Saturday, 30 April 2016 11:24

የፋሲካ እንግዳ - ድምፃዊ አብዱ ኪያር “ነፍሴ ሁሌም ኢትዮጵያ ናት”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

“መርካቶ ሰፈሬ”፣ “ፍቅር በአማርኛ” እና “ምነው ሸዋ” በተሰኙት ቀደምት ሦስት አልበሞቹ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፏል፡፡ በቅርቡ ያወጣው
“ጥቁር አንበሳ” የተሰኘ አልበምም በአድማጭ ዘንድ ተወዳጅነትን አግኝቶለታል፡፡ ላለፉት 8 ዓመታት ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገው ድምጻዊ አብዱ
ኪያር፤ባለፈው ቅዳሜ አዲስ አበባ ሲገባ ያልጠበቀው ደማቅ አቀባበል እንደተደረገለት ተናግሯል፡፡ ድምጻዊው የፊታችን ሐሙስ ሚያዚያ 27
በአርበኞች ቀን በዓል፣“ጥቁር አንበሳ” በተሰኘ አልበሙ የተሰየመ የሙዚቃ ኮንሰርት በላፍቶ ሞል እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡ አብዱ ኪያር አቀንቃኝ
ብቻ አይደለም፡፡ የግጥምና ዜማ ደራሲ ነው፡፡ ጨዋታ አዋቂ ነው፡፡ ኮሜዲያን ነው፡፡ አዝናኝ ነው፡፡ የአገራችን ዝነኛ ድምጻውያንን እያስመሰለ ሲዘፍን
አጃኢብ ያሰኛል፡፡ ቁምነገረኛም ነው - ድምጻዊው፡፡ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ባለፈው ረቡዕ ተገናኝተው በስፋት አውግተዋል፡፡
ስለ ልጅነቱ---ስለ መርካቶ---ስለ አራድነት---ስለ አይቲ ባለሙያነቱ----ስለሚወዳት ባለቤቱ (የልጅነት ፍቅረኛው) ---- ያልተጫወቱት የለም፡፡
የዓውዳመት ጣፋጭ ወግ እነሆ፡-

    በዘፈኖችህ የምታነሳቸው ሀሳቦችና የምትዳስሳቸው ማህበራዊ ጉዳዮች ሲታዩ እዚሁ አገርህ ውስጥ የምትኖር እንጂ ውጭ እየኖርክ የምትዘፍናቸው አይመስሉም -----
ወይ ጉድ! እኔ እኮ ከልጅነቴ ጀምሮ በስደት ነው ያሳለፍኩት፡፡ ሳዑዲ አረቢያ የሄድኩት በ1990 ዓ.ም ነው፡፡ ሆኖም አካሌ ውጭ ቢሆንም መንፈሴ አገሬ ውስጥ ነው ያለው፡፡ በየጊዜው ከጓደኞቼ ጋር እየተደዋወልኩ፣ “እስኪ ፉገራ ጣል አድርጉ----ምን አዲስ ነገር አለ?” እያልኩ እያንዳንዱን ነገር የሚሆነውን የሚደረገውን ኢትዮጵያ ከሚኖሩት በላይ አውቃለሁ፡፡ በሌላ በኩል አገር ቤት ስትኖሪ አጠገብሽ ለሚከሰቱት፣ አይንሽ ስር ለሚደረጉት ነገሮች ትኩረት ሳትሰጪ ያልፍሻል፤ውጪ ስትሆኚ አገርሽ ስለሚናፍቅሽ እያንዳንዷን ነገር በትኩረት ትከታተያለሽ፤ስለዚህ እኔ ሁሌም ነፍሴ አዲስ አበባ ናት፡፡
እኔ ጥያቄውን ያነሳሁት አንዳንድ የኪነ - ጥበብ ሰዎች፣ የወግ ፀሐፊዎችና መሰል የኪነ - ጥበብ ሰዎች ከአገር ሲርቁ ያ ተወዳጅነታቸውና ተቀባይነታቸው ቀንሶ ስለማየው ነው …
እንግዲህ እኔ እንደዚያ ያልሆንኩበትን ምክንያት ተናግሬያለሁ፤እየበሰልኩና እድሜዬ እየጨመረ ሲመጣ በይበልጥ እየተሳብኩ የመጣሁት ወደ መሰረቴ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሁሉም ሰው አገሩ ውስጥ ቢኖር ደስ ይለዋል፤የተለያዩ ምክንያቶች ግን በዚያው ያስቀሩታል፡፡ አልያም በጣም እንዲዘገይ ያደርጉታል፡፡ ነገሮች በምንፈልገው አቅጣጫ ሳይሄዱ ሲቀሩ እዚያው እንቀራለን እንጂ ሁሉም አገሩ መኖር ጠልቶ አይደለም፡፡ “በወረቀት የሰው በደም ያንቺ ናቸው” ማለት ይሄው ነው፡፡
መርካቶ ሰባተኛ ተወልደህ እንደማደግህ የመርካቶን ጉራንጉር ሁሉ ታውቀዋለህ ብዬ እገምታለሁ፡፡ እስኪ ስለዚያ ሰፈር አስተዳደግህ አውጋኝ…
የቤታችን የመጨረሻ ልጅ እንደመሆኔ ምንም ነገር ሲፈለግ እኔ ነኝ የምጠራው፡፡ አብዱ ይላሉ፤ ሮጬ ሄጄ እገዛለሁ፤ቤት ውስጥ ምንም ሲያስፈልግ ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት መርካቶን ከጥግ እስከ ጥግ አውቃታለሁ፡፡
ታስታውሳለህ --- ምን ምን እንድትገዛ ነበር የምትላከው?
ምን የማልገዛው ነገር አለ! እኔ ተልኬ የምገዛቸውን ነገሮች አንዳንዶቹን አንቺ ራስሽ አታውቂያቸውም፡፡ ሰባራ እንቁላል፣ ዶሮ፣ ለእማዬ እንሾሽላ፣ ለእኛ ስኳር ድንች፣ ከበቆሎ በረንዳ በቆሎ እገዛለሁ፡፡ እነዚህን ሁሉ ገዝቼ ሽርፍራፊ ሳንቲም ከተረፈ ለራሴ ሸንኮራ አስቆርጬ ወደ ቤቴ እሄዳለሁ፡፡ ብቻ ምንም ያልገዛሁት ነገር የለም፡፡ ያልተላኩት ነገር የለም፡፡
ሌሎቹስ እሺ----ሰባራ እንቁላሉ ምንድን ነው?
ሰፈር ኳስ እንጫወታለን፡፡ ስንጫወት ከጤነኛ እንቁላሎች መሀል ሰባራ እንቁላል ይገኛል፡፡ ይህ እንግዲህ እንቁላሉ እርስ በእርስ ሲጋጭ የሚሰበር ነው፡፡ እነዚህ እንቁላሎች አይሸጡም አይደለ፡፡ ታዲያ እኛ እነሱን በርካሽ እንገዛና ከኳስ ጨዋታ በኋላ ሰብሰብ ብለን መብላት ያስደስተን ነበር፡፡ እናንተ ይቺን ይቺን አታውቋትም አይደል?
ብዙ ጊዜ አብዱ ኪያር “የአራዳ ልጅ ነው” ሲባል እሰማለሁ፡፡ ለአራድነትህ የሚጠቀሰው ደግሞ የመርካቶ ልጅነትህን ነው፡፡ መርካቶና የአራዳ ልጅነት ምንና ምን ናቸው?
እንዳልሺው ይሄ ነገር እንደ ታይትል ነው የተሰጠኝ፡፡ ሁሉም ሰው አብዱኪያር ይልና የአራዳ ልጅ ይላል፡፡ እንደሚመስለኝ እኔ ሁሉንም ነገር ቀለል አድርጌ የማየት ነገር አለኝ፤ምንም ጭንቀት ይምጣ ምንም ችግር ይግጠመኝ እቀልዳለሁ፤ እጫወታለሁ፤ምናልባት ይሄ ነፃ መሆኔ ይመስለኛል የአራዳ ልጅ የሚለውን ስም ያሸለመኝ፡፡ እኛ ሰፈር አጠቃላይ መርካቶ ማለት ይቻላል----ነጋዴው ሲከስር ይቀልዳል፤ያለበለዚያ ማበድና መጥፎ ነገር ውስጥ መግባት፣ ኑሮን መጥላት ይመጣል፡፡ እኛ ሰፈር ደግሞ መውደቅ፣ መክሰርና መፎረሽ የተለመደ የህይወት ሂደት ነው፡፡ ታዲያ የመርካቶ ሰው እነዚህን ከባባድ ችግሮች የሚያልፍበት መንገድ እንደ ሌላው አካባቢ አይደለም፡፡ ወንድ ልጅ ባካችሁ ጉድ ሆኛለሁ ይላል፤ለጓደኞቹ፡፡ እነሱም ተሰብስበው ከችግሩ ቀና ያደርጉታል፡፡ ይሄ የተለመደ ነው፡፡ እየተፎጋገርንና እየተጋገዝን ነው ያደግነው፡፡ ይሄ አስተዳዳጌ ሁሉንም ነገር ቀለልና ፈታ አድርጌ እንዳይ አድርጐኛል፡፡ ይሄ ይመስለኛል አራዳነትንና መርካቶን የሚያገናኛቸው፡፡
ለአንተ ግን የአራዳ ትክክለኛ ትርጉሙ ምንድን ነው?
ይሄውልሽ፤ “የድንጋይ ልጅ ቀረ ድሮ፣ የአራዳ ልጅ በርታ ዘንድሮ” የሚል ዘፈን አለኝ፡፡ ድሮ “መገን ያራዳ ልጅ እንድንጋይ ኳሱ፣ ከመቼው ተጮኸ ከመቼው ደረሱ” ይባል ነበር፡፡ አሁን ሁለት ነገር አለ፡፡ አራዳነት የሚገለጽበት ዘመን ሲለያይም አራዳነት ይለያያል ማለት ነው፡፡ እነ ድንጋይ ኳሱ ወደ ጠብና ድብድብ የሚሄድ ነው፡፡ እነ ድንጋይ ኳሱ ከረንቡላም ሊሆን ይችላል፤ የሆነ ዘመን ላይ እንደዛ ነበር፡፡ በአሁን ዘመን አራዳ ራሱን በደንብ ያወቀ፣ ከሰዎች ጋር በደንብ የሚግባባ፣እውቀት ለሚባለው ነገር ሁሉን የከፈተ፣ ትሁት መሆን የቻለ፣ ነገሮችን ቀለል አድርጐ ወደ ጉዳዩ የሚሄድን ሰው ነው እኔ አራዳ የምለው፡፡ ለእኔ ትክክለኛ አራዳ ይሄ ነው፡፡
ከድምጽ ባሻገር የግጥምና ዜማ ደራሲ ነህ፡፡ በአራቱም አልበሞችህ ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ጀግንነታችን፣ ብቻ በአጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያዊነት ጠንከር ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን ያለፍርሃት ታነሳለህ፣በዚህም ተቀባይነት አግኝተሀል፡፡ ድፍረቱና ጥንካሬው ከምን የመጣ ነው?
እውነት ለመናገር እኔ ይሄ ዘፈን ወይም አልበም ይሸጣል ወይም ገበያ ያመጣል ብዬ ሰርቼ አላውቅም፡፡ እንደሱ እንዴት እንደሚሰራም አላውቅም፡፡ እኔ ነፍሴ ደስ ያላትን፣ ሀሴት ያደረግኩበትን ነገር እስከ መጨረሻው እለፋበትና የልቤን ተናግሮልኛል ብዬ ሳስብ፣ ስቱዲዮ ሄጄ እቀረፃለሁ፡፡ ይሄን ከሰራሁ በኋላ እከሌ ይወድልኝ ይሆን እከሌን ያስቀይመው ይሆን ብዬ ተጨንቄ አላውቅም፡፡ ነፍሴን ያስደሰተውን እሰራለሁ፤ አለቀ፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ሰዎች ለዘፈኑ ወይም ላስተላለፍኩት መልዕክት የተለያየ ትርጉም ይሰጡታል፡፡ ብዙ ጊዜ አርቲስቶች በምንሰራው ስራ ለትርጉም ክፍት እንሆናለን ማለት ነው፡፡ ክፍተቱ ለመተቸትም ለመሞገስም ለመጠቃትም የተጋለጠ ነው፤ጠባቂም የለውም፡፡ የሆነ ሆኖ አሁንም እኔ የምሰራው ነፍሴን ያስደሰተውን ነው፡፡ ከስራው በኋላ የሚሰጠውን ትርጉም ለመስማት ጊዜ የለኝም፡፡ እኔ ደስ ያለኝን የረካሁበትን ሰርቼ፣ ከዚያ በኋላ የመጣውን መቀበል ነው፡፡ ሁሉም ሰው ቢረዳኝ ደስ ይለኛል፤ካልሆነም የሚመጣውን መቀበል ግዴታዬ ነው፡፡ አንድ ዘፈን አራት ወይም አምስት ደቂቃ ርዝማኔ ነው ያለው፤በነዚህ ደቂቃዎች ውስጥ የአንድን ሰው ጆሮ ተውሼ መልዕክቴን ማስተላለፍ ነው የምፈልገው፡፡ ይህቺ ሰዓት እንዳታመልጠኝ አሪፍ ሃሳብ ለመስራት ጥረት አደርጋለሁ፤አለቀ፡፡
“መርካቶ ሰፈሬ” አልበምህን እስክትሰራ ድረስ አረብ አገር ነበር የኖርከው፡፡ እንዴት ወደ አሜሪካ ሄድክ?
ያኔ ጓደኛዬ የነበረችው የአሁኗ ሚስቴ የልጆቼ እናት፣ እኔ ወደ አረብ አገር ስሄድ እሷ ወደ አሜሪካ ነበር የሄደችው፡፡ በእሷ ምክንያት ነው ወደ አሜሪካ የሄድኩት፡
የልጅነት ጓደኛህን አግብተህ ለዚህ በመብቃትህ ብዙዎች ይደነቃሉ እስኪ ስለ ፍቅራችሁ አጫውተኝ?
እኔ “ፈንድቼ” ሴት ለመሳም ስደርስ፣ መጀመሪያ የሳምኳት ሴት የአሁኗ ሚስቴ ናት፡፡ እንዴት ጐበዝ ሴት መሰለችሽ? በጣም ነው የምወዳት፡፡ ከፍታውንም ዝቅታውንም በፍቅር አልፈን፣ ሁለት ልጆች ወልደን አብረን በሰላም እየኖርን ነው፡፡ እህቴ የልጅነቴ እንዴት ነሽ (በድምፁ እያንጐራጐረ) የሚለው ዘፈኔ የተዘፈነው ለእሷ ነው፡፡ ሁለታችንም እድለኞች ነን፤ደስተኞች ነን፡፡ በሙያዋም ጐበዝ ነርስ ነች፡፡
ምናልባት ከ10 ዓመት በፊት ይመስለኛል፣በዚሁ ጋዜጣ ላይ “ኢንፎርሜሽን ውበት ነው” ስትል ተናግረሃል፡፡ ኢንፎርሜሽንና ውበት ምን ያገናኘዋል?
እኔ በወቅቱ ይህን የተናገርኩት ጋዜጠኛው፤“ከውጭ የሚመጡ ሰዎች አዲስ አበባ ውስጥ ቆንጆ በዝቷል ይላሉ፤አንተስ ምን ትላለህ?” ብሎ ጠየቀኝና ትንሽ ገረመኝ፡፡ ከዚያ ከላይ የገለጽሽውን ነገር ተናገርኩኝ፡፡ ኢንፎርሜሽንና ውበት ምን ያገናኘዋል ያልሽው አሪፍ ጥያቄ ነው፡፡ በእኔ እምነት አንድም አስጠሊታ የሚባል ሰው የለም፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሴት አስቀያሚ ተብላ ሞራሏ ወድቆ ይሆናል፤እናም በአጋጣሚ በአንድ የውበት ሳሎን አካባቢ ስታልፍ #ነይ ነይ፤ይሄ የተሰራሽው የጸጉር ስታይል ከአንቺ ፊት ጋር አይሄድም፤ አለባበስሽም እንዲህ መሆን የለበትም” ይሉና ወደሚስማማት ነገር ይመልሷታል፡፡ የፀጉሯን ስታይል ይቀይሩና እንድታምር ያደርጓታል፡፡ ያኔ በራስ መተማመኗ ይጨምራል፡፡ ይህ የመጣው ከኢንፎርሜሽን ነው፡፡ የሚያምርባት ሲነገራት፣ እንዴት ማማር እንዳለባት መረጃ ስታገኝ በቀላሉ ትቆነጃለች ማለት ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ የፊት ውበት አጠባበቅ (facial) የሚባለው ነገር በየአካባቢው ተለምዷል:: እኛ  ድሮ የምናውቀው ከሀረሪ የሚመጡት አደሬዎች ፊታቸውን አቦካዶ ቀሲል ምናምን ይቀባሉ፡፡ እነሱ በነበሩበት ደረጃ ስለ ፊት ውበት አጠባበቅ መረጃ ስላገኙ፣ በአቦካዶ መዋብ ችለዋል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ኢንፎርሜሽን ውበት ነው ያልኩት፡፡
ያንተ ሃሳብ “አስቀያሚ ሴት የለችም፤እንዴት እንደምትዋብ የማታውቅ እንጂ” ከሚለው አባባል ጋር ይመጣጠናል ወይም ይቀራረባል ማለት ይቻላል?
ሙሉ በሙሉ ይመጣጠናል እንጂ፡፡ የቀሲሉንና የአቦካዶውን ነገርኩሽ፡፡ አቦካዶ ፊት እንደሚያሳምር ሌላው ሰው ስለማያውቅ አይጠቀመውም፡፡ የሀረሪ ሴቶች ግን መረጃ ስለነበራቸው ይዋቡ ነበር፡፡ አባባሉ ላይ እኮ “የማታውቅ እንጂ” የሚል ቃል አለ፤በቃ ይሄው ነው ዋናው ሃሳብ፡፡ ሁሉም ሰው ስለ ሁሉም ነገር መረጃ ሲኖረው፣ ሲያውቅ ያምራል፡፡ ይሄው ነው፡፡ ሳታውቂ ታምሪያለሽ፣ ስታውቂ ሰው ታከብሪያለሽ፣ በጣም ስታውቂ ትሁት ትሆኛለሽ፤ ለሰዎች ክብርና ቦታ ትሰጫለሽ፡፡ እስኪ አስቢው፤እነዚህን የሚተገብሩ ሰዎች አያምሩም? ውብ አይደሉም? ማወቅ በጣም ደስ ይላል፡፡
ማወቅ ዕውቀት---ጥሩ ርዕስ አነሳህ፡፡ አሜሪካ ከሄድክ በኋላ ከሙያህ ውጭ የIT ትምህርት በመማር ዲግሪህን አግኝተሀል፡፡ ከሙዚቃ ወደ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማለት ነው ----
እውነት ነው፡፡ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተመርቄያለሁ፤እየሰራሁበትም ነው፡፡ አሁንም ዌብ ፕሮግራመር ሆኜ ነው የምሰራው፡፡ እንኳንም ተማርኩት እላለሁ፤አንዳንዴ ቴክኖሎጂውን ዝም ብዬ ሳስበው፣ አስማት የሚመስሉ ነገሮች ይታዩኛል፡፡ ኢንተርኔት ላይ ቁጭ ብለሽ ብዙ ስራ በጣም በአጭሩ በቀላሉ ሰርተሽ፣ የምትፈልጊውን አግኝተሽ ትወጫለሽ፡፡ ማወቅ ጥሩ ነው፤ አሁን እየሰራሁበት ነው፤ስርዓቱን ሁሉ ለመልመድ በሰዓቱ እየገባሁ በደንብ ነው የምሰራው፡፡
የIT ተማሪ በነበርክበት ጊዜ ሙዚቃን እርግፍ አድርገህ ትተህ ነበር የሚባለው እውነት ነው?
አንድ መናገር የምፈልገው ነገር ቢኖር የፈለገ ነገር ይቀራል እንጂ ሙዚቃ አይቀርም፡፡ ግን አይቲውን ስማር ማጥናትና ትምህርቱ ላይ ትኩረት ማድረግ ስለነበረብኝ ሙዚቃ አልሰራም ነበር፡፡ የሆነ ሾው ሲኖር ደረስ ብዬ ሰርቼ ወደ ትምህርቴ እመለሳለሁ፡፡ እየተማርኩ ሙዚቃ ያልሰራሁት ሁለቱንም በአንድ ጊዜ መስራት ስለማይቻል ነው፡፡ ሁለቱንም በአንዴ ልስራ ካልሽ ሁለቱንም አሪፍ አድርገሽ አትሰሪያቸውም፡፡ ትምህርቱ በጊዜ የተገደበና የሚያልቅ ስለነበር ነው ሙዚቃ ያልሰራሁት፡፡
ልጆችህ የ9 እና የ8 ዓመት እድሜ ያላቸው ናቸው፡፡ አማርኛ ይናገራሉ? እንዴት ነው ወደ ሙዚቃው ያደላሉ? በስራህ ላይ ምን አይነት ስሜት አላቸው?
እኛ ቤት አንድ የተለመደ ስርዓት አለ፤እነሱም እኔም ቁጭ ብለን እናጠናለን፡፡ ልጆቼ ሲያድጉ የፈለጉትን ሙያ የመምረጥ መብት ቢኖራቸውም መሰረታቸው በትምህርት የታነፀ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ ሙዚቃም ይወዳሉ፤አብረን የምንጫወትበት ጊዜ አለ፡፡ በእኔም ስራዎች ደስ ይላቸዋል፡፡ አማርኛ ያወራሉ ወይ ላልሺው፣ማውራት ያወራሉ ግን ሲያወሩ ይሄ የሞልቃቃነት አይነት አማርኛ ነው የሚሆነው፡፡
እስኪ ምን እንደሚሉ ለምሳሌ በልልኝ ?
አንዳንዴ ግራመሩን እንደ እንግሊዝኛው ይገለባብጡታል፡፡ ለምሳሌ “He is smart” ማለት ሲፈልጉ፣ “እሱ ነው ስማርት” ይላሉ፣ “እሱ ረበሸ በጣም“ ይላሉ፡፡ ነገር ግን በደንብ ይሰሙናል÷ሁሉንም ያውቃሉ፡፡ አፋቸው ላይ የሚከብዳቸው ብዙ ስለማይናገሩት ነው፡፡ አንዴ ክረምት ላይ ባመጣቸው በጣም አሪፍ ይሆናሉ፤ምክንያቱም ከልጆች ጋር ብዙ አማርኛ የማውራት እድል ይኖራቸዋል፡፡
እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አያውቁም?
እስካሁን አልመጡም፡፡ በሚቀጥለው አመት መጥተን እዚህ በደንብ የመቆየት እቅድ አለን፤ እንደ ፈጣሪ ፈቃድ፡፡
የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ አዲስ አበባ ስትገባ ልዩ የአቀባበል ስነስርዓት ተደርጐልህ ነበር፡፡ አቀባበሉን እንዴት አገኘኸው?
የአቀባበሉ ነገር --- እንደዚህ ይሆናል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፡፡ እንደነገርኩሽ የሆነ እድሜ ላይ ስደርስ ብዙ ትኩረት የሰጠሁት ወደ መሰረቴ ሆነና ብዙ ነገር ይቆጨኝ ጀመር፡፡ ከሚቆጩኝ ውስጥ ለምሳሌ የድሮ ትምህርት ቤቴን ሻውልደማን አለመጐብኘቴ አንዱ ነበር፡፡ ያን የመሰለ አቀባበል ከተደረገልኝ በኋላ በቀጥታ ያመራሁት ወደ ት/ቤቴ ሻውልደማ ነው፤ግን ካስተማሩኝ ውስጥ ማግኘት የቻልኩት ሁለት መምህራኖቼን ብቻ ነበር፡፡ ሌሎቹ በሙሉ በህይወት የሉም፡፡ ይሄን ይሄን ሳይ ልቤ ተሰበረ (በጣም እያዘነና አይኑ በእምባ እየተሞላ) እነዚህ ሁለቱም በጣም ተጐሳቁለው ነው ያገኘኋቸው፡፡ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ ሲያገኙኝ የተሰማቸው ስሜት… ያን ቀን ሳለቅስ ነው የዋልኩት፡፡ አንዱ ያገኘሁት መምህሬ ጌታቸው በጣም የሚገርም መምህር ነበር፡፡ የዛሬን አያድርገውና ሒሳብም ህብረተሰብም አስተምሮኛል፡፡ ጌቾ በጣም የሚያምር ሉጫ ፀጉር ነበረው፡፡ የሚያምር መምህር ነበር፡፡
አሁን እሱን ሳየው እንዴት እንዴት እንደሆንኩ ብታይ (አይኑ በእንባ ተሞላ) ይህን አስተማሪዬን ስመለከት፣ እኛ አገር ክብር ለሚገባቸው እንዴት ክብር እንደምንነፍግ ነው የተሰማኝ፡፡
እንዴት ማለት?
በዚህ የግሎባላይዜሽን ዘመን ከውጭው ዓለም ልንወርሳቸውና የእኛ ልናደርጋቸው የሚገቡ ብዙ መልካም ባህሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ አሜሪካኖች ለወታደሮቻቸው ከፍተኛ ክብር ይሰጣሉ፡፡ መንገድ ላይ ሳያገኟቸው እኔንና አገሬን ለመጠበቅ ስለምትከፍሉት መስዋዕትነት እናመሰግናለን በማለት ያከብሯቸዋል፡፡ አስተማሪዎቻቸውንም እንደዛው፡፡ እኛ ይህን በፍፁም እያደረግን እንዳልሆነ በድሮ በአስተማሪዎቼ ነው ያየሁት፡፡
ስለ ኮንሰርቱ ዝግጅት አልነገርከኝም?
ለኮንሰርቱ ዝግጅት የተጀመረው በማናጀሬ ብስራት ስዩም (ቢሲ) በኩል ከሶስት ወር በፊት ነው፡፡ ቢሲ የአቡሸማኔ ኢንተርቴይመንት ማርኬቲንግ ዳይሬክተርና ባለቤት ነው፡፡ የእኔን የኮንስርት ስራ ለማመቻቸትና ለማሳመር ሁሉን ነገሩን ትቶ እዚሁ ኢትዮጵያ ለሶስት ወራት ቆይቷል፡፡ በጣም አመሰግነዋለሁ፡፡ “ጥቁር አንበሳ” አልበሜን እንዳሳመረ ኮንሰርቱንም የተዋጣለት እንደሚያደርግ እምነቴ ነው፡፡ አሁን ከአራቱም አልበሞች ውስጥ “ይሄ ይዘፈን፣ ይሄ ይዘፈን” እየተባለ ዘፈኖች ትንሽ በዝተዋል፤ እንደምንም ብዬ ከሁሉም አልበሞች 20 ያህል ዘፈኖችን ለመዝፈን ከመሀሪ ብራዘርስ ባንድ ጋር ከሰኞ ጀምሮ በተከታታይ ልምምድ እያደረግን እንገኛለን፡፡ መድረክ ላይ ከሀኖክ መሀሪ ጋር አብረን እንጫወታለን፡፡ ከናፈቁኝና ከናፈቅኳቸው አድናቂዎቼ ጋር ጥሩ ጊዜ እናሳልፋለን ብዬ አምናለሁ፡፡
ጥቁር አንበሳ ኮንሰርት ሚያዚያ 27 በአርበኞች ቀን የተደረገው ሆን ተብሎ ነው
አድምጠሽው ከሆነ… “ጥቁር አንበሳ” የተባለው ዘፈን፤ ይህችን አገር አስከብረው ያቆዩልንን ጀግኖች አርበኞች የሚያወድስ ነው፡፡ ኮንሰርቱን በ27 ያደረግነው አርበኞች ፋሺስት ጣልያንን ድል ያደረጉበት 75ኛ ዓመት በዓልን ለማሰብና አርበኞችን ለማመስገን ነው፡፡ ፕሮሞተሮቹ ይህን ሃሳብ ሲያቀርቡ፣ ደስ ብሎኝ ተቀበልኩት፡፡ ሁሉንም የሚያስደስት ይመስለኛል፡፡





Read 5458 times