Saturday, 30 April 2016 11:25

‘ምስኪኗ ሀበሻ’ እና የኑሮ ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

“ትርፍ ፀጉርና ትርፍ ዳሌ እየገዛችሁ … የምበላው አጣሁ”

እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪኗ ሀበሻ አንድዬ ዘንድ ተመልሳ ሄዳለች፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡— መጣሽ! አንቺና ምስኪኑ ሀበሻ ነገር ከያዛችሁ አትለቁም ማለት ነው!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ምን ላድርግ አንድዬ፣ ምን ላድርግ! ግራ ቢገባኝ እኮ ነው፡፡
አንድዬ፡— አንቺ፤ ጸጉር በሦስትና በአራት ቀን እንዲህ ያድግ ጀመር እንዴ!
አንድዬ፡— ወገብሽ ላይ ዘፍ ብሏል እኮ፡፡ አይደለም በምድር ያሉትን እዚህ እኔ’ጋ ያሉትን ሁሉ እንዳታስቀኚብኝ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ በቀደም ያልኩህ እኮ ነው…
አንድዬ፡— ምኑ…እህ ሂዩመን ሄይር ያልሽው?
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አዎ አንድዬ፣ ሂዩመን ሄይር ያልኩህ ይሄ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ አ…አልወፈርኩብህም!
አንድዬ፡— እኔ እኮ በእኔ ሥራ ማነው የገባው ልል ምንም አልቀረኝ፡፡ እውነትም ባለ ዳሌ ሆነሻል፡፡ እሺ፣ አሁን ደግሞ እንዲህ ተጣድፈሽ ገና ጎህ እንኳን በደንብ ሳይለቅ የመጣሽው ደግሞ ምን አድርግ ልትዪኝ ነው፡፡ ብቻ ዳሌ ጨምርልኝ እንዳትዪኝ! (ይስቃል)
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ኧረ ምን በወጣኝ አንድዬ…ምን መሰለህ ከበደኝ፣ ኑሮ በጣም ከበደኝ፡፡
አንድዬ፡— እሱንማ ምስኪኑ ሀበሻ ሲጨቀጨቀኝ አይደል የከረመው፡፡ እኔ እኮ ግራ የገባኝ ቤተ መንግሥት በሚያህል ቤት ውስጥ የምትኖሩትም፣ በወፍ ጎጆ የምትኖሩትም ሁላችሁም ኑሮ ከበደኝ፣ ኑሮ ከበደኝ ትላላችሁ፡፡ ማናችሁን ልስማ?
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ማንም ቢልህ አንድዬ እንደ እኔ አይሆንም፡፡ የእኔ እኮ የብቻ ነው…
አንድዬ፡— የሁላችሁም የብቻ ነው፡፡ እሺ፣ ንገሪኛ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ኑሮ ክብድ አለኝ፣ አንድዬ የዘንድሮ ገንዘብ ምን ልበልህ በቃ ዱቄት ሆኗል፣ ዱቄተ ታውቅ የለ አንድዬ!
አንድዬ፡— አይ፣ እስቲ አንቺ አስረጂኝ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ ይቅርታ፣ ዝም ብዬ ስለፈልፍ ነው፡፡ አንተን እንዲህ መጠየቄ ልክ አይደለም፡፡
አንድዬ፡— በቃ እንዳላልሽው ቆጥሬዋለሁ..
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ ይኸውልህ፣ ገንዘቡን እጄ ላይ ሳደርገው እንደ ዱቄት ብትን ይልልህና እጄ ባዶ ይሆንልሀል፡፡
አንድዬ፡— ታዲያ እኔ ገንዘቡን ከእጇ ላይ ውሰድ ብዬ ነፋስ አልላኩም፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ እያሾፍክብኝ ነው አይደል! እየቀለድክብኝ ነው፣ አይደል አንድዬ!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ ሽንኩርቱ በል፣ ቃሪያው በል፣ ካሮቱ በል…ጎመን እንኳን በአቅሟ ዋጋዋ ሰማይ ነክቷል፡፡
አንድዬ፡— ጎመንን በአቅሟ አልሻት!
ልማድ ሆኖ ነዋ አንድዬ፡፡ ሆድን በጎመን ቢደልሉት እያልን ስንተርት ኖረን አሁን እሷም የድሀ ሆድ አይስማማኝም ልትል ምንም አልቀራት፡፡
አንድዬ፡— እና አሁን ምድር ውረድና ዋጋ አረጋጋ ነው የምትዪኝ!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— እንደውም፣ ምን በወጣህ፡፡ አንድዬ…አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ?
አንድዬ፡— ጠየቂኝ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— በዓሉን ብናስተላልፍው ቅር ይልሀል?
አንድዬ፡— አልገባኝም…
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ማለቴ አቅም እስኪኖረን ድረስ በዓሉ ለሌላ ጊዜ ቢተላለፍ…
አንድዬ፡— አቅም እስኪኖራችሁ…አሁንስ ምስኪኗ ሀበሻ እኔንም ሳልወድ እንዳታስቂኝ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ምን አድርጌ አንድዬ?
አንድዬ፡— መቼ ነው እናንተ አቅም ኖሯችሁ የምታውቁት! እንደው ይሀ አጉል መኮፈስ ልማዳችሁ አቅም ያላችሁ ትመስላላችሁ እንጂ የእውነት አቅም ኖሯችሁ ያውቃል!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንተ ተውከና አንድዬ፣ አንተ እርግፍ አድርገህ ተውከን፡፡
አንድዬ፡— ይቺን እንኳን አንቺ ያልሻት ሳትሆን ምስኪኑ ሀበሻ ያለሽ ነው…
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ ይኸው ከፊትህ ይነጥለኝ…
አንድዬ፡— ግዴለም፣ መሀላ አያስፈልግም፡፡ ከፊቴ ብትነጠዪስ ያው ዞረሸ እኔው ዘንድ አይደል የምትመጪው…
ምስኪኗ ሀበሻ፡— እሺ አንድዬ…
አንድዬ፡— አቅም ሳይኖራችሁ መች አፍ አውጥታችሁ አቅም የለንም ብላችሁ ታውቃላችሁ! ጭራሽ አንደኛ ነን፣ ዓለም ተደነቀብን፣ የሚደርስብን ጠፋ እያላችሁ ስትፎክሩ … የምድሮቹ ብቻ ሳይሆኑ መንግሥተ ሰማያት ያሉት ሁሉ እየሰሟችሁ አይደል እንዴ!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ እኛ የፈለግነውን ብንል እንዲሁ ስታየን አቅመ ቢስ መሆናችን አይታይህም!
አንድዬ፡— አሁን አንቺ ምንሸ አቅመ ቢስ ይመስላል፡ ያማረብሽ ነው የምትመስዪው፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ የውስጥ ሱሪውና ሂዩመን ሄይሩ ነዋ…አንድዬ ለሰው ደስ አይበለው ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡— እኮ እኔስ የምለው ይሄነኑ አይደል … ሁሉንም ነገር የምታደርጉት ለሰው ደስ አይበለው ብላችሁ ነው፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ እንደሱ ሳይሆን…
አንድዬ፡— ቆይ አስጨርሺኛ፡፡ የምትለብሱት ሰው ደስ አይበለው ብላችሁ፣ በዓል የምታከበሩት ሰው ደስ አይበለው ብላችሁ…ሁሉንም ነገር የምታደርጉት ስለቻላችሁና አቅሙ ስላላችሁ ሳይሆን ሰው ደስ አይበለው ብላችሁ…
ምስኪኗ ሀበሻ፡ አንድዬ እንደ እሱ ሳይሆን…ሰው አፍ መግባት እኮ ጥሩ አይደለም፡፡
አንድዬ፡— ምን ትሆናላችሁ! አሁን አንቺ ወፍራም መሰልሽና የሚጨምርልሽ ነገር አለ! እኔ እኮ ግራ ነው የሚገባኝ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ ኧረ እኛኑ ግራ ይግባን! አንተ ምን በወጣህ!
አንድዬ፡— ግዴለም ለአሁኑ እኔ ግራ ይገባኛል እንበል፡፡ ወደ ዓለም ስልካችሁ ራቁታችሁን ነው፣ ጊዜያችሁን ጨርሳችሁ ወደ እኔ ስትመጡ ራቁታችሁን ነው፡፡ ታዲያ ማንን ለማታለል ነው የሌላችሁን ሰውነት፣ የሌላችሁን ጸጉር…ብቻ ተዪው
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንደ ሰው አፍ እኮ የሚያንገበግብ ነገር የለም፡፡
አንድዬ፡— እሺ በዓል ለሌላ ጊዜ እናስተላልፍ ስትዪኝ ነበር…
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አዎ፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡— እኔን ምን መጠየቅ ያስፈልጋል፡ ከመሰላችሁ አይደለም ማስተላለፍ መተውም ትችላላችሁ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ቢሆንም አንድዬ…
አንድዬ፡— ሰበብ እየፈለጋችሁ በዓል የምትፈጠሩት እናንተ አይደላችሁም እንዴ! ደግሞ ሁሉም በዓላችሁ ከምግብና ከመጠጥ ጋር፡፡ ኮርማ ካልገዛን ነው፣ ሙክት ካልገዛን ነው፣ ዶሮ ካልገዛን ነው፡፡ የሁለት ወር ቀለባችሁን በአንድ ቀን እያጠፋችሁ እኔን ምን አድርግ ነው የምትሉኝ!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— ታዲያ በዓል ሳናከብር እንዴት ይሆናል አንድዬ! ቢያንስ ያቺን ቀን እንኳን ደስ ብሎን እንዋል እንጂ…
አንድዬ፡— እኔ መች ደስ አይበላችሁ አልኩ! ግን መቼ ነው በዓልና ሆድን የምትለያዩት!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ እንዴ ጾመን፣ ጾመን…
አንድዬ፡— እኮ ጾማችሁ፣ ጾማችሁ በያንዳንዳችሁ ቤት ኮርማ ይግባ፣ ሙክት ይታሰር ብያለሁ!
ምስኪኗ ሀበሻ፡— እኮ…አንድዬ ሆዳችን ደርቆ ከርሞ መፈሰክ አለብና…
አንድዬ፡— ታዲያ አቅሙ ከሌላችሁ አንድ ኪሎ ስጋ ጠበስ አድርጋችሁ ቤተሰቡ አይፈስክም!…አሁንስ ንግግሬ ሁሉ የእናንተኑ መሰለ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ የአንድ ኪሎ ዋጋ ስንት እንደሆነ ብነግርህ አታምንም፡፡
አንድዬ፡— በቃ ይቅራ! ሲኖራችሁ ለብቻችሁ መፈሰክ ትችላላችሁ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንዴት አስችሎን!
አንድዬ፡— እንግዲያው የራሳችሁ ጉዳይ፡፡ እሺ አሁን እኔ ምን ላድርግ! በዓሉን ስለማስተላለፍ ያልሽውን የራሳችሁ ምርጫ ነው፡፡ እኔ አይሞቀኝ አይበርደኝ (ከት ብሎ ይስቃል) ነገ ደገሞ ሌላ ነገር ሳታናግሩኝ አይቀርም፡፡ይኸውልሽ ኑሮ ሲወደድ መላውን መፈለግ የእናንተ ጉዳይ ነው፡፡ ትርፍ ጸጉርና፣ ትርፍ ዳሌ እየገዛችሁ የምበላው አጣሁ አትበሉኝ፡፡ በይ ደሀና ሁኚ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አንድዬ አስቆጣሁህ እንዴ!
አንድዬ፡— በጭራሽ፣ ይልቅ እቤት ሂጂና ከራስሽና ከምስኪን ሀበሻ ጋር ምከሪ፡፡
    ሳትደባበቁ ተነጋገሩና ከዛ በኋላ ሁለታችሁንም አወራችኋለሁ፡፡ ደህና ሁኚ፣ ሰላም ግቢ፡፡
ምስኪኗ ሀበሻ፡— አሜን፣ አንድዬ፣ አሜን፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3971 times