Saturday, 30 April 2016 10:35

ሻምፒዮናው የተሳካ ነበር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

    45ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሚያዝያ 12-16/2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታድዬም የተካሄደ ሲሆን በሁለቱም ፆታዎች በአጠቃላይ ውጤት 362 ነጥብ በማስመዝገብ ያሸነፈው የመከላከያ ክለብ ሲሆን፤ ኦሮሚያ ክልል በ353 ነጥብ እንዲሁም ኢትዮጵያ  ንግድ ባንክ በ155 ነጥብ በሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ተከታትለው ጨርሰዋል፡፡ በወንዶች ምድብ በ199 ነጥብ በአንደኝነት የጨረሰው የኦሮሚያ ክልል ሲሆን፤ መከላከያ  በ198 እንዲሁም ሲዳማ ቡና በ58 ነጥባቸው በተከታታይ ደረጃ አጠናቅቀዋል፡፡ በሌላ በኩል በሴቶች ምድብ 163     ነጥብ     በማስመዝገብ በ1ኛ     ደረጃ ያሸነፈው የመከላከያ ስፖርት ክለብ ሲሆን ኦሮሚያ ክልል በ155 ነጥብ እንዲሁም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ122 ነጥብ በማግኘት ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ አግኝተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሻምፒዮናው በብቸኛነት ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የወከለችው አትሌት ትግስት ታማኙ  ስትሆን በ200ሜ፣ በ400ሜ እና በ4x400ሜ 3 የወርቅ ሜዳልያዎችን በማሸነፏ ነው፡፡ እያንዳንዳቸው ሁለት የወርቅ ሜዳያዎችን የተጎናፀፉ አምስት አትሌቶችም በሻምፒዮናው ነበሩ፡፡ የመከላከያ  ክለብን የወከለችው ኝቦሎ ኡጉዳ    የርዝመትና ሱሉስ ዝላይ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን በሴቶች ምድብ በብቸኝነት አሳክታለች፡፡ በተጨማሪም በወንዶች ምድብ አዳር ጉር     ከመከላከያ በርዝመትና በሱሉስ ዝላይ፤ በድሩ መሐመድ ከመከላከያ     በ100ሜና በ200 ሜ፤ አብዱራህማን አብዲ ከኦሮሚያ በ400ሜና በ4x400ሜ እንዲሁም አበበ ጫላ     ከኦሮሚያ     በ400ሜ መሰናክልና በ4x400ሜ መሰናክል  ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ያገኙ ናቸው፡፡
በአንድ የትራክ እና በአምስት የሜዳ ስፖርቶች በሻምፒዮናው ሪከርዶች የተመዘገቡ ሲሆን ፤ እነሱም በሱ ሳዶ በሴቶች 1500ሜ. ፤ አመለ ይበልጣል በሴቶች አሎሎ ውርወራ፣ አሪያት ዲቦ በሴቶች ከፍታ ዝላይ፣ ኝቦሎ ኡጉዳ በሴቶች ርዝመት ዝላይ፣ አዲር ጉር በወንዶች ስሉስ ዝላይ እንዲሁም ብሩክ አብርሀም በወንዶች መዶሻ ውርወራ ያስመዘገቧቸው ናቸው፡፡45ኛው የኢትዮጵያ  አትሌቲክስ ሻምፒዮና ካለፉት 44 ሻምፒዮናዎች በተለይ በሽልማት ገንዘብ፤ በስፖንሰርሺፕ በመጠናከር፤ በክልሎች እና ክለቦች ንቁ ተሳትፎ የተሳካ እንደነበር መግለፅ ይቻላል ፡፡ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ የተሳትፎ እና የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ ለስፖርት አድማስ  እንደተናገሩት ሻምፒዮናውን ዘንድሮ ልዩ ካደረጉት ምክንያቶች ዋንኛው የዶፒንግ ምርመራ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ባለሙያዎች እና በአዲስ አበባ ስታድዬም በአዲስ መልክ ስራ በጀመረው የፀረ ዶፒንግ ተቋም አማካኝነት ነው፡፡ የዶፒንግ ክትትል እና ምርመራው ከ25 በላይ አትሌቶችን ማካተቱን የገለፁት አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ፤ አትሌቶች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች  ከዶፒንግ በተያያዘ ከነበራቸው ልምዶች አንፃር ከፍተኛ መነሳሳት እና ግንዛቤን የፈጠረ እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡ አትሌቶች በሌሎች የዓለም ክፍሎች ኢትዮጰያዊ ካልሆኑ የዶፒንግ ምርመራ ባለሙያዎች ጋር በሙሉ ትብብር ለመስራት ይቸግራቸው እንደነበር ማስተዋላቸውን የጠቀሱት አቶ ሳሙኤል፤ በሻምፒዮናው የምርመራውን አሰፈላጊነት እንዲገነዘቡ ለማድረግ መቻሉ ትልቅ ውጤት እንደነበር አስረድተዋል፡፡ የዶፒንግ ምርመራው በሻምፒዮናው ውጤታማ የነበሩ አትሌቶች፤ በማጣርያ ውድድሮች የተሳተፉ እንዲሁም በፍፃሜ ውድድሮች ተሳትፈው ያላሸነፉትን እንዳካተተ ባለሙያው በተጨማሪ ገልፀዋል፡፡
በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ወደስራ እንዲገባ በተደረገው የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች መድሀኒት ኮሚቴ በሻምፒዮናው ላይ ለመጀመሪያ ግዜ የምርመራ ናሙናዎችን ሲወሰዱ፤ የናሙናዎቹ ምርመራም የዋዳ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ባለው የዶሀ ላቦራቶሪ እንደሚከናወኑም ታውቋል፡፡
45ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና   የተካሄደበት ዋንኛ ዓላማ በሰኔ ወር አጋማሽ በደቡብ አፍሪካ ደርባን በሚካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና  የሚሳተፉ የብሄራዊ ቡድን አትሌቶችን ለመምረጥ መሆኑንም አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ ሲገልፁ፤ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተስፋ ያላቸው እና እጅግ የተለየ ብቃት የሚኖራቸውን አትሌቶችም ለመከታተል ያገዘ እንደነበር አብራርተዋል፡፡
በሻምፒዮናው በተለይ በአጭር ርቀት ውድድሮች ተተኪ አትሌቶችን  ለማየት መቻሉን የገለፁት የተሳትፎ እና የውድድር ከፍተኛ ባለሙያው በተለይ በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና እና  በአፍሪካ  ሻምፒዮና  ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ የሚችሉ እና ለተሳትፎ የሚያበቁ ሚኒማዎች ያስመዘገቡ ምርጥ አትሌቶች ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡ በ100 ሜትር ወንዶች አትሌት በ10.35 ሰከንዶች በመግባት ያሳየው ብቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተቀመጠው የወጣቶች አትሌቲክስ 10.55 ሰከንዶች ሚኒማ ጋር በማነፃፀርም ምሳሌ አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሻምፒዮናው በተለይ በሜዳ ላይ ስፖርቶች አዳዲስ ሪከርዶች መመዝገባቸውም የሚያበረታታ እንደሆነም ባለሙያው ይገልፃሉ፡፡
በሻምፒዮናው  ለተሳተፉ ክልሎች እና ክለቦች ፌደሬሽኑ የበጀት ድጋፍ ማድረጉን ያስገነዘቡት አቶ ሳሙኤል ፤ ሁሉም ከመቼውም ጊዜ የላቀ  ንቁ ተሳትፎ እንደነበራቸው አውስተዋል፡፡ በተለይ ግን በወንዶች ምድብ ከክለቦች በአጠቃላይ ውጤት በሶስተኛ ደረጃ ለማጠናቀቅ የበቃው ሲዳማ ቡና በምሳሌነት እንደሚጠቀስ አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ ለስፖርት አድማስ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ በየክልሎቹ በመዘዋወር  የተለያዩ ፕሮጀክቶችና ክለቦች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ግምገማ ማድረጉን የሚያስታውሱት አቶ ሳሙኤል ፤ በደቡብ ክልል የሚገኘው የሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል፤ በክልሉ በመታቀፍ ከሚወዳደር ይልቅ ራሱን ችሎ በአገር አቀፍ ሻምፒዮና መሳተፍ እንደሚገባው መመከሩን አስታውሰዋል፡፡ የሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ ከ60 በላይ አትሌቶች በማቀፍ በሚያደርገው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን በመጠቆምም  በኢትዮጰያ ሻምፒዮና ለመጀመርያ ጊዜ ተሳትፎ ያስመዘገበው ውጤት በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው በማለት የተሳትፎ እና የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ ለስፖርት አድማስ  አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ክለቦች፣ክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች የሚሳተፉበት ሲሆን በከፍተኛ ፉክክር የሚካሄድ አዲስና ወጣት አትሌቶች የሚፈልቁበት መድረክ ነው፡፡ በ1.2 ሚሊዮን ብር  በጀት  የተዘጋጀው ሻምፒዮናው ከሞሐ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪያል፣ ጋራድ ኃ/የተ/የግ/ኩባንያና አራራት ሆቴል  የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ ያገኘ ሲሆን    ከእነዚህ ተባባሪ ከ900,000 ብር በላይ መገኘቱን የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ገልጿል፡፡ በሻምፒዮናው በወንዶችና በሴቶች 42 የውድድር አይነቶች ሲካሄዱ በወንድ 743፣ በሴት 516፣ በአጠቃላይ 1,259 አትሌቶች 9 ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች  እንዲሁም 30 ክለቦችን በመወከል የተካፈሉበት ሲሆን   ከ177 በላይ ልዩ ልዩ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፣ ሻምፒዮናው በክልሎች፣ በከተማ አስተዳድሮች፣ በክለቦችና በማሠልጠኛ ማዕከላት ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠር፤ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት፤ለብሔራዊ አትሌቲክስ ስልጠና አትሌቶችን ለመምረጥ፤ ለ20ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶች ለመምረጥ መሆኑን ፌደሬሽኑ ያብራራል፡፡

Read 2285 times