Saturday, 26 March 2016 11:38

ገምጋሚው!

Written by  ፍፁም ንጉሴ
Rate this item
(7 votes)

(የመጨረሻው ክፍል)
የኮምፒውተር ፅህፈት ስራ አስጨናቂ አስቀጥሮኝ ጀመርኩ… በሱ መኖሪያ አካባቢ በመሆኑ በሰፊው መገናኘት ሆነ፡፡ አስጨናቂ ብዙ ወንዶች ላይ የሌሉ ቆፍጠን ያሉ ባህርያት ስላሉት ብኮራበትም፤ግምገማው ሊያሳብደኝ ደርሷል፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ራስ ወዳድ በመሆኑ ይመስለኝ ነበር፡፡ ግን አምባገነን በመሆኑ ነው ---- ያልኩት ካልተሟላ፤ እንደፈለግሁት ካልሆነ ባይ ነበር፡፡ እሱ የሚፈልገው እሺን ብቻ ነው፡፡
“ነይ” ---“እሺ”
“ሂጂ”--“እሺ”
“አውልቂ”--“እሺ”
“ተኚ”--“እሺ”
የኮምፒውተር ፅሁፍ ስራው ተስማምቶኝ ነበር። ነገር ግን ያስቀጠረኝ ሰው ራሱ ችግሬ መሆን ጀመረ። ራሱ አስጨናቂ የፈረደበት “ለምኑን” እዚያም ይዞብኝ መጣ፡፡ በምሳ ሰዓት ጎራ ብሎ ከሰራ ባልደረባዬ ጋር ይጋብዘናል፡፡ እኛም በኤሌክትሪክ ምድጃ ቡና አፍልተን እንጋብዘዋለን፤ከስራ መልስም ይመጣል፡፡ የሚሰራው ወታደር ቤት ሲሆን ማዕረጉም ከፍ ያለ በመሆኑ ለህሊናው እንጂ ብዙም ተቆጣጣሪ የለበትም፤ግን ለሱም ራሱ ህግ ነውና ራሱንም ለምን? የሚለው ጥያቄ በሰዓቱ ስራ አስገብቶ በሰዓቱ ያስወጣዋል፡፡ አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ፡-
አንድ ደንበኛችን ወንበር ስቦ እስሬ ጥግት ብሎ ያፅፈኛል፡፡ ሽቶው ይሽተተኝ ወይ የኔም ይሽተተው አላውቅም፤ ትኩረቴ ስራዬ ላይ በመሆኑ ሰውየውን አላጤንኩትም፤ እየሞቀው ይሁን እያላበው አላስተዋልኩም፡፡ አስጨናቂዬ መጣ፡፡ ባልደረባዬ ቡና እያፈላች ነበር፡፡
“ደህና ዋልክ?” አልመለሰላትም፤ ወደ እኛ ነበር የሚያየው፤ እና ድንገት ሰውየውን ከነወንበሩ አንስቶ ከጎኔ አርቆ አስቀመጠው … ሰውየው ቢደነግጥም ከፊቱ ያለውን ዛፍ መሳይ ሰው ሲያይ እዛው ወንበሩ ላይ ስምጥ እያለ፤ “ምንድነው?” አለው
“ለምን እስሯ ገባህ?!”
“እስሯ?”
“አዎ! ጡቷ ስር---- አንገቷ ስር ምን ወሸቀህ?”
“መቼ?” ኧረ አግዢኝ በሚል አስተያየት ወደ እኔ ተቁለጨለጨ
“ለምን ታያታለህ?”
“መቼ?”
“አሁን ነዋ!” ወንበር ስቦ ከፊቱ ተቀመጠ፡፡ ጋራ የሚያህል ፊቱን በሰውየው ፊት ላይ እያንጠለጠለ ----- ያንን አንገቱን እያሰገገ … ቡጢ አይኖቹን በቁጣ … እየወረወረ
“መልስልኝ ለምን? ምንድነው … እያደረክ የነበረው?”
“ንገሪው ቤዚቲ”
“ምን ብዬ?”
 “ዝም በይ! አንቺን ሊያፅፍ እንጂ ሊያቆላምጥ ነው የመጣው?”
“እያፃፈኝ ነበር”
“ነበር? እስርሽ ለምን? እንደዚህ ተቀምጦስ አይችልም?”
“ምን ለማለት ፈልገህ ነው?”
“ተጠይቀሽ እያለ አትጠይቂ!”
“ጥያቄህ መልስ የለውም”
“ለምን የለውም?”
“ስለሌለው!”
“ለምንድነው የሌለው?”
 “መልስልኝ ለምን?” ወደ ሰውየው ዞረ
ለምን? ለምን? ሁሌ ለምን? አንገፈገፈኝ፡፡
ባልደረባዬ ሳቋ አመለጣት፡፡ አፍጥጦባት፤ “ለምን ሳቅሽ?”
“ድንገት”
“ምንድነው ድንገት?”
“ሳላስበው” አለችው፤ኡፍ በሚል ስሜት
“ለምን ሳታስቢው?”
“ይቅርታ”
“መልሱ ይቅርታ አይደለም”
ሰውየው ከቆየ መቃጠል ይጀምራል፤ ይሄንን የሚያህል ሰውዬ የሚያጠፋ ውሃ የለንም፡፡ እየፃፍን ነበር። ሌላ ያደረግነው ነገር የለም፤ ይሄ ዕውነቱ ቢሆንም ለአቶ ለምኔ መልስ ስለማይሆን መፍጠን አለብኝ፡፡ በዓይኔ ቦርሳዬን መፈለግ ጀመርኩ፡፡
ወደ ሰውየው ዞሮ፤“መልስልኝ እንጂ አንተ ባለጌ!”
በዚያ ሰፌድ መሳይ እጁ አንገቱን ይዞ አነሳው፤የቀጭኑ ሰው ፊት ፍም ሲመስል ቦርሳዬን አንስቼ ሮጬ ወጣሁ፡፡ ለዚህ ሁሉ ሰበብ የሆንኩት፣ነገሩን ማስቆም የምችለውም እኔ ነበርኩ፡፡  ሰውዬውን በቁሙ ለቆት ተከተለኝ፤እኔ እንደሆንኩ በቅቶኛል፤ የምፈራው መስሎታል፡፡ ምን አይነቱ የግንቦት ፀሐይ ነው፤ እኔን ማቃጠሉ አንሶ --- የሰው ሰው!
 ታክሲ ተሳፈርኩ … ተከትሎኝ ሊሳፈር ሲል ረዳቱ “ሞልቷል” አለው፡፡ በሩን ለመዝጋት ቢጎትተውም ከአስጨናቂ ጋር ታግሎ ሊዘጋው አልቻለም …
 “ምንድነው ---- ሰውዬው?”
“ምን ማለት ነው ሰውዬው? እኔም መሄድ አለብኝ!”
“በሌላ ታክሲ ሂዳ!”
“አይሆንም!”
“ሞልቷል ተባልክ!”
“በስርዓት ተናገር ወጠጤ! እንደ አቧራ እበትንሃለሁ”
 ወደኔ እየጠቆመ፤“እሷ ትውረድ”
“አልወርድም!” ጮኼና ተቆጥቼ
“ለምን አትወርጂም?”
ፊቴን አዞርኩበት … ሾፌሩ መኪናዋን አፈናጥሮ ሲነዳት .. በሩን ይዞ ሊከተል ቢሞክርም አልተቻለውም----- ለቆ ቀረ፤ እየሄደ በሩ ተዘጋ …፡፡ ዞሬ በቆረጣ አየሁት፤ ይወራጫል ያብዳል … ወደ ሌላ ታክሲ ሮጦ ገባ፡፡ ቤት ስገባ እናቴ ከጎረቤት ጋር ቡና እየጠጣች ነበር፡፡
“ማንም ቢፈልገኝ የለችም በይ” ብያት አለፍኩ፤ ፊቴን አይታ “እሺ” አለችኝ፤ ግን ሳትቆይ የክፍሌን በር ቆረቆረች።
“እኔ ምልሽ ቤዛዬ---”
“አንቺ ምትዪኝ----”
“ምን ሆነሽ ነው?”
“ምንም!;
“አስጨናቂ ቢመጣስ?”
“የለችም በይው”
ላፍታ ፀጥ አለች፡፡ ደስታዋ ከገጿ ላይ ሲጠፋ በሃሳብ ታየኝ፡፡
“እንዳልሽ---”
ከደቂቃዎች በኋላ አስጨናቂ ቤቱን ሲረብሸው ይሰማኛል፤ እናቴ በደግነቱ በግልፅ ተፈጥሮው ትወደዋለች፤ ያሳለፈውን ህይወትም ተርኮላት በሃዘን ከንፈሯን መጥጣለታለች፡፡  
የእኔው አይነት ናቸው ቤተሰቦቹ፤በትምህርቱም ጎበዝ ነበር፤2ተኛ ደረጃ ሳይገባ … አባቱ ሞቱ፤ችግር ወደ ቤታቸው ገባ፡፡ ቀን እየሰራ ማታ መማር ጀመረ … ሳይቆይ ዘመተ፡፡ በወታደርነት ህይወቱ ብዙ መከራ አይቷል … ንቁና ቀለም ቀመስ መሆኑ … በመሪዎቹ እንዲታይ አደረገው … በፈፀማቸው ጀብዱዎችም የማዕረግ ዕድገቶችን አገኘ … ወደ ኋላ ላይም የወታደሮች ስነ-ምግባር ተቆጣጣሪ ሆነ … በግዳጅም ላይ ሆነ በካምፕ ውስጥ ጥፋት ያጠፉ አባሎች፣ እሱና መሰሎቹ ፊት ቆመው በጥያቄዎች ቃሪያ ጥፊ .. ይወለወሉ ነበር። “ለምን” እና “ምንድን” የሚሏቸውን ከዚያ ነው ወርሶ የመጣው … ከተማ ከመጣ በኋላ ከወታደራዊ መስሪያ ቤቶች በአንዱ በአዛዥነት እየሰራ ቢሆንም … ከግምገማ አልተላቀቀም። እናም ፍቅርን በ “ለምን” ሊቀርፅ ይለፋል … ፍቅረኛን በ“እንዴት” ሊያርም ደርቆ ያደርቃል፡፡
መኝታ ክፍሌ ውስጥ መሆኔን ሳይጠራጠር መጥቶ አንኳኳ … ትንፋሽ ውጬ ፀጥ አልኩ …
“እኔ ቤት ልንሄድ አልነበረም?” - ፀጥ፡፡
“ለምን ጥለሽኝ መጣሽ? ለምን በርሽን ትዘጊብኛለሽ?”  ወይ ለምን? ፀጥ!
“እንዴት በኔ ላይ በር ትዘጊያለሽ እኔኮ አስጨናቂ ነኝ … በበዛው ሰላምሽ ውስጥ የኔም አስተዋፅኦ አለ … ሀገሬ መንግስቴ ያከብሩኛል … ታሪክ ይዘክረኛል፤ አንቺ ግን ንቀሽኝ በራፍሽ ላይ ቆሜ”-- ድምፁ ይቆራረጥ ጀመረ … “እያለቀሰ ነው እንዴ?” ሲያለቅስም---- ከትከት ብሎ ሲስቅም አይቼው አላውቅም--- ጨነቀኝ፤ ደሞ ፈራሁ …  
“በዘጋብኝ በራፍ ላይ ቆሜ ለሰከንድ የለመንኩት ሰው የለም፤ ለመጀመሪያ ጊዜ አንቺን በመውደዴ አደረኩት፤ ሆኖም አንቺን …” አላስጨረስኩትም፤በሩን ከፈትኩት …
እናቴ ከወዲያ ስታጮልቅ አየሁዋት፤ እፎይ ብላ ምልስ አለች … እንባዬን ሲጠርግልኝ መዳፉ ሙሉ ለሙሉ ጋረደኝ - “የኔ ጠረንገሎ!”
የእማዬን ምሳ በልተን ተያይዘን ወጣን ----- ብልጭ ብሎ የጠፋበት እኔን የማጣት ስጋቱ ስላከተመ ተደሰተ፡፡ የመዝናኛ ስፍራዎችን ስናዳርስ አመሸን፡፡
አንድ ቀን … ሲያቀብጠኝ  ያማረና በማዕረግ የሚንቆጠቆጥ የደንብ ልብሱን … ካልተኮስኩልህ አልኩት።  ደክሞት ስለነበርና … በቀጣዩ ቀን በአንድ ወታደራዊ በዓል ላይ መገኘት ስለነበረበት እምቢ አላለኝም … ስተኩስ ቆይቼ … ድንገት የጣድኩት ነገር ትዝ ብሎኝ ካውያውን አስቀምጩ ወደ ጓሮ ሮጥኩ ---- አልደረስኩም አሯል---- እርር እያልኩ ተመልሼ ካውያውን ብድግ ሳደርገው … የሱሪውን አንድ ጎን .. ጉምድ አድርጎ አነሳው ---- አይኖቼን ማመን አልቻልኩም---- ልቤን አመመኝ---- ሆዴ ተላወሰ ታመሰ … ራሴን የሳትኩ መሰለኝ…
ምን ነበረበት ትንሽ ቆየት ብሎ ቢመጣ … እናቴ ቤት የምሄድበት ጊዜ አገኝ ነበር---- አልሆነም ገና ወደ ቤት ሲገባ ሁለት አይነት ያልተለመዱ ሽታዎችን ባፍንጫው ማገ … ያረረውን ድስትና የተቃጠለ የደንብ ልብሱን ---- አንዴ እኔን፣ አንዴ ልብሱን ሲያይ ቆይቶ ነብር ሆነ -- ልክ በውጊያ ግንባር ላይ እንዳለ አይነት … ብድግ አርጎኝ የልብስ ሻንጣው ላይ ዘረፈጠኝ …
“ለምን … ቤዛ ለምን?”
እንባዬ ቀደመ … ሲፈጥረው “አይዞሽ በቃ” ወይም እኔን; አያውቅም---- እኔም አልጠበቅሁም-- እንባዬ እስኪያቆም ጠበቀኝ .. በዚያ መሃል ግን ወደ ጓዳ ገብቶ ተመልሷል -- “መልስ--- መልስ-- ለምን?”
“ምን እንደምልህ አላውቅም”
“ለምን?”
“ካቅሜ በላይ ነው”
“ምን ማለት ነው?”
“ጥፋቴ …”
“ለምን አጠፋሽ?”
“ተወኝ በናትህ ስሞትልህ”
“ለምን እተውሻለሁ”
“እሺ ለምን አትበለኝ ልንገርህ” ብዬው የሆነውን ሁሉ አጭሩን እውነት አርዝሜ --- አስተዛዝኜ ተረኩለት፤ በየመሃሉ ለአፍታ ቀና እያልኩ ስሜቱን ከግዙፍ ፊቱ ላይ ለማንበብ ብሞክርም ባልተለመደ ሁኔታ … ዝም ሙትት ብሏል፡፡
“ጨረስሽ?”
ራሴን በፍርሀት ደፍቼ---- በአዎንታ ወዘወዝኩ ----- “ባፍሽ ተናገሪ!” ወይኔ ዛሬ ጉዴ ፈልቷል! “አዎን”
“ምኔን እንዳቃጠልሽ ታውቂያለሽ?!”
“አዎ”
“አዎ?” አፈጠጠብኝ
“ያቃጠልኩት … ልብስህን” በጥፊ አላሰኝ --- የእጁ ፍጥነት!
“ልብስ ተራ ነገር ነው … ታሪኬን ገድሌን … በእሳት የተፈተንኩበት ዘመን --- የመከራዬን ማስታወሻ ----- የክብር ልብሴን ነው ያቃጠልሽው!!! …”
አንገበገበው … እሱም እንደ ልብሱ በንዴት ካውያ ተቃጠለ ---- በመሃል ስልክ ደውሎ አስቸኳይ ትዕዛዝ አስተላለፈ----- ምክንያቱም በዝግጅቱ ላይ መገኘት ነበረበት፡፡  
ከዚያ ቢጠይቀኝም የምመልስለት በማጣቴ ወደ ቅጣት ተሸጋገርኩ … ለሶስት ቀን ከቤት እንዳልወጣ አገደኝ፤ ጧት ሲወጣ የምበላውን ትንሽ ትንሽ ምግብ … አውጥቶ ሁሉንም ቆላልፎብኝ ይወጣል … የሚገርመው ምቾት እንዳላገኝ --- እንዳላንቀላፋ ክፍሉን ባዶ ማድረጉ ነበር---- ሆነ ብሎ ሶስቱንም ቀን … አምሽቶ ነበር የገባው፤ በአራተኛው ቀን ወደ ስራዬ ገባሁ፤ መስራት ግን አልቻልኩም፤ መወሰን ፈለግሁ --- ፈራሁ፤ መቀጠሉንም ፈፅሞ አልፈለግሁም … ደውዬ መነጋገር አለብን አልኩት።
“ስለ ምን?” እሱ ረስቶታል
“ስለኔና ስላንተ”
“ቤት ነያ!”
“ቤት አይደለም ውጪ ካፌ”
ደስ ሳይለው እሺ አለ፡፡
በዚህ ሁኔታ .. መቀጠል አልችልም---- ፍቅርን ወይም ግምገማን እንዲመርጥ ግድ አልኩ፡፡ አስጨናቂ፤ ግምገማ በሁሉም ጉዳይ፣ ስራና ሁኔታ ውስጥ መኖር አለበት ብሎ ያምናል፤ ተከራከረኝ፡፡
“እንደዚያ ከሆነ መለያየት አለብን”
አፈጠጠ፡፡ ቁና ቁና ተነፈሰ፡፡ ብርጭቆ ሲሰበር ግምገማ … ድስት ሲያር ግምገማ … አይሆንም ብዬ ነገርኩት… መቁረጤን አወቀ …
“እስኪ ተቀመጭ”
ተቀመጥኩ ---- “አንድ መንገድ ይኑረና አለ”፤ እኔ እሱን የሚያበሳጭ ነገር እንዳላደርግ----- እሱም የመተራረሚያ መንገዱን ሊለውጥ ተስማማን…
ሁሌ የሚገርመኝ ነገር በዚህ ሰብዕናው ማፍቀር መቻሉ ነው … ወደ ቤት ገባን --- አሁን መፈራራት ጀመርን --- እኔም በጥንቃቄ እሱም በጥንቃቄ … ጥንቃቄ ሲበዛ ጭንቀት ፍርሃት ይወልዳል፡፡ 

Read 3278 times