Monday, 25 April 2016 10:05

በኢቢኤስ ላይ የተሰነዘረው ትችት የተዛባ ነው

Written by  ከእውነቱ ይታይ ዘላለም
Rate this item
(6 votes)

“አሁን ያለው የመገናኛ ብዙኃን ይዘትና ቅርጽ እንዲፈጠር ተግቶ የሰራው መንግስት መሆኑን
ጸሃፊው አላስተዋሉም፣ ወይም ሆን ብለው ጆሮ ዳባ ልበስ ብለውታል፡፡----”

   የዛሬ ሁለት ሳምንት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የሚያዝያ 1 ዕትም፣ ያ ገርሰው ጥበቡ የተባሉ ጸሃፊ፣ በኢቢኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የሰነዘሩትን ትችት አነበብኩት፡፡ እኔም ታዲያ በጽሁፉ ላይ በተመለከትኳቸው የሀቅና የምልከታ ዝንፋቶች ዙርያ  ሃሳቤን ለመግለጽ ወደድኩ፡፡
ጸሃፊው በኢቢኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቶክሾዎች በዙ፣ ሀላፊነት የሚሰማው ጣቢያ አይመስልም፣ ትውልዱን ያደነዝዛል፤ ይህም የመነጨው ከሊበራል መገናኛ ብዙኃንነቱ ነው የሚል አቋም አንጸባርቀዋል፡፡ ያገር ሰው ጥበቡ፤ ለፍረጃ እንዲመቻቸው ቶክሾዎቹን በአንድ ላይ ጨፍልቀው፣ ሁሉም ይመሳሰላሉ ያሉት ጨርሶ ስህተት ሲሆን በዙ የተባሉት ቶክሾዎች በእንግዶች ምርጫ፣ በሚያተኩሩበት ርእሰ ጉዳይ፣ በዘውግ፣ በአጠያየቅ ዘዬና ብስለት ወዘተ---- ግልጽ ልዩነቶች የሚስተዋልባቸው ናቸው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የተባለው ችግር በኢቢኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ መኖሩን ከነአካቴው መካድ አይቻልም፡፡ ይህ ችግር በኢቢኤስም ሆነ በሌሎች መገናኛ ብዙኃን ላይ ለምን ተስተዋለ፣ ከምንስ መጣ? ለሚለው ጥያቄ የሰጡት ትንተና ግን ወባ ላስከተለው መንዘፍዘፍ የሳምባ ነቀርሳን መድሀኒት እንደማዘዝ የሚቆጠር፣ ፈጽሞ ከዋናው የችግሩ ምንጭ ጋር የማይገናኝ ነው።
1.  አሁን ያለው የመገናኛ ብዙኃን ይዘትና ቅርጽ እንዲፈጠር ተግቶ የሰራው መንግስት መሆኑን ጸሃፊው አላስተዋሉም፣ ወይም ሆን ብለው ጆሮ ዳባ ልበስ ብለውታል፡፡ መንግስት በሚቆጣጠራቸው የቴሌቪዥንና የሬድዮ ጣቢያዎች ምን ያህል ትውልድን የሚያደነዝዙ፣ ወደ ዋናው የፍትህና የፖለቲካ ጥያቄ እንዳይመለከት የሚያደርጉ፣ አልያም ደግሞ የደረቁ የፕሮፓጋንዳ ዲስኩሮችና እንቶፍንቶ ዝግጅቶች የተሞሉ እንደሆኑ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ይህም በአጋጣሚ የተከወነ ሳይሆን እንደ ፖሊሲ የተያዘ አካሄድ መሆኑን የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ አጥርቶ ይገነዘባል፡፡  እናም፣ የሆነው ሁሉ ልክ በኢቢኤስ የተፈጠረ ይመስል ለረብ አልባ ዝግጅቶች መብዛት ተጠያቂው የቴሌቪዥን ጣቢያው እንደሆነ ብቻ መግለጽ አመክንዮ ያልተጠጋው፣ ሸውራራ እይታ ነው ብዬ
አምናለሁ፡፡ አስተያየት ሰጪው አንድ መገናኛ ብዙኃን  ሀላፊነቱን ተወጣ የሚሉት፣ በመንግስት ልሳን ሲያወራ፣ እርሳቸው እንዳሉት ስለ ድህነት ቅነሳ፣ ስለ ገጠር ልማት፣ አገሪቱ እያስመዘገበች ስላለችው ባለ ሁለት አሃዝ እድገት ሲናገር ወይም የህዳሴውን ግድብ ግስጋሴ ሲዘግብ ወዘተ--- ብቻ በአጠቃላይ ኢቲቪን ወይም ኢብኮን ሲመስል መሆኑ አስቂኝ ነገር ነው፡፡ መጀመሪያ ነገር መገናኛ ብዙኃኑ ከመንግስት አፍ እየለቀሙ መንግስት ጉዳይ ያደረጋቸውን ሁሉ ጉዳይ የማድረግ ግዴታ የለባቸውም፡፡ ለምን ቢሉ፣ መንግስት የሚሻው የሚፈልጋቸው ጉዳዮች በሚፈልገው መንገድ ብቻ እንዲስተናገድ
ነው፡፡ ይህ ደግሞ አሁን በእጁ ካሉት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሚቆጣጠራቸው፣ በመንግስት ስምም ሆነ በፓርቲ ስም ከሚያስተዳድራቸው አይነተ ብዙ የመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚደረቱ ተቀጥላዎች ያደርጋቸው እንደሆነ እንጂ ለማህበረሰብ የሚፈይዱት አንዳች ነገር እንዲኖራቸው ስለማይረዳ ነው፡፡
 ሆኖም ጸሃፊው እነ ኢቢኤስ አላነሷቸውም ብለው የኮነኑባቸው ርእሰ ጉዳዮችም ቢሆኑ በነጻነትና በጥልቀት ማጥናትንና ከማንም ያልወገነ ዘገባ መስራትን
በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እንደማይፈቅድ አከራካሪ አይደለም፡፡
2. አቶ ያገር ሰው ጥበቡ፤ለዚህ ያቀረቡት አማራጭ ደግሞ ይበልጥ በአግራሞት  የሚያጥለቀልቅ ነው፡፡ ለማህበረሰብ ፋይዳ ያለው ሚድያ ማለት የቀድሞው ኢቲቪ የአሁኑ ኢብኮ ነው የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ እንግዲህ በእርሳቸው ሚዛን መሰረት፤ ድንቅ የቃለምልልስ ቶክሾው ማለት፣ እንግዶችን እየጠሩ በተረት ተረት አካሄድ የት ተወለድክ፣ የት አደግህ፣ የት ተማርክ እያሉ --- ቅጽ የሚያስሞሉ ጋዜጠኞች የተሰማሩበት የኢቲቪ ዝግጅቶች መሆናቸው ነው፡፡ ለመሆኑ እንደ ኢብኮ እጅግ የቸከና ከደረጃ የወረደ፣ መንግስት በጀት መድቦ ህዝቡን የሚያበሽቅበት ጣቢያ ከወዴት ይገኛል?! አቶ ያገር ሰው ያለአንዳች ሀፍረት ኢብኮን በምሳሌነት እንዲከተሉ ለኢቢኤስም ሆነ ለሌሎች በመምጣት ላይ ላሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሰጡት ምክር፣ (ጸሀፊው የት ነው የሚኖሩት? ለመሆኑ እንደ አርአያ ተከተሉት ያሉትን ጣቢያ ያውቁታል? አልያም መሀመድ ሰልማን እንደጻፈው፤ ኢትዮጵያዊ ናቸው ወይስ ኢቲቪዮጵያዊ ?) የሚሉ ጥያቄዎችን ያጭርብናል፡፡ የኢትዮያ ቴሌቪዥን በግልጽ በሚታወቁ የማህበረሰብ ክፍሎች ስያሜ ላይ በመንጠልጠል፣የሴቶች ፕሮግራም፣ የወጣቶች ፕሮግራም፣ የልጆች ፕሮግራም አልያም ደግሞ፣ በመንግስት አሰልቺ የፕሮጋንዳ ቃላት በተሰየሙ እንደ ጥቃቅንና አነስተኛ፣ የኢኮኖሚ፣ የእርሻ፣ የንግድ፣ የባህል፣ የቱሪዝም
ወዘተ ---- በዘርፍ አጥር ስር ያሉ ዝግጅቶችን ከማቅረብ በቀር፤እንኳን የህዝብን ልብ የራሳቸውን የአዘጋጆቹን ፍላጎት ቆንጥጦ መያዝ የማይችል፤ ለብዙ አመታት የግብር ከፋዩን ገንዘብ መጫወቻ ያደረገ ተቋም አይደለምን?
ኢቲቪ በተጓዘበት ጎዳና ፈጠራ፣ የጋዜጠኝነት የሞያ ብቃት፣ የተመልካችን ፍላጎት አጥንቶ መረዳትና በዚያ መሰረት መሻሻል፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂ መጠቀምና አዳዲስ አቀራረብ --- ከሚሏቸው አንዳቸውም እንኳን አልፈውበት አያውቁም፡፡
ይህንን መመልከት የተሳናቸው አስተያየት ሰጪው፤ ለቁጥር የሚታክት ጉዱን በየእለቱ የሚያሰጣውንና የመንግስት በመሆኑ ብቻ በህይወት የቆየውን ጣቢያ በምሳሌነት ሊጠቅሱልን ደፈሩ፡፡
3. በኢቢኤስ ያዩትን ሁኔታ ከሊበራል ሚድያ ማንነቱ የመነጨ እንደሆነ የገለጹትም ሀሳብ እራሱን የቻለ ችግር ያለበትና ብዙ ሊያባብል የሚችል ነው። ሊበራል ሚድያ የሚሉት በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ያሉት አገራት የፈጠሩትን የሚድያ ሞዴል መሆኑ ነው፡፡ ሊበራል ሚድያ የራሱ የሆኑ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም፣ እርሱን ተክቶ ሊቀርብ የሚገባው አማራጭ ግን ያገር ሰው ጥበቡ እንደሚመኙት ልማታዊ ሚድያ አይደለም፡፡ ልማታዊ መገናኛ ብዙኃን በ1960ዎቹ በእስያ አንዳንድ ሀገሮች የተጀመረ፣ ብዙም ሳይቆይ ግን የቁጥጥር ሱስ በተጠናወታቸው አምባገነን መንግስታት ተወዳጅ የሆነ፣ መንግስት የሚሰራውን እያንዳንዱን ነገር እያጋነነ የሚያወራ፣ መንግስት ስህተት ሲሰራ ግን ትንፍሽ ሊል አቅምም ፍላጎትም የሌለው የመገናኛ ብዙኀን አይነት ነው፡፡ የልማታዊ መገናኛ ብዙኃንን ጠቀሜታና የሊበራል መገናኛ ብዙኃንን ጉዳት አስመልክቶ የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባለስልጣናት ወደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እየመጡ ጋዜጠኞችን ያስተምሩ እንደነበር የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በሚገባ ያውቃል፡፡
ልማታዊ ሚድያ ተብዬው ገንቢ ሚና እጫወታለሁ በሚል ሰበብ፣ለመንግስት አሽከርነት ያደረ፣ በመንግስት ላይ ጫና ፈጥሮ በጎ ለውጥ ሊያመጣ ይቅርና እርሱም ከመንግስት በሚጣልለት የመረጃና የገንዘብ ፍርፋሪ ሊኖር የተስማማ የመገናኛ ብዙኃን እሳቤ ነው፡፡ ኢብኮም በዚህ ልማታዊ ጋዜጠኝነት እየተመራ ነው እንግዲህ መፈጠሩን ያልገለጸልንን ተቃውሞ፣ “በቁጥጥር ስር ዋለ” ብሎ ሲነግረን የማይሰቀጥጠው፡፡ ለዚህ ነው መጀመሪያ ስለ ችግሩ ያልነገረንን ጉዳይ መንግስት መፍትሄ ያገኘ ሲመስለው “ችግሩ ሊፈታ ነው” ሲል የሚዘግብልን። ይህንን የኢብኮን ሁኔታ በቅርብ የሚከታተል አንድ ወዳጄ፤“ለኢቲቪ መሪ ቃል ወይም ሞቶ እናውጣለት ብንል፣አሁን እንደሚለው ህዳሴውን እናበስራለን ሳይሆን “making the possible impossible” (የሚቻለውን ሁሉ የማይቻል ማድረግ ---- የሚል ይሆን ነበር ብሎኛል፡፡)
 ልማታዊ ጋዜጠኝነት፤አሁን በበርካታ አዳጊ አገራት ያለው ትክክለኛ ገላጭ ብየና ወይም ትርጉም፤ “ጋዜጠኛውና ሚድያው መንግስትን የሚሄስበት ጥርሱ ሲረግፍ” እንደ ማለት ሆኗል፡፡ ያኔ ጠጠር ያለ ቁምነገር የሚነክስበትን ጥርሱን ተነጥቋልና መንግስት ፈትፍቶ ከሚያጎርሰው መረጃና ዜና በቀር ሌላ ሀቅ መቆርጠምና ማስቆርጠም አይሆንለትም። እንግዲህ ይህንን እጅ እጅ ያለንን አካሄድ ነው አስተያየት ሰጪው፣ በኢቢኤስም ሆነ በቃና ቴሌቪዥን እንዲሁም በሌሎች ጣቢያዎች ላይ ማየት የሚሹት፡፡
ታድያ እዚህ ላይ ለአቶ ያገር ሰው ጥበቡ፤አንድ ነገር ልነግራቸው እፈልጋለሁ፡፡ በመንግስት በጎ ፈቃድ ሊኖር ከሚተሻሽ፣ ልማታዊ ከሆነው የመገናኛ ብዙኃን ፍልስፍና ይልቅ ሊበራሉን ሚድያ ከነችግሮቹ ደስ እያለኝ እታቀፈዋለሁ፡፡ ሌላም ሰበር ዜና ልጨምርላቸው፡፡ እጅግ አያሌ ዜጎች፤በልማታዊ ጋዜጠኝነት ባያምኑም፣ መንግስትን እሹሩሩ ለማለት ባይፈቅዱም፣ ከመንግስት እኩል እንደውም በላይ ስለ ሀገራቸው ሀላፊነት የሚሰማቸው ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ታላቁን ፈላስፋና ጸሀፊ ማርክ ትዌይንን ልጠቅስ እወዳለሁ፡፡ ማርክ ትዌይን፣“ታማኝነት ለሀገር ሲሆን ሁልጊዜ፣ ለመንግስት ሲሆን ግን የሚገባው ሲሆን ብቻ!” ብሏል፡፡
 4- እርሳቸው እነኢቢኤስን ከከሰሱባቸው ምክንያቶች አንዱ ስለ አርሶ አደሩ አልተናገሩም፣ ስለ ድህነት ቅነሳ አልደሰኮሩም፣ ስለ መንግስት የልማት ስኬት አላስተጋቡም የሚል ይዘት ይገኝበታል። እስኪ እንነጋገር፡፡
ኢቢኤስና ሌሎች ከዚህ በኋላ የሚመጡም ሆነ ከዚህ በፊት ብቅ ብለው በመንግስት የተዘጉ የቴሌቪዥን ዝግጅቶች ከፍተኛ ተመልካች ያገኙ የነበረው ተመልካቹ ኢቲቪን ከመሰለ አሰልቺና ለዛ የለሽ  ጣቢያ የሚገላግል ከመጣ ምንም ይሁን በሚል ምሬት አይደለም እንዴ? እስኪ መንግስት እውነተኛዎቹ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ርእሰ ጉዳዮችን መገናኛ ብዙሀን ጉዳይ እንዲያደርጓቸው ይፍቀድና ያኔ መገናኛ ብዙኃኑ ሰንፈው ይተቹ? እንኳን እነኚህን አበይት ሀገራዊ ጉዳዮችን ቀርቶ “ይህን በመናገራችሁ እገሌ የተሰኘው ባለስልጣን ከፍቶታል” እያለ እርምጃ የሚወስድ፣ በሰበብ አስባቡ ፕሬሱን የሚያቀጭጭ አስተዳደር መሆኑን እርሳቸው ሊዘነጉት ቢፈቅዱም እኛ ግን ሁልጊዜ በሀዘን የምናስበው እውነታ ነው፡፡
እስኪ ለምሳሌ አሁን የተከሰተውንና ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ለከፋ ረሀብ የዳረገውን ድርቅ አስመልክቶ እውነተኛ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አስተዳደራዊ፣ አካባቢያዊና ተፈጥሮአዊ መነሻዎችን አንስተው የነጻ ሞያተኞችን
ትንተና እንዲሁም የህዝቡን ትክክለኛ ቅሬታ እንዲያቀርቡ ይፍቀድና ሚድያው በሞያ እጥረት ይታማ? ነገር ግን እውነተኛዎቹን ጉዳዮች መወያየት የተከለከለ አንድ መገናኛ ብዙኃን፣አደጋ የሌለባቸውን ዘርፎች መርጦ ቢሰማራ ጥፋቱ
ምን ላይ ነው? ይህንን ቅጽር የከለለው መንግስት፣ ይህ ሁኔታ እንዲመጣ ያደረገውን አስተዋጽኦ ረስቶ፣ የመንግስት ፖሊሲ ሰለባ የሆነውን መገናኛ ብዙኃን መውቀስ ተገቢ አይደለም። ከ20ኛ ፎቅ ላይ የተገፈተረ ግለሰብ በመንገድ
በማለፍ ላይ ባለ አንድ መንገደኛ ላይ ቢወድቅ፣ገፍታሪውን አንጋጥጦ እንደ መውቀስ ተገፍታሪውን የሚያማርርና የሚኮንን እንደምን ያለ ህሊና ነው? ያገር ሰው ጥበቡ፤ የደረሱበትም ይህንኑ መሰል ርትእም ሆነ ፍትህ የማያውቅ ፍርደ ገምድል ድምዳሜ ላይ ነው፡፡
እዚህ ላይ ደግሜ ማንሳት የምወደው ጸሃፊው፤ሁሉም የኢቢኤስ ቶክሾዎች አንድና ያው ናቸው ያሉት አነጋገር ከእውነት የራቀና ኢ-ተአማኒ መሆኑን ነው፡፡
ነገር ግን ይህም ሁሉ ሆኖ እውነተኛውን ጉዳይ እንዳያነሳ የታፈነ ልሳን፣ ስለ እግር ኳስ ሲደሰኩር ቢውል ምን ያስገርማል? የታዘበውን በጋዜጠኝነት ሞያው ተጠቅሞ መንግስትን ከህዝብ ጋር ለማገናኘት ቢሞክር ብዙ ጣጣ እንደሚከተለው የሚያውቅ ግለሰብ፣ ስለ ምእራብ ሀገራት ታላቅነትና ስለ እነርሱ ባህል ውብነት ቢናገር ምን ይደንቃል? የተተወለት ቦታ ይህ ብቻ ነውና ያንን ከማድረግ ውጪ ምርጫ ሊኖረው አይችልም፡፡
ስለዚህም፣ አንደኛ፣ ብቸኛው ሀላፊነት የተሞላና የተዋጣለት የጋዜጠኝነትና የመገናኛ ብዙኃን ፍልስፍና፣ ልማታዊ ጋዜጠኝነት አይደለም። እንዲያውም ልማታዊ ጋዜጠኝነት ሊርቁት የሚገባ፣ ሚድያውን ለመንግስት እንጂ ለህዝብ ጆሮ እንዳይኖረው የሚያደርግ፣ መገናኛ ብዙኃንን ከህዝብ ወገንተኝነት (Watch dog) ሚናቸው ወደ ተራና ገራም ልሳንነት (Lap dog) የሚያወርድ ሞዴል ነው፡፡ እናም፣ ኢቢኤስን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሊከተሉት የሚገባ ፈለግ አይደለም። ሁለተኛ፣ ያገር ሰው ጥበቡ፤ ያነሷቸው ሀሳቦች ከአመክንዮ፣ ከሚዛንና ከፍትህ ጋር የማይተዋወቁ ከመሆናቸውም በላይ በአስተያየቶቻቸው ላይ ያገር ሰውነትም ጥበብም አላስተዋልኩም፡፡

Read 5379 times