Saturday, 23 April 2016 10:50

ውሻ በእግር መምታት፣ እንካ ሥጋ ብላ ማለት

Written by 
Rate this item
(22 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሐኪም በሽተኛውን ሊጠይቅ ወደ በሽተኛው ክፍል ይሄዳል፡፡
ሐኪም፡
“እንደምናደርክ ወዳጄ?”
በሽተኛ፡
“ደህና ዶክተር፤ አንተስ ደህና አደርክ?”
ሐኪም፤
“እኔ ደህና አድሬአለሁ፡፡ ለመሆኑ ህመምህ እንዴት ነው?”
“በጣም ያልበኛል እንጂ ደህና ነኝ”
ሐኪም፤
“ይሄ ጥሩ የመዳን ምልክት ነው፤ አይዞህ” አለውና ሄደ፡፡
በሶስተኛው ቀን ሐኪሙ ደግሞ በሽተኛውን ሊያይ መጣ፡፡
ሐኪም፤
“እንዴት አደርክ ወዳጄ?”
በሽተኛ፤
“ደህና ነኝ፡፡ እንደምነህ ዶክተር?”
ሐኪም፤
“እህ፤ ዛሬስ ህመምህ እንዴት ነው?” አለው፡፡
በሽተኛውም፤
“በጣም ደህና ነኝ ዶክተር፡፡ ግን ህመሙ ያመጣብኝ አዲስ ጠባይ ደግሞ፤ ማታ ማታ ያንቀጠቅጠኛል”
ሐኪም፤
“ኦ እሱም ጥሩ የመዳን ምልክት ነው! አይዞህ” አለውና ትከሻውን መታ መታ አድርጎት ሄደ፡፡
ሐኪሙ በሶስተኛው ቀን መጣና፤
“እህስ ዛሬስ ህመምህ እንዴት ነው?”
በሽተኛ፤
“ደህና ነኝ፣ ግን አሁን ደግሞ ትኩሳት ለቀቀብኝ”
ሐኪም፣
“እሱም፣ ጥሩ የመዳን ምልክት ነው፡፡ አይዞህ” ብሎት ሄደ፡፡
በመጨረሻ ሐኪሙ ለአራተኛ ጊዜ መጥቶ፤
“እህስ ወዳጄ ዛሬስ እንደምንድነህ? በጣም ተሻለህ አይደል?” ብሎ ጠይቆ እንደተለመደው “ጥሩ ምልክት ነው” ብሎት ሄደ፡፡ ከዚህ በኋላ አንድ ዘመዱ በሽተኛውን ሊጠይቀው መጣና፣
“እህስ ወንድሜ እንዴት ከርመሃል?” ሲል ጠየቀው፡፡
በሽተኛውም፤
“ኧረ ባክህ ተወኝ ወንድሜ፤ ‹ጥሩ ምልክት› በዝቶብኝ ልሞትልህ ነው” አለው፡፡
*           *           *
“ወፍራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል” ይላሉ አበው፡፡ የምንሄድበት ቦታ፣ የምንረግጠውን ምድር ሁሉ፣ “ቅዱስ፣ ቅዱስ” እያልን ካሞካሸነው እንከኑን ለማየት ዐይናችን ይታወራል፡፡ መልካም ነው፣ ጥሩ ምልክት ነው ማለት ለአዎንታዊ ተስፈኝነቱ (Optimism) ትልቅ ፀጋ ነው። ሙገሣው ብቻውን ከሆነና ተግባር ላይ ከለገምን በ “ጥሩ ምልክት” እንሞታለን፡፡ ስለ ሀገር ደግ አለማውራት ደግ አይደለም፡፡ ደግ ደጉን ብቻ ማውራትና ለክፉ ክፉው ዐይንንም ጆሮንም መዝጋት ግን፤ ሁኔታው ድንገት የሚያፋጥጠን ደረጃ ላይ ከደረሰ መደነባበርን ያስከትላል፡፡ አለመዘጋጀት እርግማን ነው፡፡ መረጃው ደርሶን ለመዘጋጀት አለመቻል፤ የእርግማን እርግማን ነው፡፡ አለመዘጋጀታችን ያደረሰውን ጥፋት አይተን እጅን - አጣጥፎ መቀመጥን ከመረጥን ደግሞ ከመኖር ወደ አለመኖር መለወጥ ነው፡፡ ዛሬ ሀገራችንን፣ በተጓዘችው የለውጥ መጠን ስናሰላት፤ በፖለቲካውና በዲፕሎማሲው መስክ፣ በተለይ በጎረቤት አገሮች አኳያ ስናጤናት፣ ጤናማና የበሰለ መንገድ ዘልቃለች ብንል ሀሰት አይሆንም፡፡ የራሷን ሳታስነካ፣ የሌላውን ሳትነካ ተራምዳለች ማለት አይደለም፡፡ ይሄ “ማታ የምትበላውን  ጧት አሳስቀው” በሚለው በበርናርድ ሻው ዲፕሎማሲያዊ ምፀት ሳናስበው ነው፡፡ ድንበራችንን ማስከበር፣ ጠረፋችንን መጠበቅ የዋዛ አጀንዳ አይደለም፡፡ “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ፡፡ የሚለው መሪ ብሂል፤ የዳር ድንበራችንን ነገር በውል ያፀኸይልናል፡፡ ከወረራ እስከ ተራ ሽፍታ ዘረፋ፤ በድን በርም መጣ በውስጥ ቡርቦራ፣ በአገር የመጣ ነገር ምጣት ነው፡፡ ሰሞኑን የደረሰው ሁሉ አሳዛኝ፣ አረመኔአዊ ጭፍጨፋነቱ አሌ ባይባልም፤ ሉዓላዊነትን በዘዴ ማስከበርም ጥበብንና ብልሃትን የግድ ይላል፡፡ የሞቱት ወገኖቻችን ናቸው፡፡ የታገቱት ወገኖቻችን ናቸው፡፡ በዚህም ተባለ በዚያ የዋሃንን መጨፍጨፍ አረመኔአዊነት ነው፡፡ የህዝባችን፣ የሀገራችን ዕንባ ረግፎላቸዋል፡፡ ማዕከላዊ መንግስት እያለ አረመኔያዊ ተግባር ምላሽ አልባ አይሆንም፡፡ ለዘለቄታው መንቃት ደግ ነው፡፡ ሆኖም የአጎራባች አገሮችን ታሪካዊ ዝምድና ውሉን እንዳይስት መላ መላ ማለት መሰረታዊ ፍሬ ነገር ነው፡፡ የዳር ድንበራችን ጉዳይ የአንድ አቅጣጫ ነገር አይደለም፡፡ ሀገራችን በዙሪያዋ ካሉት ጎረቤት አገሮች አንፃር ሀብት ጠገብ ናት፡፡ ምናልባትም የንፍቀ - ክበቡን የሰላም ኃላፊነት ብትወሰድ አይገርምም፡፡ የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግሥታት ወካይ ድርጅቶች መናኸሪያ ናት፡፡ የመካከለኛውን ምሥራቅ ቀጠና አሻግሮ ለማየት ዓይነተኛ ማማ ናት፡፡ የታሪክና የቅርስ አገር ናት፡፡ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ ብዙዎች ከጥንት እስከ ዛሬ የሚጎመጇት ተፈጥሮአዊ ስትራቴጂን የታደለች አገር ናት፡፡ በራሷ የግል ውስጣዊና ውጪአዊ ሁኔታ መልካም መደላድል ላይ አላረፈች እንደሆነ እንጂ በዳር - ድንበሯ እንኳ አትደራደርም!! ይህን የማያውቁ አካላት አንዳች የድፍረት እርምጃ እንውሰድ ቢሉ፤ “ውሻ በእግር መምታት፣ እንካ ሥጋ ብላ ማለት” የሚባለውን የአበው ተረት መዘንጋት ነው!!

Read 8270 times