Saturday, 30 April 2016 11:14

የቻይናው ቲቢኢኤ፤ ከፍተኛ የሃይል ማስተላለፊያ መስመር ይዘረጋል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

ፕሮጀክቱ በ12 ወራት ይጠናቀቃል ተብሏል

    የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአቃቂ ቦኮየ አቦ፣ በቂልንጦና በቦሌ ለሚ ለሚያሰራው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ከቻይናው ቲቢኢኤ ጋር ኮንትራት ተፈራረመ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ በሂልተን ሆቴል የተደረገውን የፊርማ ሥነ-ስርዓት፣ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀና የቲቢኢኤ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሽ ፋን ፈርመዋል፡፡
ኮንትራቱ ሁለት ንዑስ ማስተላለፊያ ጣቢያዎችና የትራንስሚሽን መስመር ተከላ ሲኖረው የንዑስ ጣቢያው ኮንትራት፣ የኮየ አቦ 400 ኪሎ ቮልት፣ የቅሊንጦ 230 ኪሎ ቮልትና የቦሌ ለሚ 230 ኪሎ ቮልት ዲዛይን፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ አቅርቦት፣ መልሶ ተከላና ሥራ ማስጀመርን ያጠቃልላል፡፡ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የአዲስ አበባን የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን የሪል እስቴትና በኮየ አቦ፣ በኮየ ፍቸ፣ ቂሊንጦና በቦሌ ለሚ አካባቢ ለሚቀርበ አዳዲስ የኃይል ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል ተብሏል፡፡
የትራንሚሽን መስመር ኮንትራቱ ደግሞ በሦስቱ ንዑስ ጣቢያዎች መካከል ያለውን 26 ኪ.ሜ 400 ኪሎ ቮልትና 230 ኪሎ ቮልት  ዲዛይን፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ምሰሶ ማቆምና ሥራ ማስጀመርን ያካትታል፡፡ የሁለቱም ፕሮጀጅቶች ማጠናቀቂያ ጊዜ 12 ወራት ሲሆን የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 82 ሚሊዮን ዶላርና 347 ሚሊዮን ብር መሆኗ ተገልጿል፡፡ የአጠቃላይ በጀቱ 85 በመቶ ከቻይናው ኤግዚም ባንክ በብድር የተገኘ ሲሆን ቀሪው 15 በመቶ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ይሆናል፡፡

Read 1504 times