Saturday, 25 February 2012 13:05

የላሊበላው የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(0 votes)

ከይምርሃነ ክርስቶስ ወደ ላሊበላ!

ለመሆኑ፤ ይምርሃነ ክርስቶስ ማነው?

የቅድስና ማዕረግ ከተሰጣቸው የዛጔ ነገሥታት አንዱ ነው፡ ከ10ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ እስከ 11ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ የኖረ ንጉሥ ነው፡፡ አባቱ ግርማ ሥዩም የንጉሥ ጠንጠውድም ወንድም ነው፡፡ አጐቱ መሆኑ ነው፡፡ ይምርሃነ ክርስቶስ ውሎ አድሮ እንደሚነግስ የተነገረውን ትንቢት በሰማ ጊዜ አጐቱ ሊገድለው አሰበ፡፡ ሆኖም አማካሪዎቹ “ከምትገድለው እንዳይማር አድርገው” ሲሉ ይመክሩታል፡፡ ስለዚህ ወደ ገጠር ወደ እናቱ ይልከዋል፡፡

ይምርሃነ ግን አንድም ከቅዱስ መጽሐፍ አንድም ከህይወት እየተማረ መምጣቱ ወሬው ተሰማ፡፡ ስለዚህ አሁንም አስጠርቶ ሊገድለው መልዕክተኞች ላከ፡፡ እናቱ ነገሩ ስለገባት “አጐትህ ሊገልህ ይፈልጋልና ሽሽ” አለችው፡፡ ራቅ ወዳለ ቦታ ሸኘችው፡፡ እየሩሳሌም ሄዶ ተሸሸገ፡፡ ንጉሱ ለአገለናልኝ ሰው ግማሽ መንግሥቴን ለወሮታው እለቃለሁ አሉ፡፡ አልተገኘም፡፡

ይምርሃነም ሌዋዊ የሆነችውን ቅድስት ህዝባን አግብቶ እየኖረ የቅስና ማዕረግ ተቀብሎ ያገለግል ጀመር፡፡ በእየሩሣሌም ቆይታው፤ ከሥጋዊ ጥበብ - የቀለም ትምህርት፣ የኪነ - ህንፃ፣ የስነ - ስዕል፣ የቅርፃ - ቅርጽ፤ ከመንፈሳዊ ጥበብ - ብሉይ ኪዳን፣ ሐዲስ ኪዳን እና መጽሐፈ - ሊቃውንት ተማረ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለም፣ አጐቱ እስኪሞት በቀና ሃይማኖት፣ በበጐ ምግባርና በንፁህ ክህነት ሰውና እግዚአብሔርን ሲያገለግል ኖረ!

አጐቱ ሲሞት ቅድስት ህዝባን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ መጣ፡ በላስታ ወረዳ ሳይ (የዛሬዋ ሸጐላ ማርያም) ከምትባል አገር ደረሰ፡፡ ማንነቱን ሳይገልጥ፤ በሥጋ የታመሙትን በተዓምራት፣ በነፍስ የታሙትን በትምህርት እየፈወሰ ቆይቶ፤ የአካባቢው ህዝብ “እሱ (ይምርሃነ ክርስቶስ) ሲነግስ ሃይማኖት ይቀናል፣ ፍትሕ ይስተካከላል፡፡ በዘመኑ የሮም ሰዎች (የውጪ ዜጐች) ለኢትዮጵያ ህዝብ ይገዛሉ” የሚለውን የአበው ብሂል በማስተጋባት፤ ማንነቱን እንዲገልጥላቸው ጠየቁት፡፡ ከጠንጠውድም ሞት በኋላ ይምርሃነ ክርስቶስ፤ የግርዋ ሥዩም ልጅ መሆኑን ገለጠላቸው፡፡ ህዝቡም፤ “የተነገረው ትንቢት ደርሷል፡፡ ይምርሃነ ክርስቶስም በመካከላችን አለ፡፡ ሳንዘገይ እናንግሰው ብለው በምክር ተስማሙ፡፡ በኋላም ሥርዓተ መንግስቱን ፈጽመው በዙፋን ላይ አስቀመጡት (አነገሱት)፡ ስለ ይምርሃነ ተግባራት በተፃፉ ጽሑፎች ባገኘሁት መሠረት፤

“የእግዚአብሔር ጌትነት የሚነገርበትን ቤተመቅደስ ለማነጽ አስቦ ቦታ ሲፈልግ ዛዚያ (ዟዟ) የምትባል፤ በዛፏ፤ በውሃዋና በልምላሜዋ ልዩ የሆነች ሥፍራ፤ አገኘ፡፡ ቦታዋንም በገንዘቡ ገዝቶ ቤተ - መቅደስ እስከሚያንጽ ድረስ ድንኳን ተክሎ እንደሙሴ ሰውና እግዚአብሔርን ማገልገል ጀመረ”

በዛዚያ 22 ዓመት ሲቀድስ ኖረ፡፡ ከዚያም “ይህን ሥፍራ (ዛዚያን) ልቀቅ ለምትሠራው መቅደስ ሣር የማይፈልግ ሰፊ ዋሻ ያለበት ወግረ ስሂን የሚባል ቦታ አለ፡፡ ወደዚያ ሂድ” በሚል ትዕዛዝ መሠረት ወደዚያው አመራ፡፡ ወግረ ስሂን ዋሻ ሀረጉን አስቆርጦ ሲገባ ሰፊ ባህር አገኘ፡፡ ከዚህ ባህር ላይ እንደምን አድርጌ ቤተ መቅደስ አንፃለሁ ብሎ ሲያስብ፤ በባህሩ ላይ እንጨት፤ በእንጨቱ ላይ ሣር፤ በሣሩ ላይ ጭቃ፤ በጭቃው ላይ ደረቅ አፈር አድርገህ ደልድለህ ቤተመቅደሴን ሥራ” የሚል ቃል ሰማ” የህንፃ መሣሪያዎችን ማሰባሰብ ጀመረ፡፡ የቅድስና ህይወቱን የሰሙ የሮምና የግብጽ ሰዎች ለመስኮት የሚሆኑ የከበሩ ድንጋዮችን (ዕብነ በረድ) አመጡለት፡፡ ክርስቶስ ብሃ የሚባል የክብር አገልጋዩ እየረዳው ጥቋቁር፣ ጥቃቅንና ለስላሳ በሆኑ ዐለቶችና ዞቢ (ዞጲ) ከሚባሉ በጥቃቅን ከተጠረቡ ሰፋፊ (ዕጽዋት) እንጨቶች እንዲሁም በልዩ ልዩ የመስቀል ቅርፃ ቅርጽ ውበት ካላቸው እንጨቶችና ከከበሩ ድንጋዮች ጋር በጭቃ በማያያዝ፤ በመጨረሻም ኖራ መሰል በሆነ ነገር በመለሰን ድንቅ በሆነ ኪነህንፃ ጥበብና ስነስዕል ድንቅ በሆነ የአሠራር ጥበብ ፈጽሞታል፡፡”

ውስጡ እጅግ የሚገርም ነው!

ውስጠ - ነገሩን የሚያውቁ አንድ አማኝ አዛውንት፤ ሲያስረዱ፤

“ቅዱስ ይምርሃነ የቂርቆስ ቤተቅደስን አስገባ፡፡ የሮም ሰዎች ስለቅድስናው 55 ታላላቅ መቅደሶችን ገበሩለት፡፡ የግብጽ ንጉሥ የአርዚ ሊባኖስ በር ላከለት … የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም መንበር ባለበት የመቅደስ ክፍል ላይ እንደተገጠመ ይገኛል፡፡”

“በሌላ ማቴሪያል ሊሠራው አይችልም ነበር?” ተብለው ሲጠየቁ፤

“እኸ እሱማ በወርቅና በብር ሊሠራው አስቦ ነበር”

“ታዲያ እንዴት አልቀጠለበትም?”

“አሃ ቃሉ አገደዋ! ቤተመቅደስህ የታነፀበትን የከበረ ድንጋይ አከበርኩልህ፡፡ በወርቅና በብር ያነጽከው እንደሆነ የኋላ ሰዎች ወርቅና ብሩን ሲሉ፤ ቤተክርስቲያንህን ያፈርሱብሃል፤ አለው፡፡” አሉ፡፡ ዕምነታቸው፣ የአነጋገር ጥንካሬያቸው የማተባቸውን ክረትና ጥንካሬ ያሳያል፡፡

ይምርሃነ ክርስቶስ በአደፋ አንድ ዓመት፣ በዛዚያ 22 ዓመት፣ ባነፀው ቤተ-መቅደስ 18 ዓመት በድምሩ 41 ዓመት ሲያገለግል ኖረ፡፡ 95 ዓመት ከ5 ወር ሲሆነው ጥቅምት 19 ቀን አረፈ፡፡ አስከሬኑም ባነፀው ቤተክርስቲያን በደቡብ አቅጣጫ በዋሻው ውስጥ በአበባ ጨርቅ ተሸፍኖ በክብር ይገኛል፡፡

ቤተክርስቲያኑን ጐብኝተን ስንመለስ ደረጃው አንደረደረኝ፡፡ ጥቂት ፈረንጆች ከጐኔ አሉ፡፡ ጠመዝማዛውን ደረጃ ስጨርስ የተቀቀለ ባቄላ ገዛሁ፡፡ ድካሙ ሁሉ ከዳገቱ አፋፍ ላይ ይጠፋል፡፡ ሲቀናን የእኛ መኪና የቆመበት ድረስ የሚሄድ አውቶብስ አገኘን፡፡ ሁኔታችንን አይቶ ጫነን!

መኪናችን ጋ ስንደርስ ሌሎቹን ተሳፋሪዎች ቀድመናል፡፡ ስለዚህ አረፍ እንበል ብለን እዛው አካባቢ ቤት ጥላ ሥር አረፍ አለን፡፡

አንዲት ሴት ሁለት እንሥራ ጐኗ አድርጋ ተቀምጣለች፡፡

“ምንድን ይዘሻል?” አልኳት፡፡

“ኮረፌ ነው” አለች፡፡

አንድ ሂልተን የሚሠራ ወዳጄ ገና ከአዲስ አበባ ሳልነሳ፤

“እዛኮ የሚጠጣ የለም፡፡ በየቤተክርስቲያኑ፣ በየገዳሙ የምታገኘው ኮረፌና ጠላ ነው! ያንን መኮምኮም ነው” ያለኝ ትዝ አለኝ፡፡ ደስ አለኝ፡፡

“እስቲ ኮረፌ ቅጂልኝ” አልኳት፡፡ አኩረፈረፈችው!

“ድቁስም አለ” አለች፡፡

ባለቤቴን ጠራኋት! “ነይ ድቁስ አለ” አልኳት

“ጨው ኃይለኛ እንዳይሆን!” አለችኝ፡፡ ቤታችን ጨው ስለማንበላ የትም ቦታ ትንሽ ጨው ሲኖርበት በጣም ይሰማናል

ኮረፌውን ገጠምኩት፡፡

ድቁሱን በላን፡፡ ጨው አንገበገበን፡፡

እዚያ አካባቢ የመብላት የመጠጣት ነገር የጋራ ነው፡፡ ችግሩ ዝርዝር ፍራንክ የለም፡፡ እሱ ጊዜ ወሰደ፡፡ ለማንኛውም ጨርሰን ወደ መኪናችን ሄድንና መንገድ ጀመርን!

መንገድ ላይ “ብልብላ ጊዮርጊስን መሳለም የምትፈለጉ አስራ - አምስት ደቂቃ” ተባለ፡፡ አሁን መሳቅ ጀምረናል፡፡ በላይት - ይር ይሁን፣ በእግዚአብሔር አቆጣጠር ይሁን፤ አይታወቅም፡፡ ሁሉ ነገር 15 ደቂቃ ነው የሚፈጀው፡፡ ብልብላ ጊዮርጊስ ተራራው ላይ ይታየናል፤ አስፋልቱ ዳር ቆመን፡፡ ጽሑፉን አየሁት

“ብልብላ ጊዮርጊስ ከላሊበላ ወደ ይምርሃነ ክርስቶስ በሚወስደው የመኪና መንገድ 30 ኪ.ሜ ከተጓዙ በኋላ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ከብልብላ ከተማ 500 ሜትር ወጣ ብሎ የሚገኝ ድንቅ ውቅር ቤተክርስቲያን ሲሆን፤ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ከሕንፃው ላይ ንቦች ይገኛሉ፡፡ የእግዚአብሔር ጌትነት በቤተመቅደሱ ስለሚነገርበት ከንቦቹ የሚገኘው ማር በሀገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ ሕመምተኞች የተቻላቸው ወደ ቦታው በመምጣት፣ መምጣት ያልተቻላቸው ወዳሉበት ቦታ በመውሰድ ለመድኃኒትነት ይጠቀሙበታል፡፡

በዚህም በርካታ ህመምተኞች ፈውስ አግኝተውበታል፡፡ በተጨማሪ ከህንፃው አጠገብ የሚገኘውን እምነት በፀበሉ እየለወሱ በመቀባት ከማናቸውም በሽታ እየፈወሱበት ይገኛሉ፡፡ በቤተክርስቲያኑ ውስጥም በርካታ መስህብነት ያላቸው ቅርሶች ይገኛሉ፡፡

በቦታው የሚከበር ዓመታዊ በዓል ሚያዚያ 23 ቀን የቅዱስ ጊዮርጊስ የረፍት ቀን መታሰቢያ ሲሆን፤ ሚያዚያ 23 በሰሙነ ህማማት ሲውል ግንቦት 23 ቀን በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡

አስፋልቱ ዳር ባሉት የላስቲክ ቤቶች ብርዝ ይሸጣል፡፡ ድቁስ ይቀርባል፡፡

ትናንሾቹ ገበያዎች ላይ ማር ይሸጣል፡፡ የምንችለውን ገዛን፡፡ በላን ጠጣን፡፡ በመመለሻ መንገዳችን ላይ ባንሳለማቸውም፤ ሣርዝና ሚካኤል (ውቅር) ብልብላ ቂርቆስ፣ ወልደ ንጉሥ ገብረክርስቶስ (የዋሻ)፣ አርባዕቱ እንስሳ (ውቅር)፣ ትኩርዛ ኪዳነምህረት (ውቅር)፣ የዋልድቢት ቅድስት ማርያም አንድነት - ገዳም አሉ፡፡

“ሌላ ጊዜ አያቸዋለሁ” አልኩኝ በልቤ፡፡ እንግዲህ ወደ ላሊበላ ዋና ጉዳይ መሄዳችን ነው፡፡

“እንግዲህ ዋናው ነው የቀረን ጋሽ ነቢይ” አለኝ ወጣቱ ልጅ፡

“አዎ ላሊበላን ልናይ ነው ነገ”

“የቤተ - ጊዮርጊስን ነገር ግን እንዳትዘነጉ”

“አይ አንዘነጋም፡፡ ከዋናው በፊት ፈንጠር ብሎ የተሠራ ነው የተባለው አይደለ?”

“አዎን”

ወደ ከተማ ስንደርስ ከመንገድ የጫናቸውን ሰዎች አወረድን፡፡

ከዚያ ት/ቤቱ ግቢ፤ ግቢያችን ገባን፡፡

አንድ ቀልጣፋ አስተባባሪ ሴት አለች ከኛ ማህል፡፡

“ለነገ የገና መፈሰኪያ ገንዘብ ይዋጣና በግ ይገዛ” አለች የአውስትራሊያዋ ልጅ “አሪፍ ነው!”

እኔና ባለቤቴን የተጠራጠረን የለም፡፡ “እሺ ይላሉ” ተብለናል፡፡ ከአስተባባሪዋ ጋር ባለቤቴ ግብብ ከፈጠረች ቆይታለች፡፡

ብዙም ጊዜ ሳይፈጅ ገንዘብ ማሰባሰብ ተጀመረ፡፡ ለበግ ግዢ ወጣቱና የባግዳዱ ጐልማሳ ተላኩ፡፡ በ850 ብር ምን የመሰለ ነጭ በግ ተገዛ!!

(ይቀጥላል)

 

 

Read 1899 times Last modified on Saturday, 25 February 2012 13:13