Saturday, 16 April 2016 10:55

‘ተመሳስለው የተሠሩ…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(15 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እግዚአብሔር መጀመሪያ ዓዳምን ፈጠረ፡፡ ከዚያም በደንብ አየውና ምን አለ መሰላችሁ…
“ከዚሀ የተሻለ ፍጡርስ መፍጠር እችላለሁ…” አለና ሔዋንን ፈጠረ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…
የምር ግን ዘንድሮ የአኳኋናችንን ነገር ስናይ… አለ አይደል… “ምናልባት ከሁለቱም የተሻለ ፍጡር መፍጠር አይችልም ነበር!” ልንል ምንም አልቀረን!
ከዚህ በፊት ያወራናት ነገር ነበረች፡፡ ይሄ ተመሳስሎ የመሠራት ነገር እኮ… አለ አይደል… በቃ በየቀኑ የምንሰማው ሆነ፡፡ ድሮ እኮ ፎርጅድ ነገር ከማኦ አገር ብቻ የሚመጣ ይመስልን ነበር፡
ምን ተመሳስሎ የማይሠራ ነገር አለ!
እኔ የምለው…የቻይናን ነገር ካነሳን አይቀር…በዛ ሰሞን ቻይኖቹ ምኑንም ምናምኑንም እየቸረቸሩ አስቸገሩን ነው ምናምን የሚል አቤቱታ የሆነ ነገር ላይ አንብቤያለሁ፡፡ እንዴት ነው ነገሩ!
ስሙኝማ…የቻይናን ነገር ስናነሳ ብቻ ነገርዬው “ፍቅሬ፣ ፍቅሬ በዛ እኔ አላማረኝም…” እንዳይሆን፡፡ አሀ “የፍቅርሽ ፍላጻ፡ ልቤ ተሰክቶ…” ምናምን ነገር ልክ አለዋ! የምር እኮ በዚሁ ከቀጠሉ የሰፈር ሱቆች (‘ዓረብ ቤቶች’) ጉድ ሊፈላባቸው ነው፡፡ ከዚች በፊት ካልናትም እንድገማትማ… “ማሙሽ፣ ሂድና ከአብዶ ሱቅ አንድ ሊትር ዘይት አምጣ…” ምናምን መባል ይቀርና  “ሂድና ከቹን ቺ ሱቅ ዕጣን ገዝተህ ና፣” ሊባል ነው፡፡
ስሙኝማ…‘ተመሳስለው የመሠራት’ ነገር ካነሳን አይቀር…አለ አይደል…‘‘ተመሳስለው የተሠሩ ባህሪያት አስቸግረውናል፡፡ የሆነ ሰው ትንሽ፣ ትንሽ ትዝ የሚላችሁ ሰው ሰላም ይላችኋል፡፡
“አንተ! እዚህ አገር አለሁ እንዳትለኝ! የሚገርምህ ነገር ስንት ጊዜ ስላንተ እጠይቃለሁ መሰለህ! ዩ ሉክ ፋይን ሜን!”
“አለሁ…”
“እንደውም በዛ ሰሞን ማነው…ስሙ ጠፋኝ… እሱን ይሄ ሰውዬ አለ እንዴ ምናምን ስለው ነበር፡፡ ኤቨርገሪን ነህ…”  ምናምን እያለ ይደሰኩርላችኋል፡፡ ከዛም ትለያያላችሁ፡፡
ታዲያላችሁ…ዘወር እንዳለ አብሮት ላለ ሰው ምን ቢለው ጥሩ ነው… “እዚሀ ዓለም ላይ ማየት የማልፈልገው ሰው ቢኖር ይሄ ነው፡፡ እንዴት አይነት ክሩክ መሰለህ!”
ሰወዬው እኮ ሲያቅፋችሁ በጣም ከመጭመቁ የተነሳ ጎድናችሁን ይቆጠቁጣችሁ ጀምሯል!
እናላችሁ…ተመሳስለው የተሠሩ ባህሪያት አስቸግረውናል፡፡
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን ስሙኝማ…ሰባኪው እየሰበኩ ነው፡፡ የዕለቱ ትምህርት ከመጠጥ ሱስ እንዴት ራስን መቆጣጠር እንደሚቻል ነው፡፡
“በዓለም ላይ ያለው ቢራ ሁሉ ቢኖረኝ ወንዝ ውስጥ እደፋው ነበር፣” አሉ፡፡
ምዕመናኑም “አሜን!” አሉ፡፡
“ዓለም ላይ ያለው ወይን ጠጅ ሁሉ ቢኖረኝ ኖሮ ወንዝ ውስጥ እደፋው ነበር፡፡”
አሁንም ምዕመናን “አሜን!” አሉ፡፡
“ዓለም ላይ ያለው ውስኪ፣ ጂንና ቮድካ ቢኖረኝ ወንዝ ውስጥ እደፋዋለሁ፡፡”
ምዕመናኑ እንደገና “አሜን!!” አሉ፡
ሰባኪውም ጨረሱና ተቀመጡ፡፡ የዕለቱ ስርአት አስፈጻሚው ተነስቶ እንዲህ አለ፡፡
“ጉባኤችንን ለማጠቃለል መዝሙር ቁጥር 365 አብረን እንዘምር፣” ይላል፡፡ የመዝሙሩ ርዕስ ምን የሚል መሰላችሁ… ‘ሁላችንም ወንዙ ዳር እንሰባሰብ፡፡’ አሪፍ አይደል! ያ ሁሉ መጠጥ ከውሀው እስኪቀላቀል ጊዜ ይፈጃል አይደል!
ወይ ቢራና ወይን ጠጅ!
እናላችሁ…‘ተመሳስለው የተሠሩ’ ባህሪያት አስቸገረውናል፡፡
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አሁን፣ አሁን እኮ ሰላምታ እንኳን ሲበዛብን…አለ አይደል…ይቺ ነገር እንዴት ነች ምናምን እንላለን፡፡ አንድ ቀን አብራችሁ ሻይ ያልጠጣችሁት፣ በራስ እንቅስቃሴ እንኳን በቅጡ ሰላም ብላችሁ የማታውቁት ሰው ድንገትም “አንተ፣ ሰው ይናፍቃልም አትል!” ምናምን አይነት ሰላምታ ሲሰጣችሁ…አለ አይደል…የሆነ የሚከብዳችሁ ነገር አለ፡ ጊዜው ተለዋውጧላ!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ግለኝነት የበዛ አይመስላችሁም! የምር ሁላችንም “ሁሉም ነገር ለእኔ ብቻ!” የሚል መመሪያ አልጋችን አጠገብ ለጥፈን ጧት ማታ እንደ ጸሎት የምንደጋግመው እያስመሰለብን ነው፡፡ እናላችሁ…አስተሳሰባችን ሁሉ በራሳችን ዙሪያ ጠቦ፣ ጠቦ መፈናፈኛ እንዳናጣ ያስፈራል፡፡ አሀ…አእምሯችንም ሁለት በርጩማ ብቻ ያለው ሳሎን ቤት ሊመስል ይችላላ!
ይቺን ስሙኝማ…የበሽተኛው ቤተሰቦች አልጋው አካባቢ ተኮልኩለዋል፡፡ ስለ ጤንነቱ ሁኔታ ዶክተሩ እየነገራቸው ነበር፡፡
“ሁኔታዎች ጥሩ አይደሉም፡፡ ያለው ብቸኛ መፍትሄ የአንጎል ንቅለ ተከላ ማካሄድ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ህክምና ገና በምርምር ደረጃ ላይ ያለ ነው፡፡
 ሊሠራም፣ ላይሠራም ይችላል፡፡ ግን ይሞከር ካላችሁ የምነግራችሁ ነገር አንጎል ለመግዛት በጣም ውድ ነው፡፡ ወጪውን ደግሞ ሆስፒታሉ ሳይሆን እናንተ መሸፈን አለባችሁ፡፡”
“እሺ፣ ለመሆኑ አንድ አጎል ምን ያሀል ያወጣል?” ሲል አንደኛው ዘመድ ጠየቀ፡፡
“ለወንድ አንጎል አምስት መቶ ሺህ ዶላር ይጠየቃል፡፡ ለሴት አንጎል ደግሞ ሁለት መቶ ሺህ ዶላር ይጠየቃል፣” አለ ዶክተሩ፡፡
አንዳንዶቹ ወጣት ወንዶች የደነገጡ ለመምሰል ሞከሩ፡፡ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች በመስማማት ራሳቸውን ነቀነቁ፡፡ እንደውም አፋቸውን እየሸፈኑ እንደመሳቅም አደረጋቸው፡፡ ከዛ በኋላ የበሽተኛው ሴት ልጅ “በወንዶችና በሴቶች አንጎሎች መካካል የዋጋ ልዩነት የተፈጠረው ለምንድነው?” ስትል ጠየቀች፡፡
ዶክተሩ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “የወንዶቹ አንጎል ይህን ያህል ጥቅም ላይ የማይውል ስለሆነ ባዶ ነው፡፡ ስለዚህም ዋጋው ከፍ ይላል፡፡ የሴቶቹ አንጎል ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ ስለሚውልና የሠራ ስለሆነ ዋጋው ዝቅ ያለ ነው፣” ብሏቸው አረፈ፡፡  
እናላችሁ…ተመሳስለው የተሠሩ ባህሪያት እያስቸገሩን ነው፡፡
እኔ የምለው..እግረ መንገዴን እኔ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ግለኝነት በዛ ምናምን ይባላል፡፡ ሁሉም “እኔ፣ እኔ ብቻ!” ሆነ አይደል!
የምር ግን “እኔ፣ እኔ ብቻ!” ማለቱ ሳይሆን… ለምንድነው የኛ ሰው መልካም እንዲገጥመው የማንፈልገው? ለምንድነው አጥራችንን ያልነቀነቀውን፣ ወሰናችንን ያልገፋውን ሰው (ድንቄም ‘ወሰን’!) ከመሬት ተነስቶ ክፉውን መመኘት?
እናላችሁ…‘ተመሳስለው የተሠሩ ባህሪያት’ እያስቸገሩን ነው፡፡
የሆነ አውቀዋለሁ ብላችሁ የምታስቡት ሰው ይቀጥራችሁና “ስማኝ… የሆነ ሀሳብ አለኝ፣ አብረን ብንሠራ…” ይላችኋል፡፡ እናንተም እንዲህ ሥራ በጠፋበት፣ ሁሉም ሰው ኬኩን ጠቅልዬ ካልወሰድኩ በሚልበት ዘመን አብረን እንሥራ የሚል መገኘቱ “ለካስ ደግነት ሙሉ ለሙሉ አልጠፋችም…”  ትሉና…
“ደስ ይለኛል…” ምናምን ነገር ትሉታላችሁ፡፡
“ምን መሰለህ ያሰብኩት…” ይልና አሰብኩት የሚለውን እየቆጠበ ይነግራችኋል፡፡ እናንተም…
“ፍሬሽ የሆነ ግሩም ሀሳብ ነው…” ትላላችሁ፡፡
“አንተ ምን ይመስልሀል?” ይላችኋል፡፡ ይሄን ጊዜ… እንግዲሀ ሥራም አይደል፣ እየተሠለሰ የሚበላውን ቁርስ በየቀኑ ለመብላት የሚያስችል አይደል…ምን አለፋችሁ… የምታስቡትን ትዘከዝኩለታላችሁ፡፡ እንዲህ ብናደርግ፣ በዚሀ መንገድ ብንሄድ፣ እንትን የተባለውን ድርጅት ብናናግር…እያላችሁ የምታስቡትን ትዘረግፋላችሁ። እሱዬውም በከፍተኛ ስሜት ይሰማችኋል፡፡ በኋላም…
“ይገርምሀል ይሄን ሁሉ አላሰብኩትም ነበር። በጣም አሪፍ፣ አሪፍ ሀሳብ ነው ያመጣኸው፡፡ ቆንጆ የሆነ ስፖንሰርሺፕ የሚያመጣ ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ነው የምንሠራው…” ምናምን ይላል፡፡ ከዛም በሁለት፣ በሦስት ቀናት ውስጥ እንደሚደውል ቃል ይገባላችሁና ትለያያላችሁ፡፡ ሁለትና ሦስቱ ቀን ወደ ሀያና ሠላሳ ቀናት ሲለጠጥ እንደተሸወዳችሁ ታውቃላችሁ፡፡
የምር ግን… እንደዚህ አይነት ብልጥነት በብዛት ነው ያለው፡፡ መልካም ሰው ነው፣ የሚታመን ሰው ይመስላል ያላችሁት ሰውዬ ለካስ ‘ተመሳስሎ የተሠራ’ ባህሪይ ይዞ ነው የቀረባችሁ!
ተመሳስለው ከተሠሩ ሁሉም ነገሮች አንድዬ ይጠብቃችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4446 times