Saturday, 30 April 2016 11:15

የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓቱን ከሙስና ለማጽዳት

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(8 votes)

የ33 ሚ. ዶላር ብድር ፀደቀ

    የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር ስርአቱን ከሙስና የፀዳ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት የሚደግፍ የ33 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሰሞኑን አፀደቀ፡፡ ከአለም አቀፉ የልማት ማህበር የተገኘው ይኸው ብድር፤በክልልና በፌደራል ደረጃ የወጭ አስተዳደር ስርአቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው ያስችላል ብሏል፤ምክር ቤቱ፡፡
ብድሩ የኦዲት የሶፍትዌር ግዢን ለመፈፀም፣ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር የመረጃ ስርአት በአግባቡ መዘርጋቱን የሚያረጋግጥ ኩባንያ ለመቅጠርና ሌሎች መሰል ተግባራትን ለማከናወን ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል፡፡ ከጠቅላላ የብድር ገንዘብ ውስጥ የተቋማት የተጠያቂነት ስርአትን ለማጠናከር 9.1 ሚሊዮን ዶላር፣ የወጪ ቁጥጥር የመረጃ ስርአቱን ለማዘመን 22.4 ሚሊዮን ዶላር የሚመደብ ሲሆን ቀሪው ገንዘብ የፕሮጀክቶቹን አፈፃፀሞች ለመገምገምና የግዥ ስርአት ለመዘርጋት ይውላል ተብሏል፡፡  
ብድሩ ከወለድ ነፃ ሲሆን የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 አመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑ ታውቋል፡፡ ብድሩ በረጅም ዓመታት መከፈሉ ከሀገራችን የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣምና ጫናውም ያልበዛ መሆኑን የጠቆመው ምክር ቤቱ፤መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተጀመረውን ሰፊ እንቅስቃሴ ከግብ ለማድረስ እንደሚረዳ ጠቁሟል፡፡  

Read 1967 times