Saturday, 16 April 2016 11:24

አውሮፓ በገንዘብ ቀውስ ልትመታ እንደምትችል ተነገረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 - የአውሮፓ ታላላቅ ባንኮች የከፋ ችግር ውስጥ ገብተዋል
     - የእንግሊዝ ከህብረቱ አባልነት መውጣት፣ በአህጉሪቱ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል ተብሏል

    አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ የአውሮፓ አህጉር በገንዘብ ቀውስ ልትመታ እንደምትችል ሰሞኑን ባወጣው የግማሽ አመት አለማቀፍ የገንዘብ ሁኔታ ሪፖርት፣ ማስጠንቀቁንና በአለማቀፉ የገንዘብ መረጋጋት ላይ የተጋረጡ አደጋዎች ተባብሰዋል ማለቱን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡ በአውሮፓ አገራት ከሚገኙ ባንኮች አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ትርፋማ ሆነው እንዳይቀጥሉ በሚያግዷቸው የከፉ ችግሮች መተብተባቸውን ያስታወቀው ተቋሙ፣ በአገራቱ ባንኮች ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት አፋጣኝ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለበት አሳስቧል፡፡
ባለፈው የካቲት ወር ላይ በአህጉሪቱ በተከሰቱ የባንክ ቀውሶች ክፉኛ ከተጎዱት መካከል፣ የግሪክ፣ የጣሊያንና የፖርቹጋል ባንኮች እንደሚገኙባቸው ያስታወሰው ተቋሙ፣ እየተባባሰ የቀጠለው የገንዘብ ቀውሱ በመላ አህጉሪቱ የሚገኙ ባንኮችን ተጠቂ ሊያደርግ እንደሚችልም አስጠንቅቋል፡፡ ቢቢሲ በበኩሉ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ባወጣው አለማቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ ሪፖርት፣ ለረጅም ጊዚያት አዝጋሚ ሆኖ የዘለቀው የአለማችን ኢኮኖሚ እድገት ዘንድሮም 3.2 በመቶ ብቻ ሊያድግ እንደሚችል በመጥቀስ፣ የአለም ኢኮኖሚ ለአደጋ የበለጠ ተጋላጭ ሆኗል ማለቱን ዘግቧል፡፡
በዘንድሮው አመት ከአለማችን አገራት የኢኮኖሚ እድገቷ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ተብሎ የምትጠበቀው ናይጀሪያ ናት ያለው ዘገባው፤ ብራዚል፣ ሩስያና ሌሎች በርካታ የአለማችን አገራትም ዘንድሮ ያስመዘግቡታል ተብሎ ከተገመተው የኢኮኖሚ እድገት ያነሰ እድገት እንደሚያስመዘግቡ ይጠበቃል መባሉንም ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜናም እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት መውጣቷ በአካባቢው አገራትና በአለማቀፍ ደረጃ የከፋ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ሲል አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ማስጠንቀቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የእንግሊዝ ከህብረቱ አባልነት መውጣት ለረጅም ጊዜ የዘለቁ የንግድ ግንኙነቶችን ከማቃወሱ በተጨማሪ ለእንግሊዝም ሆነ ለተቀሩት የአውሮፓ አገራት ፈታኝ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ያለው ተቋሙ፣ በጉዳዩ ዙሪያ የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ በኢንቨስተሮች ዘንድ ያለመተማመን ስሜት መፍጠሩንም ገልጧል፡፡

Read 1549 times