Saturday, 23 April 2016 10:43

የፕሬስ ነጻነት በአለማቀፍ ደረጃ እያሽቆለቆለ ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 - ኤርትራ በከፋ የፕሬስ ነጻነት አለምን ትመራለች
                - ኢትዮጵያ የ142ኛ ደረጃን ይዛለች

      ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ የተባለው አለማቀፍ የፕሬስ መብቶች ተሟጋች ተቋም ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው የ2016 የአለማችን የፕሬስ ነጻነት አመልካች ሪፖርት፣ የፕሬስ ነጻነት አፈና በአለማቀፍ ደረጃ መባባሱንና ጋዜጠኞች በሙያቸው ሳቢያ እስራትን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶች እንደሚደርስባቸው አስታወቀ፡፡
ተቋሙ በአለማችን 180 አገራት ላይ በሰራው ጥናት፣ መንግስታት ለጋዜጠኞች ያላቸው ፍራቻ እየጨመረ በመምጣቱ በ2015 በነጻው ፕሬስ ላይ ልዩ ልዩ ጫናዎችን ሲያደርጉ እንደነበርና ጋዜጠኞች ነጻ ሆነው ዘገባዎችን ለመስራት በርካታ እንቅፋቶች ይገጥሟቸው እንደነበር ማረጋገጡን ገልጧል፡፡
የሚዲያ ነጻነት፣ ግልጽነት፣ የህግ የበላይነትና ሌሎች መስፈርቶችን በመጠቀም ተቋሙ የሰራው አመታዊ ሪፖርት በ2016 የአለማችን የፕሬስ ነጻነት ደረጃ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘቺው ፊንላንድ መሆኗን ጠቁሞ፣ ኒዘርላንድስና ኖርዌይ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ መያዛቸውን አስታውቋል፡፡
የከፋ የፕሬስ ነጻነት ያለባትና ከአለማችን አገራት በመስኩ የመጨረሻውን ደረጃ የያዘቺው ኤርትራ ናት ያለው ተቋሙ፣ ሰሜን ኮርያ እንደምትከተላት ጠቁሞ፣ ኢትዮጵያ ከአለማችን 180 አገራት የ142ኛነት ደረጃን መያዟንም ሪፖርቱ ገልጧል፡፡
በሁሉም የአለማችን አካባቢዎች የፕሬስ ነጻነት እየቀነሰ መጥቷል ያለው ተቋሙ፣ በተለይ ደግሞ በደቡብ አሜሪካ አገራት ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ጠቁሞ፣ በአመቱ የፕሬስ ነጻነት በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ የመጣባቸው የአለማችን አገራት ቱርክና ግብጽ መሆናቸውን አብራርቷል፡፡

Read 1231 times