Saturday, 25 February 2012 13:47

እሰይ ስብሃት አልሞተም!!

Written by  ማትያስ ሰለሞን (ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ
Rate this item
(0 votes)

ዶርማችን ውስጥ ጠዋት አልጋዬ ላይ ሆኜ ሬድዮ እየሰማሁ ጓደኛዬ አዱኛ text አደረገልኝ፡፡ የጋሽ ስብሃትን “ሞት” የሚያረዳ ነበር - መልእክቱ፡፡ በጣም ደነገጥኩ፡፡ ተንተባተብኩ! የምናገረው ጠፋብኝ፡፡ “ምን ሆንክ?” አለኝ ጓደኛዬ መንጌ፡፡ ነገርኩት እሱም ደነገጠ፡፡ ውሸት በሆነ ብዬ ተመኘሁ፡፡ ግራ ገባኝ፡፡

ሬድዮኑን ዘጋሁና ቴንሽን ቦክሴን ሸፈንኩ፡፡ “ልፀልይ” አልኩት ጓደኛዬን፤ ዝም አለኝ፡፡ “ዛሬ የማከብረው የማደንቀውና የማፈቅረው ደራሲና ፈላስፋ “ሞተ” አሉኝ፡፡ አምላኬ ሆይ ውሸት አድርገው እባክህን! እባክህን አምላኬ!”

ፀሎቴን ስጨርስ በጀርባዬ ተጋደምኩ፡፡ አዱኛ ውሸቱን በሆነ እያልኩ፡፡ ሳላስበው ድምፅ አውጥቼ ነበረ ለካ፡፡ ጓደኛዬ ሰምቶኝ “እንደዚህ ይቀልዳል እንዴ?” አለኝ፡፡ “ግን ቀልዱን በሆነ፡፡ በናትህ እየቀለደ ቢሆን!” አልኩት፡፡

ማረጋገጥ ፈለኩኝ፡፡ ስልኬ ሰባ ሳንቲም ነው ያላት፡፡ ደወልኩለት - ለአዱኛ፡፡ “ውሸትህን በሆነ፤ ስትቀልድ በሆነ” አልኩት፡፡

“እውቴን ነው አዝናለሁ” አለኝ፤ ”ሰሞኑን ታሞ ነበር እኮ አልሰማህም?”

አሁን ተስፋ ቆረጥኩ፡፡ ስልኩን ከዘጋሁት በኋላ አዱኛ አስጠላኝ፡፡ በጣም አስጠላኝ፡፡ ምን ቸገረው እስቲ ባይነግረኝ? አልኩ፡፡ ያን ሁሉ ግጥምና ዜማ ባንቆረቆረልኝ ድምፁ ይሄን መራራ እውነት ይነግረኛል? ቀሽም ነው! በጣም ቀሽም!

ተነስቼ ልብሴን ለባበስኩ፡፡ መስታወት እያየሁ “ዛሬ April the fool ነው እንዴ?” አልኩኝ መስታወቱ ላይ አጥፍጬ፡፡ “አይደለም ገና’ኮ February ነው፡፡” አለኝ ጓደኛዬ፡፡

ካፌ ገብተን ቁርስ እየበላን በሬዲዮ የአንዲት ሴት ጋዜጠኛ ድምፅ ሰማሁ፡፡ እሷም ስብሀት “ሞቷል” ብላ እያወጀች ነበር፡፡ ተረበሽኩኝ፡፡ ማልቀስ ፈለግሁኝ፡፡ ከአይኔ ጠብ ያለ ነገር ግን የለም፡፡

ከጓደኛዬ ተለይቼ Space ገባሁ - ለመፃፍ ካልሆነም ለማንበብ፡፡ ግን ሁለቱም አልሆነም፡፡ አዕምሮዬ በጋሽ ስብሀት የ”ሞት” ዜና ተረብሿል፡፡

ሲልቪ ምን ትል ይሆን ይሄን ስትሰማ አልኩ፡፡ ክንፈስ ከራሱ ቀጥሎ የሚያከብረው ሰው ሲሞት ምን አለ? ባህራምስ? እንደ ልጅ ሚታዘዘው ጥላሁንስ? አማንዳ ዱቤስ? አይኔ በእንባ ተሞላ፡፡ አእምሮዬ ውስጥ ሽብር የተነሳ መሰለኝ፡፡ ሀሳቦቼ ከስክስ የወታደር ጫማ አድርገው አእምሮዬ ውስጥ የሚሻኮቱ የሚፋተጉ መሰለኝ፡፡ አናቴን ወቀሩት፤ በከስክሳቸው፡፡

ድንገት ሆዴን ቆረጠኝ፡፡ በፍጥነት ወደ ሽንት ቤት፡፡ 35 ደቂቃ አካባቢ እዚያ ቆየሁ፡፡ እዚያ ቁጭ ብዬ ብዙ ብዙ ስለሞት አሰብኩ፡፡ ጨርሼ ስወጣ አእምሮዬንም ሆዴንም ቀለለኝ፡፡ ጭንቀቴም ሀዘኔም መረበሼም ሳይወጣልኝ አልቀረም፡፡

ስብሀትን ሳውቀው ሰባት ስምንት አመት ይሆናል፡፡ በመፅሀፎቹ በጋዜጣ እና በመፅሄት ላይ በማነባቸው ፅሁፎቹ ነው ያወቅሁት፡፡ በአካል አግኝቼው አላውቅም፡፡ በፅሁፎቹ ውስጥ የማገኛቸው ሀሳቦቹ፣ አተያዩ፣ ፍልስፍናው እና ሰብዕናው ፍቅሬን አሸነፈው፡፡ አድናቆቴን ማረከው፣ አክብሮቴን ተቆናጠጠው፣ ነገሰበት፡፡ በየጊዜው አስበዋለሁ፣ አወራለታለሁ፣ እከራከርለታለሁ፣ እመሰክርለታለሁ - በፍቅሬና በአድናቆቴ ብርሃን፡፡ አሁንም ሀሳቤ ውስጥ አለ፡፡ ስብሃት አብሮኝ አለ፡፡ ታዲያ አዱኛና ጋዜጠኛዋ ምንድነው የሚወሻክቱት? ወይስ ሌላ ስብሀት ነው?

እነ አዱኛ ተሳስተዋል፡፡ ሞት የትንፋሽ መቋረጥ የደም ዝውውር መቆም አይደለም፡፡ ሞት ከሰው ሀሳብ፣ ከሰው ፍቅር፣ ከሰው አድናቆት መውጣት መባረር ነው (እቺ ሀሳብ ራሱዋ የሱ ነች) ስለዚህ ጋሽ ስብሃት አልሞተም፤ በፍፁም አይሞትምም!!! ምክንያቱም በብዙዎቻችን ሀሳብ ውስጥ… አድናቆት ውስጥ… ፍቅር ውስጥ… አለና! እርግጥ ነው ትንሽ እርቆናል፡፡

እርቆናል ማለት ግን ተለያይተናል ማለት አይደለም፡፡ ልክ እኔ መቀሌ ቤተሰቦቼ አዲሰ አበባ እንዳሉት ማለት ነው፡፡ እኔ መሬት ላይ እሱ ሰማይ ላይ ነው፡፡ የኪሎ ሜትሮች ልዩነት ነው፡፡

እርግጥ ነው ይዘቱንም ቀይሯል፡፡ ስጋ መጠቀም ትቷል፡፡ ያ ግን ያን ያህል ልዩነት የለውም፡፡ የመቀዳደም ጉዳይ ነው እንጂ እኛም ስጋችንን ትተን እንከተለዋለን፡፡

ኢንሻላህ!! እሰይ! እሰይ! እሰይ! ጋሽ ስብሀት አልሞተም አልኩ፡፡ ጭንቀቴ መረበሼ ለቀቀኝ፤ ሰላም ተሰማኝ፡፡ ስብሀት ሞቷል ብለው ሽብር ለቀውብኝ ከነበሩ ሰዎች ነፃ ወጣሁኝ! LONG LIVE SEBHAT!! ተመስጌን ጌታዬ!!!

 

 

Read 1737 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 13:52