Saturday, 09 April 2016 09:26

ለድርቅ ተረጂዎች ከሚያስፈልገው ግማሽ ያህሉ ከለጋሾች ተገኝቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(20 votes)

የአውሮፓ ህብረት ከ 2.9 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

    በኢትዮጵያ ለድርቅ ተጐጂዎች ከሚያስፈልገው አጠቃላይ የእርዳታ መጠን ግማሽ ያህሉ ከውጭ ለጋሾች መገኘቱ የተገለፀ ሲሆን፤ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ከ2.9 ቢሊዮን ብር በላይ  እርዳታ ሰሞኑን መለገሱን አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ የድርቁን አደጋ ለመቋቋም ወደ 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የመንግስት ሪፖርት የሚያመለክት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 48 በመቶ ያህሉን የውጭ ሃገር ለጋሾች ለመሸፈን  ቃል መግባታቸውን የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሣ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
 በአሁን ወቅት ከለጋሾች እየተገኘ ያለው እርዳታ መንግስት ለድርቁ የሚያውለውን የገንዘብ መጠን የሚቀንስለት ሲሆን ለጋሾች እርዳታውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ ተላልፏል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ለድርቁ ተጐጂዎች የሚያደርገውን ሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሶ ድርቁን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚደረግን ጥረት አጥብቆ እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡
ህብረቱ የለገሰው ገንዘብ አሁን ላለው ሰብአዊ ቀውስ ድጋፍ የሚውል ከመሆኑ በተጨማሪ የድርቅ አደጋውን በቀጣይ ለመከላከል ለሚሰሩ ስራዎችም ይውላል ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ10 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን የእለት ጉርስ ለማግኘት ከፍተኛ ትግል እያደረጉ መሆኑን የጠቀሱት በህብረቱ የሰብአዊ ድጋፍ ኮሚሽነር ክሪስቶስ ስታይሊ አንዲስ፤ ድርቁ የፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ በእጅጉ አስጨናቂ ነው ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት አለማቀፍ የልማትና ትብብር ኮሚሽነር ሚሚካ እና የሰብአዊ ድጋፍ ኮሚሽነሩ ስታይሊ አንዲስ ከትናንት በስቲያ በድርቁ ከተጐዱ የሃገሪቱ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ድሬደዋ አካባቢ ጉብኝት ማድረጋቸውንና እየተደረገ ያለውን ሰብአዊ ድጋፍ መመልከታቸውን ህብረቱ አስታውቋል፡

Read 3053 times Last modified on Saturday, 09 April 2016 15:26