Saturday, 26 March 2016 10:49

ዶ/ር መረራ ጉዲና ከሀገር መውጣት አልቻልኩም አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(26 votes)

     የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀ መንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ከትናንት በስቲያ ወደ አሜሪካ ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ እንደተሰናከለባቸው ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ “ቪዥን ኢትዮጵያ” (ራዕይ ኢትዮጵያ) በተሰኘ ተቋም ጋባዥነት በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ሊጓዙ እንደነበር የጠቆሙት ዶ/ር መረራ፤ ሻንጣቸው ተፈትሾ ከተጫነ በኋላ “ፓስፖርቱ ላይ ያለውን ቁጥር የኛ ሲስተም ማንበብ አልቻለም” ተብለው ከቦሌ አየር መንገድ እንዲመለሱ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
“ፓስፖርቱን ኬሚካል ወይም ሽቶ አሊያም ዘይት ነክቶት ይሆናል” ብለውኛል ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ከአየር መንገዱ ከተመለሱ በኋላም ለኢምግሬሽን አቤቱታ ማቅረባቸውንና እስከ ትናንት ረፋድ ድረስ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
ፓስፖርቱ የ3 ዓመታት የአገልግሎት ጊዜ እንዳለው የገለፁት ዶ/ር መረራ፤ ወደ ውጭ ሀገር መመላለስ ከጀመሩ ከ30 ዓመት በላይ እንደሆናቸውና ይህ አይነቱ ሁኔታ ሲገጥማቸው የመጀመሪያው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል “የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ህልሞች” በሚል ርዕስ ለአንባቢያን ያቀረቡት መፅሃፍ፤ ሁለተኛ ህትመት መውጣቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡  

Read 10511 times