Saturday, 12 March 2016 10:26

መንግስት በሀገሪቱ ለተፈጠሩ አለመረጋጋቶችና ችግሮች ይቅርታ ጠይቋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(31 votes)

“ይቅርታ መጠየቁ መልካም ነው፤ ይቅርታው ግን በተግባር የተደገፈ መሆን አለበት”

    መንግሥት ኦሮሚያን ጨምሮ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለተፈጠሩት አለመረጋጋቶችና ችግሮች ህዝቡን ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን፤ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሩ ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ መጠየቃቸው መልካም መሆኑን ጠቅሰው፣ “ይቅርታው በተግባር የተደገፈ መሆን አለበት፣ በግጭቱ ምክንያት የታሰሩት ተፈተው፤ ያጠፉ ባለስልጣናት በህግ ሊጠየቁና ተጎጂዎች ተገቢውን ፍትህና ካሳ ሊያገኙ ይገባል” ብለዋል፡፡   
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የመንግስታቸውን የ6 ወር አፈፃፀም ከትናንት በስቲያ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ባቀረቡበት ወቅት፣ በሀገሪቱ በተከሰተው ኤሊኖ ምክንያት የግብርና ምርት ይቀንሳል ብለዋል፡፡ የወጪ ንግዱም 75 በመቶ በግብርና ምርቶች ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዘንድሮ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እየታየ ያለው ደካማ የወጪ ንግድ አፈፃፀም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገቱን እንዳያደናቅፍ ልዩ ትኩረት እንዳሚያሻውም ገልፀዋል፡፡
የውጪ ንግዱ ለመቀዛቀዙም የሀገር ውስጥ የግብርና ምርት መቀነስና የአለማቀፍ ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ምክንያት መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ኃይለማርያም፤ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ኤክስፖርት ላይ መንግስት ጉድለት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡
በህዳር ወር አጋማሽ ላይ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ዘንድሮ ስለሚጠበቀው አመታዊ ምርት በሰጠው መገለጫ፤ ምንም እንኳ በሀገሪቱ ድርቁ ተፅዕኖ እያስከተለ ቢሆንም ሰብል አምራች የሆኑ አካባቢዎች ላይ ጉዳት ባለመድረሱ አመታዊ ምርቱ ከመቀነስ ይልቅ ሊጨምር ይችላል ማለቱ የሚታወስ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው በድርቁ አጠቃላይ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ መጎዳቱን ጠቁመዋል፡፡
የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚው የበለጠ እንዳይጎዳም ከመስኖ አማራጮች ባሻገር የበልግ ዝናብ ወቅትን ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ መሆኑን የጠቆመው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት፤ በድርቁ ምክንያት አንዳንድ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ከስራ ውጪ መሆናቸው ጥቂቶችም የማመንጨት አቅማቸው መቀነሱን አልሸሸጉም፡፡
የቀድሞዎቹ የስኳር ፋብሪካዎች መደበኛ የምርት ተግባራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አዳዲሶቹ በተለያየ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ወደምርት አለመግባታቸውንና በፕሮጀክት ግንባታዎችም መጓተት መኖሩን አመልክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ የ6 ወር የመንግስታቸውን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት  ባቀረቡበት ወቅት በኦሮሚያና በአማራ ሰሜን ጐንደር አንዳንድ አካባቢዎች ለተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ሳናቀርብ በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ህዝቡ ምሬት ስላለው የተፈጠረ መሆኑን ተገንዘበናል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገሪቱ ባለፉት ጥቂት ወራት ለተፈጠሩ አለመረጋጋቶችና ችግሮችም የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን ያሉ ሲሆን በፀረ ሰላም ሃይሎች ላይ አሁንም መንግስት እርምጃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ የተከሰተውን ግጭትና አለመረጋጋት ተከትሎ ከፍተኛ አመራሮቹን ጨምሮ በርካታ አባላቱ እንደታሰሩበት የሚገልፀው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ መጠየቃቸው” መልካም መሆኑን ገልፀው መንግስት ሃላፊነቱን ወስዶ ይቅርታ ከጠየቀ ከግጭቱና ተቃውሞው ጋር ተያይዞ የታሠሩትን መፍታት አለበት ብለዋል፡፡
“ከይቅርታው በኋላ እስረኞች ሲፈቱ ማየት እንፈልጋለን” ያሉት ዶ/ር መረራ፤ “መንግስት ይቅርታ ከጠየቀ ያጠፋው ጥፋት እንዳለ ያመለክታል፤ ስለዚህ አጠፉ የተባሉ ባለስልጣናት ከስልጣን ሲለቁ አሊያም ሲቀጡም ማየት አለብን” ብለዋል፡፡
በግጭቱ የተጐዱና የተገደሉ ወገኖችም ፍትህ ሊያገኙና ካሣ ሊከፈላቸው ይገባል ያሉት ሊቀመንበሩ፤ መንግስት ከንግግር ይልቅ ተግባርን ማስቀደም አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡  “የትኛውም መንግስት መጥፎ መንግስት መሆን አይፈልግም፤ ዋናው ፍላጐቱ ሳይሆን ሆኖ መገኘቱ ነው” ብለዋል - ዶ/ር መረራ፡፡

Read 10281 times