Saturday, 23 April 2016 10:29

ሕይወት፤ ሌስተርና ቼልሲ ናት!

Written by  ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
Rate this item
(53 votes)

“የሚሸነፍ ትግል የለም፤ የሚሸነፍ ሰው እንጂ”

ይገርምሃል  ወንድሜ፤ በሕይወትህ ድል አድርገህ ዋንጫ ወሰድክ ማለት እዚያው የልዕልና ማማ ላይ እንደተሰቀልክ ትቀራለህ ማለት አይደለም፡፡ አታየውም ቸልሲን መከራውን ሲቀበል፡፡ አምና እርሱ ዋንጫ ሲበላ ያየ ሰው ዘንድሮ መከራውን ይበላል ብሎ ማን ገመተ? ብዙዎች‘ኮ ሲወጡ መውረድን ይረሱታል፡፡ ለሚወጣ ሰው ግን መውረድ የጥላውን ያህል ቅርብ ነው፡፡ ‹እኖራለሁ ብለህ ሥራ፤ እሞታለሁ ብለህ ኑር› ሲባል አልሰማህም? መውረድን የረሳ ባለ ሥልጣን፣ ሕመምን የረሳ ጤነኛ፣ ድህነትን የረሳ ሀብታም፣ ሞትን የረሳ ነዋሪ፣ ድቀትን የረሳ ጻድቅ፣ ውርደትን የረሳ ክቡር፣ ወደረሳው ነገር ለመጓዝ እንዴት ይፈጥናል መሰለህ? ድቅድቁ ጨለማ ያለው ከሻማው ሥር ነው፡፡
እነ እገሌ ካሉ፣ እነ እገሌ ቦታውን ከያዙ፣ እነ እገሌ እዚያ ላይ ከወጡ፣ በቃ አይሳካልኝም አትበል፡፡ ሌስተርን ያየ እንዲህ አይልም፡፡ ለወትሮው የእንግሊዝ እግር ኳስ ማንቸስተር ዮናይትድና ማንቸስተር ሲቲ፣ አርሴናልና ቼልሲ በእግራቸው ርግጥ፣ በእጃቸው ጭብጥ አድርገው የሚዘውሩት ይመስል ነበር። መቼም ዋንጫውን ከእነዚህ ከአራቱ አንዱ እንጂ ሌላው ይቀምሰዋል ተብሎ አይታሰብም ነበር፡፡ ‹ሙሴ በሩቁ ከነዓንን አያት እንጂ አልወረሳትም› እንደሚባለው ሌሎቹ ቡድኖች ዋንጫውን በሩቁ ከማየት አልፈው ይወርሱታል ብሎ ማን ያስብ ነበር፡፡
ወዳጄ በዚህ ዓለም ላይ የማይነጠቅ የተጨበጠ፣ የማይንሸራተት የተረገጠ የለም፡፡ nothing for granted ይሉ የለም ስታድየሙን ሞልተው የሚጨፍሩት እንግሊዞች፡፡ የጨበጥክበት እጅህ፣ የረገጥክበት እግርህ አንድ ቀን ይዝላል፡፡ የትናንት አይበገሬነትህ፣ የትናንት ጀግንነትህ፣ የትናንት ክብርህ፣ የትናንት አሸናፊነትህ፣ የትናንት ተፈሪነትህ በዛሬ ጥረት ካልታገዘ ታሪክና ቅርስ እንጂ ድልና ውጤት አይኖርህም፡፡ አታያቸውም እንዴ እነ ማንቸስተር ዩናይትድና እነ ማንቸስተር ሲቲ ከአራቱ ውስጥ ለመግባት መከራቸው ሲያዩ? አታያቸውም እንዴ እነ አርሴናል ከቀበሮ አምልጦ ዛፍ ላይ እንደወጣ ዶሮ ካሁን አሁን ከአራቱ ወረድን እያሉ ሲጨነቁ? አላየኸውም እንዴ ስንት ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ የኖረው አስቶንቪላ ተሰናብቶ ከሊጉ ሲወርድ፡፡
ዓለም እንደዚህ ናት፡፡ ድል በታሪክ ቢሆን ኖሮ ከሊቨርፑል በላይ ማን ዋንጫ ይወስድ ነበር፡፡ ምን እዚያ ወሰደህ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የአፍሪካን ዋንጫ የጠነሰስን፣ የአፍሪካን እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንስ የመሠረትን አልነበርንምን? ከብዙዎቹ ቀድመን ኳስ ተጫውተን፣ ከብዙዎቹ ቀድመን ዋንጫ አልበላንምን? ከብዙዎቹስ በፊት የአፍሪካን የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን አልመራንምን? ዛሬ ግን የት ነን? ትዝታ ሆነናል፡፡ ዋንጫ እንደ መንግሥተ ሰማያት፣ ድልም እንደ ሰማይ ርቆናል፡፡
ሊቃውንቱ ‹ድል ማለት ጥረትና ዕድል የሚገናኙባት አጋጣሚ ናት› ይላሉ፡፡ አንተ ትታገላለህ፣ ትጥራለህ፣ ትለፋለህ፣ ትደክማለህ፣ ትወጣለህ፣ ትወርዳለህ፤ እንዲህ ባለማቋረጥ ስትታገል አንድ ቀን የአንተ የጥረትህ መንገድ ከዕድል መንገድ ጋር ይገናኝና ታቋርጠዋለህ፡፡ ያኔ አይወድቅም የተባለው ወድቆ፣ አይሸነፍም የተባለው ተሸንፎ፣ አይነቀነቅም የተባለው ተነቅንቆ፣ አይፈርስም የተባለው ፈርሶ፣ አይነካም የተባለው ተነክቶ ቦታውን ሲለቅ ታየዋለህ፡፡
አንተ ካልጣርክና ካልታገልክ፣ ካልሠራህና ካልሞከርክ ግን በዕድል ብቻ የሚሆን ነገር የለም። ዛሬ አላሸነፍክም? ተስፋ አትቁረጥ፤ ቢያንስ የማሸነፍ ሞራልና የማሸነፍ ተስፋ አለህና፡፡ የሚሸነፍ ትግል የለም፡፡ የሚሸነፍ ሰው እንጂ፡፡ ትግል ትግልን ይወልዳል፣ ጥረት ጥረትን ይተካል፣ ሙከራ ሙከራን ያመጣል፡፡ ዛሬ አንድ አካፋ አፈር ከተራራው ላይ ስታነሣ ተራራውን አልናድከው ይሆናል፡፡ በርግጠኝነት ግን የተራራውን መልክ ቀይረኸዋል፡፡ በአካባቢው የሚያልፉ ሰዎች፣ ወይም አንተ ራስህ እንኳን የተራራው መልክ መቀየሩን ላታውቀው ትችላለህ፡፡ ተራራው ራሱ ግን ያውቀዋል፡፡ የመሬት መሸርሸር የሚባለው ግማሽ ተራራ ተሸርሽሮ አይደለም‘ኮ፡፡ ውኃ እያሳሳቀ አፈሩን በየጊዜው ሲወስደው ነው፡፡  
ምናልባትም ምንም አታመጣም ብለው ሰዎች ይነግሩህ ይሆናል፡፡ ሌስተርን ተመልከቱ በላቸው። ሌስተር የት ነበረ፡፡ አምና ቼልሲ ዋንጫውን ሲወስድ፣ ማንቸስተር ሲቲ ሁለተኛ ሆኖ ሲጨርስ፣ አርሴናልና ማንቸስተር ዩናይትድ ሦስትና አራተኛ ሆነው ሲያጠናቅቁ፣ ሌስተር የት ነበር? እስከ ሰባት፣ እስከ ዐሥር  ደረጃ ብትፈልገው ታገኘዋለህን? ፈጽሞ፡፡ ሌስተር ከወራጅ ቀጠናው በአራት ደረጃ ርቆ፣ ከወራጁ ከሁልሲቲ በ7 ነጥብ ብቻ በልጦ 14ኛ ደረጃ ላይ ነበረልህ፡፡  
ዘመን መሰላል ነው፡፡ የወጣው ሲወርድ፣ የወረደው ሲወጣ ይገናኙበታል፡፡ በአንድ ዓመት ልዩነት የቸልሲን ቦታ ሌስተር፣ የሌስተርንም ቦታ ቼልሲ ይዞ አየነው። እንዳያርግ ስንፈራው የነበረው ቼልሲ እንዳይወርድ ተሳቀቅንለት፡፡ ‹የናቁት ይወርሳል› እንደተባለው አራቱን ኃያላን ገፍቶ ሌስተር መጣና እንደ ሽሮ ቅቤ በአናት ተቀመጠ፡፡ ‹ይሞታል ያሉት ተርፎ፣ ይቀብራል ያሉት ሞተ› ሲባል አልሰማህም?
እናም ተስፋ አትቁረጥ፡፡ ግፋ፣ ጣር፣ ታገል፣ ሥራ፣ ሞክር፣ ድፈር፤ ድል ይጠራቀማል፡፡ አንድ ቀን ከላይ ያየሃቸው ኃያላን እንደ ቼልሲ ደክመው፣ እንደ አርሴናል አርጅተው፣ እንደ ማንቸስተር ዩናይትድ ቀልብ ርቋቸው፣ እንደ ሲቲ ነገር ዓለሙ ዞሮባቸው ታገኛቸዋለህ፡፡ ያኔ እንደሌስተር ገፋ ገፋ አድርገህ ከላይ ቁጢጥ ነው፡፡ ሰውን መናቅ እንጂ በሰው መናቅ አይጎዳም፡፡ ሰውን መናቅ ትዕቢትን ወልዶ ስንፍናን ያመጣል፡፡ በሰው መናቅ ግን እልህን ወልዶ ትግልን ይፈጥራል፡፡ እናም አሸናፊነትህ የሚወሰነው ሰዎች ባንተ ላይ ባላቸው አመለካከት አይደለም፤ አንተ በሌሎች ላይ ባለህ አመለካከት እንጂ፡፡ እንዴት ያዩኛል? ብለህ አትጨነቅ፡፡ እንዴት አያቸዋለሁ? ብለህ ግን አስብ፡፡ እያሸነፍክ ስትመጣ የማያዩህ ሁሉ ያኔ ያዩሃል፣ የጠሉህ ያኔ ይወዱሃል፣ የናቁህ ያኔ ያደንቁሃል፡፡ የበለጠ ወደ ማይክራፎኑ በተጠጋህ ቁጥር የበለጠ ድምጽህ ይሰማል፡፡
እንዲያውም ሲንቁህ መልካም ነው፡፡ ጫና አይበዛብህም፤ ጠላት አይበዛብህም፤ ተገዳዳሪ አይበዛብህም፤ ጉልበትህን ለሥራህና ለዓላማህ ብቻ እንድታውለው ጊዜ ታገኛለህ፡፡ ሰዎች ዓይናቸውን ቼልሲ ላይ ያርጉልህ፣ ማንቸስተር ላይ ይጣሉልህ፣ ሲቲ ላይ ያኑሩልህ፣ አርሴናል ላይ ያትኩሩልህ፡፡ አንተ ዝም ብለህ ሥራና እንደ ሌስተር እየገፋህ ና፡፡ መንደርህ ትንሽ ናት? ስምህን የሚያውቀው የለም? ገንዘብህ ጥቂት ነው? የተሰጠህ ግምት አነስተኛ ነው? ባንተ የሚተማመኑ የሉም ወይም ጥቂት ናቸው? እነዚህ ሁሉ ካልለወጡህ ልትለውጣቸው ትችላለህ፡፡
እንደ ንሥር ታድሰህ፣ እንደ እባብ አፈር ልሰህ፣ እንደ ከራድዮን ራስህን ለውጠህ እስካልመጣህ ድረስ እንደ ቼልሲ ትናንት ዋንጫ በልተህ ዛሬ መውረድህ የማይቀር ነው፡፡ ወደ ላይ ከሚሄድ ሰው ይልቅ እላይ ያለ ሰው ለታቹ ቅርብ ነው፡፡ ጊዜ ይለወጣል፣ ሐሳብ ይለወጣል፣ ወዳጅ ይለወጣል፣ አሠራር ይለወጣል፣ እሴቶች ይለወጣሉ፡፡ አንተም ትናንት የሠራኸውን ብቻ እየዘፈንክ፣ የትናንቱንም ታሪክ ብቻ እየተረክህ፣ ‹ትናንት እንዲህ ያደረግኩት እኔ ነኝ› ብለህ እየፎከርክ መኖር አደገኛው አኗኗር ነው፡፡ ‹ሆ› ብለው ያወጡህ ‹ውይ› ብለው እንዳያወርዱህ፣ ‹ጀግና› ብለው የሰቀሉህ፣ ‹ፈሪ› ብለው እንዳይጥሉህ፤ ‹ጉሮ ወሸባዬ› የዘፈኑልህ፣ ‹ዋይ ዋይ የት ትሄዳለህ› እንዳይሉህ፣ ‹ያለ አንተ› ያሉህ ‹ካንተ በቀር› እንዳይሉህ፡፡ የኮሩብህ እንዳያፍሩብህ፣ ‹እዩኝ እዩኝ› ብለህ ‹ደብቁኝ ደብቁኝ› እንዳትል ከፈለግክ መንገዱ አንድ ብቻ ነው፡፡ የትናንቱን ለታሪክ ተወውና ለዛሬው የሚያስፈልግህንና የሚገባህን ሥራ ሥራ፡፡ ከታሪክ ተማር እንጂ ታሪክ ላይ አትተኛ፡፡
አታይም፤ እዚህ ሀገር እንኳን የሊቨርፑል ዘመን አልፏል፡፡ ዛሬ በሃምሳዎቹና በስድሳዎቹ ውስጥ ያሉ የኳስ አፍቃሪዎች በዘመናቸው የሊቨርፑል ደጋፊዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን የእነርሱ ልጆች እንኳን ሊቨርፑልን አይደግፉም፡፡ ያማ ቀርቶ ሌላ ዘፈን መጥቶ፡፡ ዘመን ተቀይሮ፤ ደጋፊም ተደጋፊም ተቀይሮ፡፡ አዲስ ጀግና መጥቶ፣ አዲስ ተከታይ አፍርቶ፡፡ ያም ዘመን አለፈ፡፡ የነማንቸስተርና የነአርሴናልም ዘመን መጣ፡፡ እርሱም ሊያልፍ ነው መሰል፣ ደግሞ የነ ሌስተርና የነ ቶተንሐም ዘመን መጣ፡፡
‹በቃ ጨርሻለሁ› ወይም ‹በቃ ተጨርሻለሁ› አትበል፡፡ ‹አለቀ›ም ‹አለቀልኝ›ም አትበል፡፡ ካንተ በፊት ሌሎች ነበሩ፡፡ ካንተም በኋላ ሌሎች ይመጣሉ። ‹ታግለን ጨርሰናል› ያሉ እንደ ቼልሲ ቦታ እየለቀቁ፣ ‹ገና ይቀረናል› የሚሉ ታጋዮች እንደ ሌስተር ቦታውን እየተረከቡ ይሄዳሉ፡፡ ሕይወት ሌስተርና ቼልሲ ናት፡፡  

Read 24527 times