Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 25 February 2012 13:14

ጋሽ ስብሃት አንድም ሦስትም ነው!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ደራሲ፣ አዋቂ እና ነገር-አዋቂ

ጋሽ ስብሃት ካስተማረን ነገሮች አንዱና ዋነኛው ድፍረት ይመስለኛል፡፡ ባዶ ድፍረት ሳይሆን የሥነፅሁፍ ድፍረት፡፡ ቁም ነገር ያዘለ ድፍረት፡፡ ውበት ያለው ድፍረት፡፡ ዕውቀት ያለው ድፍረት፡፡ ይህንን ዓይነቱን ድፍረት ደግሞ እንዲያው ልብን ስለሞሉና ደረትን ስለነፉ አያገኙትም፡፡ ደንፊ - ፖለቲከኛ ስለሆኑም አያገኙትም፡፡ አንድም በመማር፣ ሁለትም በማንበብ፣ ሶስትም በመኖርና በመብሰል፤ የሚያገኙት ነው፡፡ ስብሃት እነዚህ ሦስት ነገሮች ካሏቸው ጥቂት ደራሲያን አንዱ ነው፡፡ ከሦስቱ ነገሮች እጅግ የሚጠናበት ደግሞ ማንበቡ ይመስለኛል፡፡ ማንበብ ቢሉም ሥር-የሰደደ ማንበብ ነው - መመራመር፣ ማውጠንጠንና ማስታወስ የታከለበት፡፡ ከነዚህ ከሦስቱ ደግሞ ማስታወስ የጋሽ ስብሃት የጠና ችሎታው ይመስለኛል፡፡ ጋሽ ስብሃት እንግዲህ አንድም ሦስትም ነው ስል እንዲህ እንዲህ ያሉትን ጠባዮቹን ከቁጥር ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ አንድ ሌላ ምሳሌ ላክል፡፡ ጋሽ ስብሃትን በሦስት ጠባያቱ ከማይበት አንዱ አስረጅ፡- ስብሃት የሥነፅሁፍ ሰው ነው፡፡ ስብሃት የፖለቲካ ሰው ነው፡፡ ስብሃት የዕውቀት ሰው ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን “ሽፍቶችና መሪዎች” የሚለው ፅሁፉ ነው፡፡ ለእኔ እስከዛሬ ከፃፋቸው ፅሁፎች ሁሉ በእጅጉ ስብሃትን የሚገልፅልኝ ፅሁፍ ነው፡፡ ሥነፅሁፍ ነው … ውስጠ-ወይራ ነው … ታሪክ ነው፤ አንድም ሶስትም ነው!

“በሽፍቶችና መሪዎች ፅሁፉ ውስጥ፤ ካስትሮ ቼ ጉቬራን ከድል በኋላ ሹሞት ሲያበቃ በኋላ ነገሩ አላምር ሲለው፤

“እንግዲህ ቼ፤ ሂድና ሌላ ቦሊቪያ ፈልግ!” አለው፣ ይላል ጋሽ ስብሃት፡፡ በትግል ወቅት አብረው የተጓዙ ጓዶች እንዲህ ይለያያሉ እንዲህ ይከዳዳሉ፣ ነው መልዕክቱ፡፡ በየዘመኑ እንዲህ ዓይነቱን ክስተት አይተናልና የስብሃትን ነገር - አዋቂነት እንመሰክራለን! የታሪክን ሰዎች በማንሳቱ ታሪክ አዋቂነቱን እንመሰክራለን! ውሽማ እንዴት ባል እንደሚሆን በፈጠራ በማስገንዘቡም የሥነጽሁፍ ሰውነቱን እንመሰክራለን!

ስብሃትን ሳውቀው ብዙ ጊዜዬ ነው፡፡ ሲቲሆል ሻይ ቤት (ማክሲም) ውስጥ ከነሡራፌል፣ ከነሥዩም፣ ከነመስፍን ሀብተማሪያም ጋር ነው ያገኘሁት - ፌስታሉን እንደያዘ፤ መጽሀፉን እንደገለጠ፤ ስለ መጽሐፍ እንደተረከ፡፡ በኋላም ከባሴ ጋር ሦስታችን አንድ ላይ የተወያየንበት ጊዜ ትዝ ይለኛል፡፡ ባሴ ያነበበ ልጅ ነው፡፡ እኔም፣ ስብሃትም ፈዘን ነበር የምናዳምጠው፡፡ የሚያወጋን ሰው ሞቶ ፍትሐቱ ሲፈታ ቄሶቹ ስለሚቀድሱት ቅዳሴ ይዘት ነበር፡፡ ባለፈው ሰኞ የጋሽ ስብሃት አስከሬን በሥላሴ ካቴድራል ፊት ለፊት እንደተቀመጠ ያ ባሴ ሲያወራልን የነበረበትን ሁኔታ ነበር የቀሰቀሰብኝ፡፡ ነብሳቸውን ይማር ሁለቱም ሄደዋል፡፡ ታዲያ ጋሽ ስብሃት “ባሴ፤ ፍትሐት ብንፈታም ባንፈታም ዋናው መሞታችን ነው” አለ፡፡ ዛሬ ፍትሐቱ ተፈቷል፡፡

ቀጥሎ ትዝ ያለኝ ደምሴ ፅጌ ነው፡፡ አንድ ቡና ቤት ቁጭ ብለናል፡፡ መስፍን ዓለማየሁም አለ፡፡ ሽማግሌውና ባህሩን እየተረጎመ የነበረበት ጊዜ ነው፡፡ (ነብሳቸውን ይማር ሁለቱም የሉም)

“ኢህአዴግ ከገባ በኋላ ደራሲው ሁሉ የት እንደገባ እንጃ መዓት ነገር ይፃፋል ብዬ ነበር” አልኩ፡፡

“ለድርሰት ያው ጨለማው ዘመን ሳይሻለን አልቀረም፡፡ ከጨለማው ወደ ብርሃኑ ሲያወጡን ከባህር የወጣ አሣ ሆንን!” አለና ሳቀ መስፍን፡፡

ደምሴ ፅጌ “ኧረ አያስቅም መስፍን፡፡ “ደራሲ የሌለው አገር ከዘመኑ የባሰ ጨለማ ነው” ያለው ማን ነበረ?” አለ፡፡

“ለመሆኑ ምን እያረጋችሁ ነው እናንተስ?”

“ባክህ ግራ ገብቶናል” አለ ደምሴ፡፡

“ናዲን ጎርዲመር የደቡብ አፍሪቃዋ የኖቤል አሸናፊ No one to accompany me የሚለውን መጽሐፍ የፃፈችው፤ ታቋት የለም?” በአዎንታ ሁለቱም ራሳቸውን ነቀነቁ፡፡

“እሷን የደቡብ አፍሪቃ ደራሲያን ጠየቋት - “ከነፃነት በኋላ ግራ ገባን፡፡ የምንፅፈው አጣን፤ ምን ይሻላል?” አሏት፡፡ እሷም “write about your beautiful confusions” አለቻቸው፡፡ (ስለውቡ ግራ መጋባታችሁ ፃፉ) ተሳሳቅን፡፡

“ያ ሽማግሌ (ስብሃትን ማለቱ ነው) ደግሞ ምን ብሏል መሰለህ - “ድርሰት የሚመጣልህ ስትደናበር ነው!” አለ ደምሴ፡፡

መስፍን ዓለማየሁ ቀበል አድርጎ፤

“ስብሃትንኮ ደራሲ መሆኑን የምታውቀው ሲፅፍ አይደለም - ሲናገር ነው!” አለ፡፡ “ዕውነት ነው - እንደውም ሳያስብ የሚናገረው ነው - ድርሰት የሚመስለው! ለመሆኑ ትገናኛላችሁ ከጋሽ ስብሃት ጋር?” አልኩ፡፡

“እንዴታ! ሽማግሌውኮ ሲንከረፈፍ የማይገኝ ይመስልሃል እንጂ እንደ እግዚያብሔር ሁሉ ቦታ ነው የሚገኘው!” ሳቅን፡፡

መስፍን ቀልዱ ሩቅ ነው - አሪፍ የዱሮ ቴክስ ነው፡፡ ስለሙዚቃ፣ ስለፊልም፣ ስለቴያትር ሲያወራ መጽሐፍ የሚያነብ ነው የሚመስለው - ሲያወራ ይጣፍጥለታል፡፡

“ስብሃት” አለ ቀጠለና “የዱሮ የነጆን ዌይን ፊልም ላይ አንድ መጠጥ ቤት ውስጥ ቴክሶቹና እነስታሩ ሲታኮሱ ጥግ ይዞ መጽሐፍ እያነበበ ብራንዲ የሚጠጣ ሽማግሌ ይመስለኛል፡፡ ታዲያ ጠጋ ብለህ ስብሃትን - ተኩሱ ከበረደ በኋላ - እነ ቴክሱ ሲታኮሱ የት ነበርክ ብትለው - “እነሱን ራሳቸውን ስብሃት ሲያነብ የት ነበራችሁ? በልና ጠይቃቸው እንጂ! የነሱ ተኩስ ብቻ ነው የሚሰማህ? የኔ ማንበብ አይሰማህም? ብሎ ያስቅሃል!”

“አንተም የዋዛ አይደለህም፤ ሴናሪዮውን እኮ እዚሁ ድርሰት አደረግኸው!” አልኩት፡፡

መስፍን አላቆመም፡፡

“ቅድም ምን ታደርጋላችሁ? ላልከው ግን አንድ ነገር ልንገርህ፡፡ ኢህአዴግ እንደገባ ሰሞን እኔ፣ ስብሃትና ደምሴ ፅጌ ተገናኘንልህ፡፡ እንደተለመደው ፖለቲካውን ወሸከትን ወሸከትንና እንግዲህ ሁላችንም ተባራሪ ሥራ ከመሥራት በቀር ሥራ የለኝም፤ ኧረ ሥራ እንሥራ” አልኩኝ፡፡ ሽማግሌው ምን ይለኛል “ይሄው እያወራን አይደለም እንዴ? እዚህ አገርኮ ከወሬ የተሻለ ሥራ የለም” አለ ፍርጥም ብሎ፡፡

ደምሴም፤ “ቀልዱ ቀልድ ነው ጋሽ ስብሃት፡፡ ወይ ትርጉም ወይ ወጥ ልብወለድ እንፃፍ፡፡ አለበለዚያ አጭር ልብ ወለድ እናሳትም፡፡ ገና ለገና ኢህአዴግን ጠላን ብለን ሳንሠራ ልንቀመጥ ነው እንዴ?” አለልህ፡፡ መስፍን ሲያወራ እዚያው ያለህ እንዲመስልህ ያደርገዋል፡፡

“ብዙ አወጣን አወረድንና ኢህአዴግ አሪፍ ሆነም አልሆነም እኛ እምናደርገውን ሥነ ፅሁፋዊ አስተዋፅዖ እንቀጥል፤ ተባባልን፡፡ በዚህ መሠረት እኔ ሬዲዮ ፋና ገባሁ፡፡ ስብሃትና ደምሴ አዲስ ዘመን ገቡ፡፡ ይሄው ጀምረናል እንግዲህ” አለ፡፡

ጋሽ ስብሃትን የማስታውስባቸው አያሌ ነገሮች አሉ፡፡ ወደፊት ሥራዎቹንና እሱነቱን የሚመለከት ሰፋ ያለ ነገር ለመፃፍ አስቤያለሁ፡፡ ለዛሬ አንድ ትውስታ ላኑር፡፡

አንድ ጊዜ ፀጋዬ ገ/መድህንና ማንያዘዋል እንደሻው የቲያትር ዲሬክተርና ፀሀፊ በእፎይታ መጽሔት ላይ ይመላለሱ፣ ይባቀቱ ነበር፡፡ ጋሽ ፀጋዬ “ይሄ ጫታም ትውልድ ነው” ይላል፡፡ ማንያዘዋል “እሳቸውም አንድ ጊዜ ወጣት ነበሩ” ይላል፡፡ ታዲያ ወጣቶች የጋሽ ፀጋዬ ነገር ግራ ይገባቸውና ወደጋሽ ስብሃት ይመጣሉ፡፡ “ጋሽ ስብሃት የጋሽ ፀጋዬ ነገር ግራ ገብቶናል፡፡ “ይሄ ጫታም ትውልድ … ጫቱን መድረክ ላይ ይተፋል!” እያሉ ይሳደባሉ፡፡ አንተ እንዴት ታየዋለህ?” ይሉታል፡፡

ጋሽ ስብሃት እንደተለመደው ጢሙን አሸት አሸት አድርጎ፣

“አትፍረዱበት ልጆች! አንዳንዱ በትልቅ ዛፍ ያምናል፣ አንዳንዱ በትንሽ ዛፍ ያምናል!” አለ፡፡

ጋሽ ስብሃት፣ አዋቂ፣ ነገር አዋቂና የሥነፅሁፍ ሰው ነው - አንድም ሦስትም ነው! ጋሽ ስብሃት ለአዲስ አድማስ ፅሁፍ ሲያቀርብ ስልክ ይደውልና “ማስተር፣ ይሄንን ፅፈነዋል እንዴ?” ይለኛል ጉዳዩን ይነግረኝና፡፡ ወይኔ በኖረ!! እኔም “ማስተር ይሄንን ፅፈናል” እለው ነበር!

 

 

Read 4761 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 15:37

Latest from