Saturday, 26 March 2016 10:47

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት፤ አለማቀፉን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሰሰች

Written by 
Rate this item
(7 votes)

     የተከለከለ አበረታች ንጥረ ነገር ተጠቅማለች በሚል ባለፈው ነሃሴ ወር ላይ ከውድድር እንድትታገድ የተወሰነባት ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ኢቫን አቢይ ለገሰ  ውሳኔው የተላለፈብኝ ያለአግባብ ነው በሚል አለማቀፉን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኞች ማህበር መክሰሷን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
ለቱርክ የምትሮጠው አትሌቷ እ.ኤ.አ በ2005 እና 2007 በተከናወኑት የአለም ሻምፒዎናዎች በተደረጉላት የሽንት ምርመራዎች የተከለከለ ንጥረ ነገር መገኘቱን ተከትሎ፣ በቱርክ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከውድድር መታገዷን ያስታወሰው ዘገባው፣ በምርመራዎቹ ላይ የቴክኒክ ስህተቶች ተፈጽመዋል በሚል በሞናኮ የአስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ክስ መመስረቷን ጠቁሟል፡፡
የአትሌቷ ወኪል ኦንዴር ኦዝባይለን በበኩላቸው፤ በአለማቀፉ የጸረ አበረታች እጽ ተቋም እውቅና በተሰጠው አንድ የምርመራ ላቦራቶሪ ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያ በጉዳዩ ዙሪያ የሰጧቸውን መረጃዎች መሰረት በማድረግ፣ ክሱን እንደመሰረቱና በምርመራው ወቅት ዘጠኝ ያህል የቴክኒክ ስህተቶች መፈጸማቸውን አናዶሉ ኤጀንሲ ለተባለ የዜና ወኪል ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ስህተቶቹ መፈጸማቸውን ካረጋገጠ፣ የአለማቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በአትሊቷ ላይ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ውድቅ እንደሚደረጉም ወኪሉ ገልጸዋል።
አትሌቷ ባለፈው አመት የተባለውን አበረታች ንጥረ ነገር አለመጠቀሟንና እንዲህ አይነት ህገወጥ ተግባር ለመፈጸም አስባ እንደማታውቅ መናገሯን የጠቆመው ዘገባው፣ ኦሳካ ላይ በተካሄደው የ2007 የአለም ሻምፒዮና በአስር ሺህ ሜትር ውድድር የብር ሜዳሊያ ማግኘቷንም አስታውሷል፡፡

Read 7423 times