የኦስካር አሸናፊዎችን በመምረጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው የአካዳሚ ኦፍ ሞሽን ፒክቸርስ አባላት ተዋፅኦ ለጥቁሮችና ለሴቶች በቂ ቦታ አልሰጠም በሚል የሽልማት ስነስርዓቱ ተብጠልጥሏል፡፡ ከ5783 የአካዳሚው አባላት 94 በመቶ ነጮች እንዲሁም 77 በመቶ ያህሉ ወንዶች መሆናቸውን ሎስ አንጀለስ ታይምስ ይፋ ባደረገው የምርመራ ሪፖርት አረጋግጧል፡፡ ከኦስካር ምሽት በኋላ በታዋቂ ሰዎች የተዘጋጁ የፓርቲ ድግሶች አሸናፊዎችን በእንግድነት ለመጋበዝ ሽሚያ ገብተዋል፡፡ከኦስካር ምሽቱ በኋላ ብዙዎቹ አሸናፊዎች ይታደሙታል የተባለው ፓርቲ “ጋቨርነርስ ቦል” የተባለው ሲሆን በፓርቲው 1500 እንግዶች 1000 ጠርሙስ ምርጥ ሻምፓኝ ይራጫሉ ተብሏል፡፡ ከፓርቲዎቹ መካከል ማዶና እና ዴሚ በጋራ ያዘጋጁት እና የኤልተን ጆን የኤድስ ፋውንዴሽን ያሰናዳው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 84ኛው ኦስካር እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛል ተብሎ ሲጠበቅ የአምናው ስነስርዓት 74.4 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቷል፡፡