Saturday, 30 April 2016 11:19

ሠለስቱ “ፋሲካዎች”

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ)
Rate this item
(3 votes)

“በአዘቦት ተርፎ ያልተጠራቀመው
በፋሲካው ከየት ይገኛል?”

እንኳን ለትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ!!
ሦስት ምሳሌያዊ አነጋገሮች አሉ፤ ፋሲካን ተገን አድርገው ወደኛ ሲመጡ ያገኘኋቸው፡፡ ሌሎች ተረቶች ሊኖሩም ላይኖሩም ይችላሉ፡፡ “አንዳንዴ እንዲህ ነው” አለ ዘፋኝ! አለምን እጃችን ላይ ካለው አንፃር ብቻ እንመዝን ዘንድ የተገደድን ፍጡሮች ነና! ደግሞስ እጃችን ላይ በሌለን ምን መብት አለ? ቶሎ እጃችን ላይ ወዳሉ ተረቶች፡-
ፋሲካን ያሉ ህማማትን ተቀበሉ (አሀዱ)
ፋሲካን ሊያገኙ ሁዳዴን ይመኙ (ክሌዕቱ)
ፋሲካ የሌለው ጦም ደስታ የሌለው ዓለም (ሠልስቱ)
አበው እና እመው ባህርን በነጥብ የሚወክሉ የሐሳብ ጂኦግራፈሮች ናቸው፡፡ እንዳልተረጋጋ ሰው “ጓዘ ቀልጣፋነት” የህይወታቸው መርህ ነው፡፡ የተንዛዛውን፣ የተብዛዛውን በኢምንት ቋጠሮ ወክለው የመጓዝ ህይወታቸውን ያቀልላሉ፡፡ ዋርካን ያህል ሃሳብ፣ በዘር ፍሬው ወክለው ባሻቸው ጊዜ ሲተክሉት ሊያገኙት…
አሀዱ “ፋሲካን ያሉ ህማማትን ተቀበሉ”
አበው እና እመው የቋጠሩትን እኛ ልናባዝተው ነው፡፡
እዚች ምሳሌያዊ አነጋገር ውስጥ “ፋሲካ” ተስፋን ወክሏል፡፡ የዛሬን መከራ (ህማም) የምንታገሰው ነገ ላይ ተስፋ (ፋሲካ) ስትንጠለጠል ነው፡፡ ተስፋ የሌለበት ምድር “የራስ አጥፊዎች” ሀገር ነው፡፡ ይሄንን የሰው ልጅ ባህርይ የጥንቶቹ ግሪኮች (ከእኛ ባይቀድሙም) ተረድተውታል፡፡ (እንደ እኛ ቀልጠፍ አድርገው ባይሸክፉትም) አንዛዝተው ገልፀውታል፡፡
እንዲህ…
…በግሪኮቹ “ዘፍጥረት” በመጀመሪያ “ባዶ” ነበረ፣ አማልክቶቹ ያንን ባዶ ይገዙ ነበረ፤ ከተራራ፣ ከዱርና ከውቅያኖስ በስተቀር የሚንቀሳቀስ ፍጡር መታጣቱ አይናቸውን ይቀለው ጀመረ፡፡ ስለዚህ አማልክተ - አማልክቱ ዚወስ፣ ፕሮሚቲየስና ወንድሙ ኢፒሚቲየስን ጠርቶ “ሂዱ ፍጠሩ፣ ምድርንም ሙሏት” አላቸው፡፡ የተሰናዳችውን ምድር በፍጡር የሞላት ኢፒሚቲየስ ነው፡፡ ኤሊ ይፈጥርና ድንጋይ ያለብሰዋል፤ ፈረስ ይፈጥርና ውብ ጋማ እና ጭራ ይሰጠዋል፣ ወፍን ይፈጥርና ክንፍ ይቸረዋል፡፡ ፕሮሚቲየስ ይሄን ሁሉ ያይና በመጨረሻ የአማልክቱን አምሳያ ከአፈር ይፈጥረዋል፡፡ እንደ እንስሶቹ በአራት እግሩ አይሄድም፣ ምድርን ብቻ አያይም፣ ወደ ሰማየ ሰማያትና ወደ ኮከቦቹ ይማትራል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ በአማልክቶች ዘንድ ብቻ የሚታወቀውን የእሳት ምስጢር ሰጠው፡፡
ዚወስ ተበሳጨ፤ ፕሮሚቲየስን ወቀሰ፡፡ “የጭቃ አሻንጉሊትህ በኛ ፊት ግርማ እንዲያገኝ አደረክ፣ የእሣትን ምስጢር ሰጠህ፣ ኮከቦችን እንዲማትር ፈቀድክ…ለዚህም ቅጣት ታገኛለህ፡፡” ፕሮሚቲየስን የስቃይ አዙሪት ውስጥ ከተተው፤ አይሞትም ግን ተራራ ላይ ታስሮ በንስሮች ገላውን ይቦጠቦጣል፡፡ የዚወስ ንዴቱና ቅጣቱ ወደ ፍጡሩ ሰውም ዞረ፡፡ ቅጣቱ ግን ተዘዋዋሪ እንዲሆን በመፈለጉ አማልክቶች ተሰባስበው የመጀመሪያዋን የግሪኮች ሔዋን ፈጠሩ፡፡ ቬነስ የተሰኘው አምላክ ውበት ሰጣት፣ ሜርኩሪ ቀልጣፋ ምላስ ቸራት፣ አፓሎ የሙዚቃ ጥበብን አደላት… ፓንዶራ ተባለች፡፡
ነገር ለማይገባው ለኢፒሚቲየስም ተዳረች፡፡ ለሠርግ ስጦታቸው አንድ የታሸገ ሳጥን ሰጣቸው፡፡
 ሳጥኑን በፍፁም መክፈት እንደሌለባቸው ዚየስ ነገራቸው፡፡ (እንደኛ ዕፀ በለስ ፍሬ መሆኑ ነው)
በዚያ የግሪኮች ጊዜ፣ በዚያ የግሪኮች ምድር ምንም ክፋት አልነበረም፡፡ መጥፎ ነገሮች ሁሉ አይታወቁም ነበር፡፡ ፓንዶራ ከባሏ ተደብቃ ሳይኑን እስክትከፍት ጊዜ ድረስ ሞት፣ ጦርነት፣ ስስት፣ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ በሽታ፣ እርጅና፣ ጥላቻ፣ ጭካኔ…የታሰሩ ነበሩ፡፡
 በግሪኳ ሄዋን ከሳጥኑ ውስጥ ተለቀቁ፤ አለምን ናኙ፡፡ ፓንዶራ በድንጋጤ ሳጥኑን በፍጥነት ብታዘጋም ከአንድ ነገር በቀር ሁሉም አምልጠው ነበር፡፡ በመንቀራፈፉ ሳጥኑ የተዘጋበት “ተስፋ” ነበር፡፡ ከፓንዶራ ጋር ይደራደራል፡፡
“ክፈቺልኝ፣ ተስፋ ነኝ፣ ያለ እኔ የሰው ልጅ እነዚያን መጥፎ ነገሮች ሁሉ ሊታገስ አይችልም፡፡”
ፓንዶራ አመዛዘነች፡፡ ተስፋ እውነቱን ነበር፡፡ ስለዚህ ከፍታ ለቀቀችው፡፡ ተስፋ እንደዘጋበት ቢቀር ኖሮ ያንን ሁሉ ህማማት ማን ይታገስ ነበር?
ግሪኮች አንዛዙ፤ ዋርካን ነቅለው ከቦታ ቦታ የማጓጓዝ ሥራን ሰሩ፡፡ እኛ ግን ዋርካውን በዘር ፍሬው ወከልን፣ በወፍ ተንጠልጥሎ ከቦታ ቦታ የሚጓጓዝ አደረግን፡፡ ተክለን ስናበቅለው ይገዝፋል፤ ስናጓጉዘው ይቀላል፡፡ “ፋሲካን ያሉ ህማማትን ተቀበሉ”
ክዕሌቱ  “ፋሲካን ሊያገኙ ሁዳዴን ይመኙ”
አበውና እመው ቋጥረው የሰጡንን እኛ ፈትተን ዘርዝረን እንመልከት፡፡ እዚችኛዋ ምሳሌ አነጋገር ውስጥ “ፋሲካ” ደምወዝን ወክሏል፡፡ የድካም ግኝት፣ የልፋት ውጤት ተደርጓል፡፡ የዘመኑን የአቋራጭ ውጤት “የማሣለጫ ጉዞ” ይሄ ተረት አይወክልም፡፡ ከስቃይ በኋላ ፈውስ፣ ከድካም በኋላ እረፍት፣ ከመራብ በኋላ ጥጋብ እንዳለ ይሄ ተረት ይፈክራል፡፡ ለዛሬ መማሰን ነገ ላይ የተንጠለጠለችው ደምወዝ ምክንያት ናት፡፡ አንዳንዴ በደል ካሣ አለው፤ ጥቃት በቀልን ያውጃል፡፡ መረገጥም…
…አንድ ተረት ትዝ አለኝ፡፡ ቅቤና ማር ከአንድ ቤት ወጥተው ገበያ ደረሱ አሉ፡፡ ገበያውም ቀንቷቸው ለአንድ ሰው ተሸጡ፡፡ ገዢ ቤት እንደደረሱ ግን ቦታቸው ተለያየ፡፡ ማር ባለበት ደረጃ ሲቀጥል፣ ቅቤ ባለቤቱ አናት ላይ ሆነ፡፡ በነገሩ የተገረመው ማር ጥያቄአ ቀረበ፡-
“አያ ቅቤ ምነው አናት ላይ ወጣህ?”
“ስገፋ ስለኖርኩ” አለ አሉ፡፡
“አናት ላይ መውጣትን ሊያገኙ መገፋትን ይመኙ” ልንል ይሆን? መገፋት እረዝሞ አናት ላይ መቆየት ቢያጥርም ግድ የለም፡፡ ሁሌም የደምወዝ ቀን የሥራ ቀንን አያክልም፡፡ ዋናው “አረፍ” ብሎ፣ ለመጓዝ የሚያስችል ጠላ በየመካከሉ መገኘቱን ማረጋገጡ ላይ ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ህይወቱን በተመለከተ “የካቲት” መጽሔት ሚያዝያ 1978 ዓ.ም የሰጠው ቃለ ምልልስ ለዚህ ጉዳይ ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡ ቃለምልልሱን ያቀረበው እሸቴ አሰፋ ሲተርከው እንዲህ ነበር ያለው”፡-
“የስብሐት ቤተሰብ ኑሮ እጅግም የሚያወላዳ አልነበረም፡፡ ከእጅ ወደ አፍ እንኳ የሚሳካላቸው አይደሉም፡፡ ኩርማን እንጀራ በብዙ ጐመን አንጀቱም አይደርስለት፡፡ ገና ፣ ጥምቀት፣ ፋሲካ፣ ቅዱስ ዮሐንስ፣ የንግሥ ቀን የአዳጊው ወጣት የስብሐት የደስታ፣ እምብርቱ ፍም እስኪመስል የሚበላባቸው ውስን ቀኖች ናቸው፡፡ ደራሲ ስብሐት የልጅነት ረሃብ፣ ጊዜውን አሁንም አይረሳውም”፡-  
ለጥቂቶች እነ “ፋሲካ” ከአዘቦት ቀን አኗኗር ጋር መለያየት አቅቷቸው ተመሳስለው ይሆናል፡፡ ለብዙዎች ግን እነ ፋሲካ በበረኻ መካከል እንደተገኙ የጉድጓድ ውኃዎች ናቸው፡፡ ጥምን አርክቶ፣ ለቀጣይ ጉዞ በጥቂቱ ሰንቆ፣ ደግሞ “የበረሃ መንገድ” የሚቀጠልባቸው፡፡ በአመት ለአራትና ለአምስት ቀን መጥገብ ከሦስት መቶ ሃምሳ ቀናት በላይ የረበበውን ረሃብ ለመቋቋም ደሞዝ ይሆናል? ይገርማል!! ግን ደግሞ ከዚህም በላይ የሚገርም አይጠፋም፡፡
ሠለስቱ “ፋሲካ የሌለው ጦም ደስታ የሌለው ዓለም”
ማባሪያ የሌለው ዝናብ፣ መፍትሔ ያልተገኘለት ስቃይ፣ እረፍት የማይታሰብበት መማሰን፣ ዋጋ የማይቀጠብለት ልፋት አለ? ሌላው ይቅር እንዴት አዳጊው ወጣት ስብሐት በአመት በአላት አራት አምስቴ እንኳን አይታረፍም? ለምን?
እዚህ ውስጥ የተቀረቀረ ኑሮ ምን ህይወት አድርጐ አስቀጠለው?
Frank McCourt የአየርላንድ ተወላጅ አሜሪካዊ መምህር ነበር፡፡ ልጅነቱን በእንዴት ያለ መከራ እንዳሳለፈ የተረከበት መጽሐፍ አለው፡፡ “Angela’s Ashes” ይሰኛል፡፡ “ልጅነቴን መለስ ብዬ ሳስታውሰው፣ ያንን ሁሉ መከራ እንዴት ተቋቁሜ በህይወት እንደተገኘሁ ፍቺ አጣለታለሁ” ይላል፡፡ እናቱ አባቱን ጠባቂ የአምስት ልጆች እናት ናት፡፡ አባቱ ሥራ-ፈትና ሰካራም፡፡ በአዘቦት ቀን ቀርቶ በአውዳመትም ቤተሰቡ ይራባል፡፡ ስለዚህ ፍራንክ ማኮርት መንደርተኛው ለበአል ያረደውን የአሳማ ጭንቅላት እየዞረ ይለቅማል፡፡ “ፋሲካ የሌለው ጦም…” ማለት ይሄ ይሆን? እዚህ እኛ ሀገር፣ እዚህ እኛ ከተማ ውስጥ የተሰራ ሌላ የኑሮ ጥናት ታትሞ አንብቤአለሁ፡፡ “Urban Food insecurity and Coping Mechanisms” የሚል ርዕስ ያለው፡፡ አጥኚው ያሬድ አማረ ናቸው፡፡ ልደታ ክፍለከተማ ላይ መሠረት ያደረገው ይሄ ጥናት፤ ከተማችን ድምጽ በሌለው ሁኔታ እንዴት በችግር እንደምትንተከተክ የሚያሳይ ነው፡፡ ጥናት አቅራቢው ስለ አንድ ቤተሰብ ኑሮ እማወራዋን አናግሮ ይሄን ቃሏን አስፍሯል፡-  “በየሦስትና በየአራት ቀኑ ጨርሶ የሚበላ ነገር የሚጠፋበት ጊዜ አለ፡፡ ይሄንኑ ለልጆቼ ስነግራቸው አፋቸውን ሳይሽሩ ቤቱን ለቅቀው ይወጣሉ፡፡ ያለ ቀን ደግሞ እንጀራውን እቆራርስና ጥቂት ዶኬ ወጥ ጣል አድርጌ እሰጣቸዋለሁ፡፡ ምናልባት ለአንድ ልጅ ኩርማን እንጀራ ቢደርሰው ነው፡፡ አሁን አሁን ተመስጌን ነው፤ ልጆቼ አድገው ያለንበትን ኑሮ ጠንቅቀው ተረድተውታል፡፡ የለም ስላቸው አያስጨንቁኝም፣ ሹክክ ብለው ይሄዳሉ፡፡”  
በበዓሉ፤ በፋሲካስ? ብላችሁ ጠየቃችሁ? በአዘቦት ተርፎ ያልተጠራቀመ በፋሲካው ከየት ይገኛል? ይቺ ናት ኑሮ፤ “ፋሲካ የሌለው ጦም” የሆነበት፡፡ ህይወት ደስታ የሌለው አለም ውስጥ ስትቀረቀር ግን ለምን ይኖራል? እንዴትስ ይኖራል? እነርሱን ባዶ ያስቀረው የኑሮ ማጋደል እኛን ስላንበሸበሽን ማፈር አይገባም? እነርሱን ኩርማን እያናጠቀ እኛን ከጥጋብ በላይ የጠቀጠቀ ኑሮ ፍትሁና ርትኡ የት ነው?
ኡ…ፍፍፍፍፍ!!



Read 4132 times