Saturday, 19 March 2016 11:56

ገምጋሚው!

Written by  ፍፁም ንጉሴ
Rate this item
(12 votes)

ያኔ ገና ሲተዋወቀኝ እንዲሁ ድርቅ ችክ ያለ ጠያቂ ነበር፡፡ ትልቅ ፊቱን ቁምጭጭ … ወፍራም አንገቱን ወደ ተጠያቂው/ዋ ስግግ እያደረገ ይጠይቃል፤ ጥያቄዎቹ ማለቂያ የላቸውም፡፡ ወንዝ ናቸው፡፡ ጊዜው እንጂ የሱ ጥያቄ አያልቅም። ወይም የተጠያቂው/ዋ ትዕግስት ይንጠፈጠፍና ነው የሚያባራው፡፡ ያኔ … ድንገት ወደ ምሰራበት ካፌ መጣ፡፡ እንደገባ እስከ ነገ ይቀመጥበት ይመስል ለወንበር መረጣ .. በጅብራ ቁመቱ … ክፍሉ መሃል ተገትሮ ሰከንዶችን ገደለ፡፡ ተቀምጦም የአራስ ልጅ ቡጢ በሚያካክሉ አይኖቹ ጣራውን ግድግዳውን … ማስታወቂያዎቹን … ስዕሎቹን … ሲመለከት ቆይቶ … እኛንም ገርመም ገርመም አደረገን … ልታዘዘው ሄድኩ፡፡
“ምን ልታዘዝ?”
“ወገብሽ እንጂ ድምፅሽ አይታጠፍም?”
“አልገባኝም?!”
‹ጉዴ ፈላ ምኑ መጣብኝ ደሞ ዛሬ!› … “ምን ላምጣልህ?” አልኩት
“ወገብሽን ዘመም ያረግሽው ትህትናና አክብሮትን ለማሳየት ብለሽ አይደለም?”
“ነው እንጂ”
“ነው እንጂ … አይባልም … ለምን አልሽ?”
‹ወይኔ ጉዴ!› ለራሴ ነው… በካፌ መስተንግዶ ስራዬ … ብዙ ዓይነት ተስተናጋጆች … ገጥመውኛል … ይሄን አይነቱን ግን እንጃ … ቀጥሏል ሰውዬው …
“ስለዚህ እንደ ወገብሽ ሁሉ ድምፅሽም--- ቃልሽም---- እጥፍ ቅንጥስ፣ ልስልስ ማለት አለበት”
“አሃ? … እሺ ይቅርታ”
“ለምን ‹አሃ› … ለምን ‹ይቅርታ› ትያለሽ? እሺ አይበቃም?”
ዞሬ መሄድ ፈለኩ … ሊጨቃጨቅ ነው? … ሊስተናገድ ነው? ወይስ ስነ-ስርዓት፣ ግብረ ገብ ምናምን ሌክቸር ሊያደርግ ነው የመጣው?
“ምን አለ?” ከላይ እስከ ታች እያየኝ ነው። አይኖቹ የሚማቱ ነው የሚመስሉት … የፊቱ ስፋት … የሰውነቱ ግዝፈት ቢያስፈራም … እኛ የአቢሲኒያ ሴቶች ‹ዋጥ! … ስልቅጥ! … የሚያደርግን … እንመርጥ የለ? … ፊቱ ላይ ሳይሆን አይኖቹ ውስጥ ፈገግ ያለ ይመስላል … እኔን የማየት የመመኘት … ጉጉቱን ያሳብቁበታል፤ በዛች የቅፅበት ግርመማው የስራ ልብሴ አካል የሆነውን ባርኔጣ መሳይ ሻሼን ገፎ ፀጉሬን የነጨኝ፤ ስሜ ካለበት ደንብ ልብሴ ኪስ ስር ያሉ ጡቶቼን ቆንጠጥ--- ጉጥጉጥ---- ጉጥ---ጉጥጉጥ ያደረጋቸው መሰለኝ … ያሉትን ቀዝቃዛና ትኩስ መጠጦች በለመድኩት ቅልጥፍና ትርርር አደረኩለት፡፡ ማድመጡን ከፍጥነቴ እኩል ለማስኬድ እየጣረ … ብዙ እንደ ጠባሳ፣እንደ ስፌት ያሉ ጉብታዎች ያሉበት ግንባሩን ባይጨማደድም ጨምደድ ሊያደርግ እየጣረ … ወፍራምና ረዥም አንገቱን … እሱ ግመል እኔ ቅጠል የሆንኩ ይመስል እያሰገገብኝ ቆይቶ፤
“እርጎ የለም?”
“እርጎ የለም”
“ለምን?”
“እንጃ … አልቆ መሰለኝ” ላፍታ ወደ መደርደሪያው ቃኘት አደረኩ
“እንጃ … መሰለኝ ይባላል እንዴ?”
“ይቅርታ”
“ለምን?”
‹ኤጭ!› አልኩ ለራሴ፡፡ ትቼው ልሄድ ፈለኩ። … ብሄድም የሚለቀኝ አይመስልም፤እየጮኸ ‹ለምን?› ሙቀቱን ወበቁን ለቀቀብኝ … ደሞ … የሚያበሳጨው ለኔ … በዕድሜው የአባቴ ታናሽ ወንድም አይነት ቢሆንም /ለነገሩ ይሄ ከቁጥር ባይገባም…/ የምመርጠው አይነት ወንድ መሆኑ!! ባጠገቤ ስታልፍ የነበረች ባልደረባዬ፤የእርጎውን ሙግት ሰምታ በጆሮዎቼ “አንድ አለ’ኮ ….” ብላኝ አለፈች
ባለማመን ጮክ ብዬ፤
“እውነት? ወይኔ” … ድምፄን ሰማው
“ምንድነው ዕውነት?”
‹ሰውየው ጲላጦስ ሆነ!› ከራሴ ጋር ነው …፡፡
“አንድ እርጎ አለ” አልኩት÷ቃላቶቼን ለማለስለስ እየሞከርኩ
“ጥሩ፡፡ … ሳታጣሪ ለምን የለም አልሽኝ?”
መልስ መመለስ ይደክማል? ደከመኝ … “ሌላ ምን ላምጣልህ?” ወደ ባንኮኒው … እየጠቆመ “በጣም ምርጡን ግን ውድ ያልሆነውን … ከነዚያ ዳቦ ነገሮች”
እሱን አይደለሁም እንጂ ‹ዳቦ ነገሮች› አይባልም እለው ነበር---- “እሺ” እሱ ፊት የቆምኩት ከትናንት ጀምሮ እስኪመስለኝ ሰልችቶኝ ቸኮልኩ፡፡ “ስንት?” አልኩት “ሰባት”፤ ዞሮ የነበረ ፊቴን ወዲያው ወደዚህ ስመልሰው ፊቴ ፊት ሳይሆን ንፋስ ያጠነጋገረው ቅጠል ነበር የሆነብኝ፤ ‹ምኑ ግመል የመሰለ ሰው ነው!› “ስንት?!” ድምፄ ውስጥ በቁጥሩ መደንገጤን ራሴው ሰማሁት፤ እስኪ ምን አገባኝ … ለምን 16 አያዝም!
“ደነገጥሽ?”
“አዎ” አምልጣኝ ነበር የወጣችው ቃሏ!
“ለምን?”
‹ለምን› ስንት ‹ለምን›ን? ስንት ‹እንዴት›ን ጠየቀኝ? ይሄ ሰውዬ፤ሰው ነው ጥያቄ!?›
በሁኔታዬ ፈገግ አለ፡፡ ጥርሶቹ!!! … በጣም ያምራሉ፤ ማንም እነኚህን የመሰሉ ጥርሶች ከዚያ ባንድ ወቅት ውጊያ የተደረገበት ኮረብታ ከሚመስል ፊቱ ስር አይጠብቅም፡፡
“ከበዛብኝ ሦስቱን አንቺ …”
“እኔ አልበላም”
“ለምን?”
“በልቻለሁ”
“ብትበይስ? … ክኒን ክኒን የሚያካክሉ አይደሉም እንዴ?”
“ለኔ ዳቦ ናቸው”
እርጎውን በ7ቱ ዳቦዎች አስከብቤ አቀረብኩለት።
“ማነው ስምሽ?”
‹መጠየቅ አለበት? … የለበትም! የመመለስ ግዴታ አለብኝ? የለብኝም---- ከራሴ ስሟገት
“ምነው ስም የለሽም?”
“ለምን የለኝም?”
በነዚያ ጥርሶቹ ያልተገባ አገማመጥ ሲገምጣቸው ስቅቅ አልኩላቸው፡፡ ለነገሩ ለሱ ኪኒን እየዋጠ ነው ለካ! … እርጎውን በማንኪያ ዝቆ ሲጨምረው፣ ጥርሶቹ እንደነሱ የነጣ ነገር ስላገኙ የሳቁ መሰለኝ፡፡
“እሺ ውድ ነው? ወይስ ረዥም---- ለመናገር የሚያደክም?”
“ቤዛ” አልኩት ባጭሩ
“ቤዛ? ቤዛ! … ቤዛ!? …” ማላመጡን አቁሞ ለምን አሰላሰለው … ምን አገባውና ነው ስሜን ሊተረጉም የሚለፋው? አውቆ እንዳላወቀ እየሆነ … ለነገሩ ሰውየው ፈልጓል፤ ፈ…..ለ….ግ…. አርጎኛል …
“በጣም ደስ የሚል ስም ነው … አንቺም በጣም ደስ ትያለሽ?”
“እውነት?” አልኩ በገዛ እጄ
“ለምን አልሽ?”
“ምን?”
“እውነት?”
“ከልብህ ነው ወይ ለማለት?”
“ታዲያ ከልብህ ነው ወይ? አትይኝም ነበር?”
‹ቆይ አንተ የጥያቄ ፋብሪካ ነህ?› ልለው ብዬ ከከንፈሬ ላይ ነው የመለስኩት፤“የኔ ስም አስጨናቂ ነው” አለኝ ኪኒኖቹን በእርጎ እያጨናነቀ
 “እሺ”
“ለምን አልሽኝ?”
“እሺ ማለት ችግር አለው?”
“የለውም”
“ታዲያ?”
“ምንድነው ‹ታዲያ› ማለት?”
“ጉዴ ፈላብኝ!”
“እኔ ያንቺን ጉድ ላፈላ አልመጣሁም፤ይልቅ ተቀመጭ”
“አልችልም፤መቀመጥ”
“አይፈቀድም ማለት ነው!”
ቅር አለው…መቶ ብር ዘረጋልኝ፡፡ መልሱን ልሰጠው ስመለስ፣እርጎውንም ዳቦዎቹንም ፈጅቷቸዋል፡፡ ተምች የሆነ ሰው ነው፡፡ ወፈር ያለ ቲፕ ሰጠኝ፡፡ የምኖርበትን ሰፈርና የስራ ፈረቃዬን አናዞኝ … እሱም ሊያገኘኝ እንደሚፈልግ ተናዞልኝ ሄደ፡፡ የሚፈለፈሉ ጥያቄዎቹ አስጨናቂ! … ስሙ አስጨናቂ!! አመጋገቡ አስጨናቂ!! ተመላለሰ፤ተለማመድን…ስልክ ተለዋወጥን … በቃ ጓደኛሞች ሆንን፡፡
ስራን ቢያከብርም የኔን ስራ ጠላው፡፡ ወዲያው “ተይው” ማለት ጀመረ .. ገና ሳንነካካ ነበር በኔ ማዘዝ የጀመረው፡፡ የምወደውንና የማልወደውን በአንድ ላይ የተሸከመ ሰው ነበር፡፡ ሊያገኘኝ ከፈለገ በቃ ፈለገ ነው። አለማግኘት አይታሰብም፡፡ ‹አይመቸኝም› ‹ጉዳይ አለኝ› እንድለው አይፈልግም .. ሁሉን ጥዬ … ለሱ መገኘት አለብኝ፤ በዚያውም በሰዓቱ፡፡ 4፡00 ካለኝ 4፡00 ላይ! ዝንፍ ውልፍት የለም፡፡ አንድ ጊዜ … የካፌውን ስራ አስትቶኝ የኮምፒዩተር ፅህፈት ችሎታዬን እያሻሻልኩ በነበረበት ወቅት … ቤቱ ቀጠረኝ፡፡ ምሳ አብረን ሰርተን እንድንበላ .. ብሎ 5፡30 ላይ ድረሺ አለኝ፤አብዝተው የተጠነቀቁለት ነገር ላይ እንከን እንደማይጠፋ በተደጋጋሚ ያረጋገጥኩት በአስጨናቂ አስጨናቂነት ነው፡፡
እና ያን ቀን … አንዲት ጎረቤታችን ከባሏ ጋር ተጣልታ… ስትጮህ ሄድን..ገላግለን አረጋግተን ለመመለስ ነበር፡፡ ማን እንደጠራቸው እንጃ ፖሊሶች መጡ፡፡ ሁለቱንም ይዘው ሲሄዱ ‹ምስክር ትሆናላችሁ› ብለው እኛንም ይዘውን ወደ ጣቢያ፤ ለምኜ ለምኜ የምስክርነት ቃሉን ቀድሜ ሰጥቼ ስመለስ 5 ሰዓት ሊሞላ ምንም አልቀረውም፤ ጉዴ ሊፈላ ነው --- በፍጥነት ተጣጥቤ ለበስኩ…ከዚያ በፈጠነ ሁኔታ ላከናውነው አልቻልኩም … 5 ከሩብ ወጣሁ … ታክሲ … ‹የታክሲ ያለህ!› 5ቷ ደቂቃ እዛው ሞተች … ልቤ ብድግ ቁጭ … ስጋት … ጭንቀት … ልፈነዳ ደረስኩ … ተሳፈርኩ … ይሄዳል … ይቆማል … ሰው ይወርዳል ይወጣል .. ወያላው ወርዶ ይጣራል … ወዲህ ይላል፤ ወዲያ ይላል … ምን ልሁን?!?
“በናታችሁ እንሂድ” እያልኩ ስነጫነጭ፤ሲሰሙኝ ሲሰሙኝ ቆይተው…ሲበቃቸው ወያላው “አንቺን ብለን አልወጣንም” አለኝ ..
“እኔ እንደዛ አላልኩም”
“እና ባዶ ታክሲ ይዘን እንሂድ!?”
“ስለቸኮልኩ … ስለረፈደብኝ ነው”
“የራስሽ ጉዳይ! በጊዜ መውጣት ሲገባሽ የራስሽን ጥፋት በኛ እያላከክሽ አትነጫነጪ” የሚገርመው አንዷ ተሳፋሪ እዚህ ጋ ‹ወራጅ› ብላ ወርዳ፣ ከ30 እና 40 ሜትር በኋላ ሌላዋ ‹ወራጅ› ትላለች፤ አያናድድም?፡፡ ምናለበት ለቀሪው መንገደኛ ጊዜ ቢያስቡ? 30 እና 40 ሜትር በእግር ቢጓዙ ይቀልጣሉ? አስጨናቂ፤ከጭንቀት የበዛ ምን ሰጠኝ? ፍቅር? ከፍቅሩ ጭንቁ በሺህ እጥፍ ይበልጣል፤ ግን እወድዋለሁ፤ወርጄ ከርምጃ ከፍ፣ ከሩጫ ዝቅ ባለ እንደ ሶምሶማ በውስጥ ለውስጥ አስጠሊታ መንገድ ተጓዝኩ፡፡ ላብ በላብ ሆኛለሁ፡፡ እግሮቼ አቧራ ቅመዋል፡፡
የውጪውን በር ከፍቼ ገባሁ፤ ስንት ሰዓት ሆኖ ይሆን? በማን ሰዓት ሰዓቱን ልይ? ሰዓቱ የሱ! ጊዜው የሱ! … ግቢው ውስጥ አሮጌ ቅርንጫፍ የሌለው ዛፍ መስሎ ቆሟል፤ በንዴት ጭርጭር ብሏል፡፡ ከኋላው ቆም አልኩ። ትንፋሼን ይስማ ጥላዬን ይየው አላውቅም፤ ሳይዞር “ለምን አረፈድሽ? ለምንድነው የምታረፍጂው? ለምን?”
ገባሁ ---- አሮጌው ሶፋ ላይ ዝርግት አልኩ፤የላይ ልብሴን አውልቄ ጥዬ በጭንቅና በሙቀት የነደደ አካሌን ማራገብ ጀመርኩ፡፡ አስጨናቂ ገባ፡፡ ያለ ንግግር ወደ ወንበሮቹ አሳየኝ፤ስብሰባ መሆኑ ነው … ግምገማ። ከሳምንቱ 7 ቀናት በትንሹ በአራቱ ቀናት ስብሰባ ሳንቀመጥ አንቀርም፤ ለግምገማ ..
ልረፍ ብዬ ባይኖቼ ብለማመጠው የባሰ ተናደደ፤ ተቀመጥን … ትልቅ ርቱ ፊቱ ላይ ሊናድ የደረሰ አለት መስሎ ተንጠለጠለ፤ኮረብታማ ግንባሩ ወዝቶ ሳየው ዝናብ የጣለበት መሰለኝ .. አይኖቹ እንደ ቦክስ እየተሰነዘሩ … አይኖቼን ሰበሩኝ፤ የግመል አይነት አንገቱን አሰገገ፤ ሰዐቱን አሳየኝ፤ 6.25፡፡
“ለምን?”
ተጀመረ .. ሰው እንዴት “ለምን”ን፣ እንዴትን ያፈቅራል?
“ጎረቤታችን ተጣልተው”
“ይጣሉኣ! ለምን ጥልቅ ትያለሽ”
“እንዴዬ?”
“ምንድነው እንዴዬ? ቅድሚያ ለራስሽ፣ ቅድሚያ ለኔ ለፍቅር ጓደኛሽ ነው መስጠት ያለብሽ”
“ምስክር ብለው---”
“ለሚስት ብለሽ ባል ላይ--- ወይስ ለባል ብለሽ ሚስት ላይ?”
“ያየሁትን”
“ምን አየሽ?”
“ሲደባደቡ ---- ማለቴ ---- ሲደበድባት”
“ይውገራታ!”
“እህ… እንዴ?”
“ምንድነው እንዴዬ!”
“ወይኔ”
“ለምን ወይኔ አልሽ? አላጠፋሁም ለማለት ነው?”
“አጥፍቻለሁ”
“ለምን አጠፋሽ?”
“ነገርኩህ”
“አልነገርሽኝም”
“ታዲያ ምን እያረኩ ነበር?”
“እያጭበረበርሽ”
“እንዴዬ?!”
“ለምን እንዴዬ … እንዴዬ የምትይው መናገር ሲያቅትሽ ነው፤ ዕውነቱን ለመሸፋፈን … እኔን ለማሳዘን፣ ለማባበል ነው”
“አይደለም!”
“ነው!”
“ጧት ነበር ስለቀጠሮሽ ማሰብ የነበረብሽ፤ ጧት ብታስቢው ኖሮ በመሃል የሚፈጠሩ …”
“ገባኝ ገባኝ፤ ልክ ነህ በቃ ይቅርታ …”
“ቆይ ቆይ”
የሱ ግምገማ ከብዛት ርዝመቱ÷ ገብቶኛል--- ባይገባኝም ገብቶኛል ..
“እሺ ምን?
“እና ለምን ሳታስቢበት ቀረሽ?”
“እንደዚህ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበራ…”
“ለምን?”
“ስሞትልህ ለምን አትበለኝ? ለምን የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ የለም”
“ሞልቷል”
“እኔ አላየሁም”
“ስለምትሸሺ፤ እሺ--- ቅጣትሽ ምን ይሁን?”
“የፈለከውን”
“በ30 ደቂቃ ውስጥ ምሳ ሰርተሽ አብይና”
“እሺ”
(ይቀጥላል)

Read 3397 times