Monday, 04 April 2016 07:59

ክፍል-2 ባለፈው ሳምንት ጽሑፌ ከጌታሁን ግምገማ አላሳመኑኝም ያልኳቸውን ነጥቦች አንስቼ ነበር፡፡ በዚህች ጽሑፌ የጌታሁን ሒስ ከርዕሰ-ነገሩ ይልቅ በሰዎች ላይ ማተኮር የሚበዛበት (Ad Hominem)፣ ከእርሱ ሀሳብ የተለየውን ሰው የመከራከር መብት የሚነፍግ (denying right to be skeptic) ሳይንሳዊነት የሚጎድለው እና ብዙም ባይሆን አንድ ቃል አንድ ትርጉም ብቻ ያለው የሚያስመስል

Written by  አሰማኸኝ አስረስ
Rate this item
(4 votes)

      ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 17 አዲስ አድማስ ጋዜጣ በፊት ለፊት ገጹ “ጋዜጠኝነት በሙስና የተዘፈቀ ነው ተባለ” በሚል ርዕስ ያወጣው ዜና የቀረበበት መንገድና የዘገባቸው ጥሬ ሀቆች የምንጭ ስህተት ስላለባቸውና በእኔ ምልከታ የተዘጋጀው ዜና ፓናል ውይይቱ በቀረበበት አውድ (context) በአግባቡ ያልታሸና ያልተቃኘ ስለሆነ፣ በዚህም ምክንያት በርካታ አንባቢዎች (ጋዜጠኞችን ጨምሮ) የተንሸዋረረ ግንዛቤ ስለጨበጡ ማስተካከያ ማድረግ አስፈልጓል፡፡
የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት የተሻለ የእድገት መስመር ይዞ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ፣ የህብረተሰብ የበላይ ጠባቂ፣ ማህበረሰባዊ የአስተሳሰብ ልዕልና የሚያሳልጥ ከዚያም የማህበረሰብ አስተሳሰብ መድረክ ሆኖ የሚያገለግል፣ አብርሃም ሊንከን እንዳለው፤ “የህዝብ ለህዝብ በህዝብ የሆነ”፣ መመኪያው ማህበረሰብ፣ መበልጸጊያው ማህበረሰብ፣ ማሰናሰኛው ማህበረሰብ፣ በጣም ጠንካራ፣ የሚከበር፣ ለማህበረሰብ በዳዮች ብዕሩ የሚያርድ፣ የሚሸነቁጥ፣ ለመልካሞች ርካብ ሆኖ የሚያገለግል፣ ዜጎች መልካሞች እንዲፈጠሩ የሚጥር፣ በሙያ ደረጃው ልቀት ውስጥ የገባና ዜጎች የሚመኙት ሙያ እንዲሆን ከልብ ከሚመኙት ግለሰቦች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ለኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት የተሻለ መሆን የምመኘው እንዲሁም ለኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት መሻሻል የበኩሌን አበርክቶ የማደርገው ለመገናኛ ብዙኃኑ ወይም ለኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች አዝኜና ተቆርቁሬ ብቻ አይደለም፡፡ እኔ ጋዜጠኝነትን የተማርኩ፣ ጋዜጠኝነትን የማስተምር፣ ጋዜጠኝነትን የምሰራ ስለሆንኩና የሙያው መሻሻል እጅጉን የሚጠቅመኝ ስለሆነም ጭምር ነው፡፡ ይህንን ምኞቴን በተግባርም ለመደገፍ በማሰብ እኔ በምችለው አቅም ሁሉ ለኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት አስተዋጽኦ ከማድረግ ወደ ኋላ ብዬ አላውቅም፡፡
እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ በየካቲት ወር 2008 ዓ.ም. የኢፌ.ዴ.ሪ. ስነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን፣መገናኛ ብዙኃንንና ስነ-ምግባርን የተመለከተ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሑፍ እንዳቀርብ ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ ጥያቄውን በእሽታ ተቀብዬ፣ በዚህ አጋጣሚም በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን የምመለከታቸውን ከጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር ውጪ የሚከወኑ ተግባራት የማነሳበት መድረክ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ በማድረግ ዝግጅቱን ጀመርኩ፡፡
የዝግጅት መጀመሪያዬ በኢትዮጵያና አፍሪካ የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር ላይ የተሰሩ ጥናታዊ ጽሑፎችን መፈለግና መሰብሰብ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት በኢትዮጵያና አፍሪካ መገናኛ ብዙኃንና ስነ-ምግባር ርዕሰ ጉዳዮች ላያ የሚያጠነጥኑ ጥናታዊ ጽሑፎችን በመሰብሰብ፣ በመዳሰስ፣ አንዳንዶችን አሁን እየታዩ ካሉ የስነ-ምግባር ጥሰቶች ጋር በማዛመድ ለተዘጋጀው ፓናል እንደ መነሻ የሚሆንና ከተሳታፊዎች በሚነሱ ሀሳቦች ሊበለጽግ የሚችል 19 ገጾች ያሉት ጽሑፍ አዘጋጀሁ፡፡ የተዘጋጀውን ጽሑፍ ለማንበብ የሚሻ ካለ በስነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ድረ-ገጽ ላይ ተጭኖ እንደሚገኝ በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
በፓናሉ አዘጋጆች እንደተነገረኝም ጋዜጠኞች፣ የመገናኛ ብዙኃን ሀላፊዎች፣ የትምህርት ቢሮዎች ሀላፊዎች፣ የመምህራን ማህበር አመራሮች፣ አርቲስቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተሳተፉበት፣ ምንጮች በአግባቡ እየተጠቀሱ፣ የሚቀርቡት ጥሬ ሀቆች መሰረታቸው በአግባቡ እየተገለጸ ጽሑፉ ቀረበ፡፡ በፓናሉ የተሳተፉ አካላትም በጽሑፉ የተገለጹትን ሀሳቦች እያዳበሩ፣ የራሳቸውንም ገጠመኝ እያነሱ፣ ውይይቱ ተሳታፊዎች ጭምር ባካሄዱት የሞቀ ተሳትፎ ተጠናቀቀ፡፡ አንባቢዎች እዚህ ላይ እንዲረዱልኝ የምፈልገው ነገር፡- አንደኛ በቀረበው ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሱ ጥሬ ሀቆች (empirical evidences) የተገኙት ሌሎች በመስኩ የሚገኙ ምሑራን ካጠኗቸው ሰነዶች እንደሆነና የእኔ ሚና የተዛማጅ ጽሑፎችን ዳሰሳ (Review of Related Literatures) አድርጎ ለታዳሚ በሚሆን መንገድ ማቅረብ እንደነበር፤ አብዛኞቹ ያገኘኋቸው ጽሑፎች ደግሞ የተዘጋጁት በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመሆኑ ወደ አማርኛ በመመለስ እንዳቀረብኋቸው፤ ሁለተኛ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዘኃንና ስነ-ምግባር ጉዳይ አዲስ፣ ወቅታዊና ሳይንሳዊ ጥናት እንዳላደረግሁና ያቀረብሁት ጽሑፍ ውስጥ ወቅታዊ ምልከታዎቼን (observations) ጨምሬ ለፓናሉ ተሳታፊዎች ውይይት መነሻ የሚሆን ጽሑፍ እንዳቀረብሁ፤ ሶስተኛ በጽሑፉ ውስጥ የተካተቱ ሀሳቦች የእኔ እስካልሆኑ ድረስ በጥናታዊ ጽሑፍ የምንጭ አጠቃቀስ መርህ ኤፒኤ ፎርማት (citation based on APA format) አግባብ ጽሑፎቹ እየተጠቀሱ እንደቀረቡ ነው፡፡
እንግዲህ ይህንን የማስተካከያ ጽሑፍ ለማቅረብ ወደ አስገደደኝ ዘገባ ልግባ፡፡ ከዜናው ርዕስ (headline) ስጀምር፤ “ጋዜጠኝነት በሙስና የተዘፈቀ ነው ተባለ” በሚል የተቀመጠው ከፓናሉ የውይይት አላማና ከተንሸራሸሩት ውይይቶች አንጻር የሚያስኬድ አይደለም፡፡ የተነሳው ሀሳብ ስነ-ምግባርና መገናኛ ብዙኃን ሆኖ ሳለ ስነ-ምግባር የሚለው ሙስና በሚል ተተክቶ መቅረቡ አንባቢዎችን የሚያሳስት ነው፡፡ በእርግጥ ሙስናና ስነ-ምግባር የሚያመሳስሏቸውና የሚያመጋግቧቸው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም በዚህ ጽሑፍ ሊዳሰስ የተፈለገው ሙስና ሳይሆን ስነ-ምግባር ነው፡፡ የስነ-ምግባር ልሽቀት ወደ ንቅዘት እንደሚያመራ ብረዳም የቀረበው ጽሑፍ አጠቃላይ ገጽታ ግን ሙስናን ዋናው አጀንዳ አላደረገም፡፡ “ጋዜጠኝነቱ በሙያዊ ስነ-ምግባር እጦት እየተሰቃዬ ነው ተባለ” የሚል ርዕስ ቢሰጠው የውይይቱንና የቀረበውን ጽሑፍ አውድ የሚያሳይ ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ፡፡
 ዘገባው ቀጥሎ ያሰፈረው መግቢያ (lead) ደግሞ ምንጩ በአግባቡ መጠቀስና በምን አውድ በጽሑፉ እንደተገለጸ መብራራት እንደነበረበት አምናለሁ፡፡ እንዲህ ይላል፡- “90 በመቶ ጋዜጠኞች በሥራቸው እርካታ የላቸውም”፡፡ ይህ ጥሬ ሀቅ በእኔ ጽሑፍ ላይ የተገለጸውን የስራ እርካታ በተመለከተ ከሆነ (ምክንያቱም የቁጥር ልዩነትም ስላለ፣ ግን ደግሞ 89.6 በመቶ የሚለውን ወደ 90 በመቶ ተጠጋግቶ ቀርቦ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ) እኔ ያዘጋጀሁት ጽሑፍ ላይ “የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን እና የስነ ምግባር ጥሰት ምክንያቶች” በሚል ርዕስ ገጽ 15 እንዲህ ይነበባል፡- “2. ዝቅተኛ ክፍያ እና የስራ እርካታ ማነስ-----ስለ ስራ እርካታ አማኑኤል ገብሩ (እ.ኤ.አ. 2006) በኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኞች የስራ ላይ እርካታ በተመለከተ በሰራው ሰርቬይ ውጤት መሰረት፤ 89.6 በመቶዎቹ ጋዜጠኞች በስራቸው እርካታ እንደሌላቸው አመልክቷል፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ ጋዜጠኞች በዝቅተኛ ክፍያ ምክንያት ግብረ ገብነት የጎደለው አሰራር ውስጥ ኢንዲገቡ ገፊ ምክንያት እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ (ክሩገር፣ እ.ኤ.አ. 2007)፡፡”
የዚህ ቁጥር አስፈላጊነት የሚታወቀው ስለ ጋዜጠኞች የእርካታ ማነስ፣ ይህም ከምን እንደሚመነጭ ለማብራራት ሲሞከር በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን እና የስነ ምግባር ጥሰት ምክንያቶችን ስናነሳ ደግሞ ብርሀኑ ሌዳሞ እ.ኤ.አ. ለሁለተኛ ድግሪው ማሟያ ያዘጋጀው ጽሑፍ ላይ ከተጠቀሱት ነገሮች መካከል የክፍያ ማነስና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የስራ እርካታ ማነስ እንደሆነ መረዳት ሲቻል ነው፡፡ የእነዚህ ሀሳቦች አመጣጥ በመልክ በመልካቸው የማይቀርቡ ከሆነ፣ የተጻፈውን ዜና ያነበበ ሰው ግንዛቤው ቢዛባ ወይም የቀረበበትን አውድ ሳይረዳ ቢቀር አይፈረድበትም፡፡  
በዘገባው ሶስተኛው አንቀጽ ላይ የቀረበው ጽሑፍ፡- “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ትንሹ ስራቸው በሚዲያዎች ተጋኖ እንዲቀርብላቸው ጋዜጠኞችን ለመደለያ በእቅዳቸው ውስጥ በጀት እስከመያዝ ደርሰዋል ያሉት አጥኚው….” እያለ ይቀጥላል፡፡ የተባለውን ሀይል ቃል ያነበነብሁት እኔ ብሆንም ከየት እንዳገኘሁት በጽሑፌ ላይ በማቀርብበትም ጊዜ እስከ ገጹ ድረስ በመጥቀሴ፣ መሆን የነበረበት፡- “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ትንሹ ስራቸው በሚዲያዎች ተጋኖ እንዲቀርብላቸው ጋዜጠኞችን ለመደለያ በእቅዳቸው ውስጥ በጀት እስከመያዝ ደርሰዋል በማለት ብርሀኑ ሌዳሞ እ.ኤ.አ. 2008 ያጠናውን ጥናት በመጥቀስ ያስቀመጡት ጽሑፍ አቅራቢው….” እያለ ሊቀጥል ይገባው፣ ይችልም ነበር፡፡ የቀረበው ዘገባ የፊት ለፊት ገጹን ጨርሶ ወደ ሁለተኛው ገጽ ሲሻገር፣ በገጹ የቀኝ መጨረሻ ሁለተኛው መስመር ላይ የሚጀምረው ጽሑፍ እንዲህ ይላል፡- “ችግሩ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም እንደሚንጸባረቅ የጠቆሙት ጥናት አቅራቢው፣ በፖስታ ታሽጎ ከሚሠጥ ገንዘብ ጀምሮ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች፣ ከልብስና ጫማ ጀምሮ ውድ ስጦታዎች ድረስ እንዲሁም ለአንድ የዘገባ ስራ የትራንስፖርት፣ የማደሪያና የምግብ---የመሳሰሉት ወጪዎችን መሸፈን በኢትዮጵያም ይሁን በአህጉሪቱ የተለመደ መሆኑን በመግለጽ፣ ይኼም ከሙያው ስነ-ምግባሮች ጋር የሚጋጭ ተግባር ነው ብለዋል፡፡” በዚህ ጽሑፍ “ችግሩ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም እንደሚንጸባረቅ የጠቆሙት ጥናት አቅራቢው፣ በፖስታ ታሽጎ ከሚሠጥ ገንዘብ ጀምሮ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች፣ ከልብስና ጫማ ጀምሮ ውድ ስጦታዎች ድረስ እንዲሁም ለአንድ የዘገባ ስራ የትራንስፖርት፣ የማደሪያና የምግብ---የመሳሰሉ ወጪዎችን መሸፈን በኢትዮጵያም ይሁን በአህጉሪቱ የተለመደ መሆኑን በመግለጽ…” የሚለው ሀረግ ከእኔ የመነጨ ሳይሆን ቀደም ብዬ ከጠቀስኩት ምንጭ እንዲሁም ከፍራንሲስ ካሶማ (እ.ኤ.አ. 2000)፣ ክሩገር (እ.ኤ.አ. 2007) እና ሌሎች ምሑራን የተገኘ እንደሆነ መገለጽ ይገባው ነበር፤ ልክ በጽሑፌ ላይ እንደተጠቀሰው፡፡
ዜናው በወጣበት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ሁለተኛ ገጽ ላይ ሁለተኛ አንቀጽ የተገለጸው ሀሳብ ብርሀኑ ሌዳሞ ጥናቱን ያከናወነበት አመት ሳይጠቀስ ከመቅረቱ ውጪ የተሻለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የሚገኘው አንቀጽ ግን ከላይ እንደተጠቀሱት አይነት ግድፈትን ሰርቷል፡፡ “
ጋዜጠኞች ገንዘብና ጥቅማጥቅም የሚገኝባቸውን “ቡጬ ያለው” በሚል እንደሚለዩ የጠቀሱት አጥኚው ገንዘብም ሆነ ጥቅማ ጥቅም የሌላቸው ተቋማት “ደረቅ ጣቢያዎች” የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡ ገንዘብ እና ጥቅማ ጥቅም የማይቀበሉ ጋዜጠኞች፣ በተቀባዮቹ የተለያዩ ስያሜዎች እንደሚሰጣቸው ሲገልፁም፡- ‘በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያና የኤርትራ መልዕክተኛ’  ወይም ‘ወጋሚ’ የሚሉ ስያሜዎች እንዳላቸው ጥናት አቅራቢው አብራርተዋል፡፡” እነዚህ ሀሳቦች የተገለበጡት ቀደም ብዬ ከጠቀስኩት ብርሀኑ ሌዳሞ እ.ኤ.አ. 2008 ላይ በጋዜጠኞች እና ስነ-ምግባሮቻቸው ላይ ካጠናው ጽሑፍ ላይ እንደነበር፣ እኔ ጹሑፌ ላይ እንዳስቀመጥኩት ሁሉ፣ በዜናውም ላይ መገለጽ ነበረበት፡፡ ቀጥሎ ባለው አንቀጽም የተቀመጠው ጽሑፍ ተመሳሳይ ችግር ይስተዋልበታል፡፡ “በአሁኑ ወቅት ጥቅም የተገኘባቸው ዘገባዎችና ፕሮግራሞች በቀላሉ እየተለዩና እየታወቁ እንደመጡ ያመለከቱት አጥኚው፣ ጥቅም የተገኘባቸው ዘገባዎችና ፕሮግራሞች ሳቢና ማራኪ ተደርገው ሲቀርቡ ያልተገኘባቸው ደግሞ ‘እንደነገሩ’ ይቀርባሉ ብለዋል።” ይህም ሀሳብ የተመዘዘው በብርሀኑ ሌዳሞ ከተጠናው ውስጥ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
በዘገባው ቀጥሎ በሚገኘው አንቀጽ ላይ “ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ለገንዘብና ጥቅማ ጥቅም ተገዢ እየሆኑ የመጡበት ምክንያት በዋናነት በመስሪያ ቤታቸው የሚያገኙት ደሞዝና ጥቅማጥቅም ዝቅተኛ በመሆኑ ነው ተብሏል።” የተባለው አገላለጽ ከላይ እንደመጣው አይነት ስለሚመስል በትክክል በእኔ ጽሑፍ ላይ በተቀመጠበት መንገድ አጥኚውና የተጠናበት አመት ቢጠቀስ ተዓማኒነት ይኖረዋል፡፡ በዜናው መጨረሻ የተጠቀሱት ሁለት አንቀጾችም ከላይ እንዳልኩት የመጡበት ቦታ፣ ያጠናቸው ሰው፣ የተጠኑበት አመት በማያሻማ መልኩ ቢገለጽ፣ በተለይ ርዕሰ ጉዳዩ ለብዥታ የተጋለጠ በመሆኑ፣ አንባቢዎችን ከአላስፈላጊ ውዥንብር ማዳን ይቻላል፡፡ ይህንን ዜና ያዘጋጀው ጋዜጠኛ የፓናል ውይይቱ ሲካሄድ በቦታው ተገኝቶ ከነበረ፣ እኔን ቀርቦ ጥያቄዎችን ቢያቀርብልኝ ኖሮ ምንአልባት ተግባብተን፣ የሚጻፈው ዜናም የሚያግባባንና ትክክለኛ ይሆን እንደነበር ይሰማኛል። በዜናው ላይ ልንግባባ እንችል ነበር ስል ጋዜጠኛው የሚጽፈውን ነገርና የሚጽፍበትን መንገድ እነግረው ነበር፤ የዜናውን ቅኝት (angle) እመርጥለት ነበር ማለቴ አይደለም፡፡ ይኼማ የጋዜጠኛውና የተቋሙ መብትም፣ ስራም እንደሆነ በሙያው ላይ ያለ ማንም የሚያውቀው እውነት ነው፡፡ ጥሬ ሀቆቹ በዚህ ደረጃ አያከራክሩንም፤ ብዥታውንም መቀነስ ይቻል ነበር ማለቴ እንጂ፡፡
ይህንን የማስተካከያ ጽሑፍ ሳዘጋጅ ጋዜጠኛውንም ሆነ ጋዜጣውን ለመውቀስ አላማ የለኝም፡፡ መጀመሪያ ዜናውን ሳነበው ከዚህ በላይ ያነሳኋቸውን ጉዳዮች ባስተውልም ማስተካከያ ለመጻፍ አልፈለግሁም ነበር፡፡ ምክንያቴም ሀሳቦች እንደየ አቅራቢዎቹ እይታ ቢንሸራሸሩ፣ የሀሳቦች ብዝኃነት ይሰፍናል፤ ሀሳቦች እየተፋጩ ለተደራሾች የመምረጥ መብትን ያጎናጽፋሉ፤ በውጤቱም የሀሳብ ልዕልና ይረጋገጣል የሚል እምነት በመያዝ ነው፡፡ በሆነ ባልሆነው መነታረኩ፣ ለማደግ ዳዴ የሚለውን ጋዜጠኝነትም የመጉዳት አቅም ይኖረዋል ብዬ ስለማስብ ጭምር፡፡ ነገር ግን ይህንን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የወጣውንና ድሬ ትዩብ በሚሰኘው የድረ-ገጽ ሚዲያ የታተመውን ዜና በማየት ብቻ፣ አንዳንዶችም በፓናል ውይይቱ ተጋብዘው ሳለ፣ ሳይመጡ ቀርተው፣ ይቺን ቁንፅል ዘገባ በማንበብ ወይም በመስማት ብቻ፣ በሚመሯቸው የሚዲያ ተቋሞች የአየር ላይ ስርጭት እየቀረቡ ትችት ሲያቀርቡና ተሳስተው ሲያሳስቱ በመስማቴ ምክንያት፣ በአንባቢዎችም ላይ የተፈጠረ ሰፊ ብዥታ መኖሩን ስለተረዳሁ ብቻ ነው ይህን ማስተካከያ ለመጻፍ የተገደድሁት፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ የጋዜጠኝነት ዋና ጉዳይ በቂ መረጃ ማግኘት ስለሆነ መረጃ እንዲያገኙ የሚጋበዙ ጋዜጠኞችም ሆኑ በመገናኛ ብዙኃን የሚሰሩ ሰዎች እንኳን ተጋብዘው፣ በግድ እንዲጋበዙ አድርገው በየትኛውም ሁነት ተገኝተው፣ የራሳቸውን ትዝብትም እየጨመሩ፣ የሁነቶችን አውዶች እየመረመሩ፣ ለተደራሾቻቸው ያልተበረዘ መረጃ ቢያቀርቡ ተዓማኒነትን ያተርፋሉ፤ የሙያ ግዴታቸውንም በአግባቡ ይወጣሉ ብዬ አምናለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡-
አሰማኸኝ አስረስ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነት እና ኮሙዩኒኬሽን መምህር እና የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ጽ/ቤት ተ/ዳይሬክተር ሲሆኑ በተከታዩ የኢ-ሜይል አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡
(Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

Read 2398 times