Saturday, 23 April 2016 10:46

በህንድ ከ330 ሚ. በላይ ዜጎች የድርቅ ተጠቂ ሆነዋል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 በህንድ ለሁለት ተከታታይ አመታት የዝናብ እጥረት መከሰቱንና የሙቀት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ከ330 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቂ እንዳደረገ የአገሪቱ መንግስት ማስታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በአብዛኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች የሙቀት መጠኑ ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ሆኗል ያሉት የአገሪቱ ባለስልጣናት፣ የውሃ እጥረትና ሌሎች ችግሮች ተጠቂ የሆኑት የአገሪቱ ዜጎች ቁጥር በቀጣይም ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
በአገሪቱ  ላለፉት ሁለት ተከታታይ አመታት የዝናብ እጥረት መከሰቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ከፍተኛ የውሃ እጥረት መፍጠሩንና ተላላፊ በሽታዎች በርካታ ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት እየዳረጉ እንደሚገኙና ድርቁ፣ የአገሪቱን ሩብ ያህል ግዛት በሚሸፍኑ 256 አውራጃዎች መስፋፋቱን ገልጧል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውና የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸው የተነገረ ሲሆን፣ በዝናብ እጥረት ሳቢያ ላለፉት ሁለት አመታት ምርታማነት መቀነስ መታየቱ በቀጣይ የከፋ ርሃብ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩንም ዘገባው አስረድቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ለዜጎች ውሃ ከማቅረብ ባለፈ፣ ከድርቁ ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተረባረበ እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡

Read 1255 times