Saturday, 16 April 2016 10:41

ከተቃዋሚ አመራሮች ጋር በሽብር ከተከሰሱት ሶስቱ ጥፋተኛ ተባሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

      ከተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮች ጋር በአንድ መዝገብ የሽብር ክስ ቀርቦባቸው ከነበሩት መካከል 3 ግለሰቦች ጥፋተኛ ሲባሉ ሁለቱ በነፃ ተሰናብተዋል፡፡ ከሠማያዊ፣ አንድነትና አረና አመራሮች አቶ    ሃብታሙ አያሌው፣ አቶ የሸዋስ አሠፋ፣ አቶ ዳንኤል  ሺበሺና አቶ አብርሃ ደስታ ጋር በአንድ መዝገብ የሽብር ክስ ቀርቦባቸው የነበሩትና ይከላከሉ የሚል ብይን ተሰጥቶባቸው የነበሩት አቶ ዘላለም ወ/ አገኘሁ፣ አቶ ሰለሞን ግርማና አቶ ተስፋዬ ተፈሪ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ባለመቻላቸው ትናንት ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ ቀደም ሲል እንዲከላከሉ ከተበየነባቸው መካከል ዮናታን ወልዴና ባህሩ ደጉ የቀረበባቸውን ክስ በበቂ ተከላክለዋል በሚል ፍ/ቤቱ በነፃ  አሰናብቷቸዋል፡፡ ጥፋተኛ የተባሉት ሶስቱ ግለሰቦች በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ 7(1) የተደነገገውን  በማንኛውም መልኩ በሽብር ተግባር መሳተፍ ጥሰዋል ተብለው ነው ጥፋተኛ የተባሉት፡፡
አቃቤ ህግ ከአንድ ዓመት ከ9 ወር በፊት የሽብር ክስ የቀረበባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ ከ10 ግለሰቦች መካከል የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን በአሁን ወቅት ይግባኝ ተጠይቆባቸው
ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡

Read 3418 times