Saturday, 30 April 2016 11:18

የቤንሻንጉል ክልል መንግስት እና ትምህርት ሚኒስቴር ተከሰሱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(16 votes)

    ለአሶሳ ዩኒቨርስቲ ግንባታ ሲባል ከ6 አመት በፊት ለተወሰደብን የእርሻ መሬት ካሣ ወይም ምትክ መሬት አልተሰጠንም ያሉ ከ400 በላይ አርሶ አደሮች የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስትንና ትምህርት ሚኒስቴርን ከሰሱ፡፡ አርሶ አደሮቹ በወኪላቸው አቶ በለጠ አባተ በኩል ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ባቀረቡት የፍትሃ ብሄር ክስ የ63 ሚሊዮን 445ሺ 371 ብር ካሣ ጠይቀዋል፡፡
402 የሚሆኑት ከሳሾች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት አሶሳ ወረዳ ውስጥ በግብርና ይተዳደሩ እንደነበር ጠቅሰው በ2001 ዓ.ም ለልማት ተብሎ 163 ሄክታር የእርሻ መሬታቸው ምንም አይነት ካሣ ሳይከፈል ወይም ምትክ መሬት ሳይሰጣቸው ስለተወሰደባቸው ላለፉት 6 አመታት ከግብርና ያገኙት የነበረው ገቢ ተቋርጦ፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለውና ለችግር ተዳርገው እንደሚገኙ በክስ አቤቱታቸው አስታውቀዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ በመሬቱ ላይ ከሚያበቅሉት የተለያዩ ሰብሎች በአመት በአማካይ ያገኙ የነበረውን ገቢ በማስላትና እንዲሁም ቀደም ሲል ጫካ የነበረውን ይህን መሬት ለመመንጠር ያወጡትን ወጪ በመደመር ካሣው እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ ላለፉት 6 አመታት የክልሉ መንግስት ካሳውን እንዲከፈላቸው ወይም ምትክ የከተማ ቦታ እንዲሠጣቸው በሠላማዊ ሠልፍ ጭምር መጠየቃቸውን ጠቁመው እስካሁን ምላሽ ባለማግኘታቸው ወደ ክስ ማምራታቸውን አስረድተዋል፡፡
ህገ መንግስታዊ መብታችን ተጥሶ፣ እስካሁን ማግኘት የሚገባንን ጥቅም በማጣታችን አጠቃላይ ቤተሰባችንም ሆነ ህይወታችን ለከባድ ችግር ተጋልጠናል የሚሉት አርሶ አደሮቹ ለጠቅላይ ሚኒስትርና ለተለያዩ የመንግስት አካላት አቤቱታ አቅርበው ምላሽ ማጣታቸውንም አስረድተዋል። ለአርሶ አደሮቹ ወኪል በመሆን በፍ/ቤት ክስ የመሰረቱት አቶ በለጠ አባተ ከወር በፊት (መጋቢት 19 ቀን 2008) የፍ/ቤት የክስ መጥሪያ ለክልሉ መንግስት ለመስጠት በሄዱበት ወቅት ለእስር መዳረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ ግለሰቡ ከ3 ጊዜ በላይ ፍ/ቤት የቀረቡ ቢሆንም እስካሁን ምንም አይነት ክስ እንዳልቀረበባቸውም አቤቱታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ ተፈናቃይ አርሶ አደሮቹ የአማራ ብሄር ተወላጆች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በተለየ መልኩ በክልሉ መንግስት በደል እየተፈፀመባቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የክልሉ መንግስትም ሆነ ትምህርት ሚኒስቴር ለቀረበባቸው ክስ መልሳቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ፍ/ቤት ለግንቦት 8 ቀን 2008 ዓ.ም መቅጠሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አርሶ አደሮቹ ከሶስት አስርት አመታት በፊት በደርግ ዘመነ መንግስት በአካባቢው በየገበሬ ማህበራት ተደራጅተው እንዲሰሩ የተደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በወቅቱ በአንድ ገበሬ ማህበር 500 አባወራዎች እንዲሰፍሩ የተደረገ መሆኑን ያስረዱት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ በዚህ መልኩ በክልሉ 12 የገበሬ ማህበራት ተዋቅረው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ የዝግጅት ክፍላችን ከክልሉ አስተዳደር ምላሽና ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ መከራ ፣የክልሉ ም/ፕሬዚዳንት አምባሣደር ምስጋናው አድማሱ መልሼ እደውላለሁ ብለው ባለመደወላቸውና ሲደወልላቸውም ስብሰባ ላይ ነኝ በማለታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡  

Read 5279 times