጅም ጊዜ የተደመጠለት የሬድዮ ድራማ አለው፤ እንደ ጸሐፌ ተውኔት በስላቅ፥ በጉንተላ፥ በትዝብት ... ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ በአንድ ተዋናይ ይመደረካል። ደራሲና ሀያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ “እያዩ ፈንገስ”ን ከሮማኒያው ትያትር አነጻጽሮ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጽፏል፤ ያስተዋለው ያወያያል። “የ`እያዩ ፈንገስ` ባለታሪክ እውነታን በጤንነት ከማየት ሆን ብሎ ያፈገፈገ አሽሟጣጭ ነብይ ነው። ሳቅ እንጂ ሰው አልከበበውም። ስለ ጐረቤት ያወራል ጐረቤት የለውም። ስለ ደንበኛ ያወራል ደንበኛ የለውም። ስለ ሙሰኞች ያወራል ሱባኤ የሚገባለት የለውም።
እያዩ የዘመኑ ነብይ ነው። ቀልድ ታጥቋል፥ ቀልድ ሰንቋል። ቀልዱ ከአፎት እንደ ተመዘዘ ሰይፍ በሰው አንገት ላይ ያሽካካል። ከመሳቅ ግን አንታቀብም፤ እየሳቁ መሞት ዕጣ ፈንታችን ሆኖ ይሆን?” ]   
የበረከት ስላቅ በግጥም ሆነ በቃለ-ተውኔት ተራ አይደለም። “`ሁለት ዛፍ በሁለት ሺህ!` ይሉትን መፈክር በእኩል ድምጽ ሰምተው፤/ ጥቂቶች ሲተክሉ፥/ ብዙዎቹ ቆረጡ፥ ሁለት አስቀርተው።” [የመንፈስ ከፍታ፥ ገፅ 84] ክፋትና በጐነት ተማሰሉ። “የለቅሶ ቤት አዝማች” ግጥሙ ይህን እሳቦት ያባብሰዋል።
ገጣሚው መብሰክስክ ሲገባው የሚፈዝ፥ የሌላው እንግልት ሊያሳስበው ሲችል የሚገለፍጥ ተደራሲ አይመቸውም። ለንባብ፥ ለዕይታ ብቻ ሳይሆን ኑሮን በጥሞና አለማፍተልተል ያውከዋል። ይህን በብስለት“መራራቅ”  ባለቅኔን ይሻክረዋል።
ቅዠታም አዳሩን፥
ጨፍጋጋ ውሎውን፥
ዝብርቅርቅ ተስፋውን፥
በዩልኝታ ከፈን እየጠቀለለ፥
 ከጥርሱ ሲጥለው፤
ተቀባይ ይሻማል፥ ሳቅ እየመሰለው። [ገፅ 68]
በፋርስ አንጋፋ ገጣሚያን የመንፈስ ከፍታ የተደመመው በረከት፥ በአማርኛ ለዛ ውስጥ እየደፈቀ ዳግም ፈጠራቸው። የግል ግጥሞቹም ተናዳፊ ናቸው፤ እስቲ በአንዱ ብቻ አብረን እንመሰጥ።
-- ቁጥር 8 --
[ተናዳፊ ሥሩ ነደፈ ነው። ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ሲተረጉሙት የቃሉ ጨረር አይመክንም። (ገጽ 667) “ ንብ ነደፈ፥ በመርዙ ጠዘጠዘ ወጋ ጠቀጠቀ ” ወይም “ በፍቅር ተነደፈ ተያዘ ተቃጠለ ” እንዲሁም“ ባዘቶውን አፍታታ በረበረ ” ..... ግጥም ለጭብጡ፥ ለስንኝ አደራደሩ ወይም ለቋንቋው ምትሀት ምናባችንን ከቧጠጠ ተናዳፊ ነው፤ አንብበነው የምንዘነጋው፥ ጥፍሮቹ የተከረከመው ግን ኢ-ግጥም ነው።]
     ተቃርኖ
ያልሰማችው ጥሪ ያልገባት ብዛቱ
የሽሽቷ ጥጋት ያልገባት `ርቀቱ፤

ከትላንት በሚሸሽ አይደክሜ ሶምሶማ፤
ግለኛ ተስፋዎች ስታሳድድ ከርማ፤

ትዝታን በረሳ ጥድፍድፍ በረራ፤
አጥር-አልባ ድንበር ስታካልል ኖራ።
ድንገት!
`ያ ሳቋ` የሌለበት፥
`ያ ዕንባዋ` የሌለበት፥
`ያ ጐኗ` የሌለበት፥ እንግዳ ነፍስ አዝላ፤
እጆቿን ዘረጋች፥ “ተቀበሉኝ” ብላ።

ዝም አላት መንደሩ፤
አኮረፈ አድባሩ፤
ፊት ነሳት ሀገሩ።

ይብላኝ ለእሷ አይነቶች!
የቤት ጥሪ ንቀው መጓዝ ለወደዱ፤
የመጡ መስሏቸው፥ ርቀው ለሄዱ፤
ለጭፈራ መጥተው፥ ሙሾ ለወረዱ።
------------------------------------
     © በረከት በላይነህ
     [ የመንፈስ ከፍታ፥ ገፅ 86]

ተናጋሪው ስለ አንዲት እንስት እየወቀሳት ያወጋል። ገለልተኛ ታዛቢ ወይም ለገፀባህሪዋ የሚያደላ አይደለም፤ በመከፋት ድምፀት ታፍኗል። በአስራ ስምንት ስንኞች፥ በስድስት አንጓ የተቀረፀው ግጥም ለቆምታ እንጂ ለጥድፊያ ያዳልጣል። ከግጥሙ የፈለቀ የስንኞች ንዝረተ-ዜማ፥ ስሜት እየለጠጠ ያረግባል። ትሸሻለች፥ ተመልሳ ትመጣለች። ያልሰከነ መዋከብ አለ እንጂ፥ የእንስቷ ድምፅ አይሰማም። ተናጋሪው እንደ ጥፋተኛ ይኰንናታል። ግጥሙ እንደ ርዕሱ “ተቃርኖ” የሚፋለሱ ሁነቶች ተርመሰመሱበት። “የመጡ መስሏቸው፥ ርቀው ለሄዱ” ሲል ጉዞው አካላዊ ብቻ ሳይሆን ምኞታዊም ነው። ከሄደችበት ርቀት አቀርቅራ ወይም ደንዛ ብትመለስም ገላዋ እንጂ ልቦናዋና ስሜቷ እንደ ባይተዋር ጉዞ ላይ ናቸው ማለቱ ይሆን? “አጥር-አልባ ድንበር፥ ስታካልል ኖራ” መፋለስን ያባብላል። አካለለ አንድም አዋሰነ ነው፤ አንድም ብዙ ቦታ ዞረ ነው። የሀገር ድንበር ከሆነ በዘብ ይጠበቃል፤ የቤት ከሆነና አጥር-አልባ ከተባለ ማንም ይመላለስበታል። ጥረቷ፥ ልፋቷ የመከነባት መሰለ።
“ያልሰማችው ጥሪ፥ ያልገባት ብዛቱ” ሲል፥ ተናጋሪውን ምን ያክል እንመነው? ገብቷት ከሆነስ? ብዙሃኑን ማድመጥ ታክቷት አንዳች የምትሾልክበት ሰርጥ ስታስስ ከሆነስ? “የሽሽቷ ጥጋት፥ ያልገባት ርቀቱ” ሲል ይህ ስንኝ የነከሰው ምስል አይዳኝም። አልተመቻትም ወይም ርዕይና ህልም ፋታ አልሰጡዋትም። ያልፍልኛል ብላ ኮከብ ተከትላ የምትጓዝ ሣይሆን የትም ይሁን ብቻ ተፈትልካ የሆነ መወሸቅያ ስፍራ ታፈላልጋለች። ያልሰማችው ጥሪ ምንድነው? ከምንስ ነው እንዲህ የምትሸሸው? ተናጋሪው ፍርጥ ያደረገው ምክንያት የለም። አሻሚነት -ambiguity- ብቸኛ አንድ ትርጉም አይደምቅበትም። ለጥቂት ፍካሬዎች የቋጠረው ሰበዞች ይመዘዛሉ። አሻሚነት ግጥምን ጥልቀት ይለግሰዋል። ግጥም ግን ሲያነቡት የማይገባን፥ የማይለዝብ የተድፈነፈነ ከሆነ ይህ ደብዛዛነት -obscurity- ጥበባዊ ጣዕሙን ያቸከዋል፤ ለግጥም ጠንቅ ነው። ይህ የበረከት በላይነህ “ተቃርኖ” አሻሚ ነው ደብዛዛ? ጥሬ ቃላት፥ የነተበ ሀረግ ሆነ ስንኝ ስላልተሰገሰገ ቋንቋው ይመስጣል። የተናጋሪው ስሜት፥ ስለ ሴቷ የሰቀዘው እኩይ ግምትና የእሷ አለመስከን ያልገታው እንቅስቃሴ፥ ለድርጊቶች “ምንም” ምክንያት አለመገለጡ ወደ ደብዛዛነት ያስጐነብሰዋል። የውጭ ሁኔታዋን እየተረከ ተሳለቀባት እንጂ ለማኅበረሰቡ ጀርባዋን አዙራ፥ ጆሮዋን ደፋፍና ሌላ መሸሸጊያ፥ የሩቅ ከለላ ሳትታክት ለምን ትቃብዝ ነበር? ለምንስ “ግለኛ ተስፋዎች” ከኅላዌ ለመንጠቅ መንጠራራቷ አስወቀሳት? ለነዚህ መልስ የለንም።
 ተናጋሪውን እንዴት እንመነው? ከልጅቷ ነፍስ መብከንከን ተፈናጥሮ፥ በአጠቃላይ ጉዳይ ትረካውን ደመደመው። “ይብላኝ ለእሷ አይነቶች!/ የቤት ጥሪ ንቀው፥ መጓዝ ለወደዱ፤”  ሲል ሁሉንም አንድ ቅርጫ ውስጥ አጐራቸው። እነኚህ ሁለት ስንኞች የግብረገብ አቋም ሆነው፥ ለግጥሙ ሰንኮፍ አክለው የግለሰቧን ማኅበራዊ እንግልት አድበሰበሱት።
እንስቷ ማኅበረሰቡን መምሰል በነሱ መመራት ያልፈቀደች ናት። የ Ionesco “አውራሪስ” ተውኔትን ታስታውሰኛለች። ለዕውነታዊ ትያትር ብቻ ይታደም የነበረን ተደራሲ፥ ከእሳቦት ይልቅ ወደ ህልም ወደ ታህተ-ንቃት subconcious ሰዋዊ ቅዠት እንዲመጣ ካለማመዱት ጸሐፍተ ተውኔት አንዱ ፈረንሳዊ Ionesco ነበር። የአንድ መለስተኛ ከተማ ነዋሪዎች ተራ በተራ ወደ አውራሪስ ይለወጣሉ። አብይ ገፀባህሪ ብቻ ነው አልታዘዝ ብሎ ሰው ሆኖ የቀረው። ለማኅበረሰቡ ጥያቄ አልገዛ ብሎ ከጀማው ያፈነግጣል። ብቻውን ስለቀረ፥ ኅላዌውን መጠራጠር ጀመረ -- ቋንቋውን፥ ሰው መምሰሉን፥ አእምሮውን ጭምር። የ“ተቃርኖ” እንስት እንደ ግለሰብ ስለአፈነገጠች፥ ለመንደሩ ነዋሪ ጥሪ፥ እምነትና ፍላጐት አልዳኝ ማለቷ ተናጋሪውን ኮሰኮሰው። ልክ በአንድ ወቅት ያፈቅራት የነበር፥ የግል ንብረቱ እንድትሆን መረቡን ቢዘረጋላትም ሾልካ ያመለጠች ይመስል ቂም ቋጠረ። ችላ ብላው ሌላ ፍለጋ መቃተቷ የጐዳው ተናጋሪ፥ የቆሰለ ማንአህሎኝነት ለማስታገስ አበሻቀጣት እንጂ ገጣሚው እቺን እንስት ሲቀርፃት ረቀቀ። ወንበር ላይ ተኮፍሳ ከመማቀቅ፥ ለስሜቷ ለህልሟ ተስፋን ለማባበል ሸፈተች፥ ተጓዘች። ከመንደሯ ውጭ ከራርማ ተመለሰች።
ድንገት!
`ያ ሳቋ` የሌለበት፥
`ያ ዕንባዋ` የሌለበት፥
`ያ ጐኗ` የሌለበት፥ እንግዳ ነፍስ አዝላ፤
እጆቿን ዘረጋች፥ “ተቀበሉኝ” ብላ።

ዝም አላት መንደሩ፤
አኮረፈ አድባሩ፤
ፊት ነሳት ሀገሩ።
እጅጉን ተለውጣ ተመለሰች። እንደ ማንም ትስቅ፥ ታለቅስ የነበረች ጭምት ብቸኛ (ያለ ጐኗ?) ሆና ዘመድ፥ መንደሬ ብላ ተንደረደረች። እጆቿን ብትዘረጋም፥ ገላመጧት እንጂ አላቀፏትም፤ አሁንም እንደ አቄሙ፥ እንደ አኮረፉ ናቸው። እመጫት ሆና ጨቅላ አዝላ ተመልሳለች የሚያሰኝ አንድምታ ቢኖርም፥ በአራስ በማይድህ ህፃን ወግ አጥባቂው ባህል አይጨክንም። ይልቅ ያለ ሳቋ፥ እንባዋና ጐኗ “እንግዳ ነፍስ አዝላ” ሲል ስለ ማንነቷ ነው። የሆነ የርዕይ መነጠቅ፥ ሽንፈት የመሰለ ገፅታ፥ ይህን ነፍሷን አዝላ አስጠጉኝ ያሰኛት ጉጉት አንድምታው ያደናግዛል። ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ለደበበ የተቀኘው ግጥም ይወክላታል።
አንተን በእኔ ውስጥ አየሁት፤
ዘመንን አኩርፎ፥
በራፉን ቆልፎ፥
ካንዲት ቀሪ ወዳጁ፥ ከነፍሱ ተቃቅፎ።
[እውነት ማለት፥ ገፅ iv]
በረከት በላይነህ “ተቃርኖ” ሲል የእንስቷ የተፋለሰ ድርጊትን ለመግለፅ ያኮማተረው ርዕስ አይደለም።
 ግለሰቧ የተወሳሰበች ፍጡር ብትሆንም ተናጋሪው ሊገነዘባት አልቻለም። ገጣሚው የነዘረው በገፀባህሪዋና በተናጋሪው መካከል በተሰነጠቀ ተቃርኖ ነው።
 እንደ Frued አባባል “Neurosis is the inability to tolerate ambiguity” የሰውን አሻሚ ባህሪያት፥ የግለሰብን ውስብስብነት መታገስ አለመቻል ማለት የሚደብት የአዕምሮ በሽታ ነው እንደማለት። ይህ ኑሮሲስ ተናጋሪ ነው ያመፀች፥ ከመንደሯ ውጭ ከራርማ፥ ተስፋን ከየጥሻው ስር ስትቃርም ተግታ፥ ድንገት ስትጨምት በረገገ። እሱ ለገፈተራት፥ እሱ ለገረመማት መንደር፥ ሀገርና ታቦት እሱን እንዳገዙት ቆጠረው። እምብዛም በአማርኛ ሥነግጥም ያልተለመደ ተራኪና ገፀባህሪ የተገፈታተሩበት ግጥም ነው በረከት በላይነህ ያስነበበን። በረከት ይህን “የምኞት ቅኔ” ይለዋል።
ከሰኞ እስከ እሁድ፥
ከመስከረም ጷጉሜ፤
የትኛው ነው ኑሮ?
የትኛው ነው ዕድሜ?
[ገፅ 83]
 ግራ ቀኝ ገላምጣ ድባቡ ሲጨፈግግባት፥ ለኑሮ ይሁን ለፍቅር ጉዳይ ያመፀች እንስት ልንስገበገብላት ይገባል። ግን ነገረኛ ሰው አለ፡፡ ጐረቤትና መንደርተኛ አይንሽ ላፈር እንዲሏት የሚቀሰቅስ፤ ይህ ተቃርኖ የኅላዊ አንኳር ጠባይ ነው።                * * *


Read 4428 times