Saturday, 23 April 2016 10:13

ህፃናት አግተው በደቡብ ሱዳን ጫካ የመሸጉ ታጣቂዎች ተከበዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(85 votes)

የደቡብ ሱዳን ወታደራዊ አዛዥና የክልል ገዢ እርስበርስ ተወነጃጅለዋል
     በጋምቤላ ከ200 በላይ ሰዎችን ገድለው ከ100 በላይ ህፃናትን አግተው የወሰዱ ታጣቂዎችን ለማደን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወደ ደቡብ ሱዳን ዘልቆ የገባ ሲሆን፤ ታጣቂዎቹን በመክበብ ታጋቶቹን ህፃናት በድርድር ለማስለቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የደቡብ ሱዳን መንግስት በጅምላ ግድያውና እገታው እንዳዘነ ጠቅሶ ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚተባበር በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ ጦር ከመጠን አልፎ ብዙ ርቀት ወደ ደቡብ ሱዳን ባይገባ ይመረጣል ብሏል፡፡
“የሙርሌ ተወላጅ” በሚል በጐሳ የተቧደኑት ታጣቂዎች፣ ደቡብ ሱዳን ውስጥ የመሸጉበት ጫካ በኢትዮጵያ ጦር እንደተከበበ መንግስት የገለፀ ሲሆን ህፃናቱን ከጉዳት ለመከላከል ከሃይል እርምጃ በፊት ለድርድር ቅድሚያ ሰጥቷል ተብሏል፡፡
“ህፃናቱን ለማስለቀቅ በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሰራ ነው”  በማለት ለአዲስ አድማስ የተናገሩት የፌደራልና አርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ወርቄ፤ በዲፕሎማሲ የማይሆን ከሆነ ጥንቃቄ የተሞላበት የኃይል እርምጃ ተወስዶ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲለቀቁ ይደረጋል ብለዋል፡፡ የህፃናቱን ደህንነት በሚያረጋግጥ መንገድ በመከላከያ ሃይል እየተከናወነ ያለው ስራ በጥሩ ሂደት ላይ ነው ብለዋል - አቶ አበበ፡፡
በኢትዮጵያ ጦር እየተወሰደ ያለው እርምጃ፣ በአየር ኃይልና በአየር ወለድ ኮማንዶዎች የታገዘ መሆኑንም ምንጮች አመልክተዋል፡፡
መንግስት በጥቃቱ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ከ20 ሺህ በላይ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እየሰራ ነው ያሉት አቶ አበበ፤ “ከእንግዲህ ጥቃቱ እንደማይደገም ተፈናቃዮቹን ማሳመን ስለቻልን አሁን ተረጋግተዋል” ብለዋል፡፡
የተቃጠሉ ቤቶችና የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሰው እንዲስተካከሉ ከተደረገ በኋላ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀዬአቸው ይመለሳሉ ብለዋል አቶ አበበ። በጋምቤላ በተፈፀመው ጥቃት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ከትናንት በስቲያ ሃዘናቸውን የገለፁ ሲሆን፤ ህፃናቱን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት በወታደራዊ ኃይል ጭምር ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
የውጭ ገዳይ ሚኒስትራቸው ፒተር በሽር ጊባንዲ በበኩላቸው፤ በዘመቻው ጉዳይ ላይ ለመወያየት ትናንት ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ድንበር ተሻግሮ እንዲገባ የተስማሙ ቢሆንም፤ ከመጠን በላይ ዘልቆ ባይገባ ይመረጣል ሲሉ ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡
“የሙርሌ ጎሣ ተወላጅ” በሚል የተቧደኑት ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት የተነሳ፤ በደቡብ ሱዳን ወታደራዊ ጀነራልና በክልል አስተዳዳሪ መካከል ውዝግብ መፈጠሩን “”ሱዳን ትሪቡን” ዘግቧል፡፡
ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት በየፊናቸው የሙርሌ ጐሳ ተወላጆችን እየመለመሉ ታጣቂ ቡድን የሚያደራጁ ናቸው ተብለዋል፡፡ ከከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች መካከል አንዱ የሆኑት ሌተናል ጀነራል ዴቪድ ያኡያኡ፤ ጥቃት ፈፃሚዎችን ያስታጠቀውና ያደራጀው የቦማ ክልል አስተዳዳሪ ነው ሲሉ ወንጅለዋል፡፡ አስተዳዳሪው በበኩላቸው፤ ጥቃቱን የፈፀሙት በጀነራሉ ስር የተደራጀ የሙርሌ ተወላጅ ታጣቂዎች ናቸው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ወረዳዎች ላይ በሌሊት በተፈፀመው ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፤ 108 ህፃናት ታፍነው ተወስደዋል፣ 2000 ከብቶች ተዘርፈዋል፣ 20ሺህ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡
ፓርላማ የ2 ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ቀን ያወጀ ሲሆን፤ የአፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ዩኒሴፍ እና ሌሎች አለማቀፍ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ ተቋማት ሀዘናቸውን ገልፀዋል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በጥቃቱ የተሠማቸውን ሀዘን ገልፀው፤ በድንበር አካባቢዎች የሚፈፀም ጥቃት እየተደጋገመ በመሆኑ መንግስት ተጠያቂ ነው በማለት የድንበር ጥበቃው አስተማማኝ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡

Read 12813 times