Saturday, 16 April 2016 11:27

ዱባይ የአለማችንን ረጅም ህንጻ በ1 ቢ. ዶላር ልትገነባ ነው

Written by 
Rate this item
(9 votes)

 የአለማችን ረጅሙ ህንጻ የሆነውና 828 ሜትር ቁመት ያለው ቡርጂ ከሊፋ መገኛ የሆነቺው ዱባይ፣ በቁመቱ አዲስ የአለም ክብረወሰን እንደሚያስመዘግብ የተነገረለትን አዲስ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ በ1 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለመገንባት ማቀዷን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ እጅግ ያማረ የስነ-ህንጻ ጥበብ የተገለጠበት ነው የተባለውን የዚህን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ግንባታ ፕሮጀክት የያዘው “ኢማር ፕሮፐርቲስ” የተባለው ተቋራጭ ኩባንያ ስለሚገነባው አዲስ ህንጻ ቁመት ባይገልጽም፣ ግንባታው በአራት አመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡
20 የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ወለሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የመኖሪያ ክፍሎች፣ ሆቴልና ሌሎችን ይይዛል የተባለውንና የዱባይን ገጽታ ሙሉ ለሙሉ ሊያሳይ የሚችል ማማ ያለውን ይህን ህንጻ ዲዛይን ያደረገው ስፔናዊው የኪነ-ህንፃ ባለሙያ ካልትራቫ ቫልስ ሲሆን፣ የሚገነባውም በዱባይ መካከለኛ ስፍራ ላይ እንደሚሆን ተነግሯል፡፡
በቁመቱ እርዝማኔ የአለማችንን ክብረወሰን ይዞ የሚገኘው የዱባዩ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ቡርጂ ከሊፋ፣ ለግንባታው 1.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገበትና በ2010 መጀመሪያ ላይ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 5789 times