Saturday, 30 April 2016 11:22

የተሰነጠቀ ቅልን ለማወቅ ውሃ ጨምርበት

Written by 
Rate this item
(13 votes)

   ከዕለታት አንድ ቀን መልኩ ወደ ቁራ የሚሄድ አንድ ጥቁርና ነጭ ዥጉርጉር ወፍ በአንድ ጫካ ውስጥ ይኖር ነበረ፡፡ በእርሻ ማሳው ውስጥ የሚያማምሩ ነጫጭ እርግቦች እየተመገቡ፣ ብር ትር እያሉ ሲጫወቱ አየ፡፡ ከወፋፍርነታቸው መልካም ተመግበው እንደኖሩ ያስታውቃሉ፡፡ የገላቸውና የላባቸው ንጣት ዐይን ይስባል፡፡ ያ ዥጉርጉር የቁራ ዝርያ የሆነ ወፍ እጅግ አድርጐ ቀና፡፡
“ምነው እኔም መልኬ እንደነዚህ እርግቦች ሙሉ በሙሉ ነጭ በሆነ ምነው… ምን በድዬ ነው እኔን አምላክ አስቀያሚ ዥጉርጉር አድርጐ የፈጠረኝ?” ሲል አማረረ፡፡
ጥቂት ቆይቶ ግን አንድ መላ መጣለት፡-
“ቆይ እኔስ እንደ እርግቦቹ ለመሆን ምን ያንሰኛል? ሙሉ ለሙሉ ከእግር እስከ አናቴ ነጭ ብቀባና ከነሱ ብቀላቀልኮ እንደነሱ እበርራለሁ፤ እንደነሱም እመገባለሁ፡፡ እንደነሱም አምራለሁ” አለ፡፡
እንዳሰበው ሙሉ ነጭ ተቀባና እንደ እርግቦቹ መሰለ፡፡ ሄዶም ከእርግቦቹ ጋር ተቀላቀለ፡፡ ምንም ድምጽ ሳያሰማ፤ በሰላም ከእርግቦቹ ጋር መቀገሩን ተያይዘው፡፡ ለጥቂት ጊዜም ደስተኛ ሆነ፡፡
አንድ ቀን ግን ያልታሰበ ነገር ተከሰተ፡፡
“እስከ መቼ ዝም ብዬ እዘልቀዋለሁ፤ እኔም ከነሱ ጋር መጫወት አለብኝ፤” ብሎ በራሱ ቋንቋ ሊያናግራቸው ሞከረ፡፡
እርግቦቹ እስከ ዛሬ ሲያጭበረብራቸው እንደከረመ ነቁበት፡፡ በጋራ ይጠቀጥቁት፤ ይተከትኩት ገቡ፡፡
“አንት ወስላታ አጭበርባሪ! ያለቦታህ መጥተህ እስካሁን አታለልከን! ሂድ ድራሽህ ይጥፋ! ወገኖች ህጋ ተቀላቀል!” ብለው አባረሩት፡፡
ዥጉርጉሩ ወፈ አዝኖና ተስፋ ቆርጦ ወደ ራሱ ዝርያዎች ሄደ፡፡ ሆኖም እዚያም እንደዚህ መልኩ ነጭ የሆነ ወፍዘ ከኛ ዝርያ ውስጥ የለም፡፡ ከእኛ ጋር መኖርም ሆነ መመገብ የለበትም” ብለው አባረሩት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤት - የለሽ፣ ዘመድ - የለሽዘ ብቸኛ ሆኖ ቀረ!
*   *   *
መምሰል ክፉ በሽታ ነው! ያልሆኑትን ሆኖ ለመታየት መሞከር ዕውነተኛ ማንነትን ማጣት ከመሆኑም በተጨማሪ የተነቃለታ ትልቅ ኪሣራ ያስከትላል፡፡ ወገን የሚመስሉን ወገኖችም ቢሆኑ “ከጠላትህ ውሰድኀ ወደ ዘመድህ ዞረህ ጉረስ” የሚለውን ተረት አሳምረው ያውቁታል፡፡ ይህን አለማስተዋል የማታ ማታ ዋጋ ያስከፍላል!
“መሆንህ እንጂ፣ መምሰልህ፣ ከቶ ለኔ ምን ፋይዳ አለውኀ ዓለምን ዓለም ያረጋት፣ መልክ ሳይሆን ማንነት ነው” የሚለውን ግጥም አለመዘንጋት ነው፡፡
ሀገራችን ብዙ አስመሳዮችን አስተናግዳለች፡፡ ነገም ገና ብዙ ታስተናግዳለች፡፡ የአስመስሎ ማደር ወይም አድርባይነት ጊዜያዊ ወረት ነው፡፡ ወረቱ ሲያልቅ “ጨዋታው ፈረሰ፣ ዳቦው ተቆረሰ” ማለት ግድ ይሆናል፡፡ የዚህ ዓይነት ጨዋታዎች ሲፈርሱ፤ በአፄ ኃይለሥላሴም፣ በደርግም፣ በኢህአዴግም ዘመን፣ ታዝበን አልፈናል፡፡
“ጠላትማ ምንጊዜም ጠላት ነውኀ አስቀድሞ መቅጠፍ አሾክሻኪውን ነው”
የሚለውዘ ለረዥም ጊዜ ስንሰማ የኖርነው ቀረርቶ ነው!
ሌላው ችግር ትምህርት ነው፡፡ ኩረጃና የትምህርት ጥራት እንዲህ ለያዥ ለገራዥ ያስቸግራል ብሎ ማሰብ አስገራሚ ነው፡፡ በልማት ላይ ላለች አገርዘ በብሔራዊ ደረጃ ኩረጃ ችግር ሲሆን ያሳፍራል። ምን ዓይነት ትውልድ እየቀረፅን ነው ብለን ስናስብዘ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ይሆንብቀሐል፡፡ ህብረተሰባችን ራሱ ስለ ትምህርት ጽሕለው አመለካከት እየተንሸዋረረ ነው፡፡ የት/ቤት ገንዘብ መክፈል፣ የትምህርት ቁሳቁስ መግዛት፣ ብቻውን የትምህርት ጤናማነት ማረጋገጫ አይደለም፡፡ የተማሪዎቹ ባህሪ በሚገባ መጤን አለበት፡፡ ክትትል፣ ክትትል፣ አሁንም ክትትል ያስፈልጋል!
ሌላው ችግር ጤና ነው፡፡ የህክምና ስህተቶች፣ የኮንትሮባንድ መድሀኒቶች አላግባብ መግባት፣ የሀኪሞች ስግብግብነት፣ የነርሶች ንዝህላልነት፣ የበሽተኞች መጉላላት ወዘተ… በከፍተኛ ደረጃ በሚታይበት አገር፤ ስለ ጤና ልማት ማሰብ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ የክሊኒኮች መብዛት ለበለጠ ብዝበዛ የሚዳርግ ከሆነ ስለ ጤና ልማት ማለም  ሞኝነት ነው፡፡
በሀገርና በህዝብ ጉዳይ ምን ጊዜም ደግ ደጉን፣ ቀና ቀናውን ማሰብም ቢያንስ አዎንታዊነትና ብሩሃዊነት (Optimistic) መሆን ነው፡፡ መንገድ መስራት መልካም ልማት ነው፡፡ የትራፊክ አደጋ ከበዛ ግን የመንገዱን መሰራት አሉታዊ ያደርገዋል፡፡ ይሄን ችግር ለመፍታት ትራፊኩ ሰውዬ ጉቦ የሚበላ ከሆነ ደግሞ የመንገዱ አዎንታዊነት ይብስ አሉታዊ እየሆነ መጣ ማለት ነው፡፡ ሰንሰለታዊ ብልልት (Chain Reaction) አለበት ውስጡ፡፡ መሰረተ ልማት ውስጥ መብራትና ውሃ ተገጠመ ማለት ዋና ነገር የመሆኑን ያህል፣ መብራትም፣ ውሃም፣ ከሌለ ግን ቅርፅ ብቻ ይሆንብናል፤ ከጥቅም የተለየ ልማት የለምና፡፡ ይሄ በህዝብ ዘንድ የመንግስትን ህዝባዊነት ጥያቄ ላይ ቢጥለው በህዝብ አይፈረድም፡፡ መብራት ለምን ይጠፋል - እስኪሰለቸን ድረስ ተነግሮንም ቢሆን ማወቅ አለብን፡፡ ለሱዳንና ለጅቡቲ እየሸጥን እኛ ለምን ይቸግረናል? የሚለው ጥያቄ፣ መሬት የያዘ መልስ ቢኖረው፤ ቢያንስ “የዐባይን ልጅ ውሃ ጠማው” ከሚለው ተረት እንገላገላለን፡፡ አንዳንዴ ዝርዝር ላይ ስናተኩር ትልቁ ስዕል ይጠፋብናል (እናምታታዋለን Lose sight of the forest for the trees - ይላሉ ፈረንጆች፡፡
ደህንነታችን መደፈሩ ያሰጋናል፡፡ ሉዓላዊነታችን እንዲጠበቅ መፈለጋችን የማንደራደርበት ነው። ለማናቸውም ጥቃት፣ የምንከፍለው አፀፋ ከብሔራዊ ማንነታችን ጋር በጥኑ የተሳሰረ ነው፡፡ ዛሬም “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” ወቅታዊ ተረት ነው፡፡ ዛሬም “ዳሩ ሲነካ መካከሉ ዳር ይሆናል” ወቅታዊ ተረት ነው፡፡ ችግሮች መቆሚያ ሊያጡ በፆም አንጀት ሆኖብን “ግዴለም፣ እንችለዋለን” እያልን ይሆናል፡፡ ነገሩ በፍስክ ሲቀጥል ግን ስጋታችን ዕጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡ የዜጎቻችን አላግባብ መጨፍጨፍ የሚያወላዳ ምላሽን ይሻል፡፡
በምንም ሰበብ ይከሰት የዜጎቻችን እልቂት ያሳስበናል፡፡ ወደን እደለም ደግሞ እንዲህ ያለ ግልፅ ጭፍጨፋ በግላጭ አጋጥሞን ስለማያውቅ ነው! የከብቶቻችን ይዞታ የራሳችን እስከሆነ ድረስ፣ ማንም ምንም ዓይነት የባለ ይዞታን ዕምነት አለኝ ቢል ከቶም ለኛ ለውጥ አያመጣም! የእኛ ንብረት የእኛ ነውና! አሁንም ጠንቀቅ ብለን በብቃት መጠበቅ አለብን፡፡ የጎረቤት ሰላም ደፈረሰ ማለት የሁላችንም ውስጣዊ ህልውና ደፈረሰ ማለት ነው፡፡ ሰላም ለዘለዓለም ትኑር!
ዛሬ ያልተፈተሸ ብዙ ተቋማት፣ ብዙ ማህበራት፣ ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች፣ ትላልቅ ሆቴሎች፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከመንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ተሞዳማጅ መንግስታዊ ድርጅቶ ወዘተ እንካ በእንካ ተያይዘው ሳሉ ችግሮቻቸው በልማት ስም እየተሸፋፈነላቸው፡፡ ንፁህ መስለው በኩራት ይኖራሉ፡፡ አካሄዳቸው አገርንና ህዝብን ጎጂ መሆን አለመሆኑን በግድ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ “ተሸፋፍነው በተኙ፣ ገልጦ የሚያይ አምላክ አለ” የሚለውን አባባል በቅጡ ጨብጦ ነገሮችን ማብጠልጠል ተገቢ ነው፡፡ “የተሰነጠቀ ቅልን ለማወቅ ውሃ ጨምርበት” ነው ነገሩ፡፡
ለክርስትና አማኞች የትንሳኤ በዓል የሞቀ የደመቀ ይሆን ዘንድ ከልብ እየተመኘን፤ የኢትዮጵያንም ትንሳኤ እንደዚሁ ይባርክልን እንላለን!!

Read 6276 times