Saturday, 25 February 2012 13:32

ዴንዝል ዋሽንግተን ቦክስ ኦፊስን ይመራል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የዴንዝል ዋሽንግተን አዲስ ፊልም ‹ሴፍ ሃውስ› በቦክስ ኦፊስ ሳምንታዊ የገቢ ደረጃ እየመራ ነው፡፡ ሰሞኑን በሰሜን አሜሪካ 24.8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኘው ፊልሙ ለእይታ ከበቃ 11 ቀናት ሆኖታል፡፡ የዓለም ዙርያ ገቢው ደግሞ 102.2 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡  በ85 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተሰራው ፊልሙ፤ አንድ ከእስር ያመለጠ ሰው ከሲአይኤ ጋር በተያያዘ ጉዳይ የገባበትን ሰዶ ማሳደድ ያሳያል፡፡

በዳንኤል ኢስፒኖዛ ዲያሬክት የተደረገው ፊልሙ፤ በደቡብ አፍሪካ  የተቀረፀ ትእይንት ተካቶበታል፡፡ የ57 ዓመቱ ዴንዝል ዋሽንግተን በዚህ ዓመት ለእይታ የሚበቃ “ዘ ማትሪስ ሰርክል” በተባለ ፊልም ላይ እየሰራ ሲሆን “ፍላይት” የተባለው ሌላ ፊልሙ ከዓመት በኋላ እንደሚታይ ይጠበቃል፡፡

የ57 ዓመቱ ዴንዝል ዋሽንግተን በፊልም ትወና ሙያ ለ30 ዓመታት የሰራ ሲሆን ሁለት ጊዜ የኦስካር ሽልማት ወስዷል፡፡  ዴንዝል ከ40 በላይ ፊልሞችን መስራቱን የሚገልፀው የቦክስ ኦፊስ ሞጆ መረጃ፤ ፊልሞቹ በሰሜን አሜሪካ 1.94 ቢሊዮን ዶላር በመላው ዓለም ደግሞ 3.19 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘባቸው አመልክቷል፡፡

 

 

 

Read 1669 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 13:33