Saturday, 26 March 2016 10:14

ማኅበረ ቅዱሳን: ዐውደ ርዕዩ የተከለከለው በመንግሥት ነው፤ አለ

Written by  ማሕሌት ኪዳነ ወልድ
Rate this item
(9 votes)

“ጥያቄው የቀረበበት ጊዜ በማጠሩ እንጂ ዕውቅና አልከለከልንም” /የአዲስ አበባ አስተዳደር/

    ባሳለፍነው ሐሙስ፣ በማኅበረ ቅዱሳን አዘጋጅነት በኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚታይ ሲጠበቅ የነበረው 5ኛው ዙር ልዩ ዐውደ ርዕይ የታገደው በመንግሥት መሆኑን ማኅበረ ቅዱሳን አስታወቀ፡፡
“ለእኛ መንገር ባልተፈለገና በማናውቀው ምክንያት መንግሥት ከልክሎናል፤” ሲሉ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ፀሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፣ መስከረም 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ዐውደ ርዕዩን ለማካሄድ ከኤግዚቢሽን ማዕከሉ ጋር የውል ስምምነት ፈጽመዋል፤ ለስምምነቱም ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው ማኅበሩ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የተጻፈ የድጋፍ ደብዳቤ አቅርቧል፡፡ ሆኖም ሐሙስ ለሚቀርብ ዐውደ ርዕይ ረቡዕ ከሰዓት ዕቃ በማዘጋጀት ላይ ሳሉ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፈቃድ ደብዳቤ ካላመጡ ዐውደ ርዕዩን ማካሄድ እንደማይችሉ ከኤግዚቢሽኑ አስተዳደር ይነገራቸዋል፡፡
ይህን ተከትሎም ማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ አስተዳደር ፈቃድ እንዲሰጠው ቢጠይቅም አስተዳደሩ ግን ለዐውደ ርዕይ ፈቃድ የምንሰጥበት አሠራር የለንም በማለት ምላሽ ሰጥቶናል፤ ብለዋል፡፡
ዐውደ ርዕዩ በማን እንደተከለከለ እንጂ ለምን እንደተከለከለ እስከ አሁን አላወቅንም ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ዐውደ ርዕዩ ምንም ዓይነት ችግር የሌለበት መሆኑን በማስረዳትና በመወያየት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው፤ ብለዋል፡፡
ችግሩ በቅርቡ መፍትሔ አግኝቶ እዚያው ኤግዚቢሽን ማዕከል እንደምናሳይ ተስፋ እናደርጋለን፤ ያሉት ዋና ጸሐፊው፤ ይህ ካልሆነ ግን የማኅበሩ አመራር ተነጋግሮበት በኤግዚቢሽ ማዕከልም ባይሆን በሌላ ቦታ ለማካሄድ ጥረት እንደሚደረግ አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡
በዐውደ ርዕዩ መሰረዝ ማኅበሩ የደረሰበት ጉዳት የለም ወይ? ብለን የጠየቅናቸው አቶ ተስፋዬ፥ “ዐውደ ርዕዩ ሰፊ ዝግጅትና ትልቅ ገንዘብ ጠይቋል፤ መንፈሳዊ በመሆኑ አብዛኛው ምእመን በነፃ ቢያገለግልም በማኅበሩ የተደረገው ወጪ ቀላል አይደለም፡፡ ሐሙስ የሚጀምር ፕሮግራም ረቡዕ ሲታገድ ጉዳቱ ሰፊ ነው፡፡ እንግዲህ በቀጣይ ጉዳቱን እንቀንሳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን እንጂ ጉዳቱማ ብዙ ነው፤” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና የስብሰባ ፈቃድ ክፍል በበኩሉ፤ “እኔ የምሰጠው ዕውቅና እንጂ ፈቃድ አይደለም፤  ነገር ሲሆን የጥበቃ ሽፋን ለመስጠት ዕውቅና እንሰጣለን፡፡ ሆኖም ማኅበሩ ዕውቅናውን የጠየቀው ለጠዋት ዐውደ ርእይ ማታ ነው፡፡ ምናልባት ሕጋዊ ላለመሆን ብለው ሳይሆን መረጃው ስለሌላቸው ይመስለኛል፡፡ ማዕከሉን የሚያከራየው አካልም ለምን እንዳልነገራቸው አላውቅም፡፡ ሆኖም የጠየቁበት ጊዜ ስላጠረ እንጂ አሠራሩን ተከትለው በደብዳቤ ከጠየቁ ማንም የሚከለክላቸው አይሆንም፤” ብሏል፡፡
ለዐውደ ርዕዩ ካለፈው ታኅሣሥ ወር ጀምሮ ከ40ሺሕ በላይ የመግቢያ ቲኬቶች የተሸጡ ሲሆን ለጉብኝት ክፍት ሆኖ በሚቆይባቸው ሰባት ቀናትም ከመቶ ሺሕ በላይ ሕዝብ እንዲጎበኘው ታቅዶ  እንደነበር በዝግጅቱ ዐቢይ ኮሚቴ ተገልጿል፡፡
ማኅበሩ ከዚህ ቀደምም የሚሌኒየሙን መባቻ ምክንያት በማድረግ በመስቀል አደባባይ ያዘጋጀው ትእይንት፤ የጥናት ጉባኤ፤ የአብነት መምህራን ሀገር አቀፍ ጉባኤና የመሳሰሉት መርሐ ግብሮች በመጨረሻው ሰዓት፣ በተለያዩ አካላት እንደታገደበት የሚታወስ ነው፡፡

Read 3326 times