Saturday, 16 April 2016 11:19

ቦኮ ሃራም ለጥፋት የሚያሰማራቸው ህጻናት ቁጥር በ11 እጥፍ ጨምሯል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 - የ8 አመት ህጻንን ለአጥፍቶ መጥፋት አሰማርቷል

     በምዕራብ አፍሪካ አገራት የሽብር ተግባራት መፈጸሙን አጠናክሮ የቀጠለው ጽንፈኛው ቡድን ቦኮ ሃራም፤ በተለያዩ አካባቢዎች ለአጥፍቶ መጥፋት ተግባር የሚያሰማራቸው ህጻናት ቁጥር ባለፈው አመት በ11 እጥፍ እንዳደገ ዩኒሴፍ መግለፁን ሮይተርስ ዘገበ፡፡ ዩኒሴፍ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርቱ እንዳለው፣ ቦኮ ሃራም ባለፉት ሁለት አመታት በናይጀሪያ፣ በካሜሩንና በቻድ በፈጸማቸው የሽብር ጥቃቶች ላይ ካሰማራቸው አጥፍቶ ጠፊዎች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት ሲሆኑ አብዛኞቹም ሴቶች ናቸው፡፡ ቦኮ ሃራም ለሽብር ተግባሩ የሚመለምላቸውና ለጥቃት የሚያሰማራቸው ህጻናት ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በ2014 አራት ህጻናትን በአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ላይ ያሰማራው ቡድኑ፣ ድርጊቱን በማጠናከር ባለፈው አመት 44 ህጻናትን ለጥቃት ማሰማራቱን አስታውቋል፡፡ ቡድኑ በአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ካሰማራው ህጻናት መካከል ዝቅተኛውን ዕድሜ የያዘው የ8 አመት ህጻን እንደሆነ ዩኒሴፍ ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ ቡድኑ በናይጀሪያ፣ ካሜሩን፣ ቻድ እና ኒጀር በፈጸማቸው የሽብር ጥቃቶች ሳቢያ 1.3 ሚሊዮን ህጻናት ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸውንና 670 ሺህ ያህሉም ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን አመልክቷል፡፡

Read 1302 times