Saturday, 23 April 2016 10:48

የአትሌቶች ስልጠና፣ አመጋገብና ጤና

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(5 votes)

 ክፍል 2

     አቶ ዘሩ በቀለ የአትሌቲክስ ተመራማሪ ናቸው። የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በስፖርት ሳይንስ ሲቀበሉ በአትሌቲክስ ስልጠና ደግሞ የማስተሬት ዲግሪያቸውን ሰርተዋል፡፡ በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ (IAAF) የአሰልጣኞች አሰልጣኝነት ደረጃ 1 (LEVEL 1 ) ማዕረግ አላቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአትሌቲክስ ፊዚዮሎጂን  ከአልቲቲዩድ በሚያገናኝ ጥናት ፒኤችዲ ድግሪያቸውን በዩኒቨርስቲ ኦፍ ኩዋዙሉ ናታል ደቡብ አፍሪካ እየተከታተሉ ይገኛሉ። በተማሪነት ዘመናቸው በአምቦ ዩኒቨርስቲ እግር ኳስ ቡድን ተጨዋች ነበሩ፡፡ በእግር ኳስ ፌደሬሽን ተመዝግቦ የሚወዳደር የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቡድን አሰልጣኝ በመሆንም አገልግለዋል፡፡ በስፖርቱ አስተዳደር ላይም ሰፊ ልምድ ያላቸው አቶ ዘሩ በቀለ፤  በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ማህበር በመመስረትና ማህበሩን በምክትል ፕሬዝዳንትነትና ዋና ፀሃፊነት ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ‹‹የኤክስትራ ካሪኩለር ኤንድ ስፖርትስ አሶሴዬትስ›› ዲን የነበሩም ሲሆን በኢትዮጵያ  ወርልድ ቴካንዶ ፌደሬሽንም በስራ አስኪያጅነት ሠርተዋል፡፡ ከአትሌቲክስ ጋር በተገናኘ እንደ ባለድርሻ አካል የሚጠቀሱ ባለሙያ ናቸው፡፡ በአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥ ያገለገሉ ሲሆን በከፍተኛ ደረጃ ባለሙያነት በተለያዩ ምርምሮች፤ በቡድን በማካሄዱ ጥናቶች በቅርቡ ‹‹ንፁህ ስፖርት፤ ንፁህ አትሌቲክስ›› በሚል ጥናታቸው ሳይንሳዊ የስልጠና መዋቅሮችን ለማስፋፋት በሚያግዙ አቅጣጫዎች ዙርያ ለስፖርት ጋዜጠኞች ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ ከስፖርት አድማስ ጋርም ሰፊ ቃለምልልስ  አድርገዋል። የቃለምልልሱ ሁለተኛው ክፍል ከዚህ በታች የቀረበው ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት በዚህ አምድ የቀረበው ቃለምልልስ የተቋጨው፤ አትሌቶችን የሰፕልመንት መድሃኒቶች ለመውሰድ እንዲገደዱ እና ለዶፒንግ ችግር እንዲጋለጡ ከሚገደዱባቸው ሁኔታዎች አንዱ ስልጠናው በሳይንሳዊ መንገድ ባለመመራቱ መሆኑን በገለፁበት ማብራርያ ነበር። ተጨማሪ አስተያየቶችን በመስጠት ወደቃለምልልሱ ሁለተኛው ክፍል እንሸጋገር…
አንድ አሰልጣኝ የሚያሰለጥነውን አትሌት በየዕለቱ መከታተል አለበት፡፡ ትናንት በልምምድ የነበረው ብቃት ወይም ሁኔታ፤ አመጋገቡ፤ እንቅልፉ ላይ ችግር መኖሩን ካወቀ  ዛሬ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ብቃት በየጊዜው በሚለካበት ሁኔታ አስፈላጊውን ግምገማ ማድረግ ይቻላል። ብቃት በየጊዜው እየወረደ የሚመጣ ከሆነ ማስተካከያዎች ለማድረግ ያግዛል፡፡ የሚሰራበት ስልጠና እና ልምምድ ችግር ካለበት የሚረጋገጥበት ነው፡፡ ምናልባትም በቂ እረፍት ካለማግኘትም ፕርፎርማንስ ሊወርድ ይችላል፡፡  አትሌቱን በቅርብ በመከታታል ግን መፍትሄዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡ በሳይንሱ የአትሌቱ ብቃት በተወሰኑ ልምምዶች እየወረደ መጥቶ ተመልሶ እያደገ የሚመመጣበት ሁኔታ ማወቅ ይቻላል፡፡ ይህን ክትትል በአግባቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ብቃት በየጊዜው እየወረደ ከሄደ ከውድድር ሊያስወጣ ይችላል፡፡
በአጠቃላይ ስለዶፒንግ፤ ስለ ስልጠ እና ልምምድ ስናወራ ከሁሉ ነገር ቀድሞ የሚመጣው የአትሌት ጤንነት ነው፡፡  በዶፒንግ ብቃትን ማሳደግ መቻሉ ሳይሆን የተወሰደ መድሃኒት ጤናን ይጎዳል አይጎዳም ወይ የሚለው ሁኔታ ነው በመጀመርያ መጠየቅ አለበት፡፡ ለምን በስፖርቱ መርህ የመጀመርያው ትኩረት ቅድሚያ የአትሌት ጤና የሚል ነው፡፡ ከዚያም የውድድር ተሳትፎው እና ውጤቱን መመልከት ነው፡፡ በተለያዩ የስልጠና አካሄዶች ላይ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባ ነገር የአትሌት ጤንነት ነው።  በተከታታይ ውድድሮች የሚዳክሙ፤ በቂ የማገገሚያ ጊዜ የሌላቸው አትሌቶች በየጊዜው ብቃታቸው እየወረደ ይሄዳል፡፡ ይህን ለመከላከል ምናልባትም ወደ ዶፒንግ ተጠቃሚነት ሊገነባ ይችላል፡፡ አትሌት በዶፒንግ ዋናው ተጐጂ መሆኑን ቅድሚያ ሰጥቶ መነጋገር ያስፈልጋል። አትሌቶችን  ዶፒንግ ወስደዋል ተብሎ በሚዲያውም በሌሎች ባለድርሻ አካላትም መወንጀል እና በጥፋተኝነት መፈረጅ ተገቢ አይደለም፡፡ አትሌቶቹ በመድሃኒቱ ምክንያት በጤናቸው እና በህይወታቸው ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ማመዛዘን ተገቢ ይሆናል፡፡
ንፁህ ስፖርት የምንለው አትሌቶች  ጤናማ ሆነው፤ በስነልቦናው ጠንክረው፤ ሰርተው ለፍተው ጥሮ ግሮ  ውጤት ማግኘት ሲችሉ ነው፡፡ ለጤናቸው ትኩረት የማይሰጡ፤  ህግና ደንብን የማያከብሩ አትሌቶች ስለንፁህ ስፖርት አያውቁም፡፡ ዶፒንግ የሚጠቀም አትሌት ጤንነቱ ትኩረት ያልሰጠ ነው፡፡ የዶፒንግ ክለከላውም ከአትሌት ደህንነት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የአትሌትን ጤንነት ጉዳት ላይ የሚጥል፤ አግባብ ያልሆነ ብልጫ እንዲኖረው እና የውድድር ውጤት ሊያዛባ የሚችል ተግባር ዶፒንግ ነው፡፡ የተከለከለ እና የሚያስቀጣም ሆኗል፡፡
ስለልምምድም ስናወራም  አትሌት ጫና ሲበዛበት ውጤት አያመጣም ብሎ ለመጨነቅ አይደለም፡፡   የጤንነት መጓደል እንዳይፈጠር፤ ጉዳት እንዳይጋለጥ፣ በሴቶች ደግሞ የወር አበባ ኡደት መዛባት እንዳይኖር ለመከላከል ነው፡፡ ጤነኛ አትሌት ሲኖር ነው ወደ ብቃት ማተኮር የሚገባው፡፡
በነገራችን ላይ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በረጅም ርቀት በዓለም አትሌቲክስ ላይ ያሳዩት የበላይነት በሳይንሳዊ መንገድ ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ ለምን ቢባል በሁለቱም አገራት ከሳይንሳዊ ስልጠና ይልቅ በልምድ እና በተፈጥሯዊ ብቃት የማሸነፉ እድል ለብዙ ዓመታት ሲታይ ቆይቷል፡፡ አንተ ንፁህ ስፖርት፤ ንፁህ አትሌቲክስ ብለህ ባቀረብከው የጥናት ወረቀት ስለምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ውጤታማነት በዝርዝር ያስቀመጥካቸው ነጥቦች አሉ ፤ ለመሆኑ ለስኬታቸው ምስጥሩ ምንድነው ከምን ጋርስ የተገናኘ ነው?
ጥናቶች መደረግ የጀመሩት በቅርቡ ነው፡፡ በተለይ በኬንያ አትሌቶች ላይ ብዙ ጥናቶችና ምርምሮች ተካሂደዋል፡፡ የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ከሌላው ዓለም የተለየ ዘረመል (Gene) የላቸውም፡፡ በፅናት ፈታኝ ሁኔታዎችን የሚቋቋሙበት ዘረመል በጠንካራ የልምምድ መርሐግብር ማሳደግ ችለዋል፡፡  በርግጥ መላምቶች ነበሩ። ቀነኒሣም ሆነ ኃይሌ ከሌላው ዓለም የተለየ አፈጣጠር የላቸውም፡፡ በከፍተኛ አልቲትዩድ ላይ ተወልደው፣ አድገዋል፡፡ ስለሆነም ፅናት በሚጠይቁ የስፖርት ውድድሮች ውጤታማ መሆን ችለዋል፡፡ በጠንካራ ልምምድ እና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተሻለ ብቃት አሳይተው ተሳክቶላቸዋል፡፡
ነባሮቹ አትሌቶች ከብዙ የስፖርት ባለሙያዎች ምክሮችን በተለያየ መንገድ ያገኛሉ፡፡  ማናጀሮቻቸው ከዓለምአቀፍ የስፖርቱ ኤክስፐርቶችና ሳይንቲስቶች ጋር ይሰራሉ፡፡ ስለሆነም በፊዝዮሎጂ፣ በስነምግብ እና በጤና ጉዳዮች የሚያገኙአቸው ምክሮች ይኖራሉ፡፡ አሰልጣኞችም አትሌቶችም የሚያውቋቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የልምምድ ጫና እንዴት ይጨምራል ፤ ወይም ይቀንሳል  በሚሉ የሳይንሳዊ ስልጠና መርሀ ግብር ይሠራሉ፡፡
ወሳኝ የሆኑ ተጨማሪ ስራዎች ግን እየተካሄዱ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የላብራቶሪ ክትትሎች ምዝገባዎች እና ጥናቶች እየተሠራባቸው ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ሳይንሳዊ የስልጠና መንገዶች አልተቀረፁም፡፡ የአትሌቶች የልምምድ ደረጃ፣ አመጋገብ፣ የውሃ አጠቃቀም ሳይንሳዊ በማድረግ ለኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች የተሻለ ብቃት መፍጠር ይቻላል፡፡
በርካታ ጥናቶችና ምርምሮች  የተደረጉ ሲሆን ከልሶ በመመልከት እና በማገናዘብ አንዳንድ መላምቶች ተቀምጠዋል፡፡ በሳይንስ ብዙ የተረጋገጡ ነገሮች የሉም፡፡ ኢትዮጵያውያኖች ከሌላው በተለየ ለጽናት የሚሆን የተለየ አፈጣጠር የላቸውም፡፡ የእንግሊዟ ፓውላ ራድክሊፍ፣ የብራዚል፣ ሠሞሮኮ ምርጥ የማራቶን ሯጮች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ማራቶን ሯጮች የተለየ ተፈጥሮ ቢኖራቸው ሁሉንም ውድድሮች ያለተቀናቃኝ ባሸነፉ ነበር፡፡
ስለዚህ ከፍተኛ አልቲትዩድ ከተፈጥሮ ብቃት ጋር ተደምሮ በማያቋርጥ ጠንካራ የልምምድ መርሃ ግብርና ዲሲፕሊን ለውጤታማነት ያበቃል፡፡ ከፍተኛ አልቲትዩድ ላይ በመፈጠር ብቻ ቢሆን ኖሮ ከቦልቪያ፣ ከፔሩ እና ከሜክሲኮ ምርጥ ማራቶን ሯጮች መውጣት ነበረባቸው፡፡ የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች በረዥም ርቀት ላይ ያላቸው የተለየ ብቃት ጠንካራ የልምምድና የዲሲፕሊን መርሃ ግብራቸው ተጨምሮ ነው፡፡
ነባሮቹ  የኢትዮጵያ አትሌቶች የሩጫ ዘመናቸው በአማካይ ከ10 ዓመት በላይ መሆኑን ማንሳት እፈልጋለሁ። ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ ቀነኒሣ በቀለ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ጥሩነሽ ዲባባ መሠረት ደፋር የብዙ ዓመት ልምድ አግኝተዋል። ያለመዋዠቅ የሄደ ነው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመጡ የኢትዮጵያ አትሌቶች ግን የሩጫ ዘመናቸው በጣም አጭር ነው፤ ከምን የተፈጠረ ነው፡፡
በሳይንሳዊ ሁኔታ ምላሹን ባስቀምጥልህ  አትሌቲክስ ስፖርት በረዥም ጊዜ ልምድ ውጤቱ የሚጠናከር ነው፡፡ “Late specialization” ይባላል፡፡ ይህ ማለት አንድ አትሌት ልምምድ ከጀመረ ከ10ና ከ15 ዓመታት በኋላ የብቃቱ ጫፍ ላይ እነ ኃይሌ ከ20 ዓመታት በላይ ሮጠዋል፡፡ የዛሬ አትሌቶች በ20 ዓመታቸው ማራቶን ሮጠው በ2 እና በ3 ዓመት ከውድድር ይሆናሉ፡፡ አሁን በብዛት አትሌቶች በአማካይ 4 እና 5 አመት ቢሮጡ ነው፡፡ ኃይሌ ለ15 እና ከዚያም በላይ ከሮጠበት ብቃት ጋር ለመወዳደር አይቻልም፡፡ ፅናት በሚጠይቁ የስፖርት ውድድሮች የድሮዎቹ አትሌቶች የደሱበትን የብቃት ደረጃ ያመለክታል፡፡
አትሌቶች ከረዥም የሩጫ ዘመናቸው በኋላ አስፈላጊውን የዕድገት ሂደቶች በማለፍ ወደ ማራቶን ሲሸጋገሩ ውጤታማነታቸው አስተማማኝ ይሆናል፡፡ የማራቶን ውድድርን ለማሸነፍ ብዙ ዓመታት የሩጫ ልምድ ያስፈልጋል፡፡
ውጤታማ አትሌቶች የበርካታ ዓመታት የሩጫ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ የሩጫ ልምድ ብዙ ኪሎሜትሮችን መሮጥ ነው፡፡ የውጤቱ ድርብርብ የጡንቻዎችን ጥንካሬ ያሳድጋል፡፡ አንዱ የንፁህ ስፖርት፣ የንፁህ አትሌቲክስ መርህ በስፖርት ዲስፒሊንህ ደረጃ በደረጃ እያደጉ መሄድ እና የረዥም ጊዜ ልማድ ማካበት ነው፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የሚያሳስቡ ሁኔታዎችን ትመለከታለህ፡፡ ብዙ ክለቦች ያለባቸው ችግር ነው፡፡ የሚይዟቸው አትሌቶች ገና በ20 ዓመታቸው ብቅ እያሉ ተቃጥለው ጉልበታቸውን አቃጥለው የሚጠፉበት ሁኔታ ነው፡፡ አንዳንድ አትሌቶች አንድ ውድድር አድርገው ከዚያም ከሩጫው ይጠፋሉ፡፡ አሰልጣኞችን ለዚህ ጉዳይ ብታነጋግራቸው የሁኔታውን አሳሳቢነት ትረዳለህ፡፡  በአገር አቀፍ ደረጃ ምክክር ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ  ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ አንድ አትሌት ማራቶን መሮጥ ያለበት በስንት ዕድሜው ነው፣ የአትሌቲክስ ስፖርት ዕድገትም የራሱ መዋቅር ያስፈልገዋል፡፡ ከመካከለኛ ርቀት ወደ ረጅም ርቀት ከዚያም ወደ ማራቶን ደረጃውን የጠበቀ እድገት መፈጠር ይኖርበታል፡፡ የአትሌቶች የውድድር ዕድገት አስፈላጊ ነው፡፡ በ20 ዓመታቸው ማራቶን የሚሮጡ አትሌቶች አንድ ከሮጡ በኋላ ሌላ ውድድር ለመካፈልና ውጤታማ ለመሆን ይቸግራቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ አንዳንድ አትሌቶችን ያላቸውን ብቃት ለማሳደግ በማለት ወደ ዶፒንግ ተጠቃሚነት ሊገፋቸው ይችላል፡፡
ይህን የአትሌቶችን ያለአግባብ መቃጠል መቆጣጠር በዋናነት የአሰልጣኞች የስራ ኃለፊነት እና ድርሻ ነው። የአሰልጣኝ ሥራው የውድድር መርኅ ግብር ሰጥቶ ብቻ መቆጣጠር አይደለም፡፡ የአትሌቶች የዕውቀት ደረጃን አገናዝቦ በልዩ ክትትልና ምክክር መስራት ይኖርበታል። አትሌቶች አስፈላጊውን ሂደት በጠበቀ መልኩ እንዲሠሩ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል የድሮዎቹ አትሌቶች ያላቸውን ልምድ በማካፈል መስራት አለባቸው። የነባር አትሌቶችን ልምድ የውጭ አትሌቶች በተለያዩ መንገዶች ይጠቀማሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥም የልምምድ ልውውጥ የሚኖርበት አሰራር መፍጠር አለበት፡፡ ለአትሌቲክስ ዕድገት የሚያስፈልጉ የምክክር መድረኮች ተፈጥረው ብዙ መሠራት አለበት፡፡ እነ ኃይሌ፣ ደራርቱ ቀነኒሣ የሩጫ ዘመናቸውን ለረጅም ጊዜ ጠብቀው የሄዱበት የውጤታማነት ምስጢር የሚያካፍሉበት መድረክ መፈጠር አለበት፡፡ አዳዲስ አትሌቶች ከነባሮቹ የሚያገኙትን ልምድ በቀላሉ ይቀበላሉ፡፡
ወጣት እና አዳዲስ አትሌቶች ከነባር አትሌቶች የሚያገኙትን ምክርን ተጠቅመው ሲሰሩ እና ሳይንሳዊ መንገድን ከተከሉ ብቃታቸውን በአግባቡ ገንብተው በንፁህ ስፖርተኛነት ይሳካላቸዋል፡፡ ነባር አትሌቶች ልምዳቸውን ለማካፈል የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በራሳቸው ተነሳሽነት ማከናወን አለባቸው፡፡ ነባር አትሌቶች በሚዲያ ወይንም በሌላ መድረክ እንዴት እንደሚሮጥ፤ ስለ አመጋገብ፤ በአጠቃላይ ያላቸውን ልምድ ቢመክሩ ጥሩ ነው፡፡ ይሄ ብሄራዊ ግዴታ ነው፡፡ የዳበረን ልምድ ማካፈል እና ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ይህን ተግባር በአትሌቶች ማህበር በኩል ሊዘጋጅም ይችላል፡፡ ነባር አትሌቶች በንፁህ ስፖርት፤ በንፁህ አትሌቲክስ ያለፉበትን ሂደት ሲያስተምሩ አዳዲስ እና ወጣት አትሌቶች ብዙ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
ነባር አትሌቶች እነዚህን ያልካቸውን ወሳኝ ተግባራት ለማከነናወን በቂ ጊዜ ላይኖራቸው ይችላል፤ ወይም ተነሳሽነቱ ደካማ ይሆናል፤ በሌሎች ባለድርሻ አካላት በኩልም ምንም አይነት የጥናት ፅሁፎች ምርምሮችእየተደረጉ አይደለም፤ በአትሌቶች የሩጫ ዘመን ተመክሮ መፅሃፍት እየተዘጋጁ አይደለም እና ምንድነው ለማነሳሳት መሰራት ያለበት
ከዘረዘርካቸው ነገሮች በተለይ ስለመፅሃፍት ያነሳኸው ላይ አስተያየት መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ ለምሳሌ በወታደራዊ ሙያ የሚያልፉ ሰዎችን ላንሳልህ፡፡ የዕለት ስራቸውን በማስታወሻ የመያዝ ልምድ ስላላቸው ብዙዎቹ መፅሃፍ በቀላሉ ይፅፋሉ፡፡ በተለይ ግን በአገራችን የስፖርት ሰዎች የየቀኑን ተግባር በማስታወሻ መልክ ፅፎ የማስቀመጥ ባህል የላቸውም፡፡  በአትሌቲክሱም አሰልጣኞችም ሆነ አትሌቶች ይህን ሲያደርጉ አይሰተዋልም፡፡ በየእለቱ ማስታወሻዎችን የማትይዝ ከሆነ ደግሞ ለብዙዎች የሚጠቅም መፅሃፍ አደራጅቶ ለማዘጋጀት አይሆንም፡፡ አትሌቶች በሩጫ ዘመናቸው የሚያልፉበትን እድገት እና ውጤት በአግባቡ ማስታወሻ የመያዝ ልምድ ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ለተተኪው ትውልድ ከፍተኛ ጥቅም እና አስተዋፅኦ የሚኖረው መፅሃፍ ለማዘጋጀት ያስችላል፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ያሉት ነባር አትሌቶች የሩጫ ዘመን ተመክሯቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ በማራቶን ላይ ያተኮረ መፅሃፍ ቢያዘጋጅ፤  ቀነኒሳ በረጅም ርቀት እና በአገር አቋራጭ ስላለው ልምድ የሚተርክ መፅሃፍ ቢኖር… የኢትዮጵያ  አትሌቶች ብቻ አይደለም በመላው የአትሌቲክስ ዓለም ከዳር እስከዳር ተፈላጊ ይሆኑበታል፡፡ ነባሮቹ አትሌቶች ብቻ ሳይሆን አሁን ያለውም ትውልድ አትሌቱም አሰልጣኙም  በዚህ አቅጣጫ መስራት ይኖርበታል፡፡
በአጠቃላይ በሳይንሳዊ መንገድ የአትሌቶችን ብቃት ማሳደግ ይቻላል ነው
አዎ በሳይንሳዊ መንገድ ብቃትን ማሳደግ ይቻላል፡፡ በንፁህ ስፖርት ሳይንሳዊ መንገድ እየተከተሉ ብቃታችውን እያሳደጉ ያሉ ኢትዮጵያውን አትሌቶችም አሉ፡፡ ምንም አይነት ሰፕልመንት እና መድሃኒት የማይወስዱ ናቸው። በየእቤታቸው የሚዘጋጅላቸውን ምግብ ብቻ እየወሰዱ የሚሰሩ አሉ፡፡ በጅምናዚዬም እየሰሩ፤ አመጋገባቸውን በጥሩ እና በተመጣጠነ ሁኔታ እየተከተሉ፤ የግል አሰልጣኝ ያላቸው ናቸው፡፡ በተለይ በግል አሰልጣኝ የሚሰራ አትሌት ተጠቃሚ ነው፤ ስለሚያሰለጥነው አትሌት ቅርበት እና ሙሉ መረጃ ያለው አሰልጣኝ በአትሌቱ ዕድገት ከፍተኛ እገዛ ማድረግ ይቻላል፡፡ አንድ አሰልጣኝ መቼ እረፍት ማድረግ እንዳለብህ ፤ መቼ መስራት እንዳለብህ ጠንቅቆ ማወቅ አለበት፡፡ የአሰልጣኙ እና የአትሌቱ ግንኙነት እንደ አባት እና ልጅ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሳይንሳዊ ስልጠና ሂደት ውስጥ አንድ አሰልጣኝ የሚያሰልጥናቸውን አትሌቶች የፍቅር  ወይም የትዳር ግንኙነት፤ ከቤተሰቡ ጋር ያለው ሁኔታ፤ በልምምድ ሰዓት ከጭንቀት እና ከማናቸውም ውጥረት ውጭ ለመስራት የሚችልበት እውቀት ያስፈልገዋል፡፡
በኢትዮጵያ  ውስጥ በሳይንሳዊ ስልጠና መንገድ ለመስራት አቅሙ ያላቸው አትሌቶች አሉ፡፡  በአመጋገብ፤ በጂም ስራቸው፤ በጤንነታቸውን ክትትል የስፖርት ባለሙያዎችን ቀጥረው ማሰራት ይችላሉ፡፡ የአንድ አሰልጣኝ ድጋፍሰጪ ባለሙያዎች እንደተዘረዘሩት ነው፡፡ በአሁኑ ግዜ በአገሪቱ ተገንብተው የሚሠሩት አካዳሚዎች፤ ክለቦች እና ቡድኖች በስልጠና መዋቅራቸው መጠናከር የሚኖርባቸው በዚህ መንገድ ነው፡፡ በሳይንሳዊ መንገድ ለመስራት ለምሳሌ ያህል አንድ ክለብ በአሰልጣኞች ቡድኑ የአትሌቲክስ አሰልጣኝ በረጅም ርቀት ወይምን በአጭር ርቀት፤ ከዚያም የአካል ብቃት ኢንስትራክተር፤ የስነምግብ ባለሙያ፤ ፊዝዮቴራፒስት እና የህክምና ባለሙያ አብረው መስራት አለባቸው፡፡ በተለይ ለፊዝዮቴራፒ ባለሙያዎች  በቂ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ የአሰልጣኞች ቡድኑ በዚህ መንገድ በተሟሉ የባለሙያዎች ስብስብ የሚሰራ ክለብ አትሌቶች በንፁህ ስፖርት ብቃታቸውን አሳድገው ከፍተኛ ተፎካካሪ ለመሆን ይበቃሉ፡፡
በኢትዮጵያ  አትሌቲክስ ስፖርት  አንድ ትልቅ ችግር አለ፡፡ ቀላል ተግባር ነበር፡፡ የአትሌቶችን የዕለት ተግባራት፤ እንቅስቃሴ፤ የልምምድ መርሃግብርና አፈፃፀም በዝርዝር መመዝገብ ብዙ የተለመደ አይደለም፡፡ ይህንን  በተገቢው መንገድ ማከናወን በአሰልጣኙም በአትሌቱም መለመድ አለበት፡፡ ሳይንሳዊ የስልጠና ስርዓት ተከትሎ ወቅታዊ ብቃትን በመገምገም መስራት ያስፈልጋል፡፡ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በጥናት እና ምርምር ላይ የተመሰረቱ ሳይንሳዊ የስልጠና መዋቅሮችንም ለመቅረፅም ያግዛል፡፡
አሰልጣኞች እና በየአካዳሚው የሚሰሩ ባለሙያዎች ደረጃውን የጠበቀ የስልጠና ፖሊሲ እና አካሄድ መፈጠር አለበት፡፡ የምል መላ፤ የውድድር አይነት አመዳደብ ፤ የስልጠና ደረጃዎች እና ሂደቶች ላይ አገር አቀፍ መመርያ ያስፈልጋል፡፡ ክለቦች በሳይንሳዊ መንገድ ለመመራት በቀላሉ ብዙ ማድረግ ይችላሉ በየዓመቱ የሚመለምሏቸውን አትሌቶች ከሚያሰሯቸው አሰልጣኞች አንፃር ባለሙያዎች ቀጥረው መሻሻላቸውን ፤ወይንም አለመሻሻላቸውን በማስገምገም መስራት ይችላሉ፡፡ በየአካዳሚዎቹ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መሳርያዎችን ማስገባት እና መጠቀም እየተጀመረ ነው፡፡ አትሌቶች በተመጣጠነ ደረጃ የአሰልጣኝ እና የድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች ካሏቸው በንፁህ ስፖርት በንፁህ የአትሌቲክስ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

Read 7461 times