Saturday, 23 April 2016 10:10

በሜድትራኒያን ባህር የሞቱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር አልታወቀም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

- ከ500 የባህር ተጓዦች 41 ሲተርፉ፤ 11 ኢትዮጵያውያን ናቸው
- መንግሥት ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል

      ከሰሞኑን በሜድትራኒያን ባህር ላይ ከ500 በላይ ሰዎችን አሳፍራ ወደ ጣሊያን ስታመራ የነበረች ጀልባ በመስጠሟ ከ450 በላይ ሰዎች በአደጋው ህይወታቸውን እንዳጡ የተዘገበ ሲሆን እስካሁን በአደጋው የሞቱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር በትክክል አልታወቀም፡፡ መንግስት በበኩሉ ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል፡፡
የጀልባዋ መስጠምና የአደጋው ዜና የተሰማው ባለፈው እሁድ ሲሆን ከትናንት በስቲያ በጉዳዩ ላይ ከአዲስ አድማስ ጥያቄ የቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ በሰጡት ምላሽ፤ ግብፅና ሮም ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጉዳዩን እየተከታተሉ መሆኑን ጠቁመው ዝርዝር መረጃዎች እንደተገኙ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ከግብፅ ተነስተው የሜድትራኒያን ባህርን በማቋረጥ ጣሊያን ለመግባት ካቀዱት 500 ያህል ኤርትራውያን፣ ኢትዮጵያውያንና ሶማሌያውያን መካከል በህይወት የተረፉት 41 ብቻ መሆናቸውን ሲኤን ኤን ዘግቧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ እንደገለፀው፤ ከተረፉት ውስጥ 37ቱ ወንዶች፣ ሶስቱ ሴቶች ናቸው፡፡ በዚህ አሳዛኝ አደጋ የአንድ የሁለት ወር ህፃንና እናቱ ህይወታቸው ሲያልፍ አባት ሊተርፍ ችሏል፡፡
ከሞት የተረፉት 11 ኢትዮጵያውያን፣ 25 ሱማሌያውያን፣ 6 ግብፃውያንና አንድ ሱዳናዊ መሆናቸውን ያመለከቱት ዘገባዎች፤ በህይወት የተረፉት ወደ ግሪክ መወሰዳቸውንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
መርከቧ አደጋው ያጋጠማት በሊቢያና በጣሊያን መካከል ባለ የባህሩ አካል መሆኑን የጠቀሱት ዘገባዎች፤ አደጋው ከደረሰ በኋላ የነፍስ አድን ስራውን አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ አደጋው የተፈጠረው በውሃ ላይ ሁለት ጀልባዎች ተሳፋሪዎችን ለመቀባበል ጥረት ሲያደርጉ በነበረበት ወቅት መሆኑን ከአደጋው የተረፉት ሰዎች አስረድተዋል፡፡
ከሊቢያ የተነሳችውና 200 ሰዎችን ጭና የነበረችው ጀልባ፤ ሌሎች ከ300 በላይ ተሳፋሪዎችን ከግብፅ ለመጣችው ጀልባ ስታቀብል በተፈጠረ ከአቅም በላይ ጭነት መስመጧ ታውቋል፡፡ ከአደጋው ተርፈው ግሪክ ከሌማታ በተባለ አካባቢ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሶስቱን የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው አገልግሎት (ቪኦኤ) ያነጋገራቸው ሲሆን ከነዚህ መካከል የሁለት ወር ልጁንና ባለቤቱን በአደጋው ያጣው ሙሃዝ መሃመድ፤ “አደጋው ሲፈጠር ሌሊት ጭለማ ነው፤ ሚስቴንና ልጁን ማትረፍ አልቻልኩም” ብሏል፡፡ እሱ ዋና ስለሚችል ህይወቱን ማትረፍ እንደቻለም ገልጿል፡፡
ሌላው ህይወቱ የተረፈ ኢትዮጵያዊ ኢብስራ አብዱ ሰላም በበኩሉ፤ ከድሬደዋ 30 ሆነው ወደ ግብፀ እንዳመሩና በአደጋው እህቱን፣ የእህቱን ልጅ ጨምሮ 28 ጓደኞቹን በሞት ማጣቱን ገልጿል፡፡
በህይወት የተረፉት ኢትዮጵያውያን የግሪክ መንግስት የ1 ወር የመንቀሳቀሻ ቪዛ የሰጣቸው ሲሆን ከወር በኋላ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ ገልፆልናል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደማይፈልጉና በአውሮፓ ለመኖር የኢትዮጵያውያንን እርዳታ እንደሚሹ ተናግረዋል፡፡  
በተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆች ላይ በአደጋው ከ100 እስከ 250 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን መሞታቸው የተገለፀ ሲሆን የአንዳንዶቹ ሟቾች ማንነት መታወቁን በመግለፅም ፎቶግራፋቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ሚያዚያ 23 ቀን 2007 ዓ.ም ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 950 አፍሪካውያንን ከሊቢያ ወደ ጣልያን ስታሸጋግር የነበረች መርከብ ሰጥማ ከ900 በላይ የሚሆኑት መሞታቸው የሚታወስ ነው፡፡

Read 4289 times