Saturday, 30 April 2016 11:12

የቦሌ መድኃኔዓለም ካቴድራል፤“የሕዳሴ ግድብ ቦንድ መዋጮ” ዘገባን አስተባበለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

    አዲስ አድማስ ሚያዝያ 8 ቀን 2008 ዓ.ም፤“የካቴድራሉ ካህናትና ሠራተኞች፤ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያዋጣነው ከ400ሺ ብር በላይ ገንዘብ የገባበትን አናውቅም፤አሉ” በሚል ያወጣው ዘገባ የተሳሳተ ነው ሲል አስተዳደሩ አስተባበለ፡፡
የካቴድራሉ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ሚያዝያ 7 ቀን 2003 ዓ.ም. ባካሔዱት ስብሰባ፤በስድስት ወር ተከፍሎ የሚያልቅ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለመስጠት መወሰናቸውን በማስተባበያው ያስታወሰው አስተዳደሩ፤በውሳኔው መሠረት “ከደብራችን ሙሉ ካህናት የተዋጣው ገንዘብ 117 ሺ 549 ብር እንጂ በዘገባው እንደተጠቀሰው፣400 ሺ ብር አይደለም፤” ብሏል፡፡
የተሰበሰበውም ገንዘብ የክፍያ ሰርተፊኬት ተዘጋጅቶለት፣በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ገቢ መደረጉንና ለዚኽም የማረጋገጫ ሰነድ መሰጠቱን ካቴድራሉ ገልጿል፡፡ ካህናቱ የቦንድ ሰርተፊኬቱን የሚያገኙበትንም መንገድ በተመለከተ፣“ቤተ ክርስቲያኒቱ ከግድቡ ጽ/ቤት ጋር እየተከታተለች ነው፤” ብሏል - ካቴድራሉ በማስተባበያው፡፡
ሚያዝያ 8 በወጣው ዘገባ የተጠቀሰው 400ሺ ብር ከካህናቱና ከሠራተኞቹ ተሰብስቦ እንደኾነ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም አባ መንግሥተ ኣብ ገብረ እግዚአብሔር ከአዲስ አድማስ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤“ያ ገንዘብ ተሰብስቧል፤ከእኔ ጀምሮ ተቆርጧል፤ሒሳብ ሹሙና ቁጥጥሩ ናቸው ገንዘቡን ተቀብለው ገቢ ያደረጉት” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በተመሳሳይ ዘገባ ላይ ለህዳሴው ግድብ ከሠራተኛው የተሰበሰበው ገንዘብ ገቢ የተደረገው በንግድ ባንክ ሥላሴ ቅርንጫፍ እንደነበር የተናገሩት የወቅቱ የካቴድራሉ ሒሳብ ሹም እማሆይ እኅተ ማርያም ገብረ ሥላሴ፤ያንን ያሉት በስሕተት መኾኑን አምነው፣ በማስተባበያው የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ተብሎ የተጠቀሰው ትክክል እንደኾነ አረጋግጠዋል፡፡  ሒሳብ ሹሟ ወደ ባንክ የገባው ገንዘብ ምን ያህል እንደነበር በወቅቱ ተጠይቀው፣ መጠኑን እንደማያስታውሱት መናገራቸው አይዘነጋም።


Read 1564 times