Saturday, 23 April 2016 10:35

የሾላው ጥላ

Written by  ፍጹም ንጉሴ
Rate this item
(8 votes)

   ሾላው ሽማግሌ ነው፡፡ ሥሩ የተቀመጡትም አዛውንት፡፡ ከሁለት ሰው እቅፍ የሚተርፍ መቀመጫው ተገማምጧል፡፡ ጋደም ብለው ቢያዩት አሥቸጋሪ መልክአ ምድርን ይመስላል፡፡ አዛውንቱ በአንዱ ስንጥቅ ተሸንቁረዋል፡፡ ዕድሜ ቢቋጠሩ እኩያሞች ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ እንደውም አዛውንቱ ባይበልጡ፡፡ ወደ ዘጠና ተጠግተዋል፡፡ ሁልጊዜም ሾላውን ከሳቸው ዕድሜ ጋር ያመሳስላሉ፡፡ ያናጽራሉ፡፡ ሾላው ድሮ ድሮ ብዙ ፍሬ አብልቷል፡፡ እሳቸው አንድ ልጅ ብቻ ነው ያላቸው፡፡ ታዲያ ሃሳባቸው ሲነክሳቸው ፍሬያቸውን በህይወት ዘመናቸው ከከወኑት አስልተው ወደ ሾላው ይጠጋሉ፡፡ የሾላው ግርማ ሞገስ ይጋባባቸውና ቀጭን አጥንታም ደካማ ሰውነታቸውን በጋቢያቸውና በካፖርታቸው ውስጥ ሊያሳብጡት ይሞክራሉ፡፡ የዛጉ ጥርሶቻቸው ስለሚያሳፍሯቸው በተጨማጨሙ ዓይኖቻቸው ይስቃሉ፡፡ ቅርብ ያለ እንባቸው ይጨመቃል፡፡ በንቃቃታም ጉንጮቻቸውም ይሰርጋል፡፡
ከነጭ ጸጉራቸው የተሰራ የሚመስለው ጭራቸውን ወዲህ “ሿ” እያደረጉ ዙሪያቸውን አስተዋሉ፡፡ እግራቸው ስር ውሻና ድመት ለጥ ብለው ተኝተዋል። ፈቅ ብለው ዶሮዎች ክንፎቻቸውን ጠይሙ መሬት ላይ ዘርግተው ከቅንቅኖቻቸው ጋር ያቀነቅናሉ። ዘወር ብሎ ደሞ የሞላ ሆዳቸውን ቆዝረው የተኙ በግና ፍየሎች ያመሰኳሉ፡፡ ድንገት ደስ አላቸው። ሆኖም ሳይቆይ ፍርሃት ወረራቸው፡፡ ቀና አሉ፤ወደ ሾላው፡፡ ሰበብ ሆነና ተጣጥፎ የተነባበረ ቆዳቸውን ደጋግሞ ነባበረው፡፡ አጣጠፈው፡፡ ቀና ባሉበት ቅጽበት ፀሐይዋ በሾላው ፈዛዛ አረንጔዴ ቅጠሎች መሃል አጮለቀችባቸው፡፡ ከሾላው ጥላ ውጪ ሀሩሩ ይወርዳል፡፡ አዛውንቱ በሽንቁሩ የበለጠ ተሸነቆሩበት። ሌላ እሳቸውን መጨመር የሚችለው የግንዱ ሸለቆ ጐረሳቸው፡፡
የግንባታ ባለሙያ ከሆነው ልጃቸው ጋር ነው የሚኖሩት፡፡ አቅማቸው ከደከመና ባለቤታቸው ከሞቱ ወዲህ እዚህ ናቸው፡፡ ልጃቸው ጥሩ ሚስት አግብቶ ሦስት ልጆች ወልዷል፡፡ የመጀመሪያው አስራ ስድስት ዓመቱን ደፍኗል፡፡ ልቡ ሞልቷል። እኔን ያለእኔ ማንም አይናገር ብሏል፡፡ ህይወቴን በሙሉም ሆነ በጐዶሎ የሚያይብኝ አያስፈልገኝም ሲል ወስኗል። ትምህርቱን ወደማገባደዱ ከደረሰ በኋላ ይቁም ይቀጥል አይታወቅም፡፡ ይሄዳል…ይመጣል፡፡ ይገባል-----ይወጣል፡፡ ለሳቸው ሌላ ዜግነት ሳይቀይጥ አይቀርም፡፡ ሁለት ሆኖባቸዋል፡፡ ዓመሉም ቋንቋውም አለባበሱም። የሱ ታናሽ ሴት ናት ---- አስራ ሶስት ዓመት ሆኗታል፡፡
የተፈጥሮ ህግን የጣሰ ዕንስታዊ ለውጥ ይታይባታል፡፡ ደጋግማ ስለምትወድቅ ገና ሰባተኛ ናት። የቤት ውስጥ ስራ ብትሰራም የደጅ ሃሳቧ ያፈዛታል፡፡ በስራ ደክማ የምትመጣ እናቷ “አፎይም” “እግዚዎም” ለማለት አልተመቻትም፡፡ ሶስተኛው አስራ ሁለት ሆኖታል፡፡ ደፋርና ልባም ነው፡፡ ዕልኸኛ። ሰባተኛ ክፍል ደርሷል። መማር ይወዳል፡፡ ደጋፊ ይፈልጋል። አላገኘም፡፡ ያቅሙን ተፎካካሪ ሲያጣ ከሚፈራው ተፋጧል፡፡
አዛውንቱ በነዚህ ልጆች መኩራት ይፈልጋሉ። ደሞ ይፈሯቸዋል፡፡ የለውጣቸውን ፍጥነት የሚቆጣጠራቸው የለም፡፡ ወላጆቻቸው ግብግባቸው ከኑሮ ጋር ብቻ ሆኗል፡፡ በተለይ አባትየው ወደ መስክም እየወጣ ይከራርማል፡፡ ልጆቹን ማየት እንጂ መፈተሽ ተስኖታል፡፡ በቀለም ትምህርቱ የገፋ አለመሆኑም ሌላው ችግር ነበር፡፡ አዛውንቱ ይጨነቃሉ፡፡ በዕድሜ እንጂ በሌላ ከልጆቹ ፊት መሆን ተስኗቸዋል፡፡ ጨዋታቸው ቋንቋቸው አይገባቸውም። በሳቸው ዕድሜ አማርኛ ራሱ ስንቴ ራሱን እየገደለ ወለደ፡፡ ተረቶቻቸው ታሪኮቻቸው ባክነዋል፡፡ ወደ ሾላው አንጋጠጡ፡፡ ያለ እሳቸው ይህንን ሾላ በተስፋ የሚያየው የለም፡፡ ያፈራል ብለው ያስባሉ፤ ይጠብቃሉ፤ የሾላው ማፍራት የሳቸው ማፍራት እንደሆነም ያምናሉ፡፡ ጭራቸውን አወናጨፉ፡፡ ቀዝቃዛ ግን ብዙ ትንፋሻቸውን ለቀቁ፡፡ ሆኖም የሾላውን ጥላ ሳያጋምስ ጠፋ፡፡ ሀሩሩ ይወርዳል፡፡
መካከለኛ ግቢ ውስጥ ናቸው፡፡ ወደ ጥግ ብዙ ክፍሎች ያሏት ረዘም ያለች ዛኒጋባ ቤት አለች፡፡ ከጐኗ በጠቆሩ ቆርቆሮዎች የተቀጠለችው የእንስሶች ቤት የህልውና ጥገኝነት የምትጠይቅ ትመስላለች፡፡ ሾላው ካለበት ጥጋት በቀር ግቢው ስራ ፈት ሆኗል፡፡ ይህ ሾላ በልጃቸው ግቢ መገኘቱ ስንቱን እንዳስቀና ታዝበዋል፡፡ ሆኖም ማናቸውም አልተረዱትም፡፡ በተለይ “ማዕድ”…የሚሉት “ማድ”
ልጆቹ የውጭውን በር ለመክፈት ሲታገሉ ሰሟቸው፡፡ በጸሃይዋ ተዳክመዋል፡፡ በሩን ወርውረውት ወደ ሾላው ጥላ ወደሳቸው መጡ፡፡ ሴቷ መሃል ላይ ዝርግት ስትል ወንዱ እግራቸው ስር ዝርፍጥ አለ፡፡ አዛውንቱ በሃዘንና በፍቅር አዩዋቸው፡፡ ጭንቀታቸውን ለአፍታ ረሱት፡፡ የሾላውን ጥላነት እንዲህ በተግባር እያዩት አለማጣጣማቸው ግር ቢላቸውም ሾላውን እንደ ራሳቸው፣ እራሳቸውንም እንደ ሾላው እንደቆጠሩ ስለተሰማቸው በተዳከሙ ዓይኖቻቸው ፈገግ ሊሉ እየሞከሩ “ደከማችሁ ልጆቼ” አሉ፤ቆርፋዳ አጥንታም እጃቸውን ትንሹ ልጅ ራስ ላይ ጫን እያደረጉት፡፡ ልጁ እጃቸውን ገሸሽ ሲላቸው ደንገጥ ብለው በጥያቄ ሲመለከቱት፤
“አባባ ለምንድን ነው እንግሊዘኛ የማትችለው…?”
“ባለመማሬ…”
“ጣልያንኛ ይችል የለ እንዴ..” ስትል ሴቷ ጣልቃ ገባች፡፡ ልጁ እጁን “ወዲያ” እንደማለት አወናጨፈ፡፡ ከንፈሩን በቁጭት ነከሰ፡፡ ወደ በሩ አየ፡፡ እህቱ የገባት ትመስላለች፡፡
“ምን ሆነሃል ዳንኤል?” አሉ አዛውንቱ፡፡
“ዝም ብለህ ተረት ተረት ከምትነግረን ለምን ጣሊያንኛ አላስተማርከንም?” የፈሩት ባልጠበቁት መንገድ ገጠማቸው፡፡ ዝም ብለው ቆዩ፡፡ ዳንኤል ግን እንዳፈጠጠባቸው ነበር፡፡ እየቻሉ አለማድረጋቸው ለሳቸውም ግልጽ አልነበረም፡፡
“ፋቢዮ የሚሰድበንን እናውቅ ነበር” አለች ሴቷ ጥቂት ቆይታ፡፡ ዳንኤል “አዎ” ለማለት ከንፈሩን ነከሰ። ፋቢዮ የጣሊያን ክልስ ጐረቤቱ ነው፡፡ አንድ ዓመት የሚያንሰው ጓደኛው፡፡ ይቀናበታል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሰዎች ፋቢዮን ይወዱታል፡፡ ያከብሩታል፡፡ ቅላቱን ፀጉሩን ያደንቁለታል፡፡ አስተሳሰቡን ያወድሱለታል። ከፋቢዮ ጋር ካልሆነ ማንም ጉዳዬ አይለውም። ብቻውን ቢያገኙት “ፋቢዮስ” ሲሉ ይጠይቁታል እንጂ “ዳኒ ታዲያስ” አይሉትም፡፡ በትምህርትም ድሉ ሁልጊዜ የፋቢዮ እየሆነ ትንሽ ጨጓራው ትላጣለች። በአማርኛ ሳይቀር፡፡ በርግጥ ፋቢዮ በሃብታሞች ትምህርት ቤት ነው የሚማረው፡፡ ዳንኤልን ከንዴት የሚያስጥለው አልተገኘም፡፡
 “ዳንኤል…” አሉት አዛውንቱ፡፡ “እባክህ አትናደድ፤የኔ ልጅ ካሁን በኋላም ላስተምርህ እችላለሁ” አሉት በፀፀት፡፡
“አልደርስበትማ…” እጆቹን ሲያወናጭፍ ደብተሮቹ አዋራው ላይ ይበተኑበታል፡፡ በምሬት እየሰበሰበ፤“በዛ ላይ በእንግሊዝኛም በልጦኛል…” ሴቷ “ምሳችንን እንብላ..” ብላ ወደ ቤት ገባች፡፡
አዛውንቱ ፋቢዮን እንደ ልጅ አያዩትም፡፡ ይፈሩታል፡፡ ይጠሉታል፡፡ ግራ ይገባቸዋል፡፡ ጣሊያናዊ አባቱ ከሞተ አንድ ዓመት አልፎታል፡፡ ፋቢዮ አስራ አንድ ዓመቱ ነበር፡፡ ለአዛውንቱ የቅርብ ጓደኛቸውና ጐረቤታቸው ነበር፡፡ አክብሮቱና ሽቁጥቁጥነቱ፣ እንክብካቤው ---- ጣሊያናዊነቱን ቂምና ጥላቻቸውን ያለ ጠባሳ አስጠፍቷቸው ነበር፡፡ ሆኖም ፋቢዮን ሲያዩት የዱሮው ጣሊያናዊ ሰው ይታያቸዋል፡፡ ፋቢዮ እውነተኛ ጣሊያናዊ ነውና፣ በፎቶ በፊልም በወሬ የሚያውቃት ጣሊያን---- ያሳደገችውን የእናቱን ሀገር አስረስታዋለች፡፡ ናፍቆቱ ጣሊያን ናት፡፡ ወሬው ጣሊያን ናት፡፡ የሀገሮች ሀገር፣ የዘመነኞች ዘመነኛ፣ የሃብታሞች ሃብታም ጣሊያን ናት ለፋቢዮ…፡፡ አባቱ ከዘመዶቹ አስተዋውቆታል፡፡ በሁሉም መንገድ ይገናኛል፡፡ ለነገ ህይወቱ እስኪበቃ ድረስ የሚጠቅመውን ገንዘብ በስሙ አስቀምጦለታል፡፡ የእናቱ አለመወሰን ብቻ ነው እዚህ ያቆየው፡፡ ስትወስን በቃ…፡፡
ብዙ ሲያስቡ ቆዩና ቀና ቢሉ ዳኒ የለም፡፡ ጭራቸውን ወዲህ ወዲያ አወናጨፏት፡፡ ከአሳዛኝ እውነት ጋር ተፋጠጡ፡፡ ወደ ሾላው ቀና አሉ፡፡ ግዑዝ ሆነባቸው፡፡ የደረቀ የመከነ፡፡ ወፋፍራም ቅርንጫፎቹ ወዲህ ወዲያ ተዘረጋግተዋል፡፡ ጥቂት…ሂድ ሄድ ብለው ወደ መንታ ቅርንጫፍነት ይዘረጋሉ፡፡ መንታዎችም በመጠን እየቀጠኑ ወደ ሌላ መንታ ቅርንጫፍ…ይበተናሉ። አዕዋፋት ይፈነጩባቸዋል፡፡ እሳቸው በአካል ቢያንሱም ይህ ግዝፈት ያለፈ ህይወታቸው ግዝፈት ይመስላቸዋል፡፡ መቼም ከተስፋ ርቀው መጥተው በትዝታ ሀገር ዜግነትን ከተቀበሉ ቆይተዋል። በልጅ ልጆቻቸው ውስጥ ማየት የሚፈልጉት ተስፋ ቢኖርም ፈዞባቸዋል፡፡ የሳቸው ጥላ በእነሱ ውስጥ የለምና፡፡ ይተክዛሉ፡፡ ትዝታቸው ሀገር እንደሚያካልል መንገድ ይዟቸው ጥርግ ይላል፡፡ ጢሻ ለጢሻ ሸለቆ ለሸለቆ ይወስዳቸዋል፡፡ የተጐለተው የተደገፉት የሾላው ቂጥ የታሪክ ጉቶ ቢሆን ከላይ ያለው አካሉ ከልጅነት እስከ እርጅና ያለፉበትን ህይወት ወክሎ የኋሊት ወስዶ ሊያስጐበኛቸው ይችላል፡፡ “ለመሆኑ ይህ ሾላ ለምን ማውራቱን ተወ…” ቦታው ስላልተመቸው ስላረጀ ስለገረጀፈ፡፡ መልሶቹን ፈሯቸው፡፡
“ዳኒ ቤቲ…” ፋቢዮ ከደጅ እየተጣራ ገባ። አዛውንቱ እሱ አልነበረም የታያቸው…የጥንቱን የጣሊያን ወታደሮች ልብስ የለበሰ አባቱ…፡፡ “አባባ…” ሳይጠጋቸው ቆም አለ፡፡ “ምሳቸውን እየበሉ ነው?”
“አዎ” አሉት በጭራቸው ሸበቶ ውስጥ እያዩት፡፡
“ብዙ መብላት አይጠቅምም” ጀመረው አሉ አዛውንቱ፡፡ “ትንሽ ጥሩ ምግብ ይበልጣል ይለኝ ነበር አባቴ…”
የሚናገረው ምን ትክክል ቢሆን አይጥማቸውም። ያናድዳቸዋል፡፡ ፋቢዮ በትናንሽ ብልህና ንቁ አይኖቹ አስተዋላቸው፡፡ ቀጥ ብሎ የወረደው ቅስር አፍንጫው ውስጣቸውን ያነፈነፈባቸው መሰላቸው፡፡ ቀና አሉ ወደ ሾላው፡፡ “አባባ፤ ይሄ ሾላ ይቆረጥ” አለ እንደ ዘበት፡፡ አዛውንቱ ክው ብለው ደነገጡ፡፡ ደካማ አይኖቻቸውን አጐብዘው አፈጠጡበት፡፡ ደሙ የጠለሽ በተንኮል የተመረጠ ሆኖ ታያቸው፡፡ “አንተ ሰላቶ….የሰላቶ ልጅ…” ብለው ሊያንቁት እየከጀሉ ከራሳቸው ጋር ሲታገሉ ቆይተው “ለምን?” አሉ በጎረነነ ድምጽ፡፡  
“እንቅልፍ ያመጣል…አሮጌ ስለሆነ ያፈዛል…” አዛውንቱ ጭራቸው አወነጫጨፏት “ማድም ብሏል” አለ ፋቢዮ
“ማዕድ” አሉ ከናፍሮቻቸውን አልፈው ወዳፋቸው የገቡትን የሪዝ ፀጉራቸውን በድዳቸው እያሻመዷቸው። “ማዕድ” አለ ፋቢዮ እየተንከተከተባቸው፡፡ “ማድ ነው። ማድ እብድ ማለት ነው”
“እብድ ብሎ ስም አለ?” ሲሉ አፈጠጡበት፡፡
“አዎ “ማድ”…ሲሉት አቤት ይላል፡፡ “እብድ” ሲሉት ይማታል፡፡” ብሎ ሳቀ ፋቢዮ፡፡ ሳቁ ሊያስቃቸው ቢከጅልም እፍን አርገው ያዙት፡፡ “አባባ ኢትዮጵያኖች ቋንቋቸውን ለምን ይጠላሉ?”
“አይጠሉም” አሉት፡፡ በደፈናው፤ሊያዩት ባልፈለገ ስሜት ተውጠው፡፡ “ማድ ሲሉት ሳይማታ ዕብድ ሲሉት ለምን ይማታል ታዲያ?”
 መልስ አልነበራቸውም፡፡ ፋቢዮ ልክ ነው። አባቱ አልሞተም ሲሉ አሰቡ፡፡ ጐበዝ ገበሬ ነውና በልጧቸዋል፡፡ አታሏቸዋል፡፡ ያኔ በአርበኝነት ዘመን በጠላትነት ተፋጠው ነበር ያገኙት፡፡ ያኔ አሸንፈውታል። አሁን እሱ አሸንፏቸዋል፡፡ ለዛውም ለዘለቄታው፡፡ “እኔ ጣሊያናዊ አይደለሁም…ኢትዮጵያ ነኝ…ከእንግዲህ አልሄድም…እብዱ መንግስታችን የአንበሶችን ሀገር አስወርሮ አዋረደን…እኛ ግን አንድ ነን ---- እኔና አንተ ሰላም ነን…” እያለ አብሯቸው ኖረ። አምነውት ነበር፡፡ እሳቸው ከልባቸው ቂማቸውን ሲፍቁ እሱ ከአፉ ነበር። ልቡ ይኸው…ልጁ ፋቢዮ ያለሀገሩ የዘራው ዘር በሩቅ ላለችው ጣሊያን እውነተኛ ተክል ሆኖ ተገኘ…
“አንተ ኢትዮጵያዊ አይደለህም?”
“አይደለሁም” አለ ኮምጨጭ ብሎ፡፡ “አባቴ ጣሊያናዊ መሆኔን ነግሮኛል” ፊቱ እየቀላ ሄደ፡፡ “መቼ ትሄዳለህ?”
“እናቴ ዝም ብላለች፡፡ ካልሆነም እኔ ራሴ እሄዳለሁ” እውነት አለው ብለው አሰቡ፡፡ ቢሆንም የጠባውን ጡት ረስቶ በደሙ ያለ ዘሩን የሚፈልግ ነውና ከሃዲነቱ አመዘነባቸው፡፡ “እዚህ ተወልደህ አድገህ እናትህ ኢትዮጵያዊ ሆና..ውለታ በላ ትሆናለህ?”
“ኢትዮጵያ የጣሊያን ውለታ አለባት ብሎኛል”
“ምን” ሊነሱ ቃጣቸው፡፡ “አባቴ ነግሮኛል”
“ታሪክ ነግሮሃል?”
“አዎ ሁሉንም…ይቺን ደሃ ሀገር ልናሳድጋት ሞክረን ነበር” ብሎኛል፡፡ የአዛውንቱ ዓይኖች ነደዱ፡፡ ከንፈሮቻቸው የሪዝ ክዳናቸው ነቀነቁ፡፡ “መንገድ ልንሰራ --- ፋብሪካ ልንገነባ----- ህዝቡን ልናስተምር----- ልናሰለጥን መጣን” ብሎኛል፡፡
“ውሸት …ውሸታም…ቀጣፊ!”
“የኔ አባት አይዋሽም” አለ ፋቢዮ በንዴት ቲማቲም እየመሰለ፡፡
 “እኔ እዋሻለሁ?”
“እኔ አላልኩም፤ አባቴ የነገረኝን አምናለሁ…ኢትዮጵያ ለመኖሪያ ጥሩ ናት፤ ለዜግነት ግን ጣሊያን ትበልጣለች ብሎኛል”
ያኔ እንደቀነጠሱት የሰላቶ አንገት የፋቢዮን አንገት ሊቀሉት ተመኙ፡፡ እውነታቸው ውሸት ሆነች። የሞተው አፈሩን ሲያራግፍ ያልሞቱት አፈር ለበሱ። ፋቢዮ ላይ አንድ እርምጃ መውሰድ መዋረድ ነው፡፡ ያጠፋው ነገርም የለም፡፡ አባቱን ይሰማል፡፡ ያምናል። የሳቸው ልጅ ግን አልሰማቸወም፡፡ የሱ ቦታ ሰጥቶ አለመስማት ወደ ልጆቹም ተጋባ፡፡ መና አስቀራቸው። ኑሮ ብቻ ይላል፡፡ ሆድ መሙላት ብቻ፡፡ መሸመት ብቻ። አባት ሆኖ ጨርሷል፡፡ ፋቢዮ በራሱ አፍ የአባቱን ቋንቋ የአባቱን ታሪክ እውነት ነው የሚናገረው፡፡ አዛውንቱ በቆረፈዱ እጆቻቸው ነጭ ፀጉራቸውን ጨመደዱት፡፡
 “አባባ…” አሁን ለዘብ ብሏል፡፡ መልስ ሳይጠብቅ ቀጠለ “አባቴ አበሾች በጦርነት ጀግኖች ናቸው ግን…” ቀና አሉ…”ጦርነት ከሌለ የሚተባበሩበት ነገር የላቸውም”
“በቃህ…በቃህ!” ጮሁ ደነፉ፡፡ “ቆይ አባባ…አባቴ “እኔ ከአባባ ተምሬያለሁ እሳቸው ግን ከኔ አልተማሩም” ብሎኛል” በታሪክ ጉቶ ስር ሆነው…እሳቸው ቀዝቅዘው ከታሪካቸው ሙቀት ሲጠብቁ…”እናቴ…ደሞ---” በሁኔታቸው ደስ እያለው “አበሻ ባለማግባቴ ደስተኛ ነኝ ትላለች…”
አዛውንቱ በቀጫጭን ጭኖቻቸው ላይ ድፍት ብለዋል፡፡ ትግል ወራሪው መሬቱን ለቆ ሲወጣ አበቃ። ከዚያ መልስ ሌላ የማጽዳት የማረም ዘመቻ ያስፈልግ ነበር እያሉ በውስጣቸው ተጸጸቱ፡፡
ዳኒ ፊቱን እንደቋጠረ መጣ፡፡ “ምነው ዳኒ?”
“ምንም”
“አንተም ትዋሻለህ?”
“ማን ዋሸህ?” ፋቢዮ ወደ አዛውንቱ ጠቆመው፡፡ ዳኒ ትከሻውን በንዴት አንጥሮ “ተወው ባክህ እሱ ተረት ተረት እያለ ያልዋሸን የለም፡፡” ጥቂት በዝምታ ቆዩ፡፡ ሌላው ጓደኛቸው ከደጅ ገባ፡፡ ጥቁር ነው፡፡ ጐስቋላ። ፋቢዮን እንደ ነፍሱ ይወደዋል፡፡ “ፋቢ…ፋቢ…” እያለ ቀረባቸው፡፡ እነሱ ዝም ብለዋል፡፡ “ምን ሆናችኋል?”
“ዳኒ አኩርፏል” አለ ፋቢዮ፡፡ “እ…” ቸኮለ ለማውራት፡፡ “እሱማ’ኮ ባንተ ነው፡፡” አለ ጥቁሩ ልጅ ድንገት ደስ እያለው፡፡
“እኔ ምን አደረኩት” አለ ፋቢዮ እየደነገጠ። ለማወቅም ጓጓ፡፡ ልጁ የነተበች ቀዳዳ ሱሪውን እጁን ከቶ እያሰፋና ወደ ፋቢዮ ዓይን እያስጠጋለት ተቁለጨለጨ፡፡ ዳኒ በቁጣ ቢያየውም ግድ ሳይሰጠው በልቡ “…ፋቢ ያቺን አረንጓዴ…ሱሪ ቢሰጠኝ”…መልሶ “ግን ባዶ እግሬን እያየኝ…እንዴት ዝም አለኝ…” እያለ ተብሰለሰለ፡፡ “አንተ እንግሊዘኛ ስለበለጥከው---” ሲል ተናገረ፡፡
“አሃ…የስ…ታዲያ…” ተነቃቃ ፋቢዮ፡፡ ልጁ ደስ አለው፡፡ ዳኒ እያረረ “አንተ አቃጣሪ ውሸታም”
“ዳኒ አትናደድ…” አለው ፋቢዮ በበላይነት ስሜት፡፡
“አስረዳኝ ብትለኝ አስረዳህ ነበር…አባቴ ያስተምረኝ ነበር እናቴም ጭምር…” ዳኒ የበለጠ ተወራጨ፡፡ ልጁ ተደስቷል፡፡ የፋቢዮን ዓይን ዓይን እያየ ሌላ የሚነገር ይፈልጋል፡፡ “ዳኒ አትናደድ አባቴ ጭስስ ይል ነበር ግን “አትናደድ ንዴት የደደብ ስራ ያሰራሃል” ይለኝ ስለነበር አልናደድም”
“አንተ ታድለሃል” አለ ዳኒ በትካዜ፡፡
“ክልስ ስለሆነ ነዋ…እኛ ባሪያዎች ስለሆንን ነዋ…ፀጉራችን ሸካራ …ኤጭ” አለ ጥቁሩ ልጅ፡፡
“ጓደኛሞች ነን…እኔ ጣሊያን ሄጄ ስራ እይዝና እወስዳችኋለሁ” አለ እንደ ቀልድ፡፡ ሁለቱም ልጆች ነቃ አሉ፡፡ በሚንቦገቦጉ ዓይኖቻቸው ባለማመን አፈጠጡበት፡፡ “እስኪ…እስኪ…እጄን ምታ” አለና ጥቁሩ አዳፋ እጆቹን ወደ ፋቢዮ በልመና ዘረጋቸው። የፋቢዮን ነጭ እጅ ሲመታው “ጡ” የሚል ድምጽ ተሰማ፡፡ አዛውንቱ በስርቆሽ ይመለከታሉ፡፡ ንዴታቸው እንደ ጥንቱ ለሽለላና ቀረርቶ አላስነሳቸውም፡፡ አደከማቸው እንጂ፡፡
“ሁለታችንንም አንድ ላይ” አለ ዳኒ መሀላቸው እየገባ፡፡ “ኖ…ኖ…በየተራ”
“መጀመሪያ ማንን?” ሲል ጠየቀ ጥቁሩ ዳኒን ገፍቶ ፋቢዮ ፊት እየቆመ “መጀመሪያ እኔን” አለና ዳኒ ጓደኛውን በጥላቻ ገፋው፡፡ ልጁም ዳኒን ገፋው…። ቀስ በቀስ ተያያዙ…፡፡ አዛውንቱ እርር አሉ፡፡ ፋቢዮ እጁን ኪሱ ከቶ “ቆይ…ቆይ” አላቸው በሁኔታቸው እየተገረመ። “አይወስድህም” አለ ዳኒ በንዴት፡፡
“ይወስደኛል እኔን ነው የሚወደው” አለ ላቡ ጥቁር ፊቱን እያወዛወዘው፡፡ “ማንን ነው የምትወደው?” አፈጠጠ ዳኒ ወደ ፋቢዮ…”ሁለታችሁንም”
“ይበልጥ የምትወደው?” ጥቁሩ በተራው ጠየቀ። ፋቢዮ አዲስ ሃምሳ ሳንቲም አውጥቶ እያሳያቸው “ያወቀ መጀመሪያ ይሄዳል” ሁለቱም በመስማማት ተገለማመጡ፡፡ መረጡ፡፡ ፋቢዮ ሳንቲሟን አጦዛት፡፡ ርቃ ሄዳ ወደቀች፡፡ ሶስቱም እኩል ሮጡ፡፡ “ወንዳታ! ወንዳታ!…” አለ ጥቁሩ ልጅ፡፡ የዳኒ ስሮች ተገታተሩ። “መጀመሪያ እኔን” አለው ዳኒን በማብሸቅ ቅላጼ። ዳኒ በንዴት የሰነዘረው እርግጫ የልጁን ባዶ ሆድ አጮኸው፡፡ ልጁም ጮኸ፡፡ ሆዱን ደግፎ ብርክክ አለ፡፡ ፋቢዮ ደነገጠ፡፡ “አገላግላቸው አንተ ሰይጣን!” አንቋረሩ አዛውንቱ፡፡ ተወራጩ፡፡ ዶሮዎቹም እየጮሁ ሸሹ፡፡ በግና ፍየሎቹም እየተሯሯጡ ወደ ቆርቆሮዋ ቤታቸው ሄዱ፡፡ ግቢው ላንድ አፍታ ቀውጢ ሆነ፡፡ “እኔ ምን አደረኩ?” አለ ፋቢዮ፤ልጁን ሊያነሳው እየሞከረ፡፡
“እውነት ምን አደረገ…የልጆቹን ልብ መናኝ ያደረገው እሱ አይደለም…”….”ተነስ በቃ ተነስ…” ሲጐትተው ቀዳዳ ሱሪው ተቀደደ፡፡ “ተነሳ አረንጓዴዋን ሱሪ እሰጥሃለሁ፡፡ ጫማም አለ …ተነስ፡፡” የጥቁሩ ልጅ ገጽታ እየፈካ ቀና ብሎ ፋቢዮን አየው፡፡ አይኖቹ ውስጥ ያሉት…የመለማመጥ የመሸነፍ ዕይታ ለአዛውንቱ ቦግ ብለው ታዩዋቸው፡፡ “እናንተ ደካሞች፤ እሱ ባልያዘው ዜግነት የራሳችሁን ትጥላላችሁ” ማንም አልሰማቸውም፡፡
ፋቢዮ ዳኒን “ይቅርታ ጠይቀው” አለው፡፡
“አልለውም” አለ ዳኒ ተቆጥቶ፡፡
“አባቴ እንዳላጠፋ ይመክረኝ ነበር፡፡ ካጠፋሁ ሰው ካስቀየምኩ ግን ወዲያው ይቅርታ ማለት እንዳለብኝ አስተምሮኛል” አለ ፋቢዮ በኩራት፡፡ ሁልጊዜም በአባቱ የሚሰማውን ክብር ማሳየት ይፈልጋል፡፡
“ዳኒ አታጠናም” እያለች ተቀላቀለቻቸው ሴቲቱ፡፡
 “አላጠናም”
“ፈተና አለኝ አላልክም?”
“ልውደቅ” አለ በዛው ስሜት፡፡ ጥቁሩ ልጅ በደስታ ይስቃል፡፡ ዳኒ በቅናት በዛሉ ዓይኖቹ ፋቢዮን ገልመጥ አደረገው፡፡
“ላስረዳህ” አለ፤ፋቢዮ፡፡
“አልፈልግም”
“ቤቲ፤ፋቢ ጣሊያን ይወስደኛል” አላት ጥቁሩ ልጅ እየቦረቀ፡፡ “መቼ…” ወደ ፋቢ እየተጠጋች፡፡ “እኔንስ ፋቢ እኔንስ…” አጐንብሳ ነበር የምትለማመጠው፡፡ “እናንተ ዲቃሎች…ይቺስ ሀገር አይደለችም…ኢትዮጵያ ሀገር አይደለችም”
“ኢትዮጵያ?” አለች ቤቲ፡፡
 “ዝም ብላ ሀገር ነቻ” አለ ጥቁሩ ልጅ፡፡
“ከማንም የማታንስ ሀገር ነች…ስሙ ልጆቼ…ዳኒ ያልነገርኳችሁ ታሪክ አለ”
“እሱ ምን ያረጋል አባባ” አለች ሴቷ “ውሸት ነው እሱማ” አለ ዳኒ፡፡
“እውነተኛ ታሪክ ነው…”
“ኢትዮጵያ ታሪክ ፀሐፊ አልነበራትም ብሎኛል አባቴ” አለ፤ፋቢዮ፡፡
“ሌባ በለው! አንተ ከሃዲ…ነህ! እናትህ ክደሃል…!”
“አብረን ነው’ኮ የምንሄደው” አለ ፋቢዮ በኩራት፡፡
ማድ ከደጅ ሲገባ ሁሉም ዝም አሉ፡፡ ቀጥታ ወደ አዛውንቱ ሄደ፡፡
 “ማድ..” አለ ፋቢዮ እየፈገገ፡፡
“ሃይ ፋቢ”
 አዛውንቱ ላይ አፈጠጠባቸው፡፡ “ሼባው ተነስ” አለ፡፡ በዝምታ አዩት፡፡ ሙልጭ ያለው የራስ ቅሉ ባንገቱ ላይ በክንዶቹ ላይ ያሉት ሰንሰለቶች…የወረደ ሱሪው ግዙፍ ጫማው…”ለምን ማዕድ”
“ማድ ነኝ…ማድ በል” ተቆጣቸው፡፡ አይኖቻቸው ከኋላው የቆሙትን ሰዎች አዩ፡፡ ዛፍ ቆራጮች…ስለታም መጥረቢያዎች…ረዥም ሃገር ጠልፈው የሚጥሉ ገመዶች…በላያቸው በረዶ የፈሰሰባቸው ያህል ቀዘቀዛቸው፡፡ “ተነስ…ኖ ካልክ…ላይህ ላይ…ከት ያደርጉብህና ዳይ ትላለህ”
ልጆቹ ዙሪያውን ከበዋል፡፡ ማድ ለቆራጮቹ ምልክት ሰጥቶ እየነጠረ ወደ ቤት ገባ፡፡ ቆራጮቹ ተዘገጃጅተው አዛውንቱን ዘለው ወደ ሾላው ወጡ። ስራቸውን በደስታ ማከናወን ጀመሩ፡፡ ቅርንጫፎቹ ወርደው ተነጠፉ፡፡ የአዛውንቱ ---- ክንዶች የታሪክ ---- የህይወት አካሎች በየተራ፡፡ ልጆቹ ፋቢዮን ተከትለው እየተንጫጩ ወጡ፡፡ አዛውንቱ አልተነሱም። በተሸረኮቱበት ሽንቁር ቀርተዋል፡፡ የሚያምኑትን የሚያምን፣ የሚናገሩትን የሚቀበል ጥላነታቸውን የሚፈልግ አጥተዋልና የመረረ ለቅሷቸውን ለራሳቸውና ለሾላው እንዲሁም ለልጅ ልጆቻቸው አለቀሱ…፡፡ ኋላቸው ወደቀ…ቀና አሉ፡፡ ስትፈልጋቸው የቆየችው ፀሐይ ወጋቻቸው…በቃ ተዳከሙ…አልተነሱም…፡፡     






Read 3241 times