Saturday, 16 April 2016 10:31

ኢትዮጵያ በኤሌክትሮኒክስ የገንዘብ ማስተላለፍ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

   ኢትዮጵያ በዘመናዊ የፋይናንስ አገልግሎት (ዲጂታል ፋይናንሻል ሰርቪሰስ) አጠቃቀም ከዓለም አገራት ጋር ስትነፃፀር እጅግ ኋላ ቀርና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የጠቆመው አንድ ጥናት፤ ከ10 አዋቂ ሰዎች ሰባቱ፣ የባንክ፣ የማክሮ ፋይናንሻል ተቋም ወይም የቁጠባና ብድር ኅብረት ማኅበራት ሂሳብ እንደሌላቸው ያመለክታል፡፡  በኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ ጋባዥነት ጥናቱን ያካሄዱት በዓለም ታዋቂው ኤክስፐርትና በዲጂታል  ፋይናንሻል ሰርቪስስ (ዲ ኤፍ ኤስ) በኤሌክትሮኒክስ የገንዘብ አጠቃቀም ላይ ትምህርት የሚሰጡት  ሚ/ር ላግናሲዮ ማስ፣ ኢትዮጵያውያን ለሀብት ፈጠራ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱት አስተማማኝ  ቁጠባና ኢንቨስት ማድረጊያ ዘዴዎች እየራቋቸው ነው ብለዋል፡፡  ዲኤፍኤስ በመደበኛው የባንክ ሲስተም ተጠቃሚ ያልሆኑትን እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸውን  ኢትዮጵያውያን በአጭር መንገድ መድረሻ መንገድ ነው ያለው ጥናቱ፤ የዲኤፍ ኤስ አሰራር የሚመራው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስለሆነ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ማብቂያ ዓመት በ2012፣ በአሁኑ ወቅት የባንክ አገልግሎት የማያገኙ ሰዎች ባንኮች፣ ማይክሮ ፋይናንሻል ተቋማትና ወኪል ባንኮች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ በሞበይል ስልኮችና በፓሳ (Point of Sales) መሳሪያዎችና በኔትዎርክ ወኪሎች አማካይነት መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት በተሻለ ምቾትና አሁን ባንክ ከሚያስከፍለው ዋጋ ባነሰ ክፍያ ያገኛሉ ሲል ገልጿል፡፡ በበርካታ አገሮች ዲ ኤፍ ኤስ በሽግግር ደረጃ ቢሆንም ብዙ አገሮች ገንዘብ ለማስተላለፍና ክፍያ ለመፈጸም ይጠቀሙበታል፡፡ ይህም ገንዘብ ተሸክሞ መሄድን ያስቀራል፣ ገንዘብ የሚለዋወጡበትን ዋጋ ይቀንሳል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሜክሲኮ ናት፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁሉም የመንግሥት ክፍያዎች የሚፈጸሙት በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ነው ብሏል፡፡ ጥናቱ ዲኤፍኤስ ያለበትን ደካማ ጎንም አመልክቷል፡፡ በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ  የራሳቸውን ፕሮጀክት ከፍ ለማድረግ በሚታገሉ የተለያዩ የገበያ ተዋናዮች መካከል የተበታተነ ነው፡፡ የተበታተኑትን አሰባስቦ በመላ አገሪቷ ተግባራዊ የሚሆን የወኪል ኔትወርክ ለመፍጠር ከ30 ሚሊዮን ዶላር እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚፈጅ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል በማለት
አመልክቷል፡፡ ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ በ2002 የተመሰረተ ሲሆን በሴቶችና በኢንቫይሮመንት ላይ በማተኮር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ሀብትና የሥራ ዕድል እንዲፈጠር የሚሠራ ድርጅት ነው፡፡ በአራት
ዘርፎች ላይ አተኩሮ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን እነሱም ጥጥ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳት፣ ከብቶች
ፍራፍሬና አትክልት እንዲሁም ገንዘብ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት 4,000 ሄክታር መሬት አልምቷል፡፡
ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ፤ በ150 የገበሬ ኅብረት ሥራ ማህበራት ስር የተደራጁ 8,360 አባላት
ሲኖሩት ካፒታሉም 51.5 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ 

Read 1711 times