Saturday, 19 March 2016 10:58

አዳማ ስጋት ውስጥ ሰነበተች

Written by 
Rate this item
(24 votes)

- በዩኒቨርሲቲው ጀኔሬተር ፈንድቶ በተነሳ ቃጠሎ ትምህርት ተቋርጧል
- ህገወጥ ተብለው 250 ቤቶች ሲፈርሱ ከፖሊስ ጋር ግጭት ተከስቷል

    አዳማ (ናዝሬት) ከተማ ላይ፣ የስጋት መንፈስ ሲያንዣብብባት ሰንብቷል፤ የዩኒቨርስቲ ትምህርት ተቋርጦ በርካቶች ወደየትውልድ አካባቢያቸው ተመልሰዋል፡፡ በከተማዋ አንድ ዳርቻ ህገወጥ ናቸው የተባሉ ቤቶች ለማፍረስ በተጀመረ ዘመቻም ግጭት ተፈጥሮ ጉዳት ደርሷል፡፡
በከተማዋ በተፈጠረው አለመረጋጋት ስጋት እንዳደረባቸው የገለፁልን ነዋሪዎች፤ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ በርካታ አመታት ሲያገለግል የነበረ ጀኔሬተር ፈንድቶ የእሳት ቃጠሎ እንደተነሳና በተለያዩ ክፍሎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች ተደናግጠው አለመረጋጋት በመፈጠሩ ትምህርት እንደተቋረጠ ምንጮች ጠቅሰው፣ አንዳንዶቹ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወደየመጡበት አካባቢ መሄዳቸውን ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ኩሽነን እና ቀበሌ 03 በተሰኙ ቦታዎች፣ ህገወጥ ናቸው የተባሉ የጨረቃ ቤቶችን ለማፍረስ በተጀመረ ዘመቻ፣ ከነዋሪዎች ጋር ግጭት ተፈጥሯል፡፡ ከ250 በላይ ቤቶች እንደፈረሱ ምንጮች የገለፁ ሲሆን፤ ነዋሪዎች ከፖሊስና ከአፍራሽ ግብረ ሃይል አባላት ጋር ተጋጭተው ጉዳት የደረሰ መሆኑን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡
በእነዚህ ክስተቶች ሳቢያ አለመረጋጋትና ስጋት ቢፈጠርም፣ ከዚሁ ቀበሌ አቅራቢያ በሚገኘው 10 ቀበሌ ተጨማሪ ህገ ወጥ ቤቶችን ለማፍረስ ተወስኗል ብለዋል ምንጮቹ፡፡ በሰባት ቀናት ውስጥ ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው የተናገሩ ነዋሪዎች፤ በሰባተኛው ቀን አፍራሽ ግብረ ሃይል መጥቶ ቤቶችን እንደሚያፈርስ ተነግሮናል ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅና ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ  ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ 

Read 6725 times