Saturday, 18 February 2012 12:14

የባለቤቱን አይኖች በስለት የወጋው አመለጠ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(1 Vote)

ሁለቱም አይኖቿ ለጊዜው አያዩም

በጐጂ አውራጃ በቡሬ ወረዳ የተወለደችው የ24 ዓመቷ ፀዳለች አስረስ ለቤተሰቦቿ 12ተኛ ልጅ ስትሆን ከአሁኑ ባለቤቷ ጋር የምትታወቀው ገና ከልጅነቷ ጊዜ ጀምሮ ነበር፡፡ ፀዳለችና የ26 ዓመቱ መሰለ ግርማ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው ቡሬ አብረው የተማሩ ሲሆን ሁለቱም ዩኒቨርስቲ የሚያስገባ ነጥብ በማምጣታቸው  ፀዳለች አምቦ ዩኒቨርስቲ ስትገባ መሰለ ጅማ ዩኒቨርስቲ ተመደበ፡፡ መለያየታቸው ያላስደሰተው መሰለ፤ ባቀረበው ሃሳብም ፀዳለች እንደምንም ብላ እሱ ወዳለበት ዩኒቨርስቲ እንደተቀየረች ትናገራለች፡፡

የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን አንድ ላይ መከታተል ከጀመሩ በኋላ ግን ፀዳለች ውጥረት ውስጥ እንደገባች ታስታውሳለች፡፡ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር የነበራትን ቀረቤታና ግንኙነት ያልወደደው ፍቅረኛዋ፤ ክፉኛ ይጨቀጭቃትና ያስጠነቅቃት እንደነበር ፀዳለች ተናግራለች፡፡የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን በ2001 ዓ.ም የጨረሱት ሁለቱ ወጣቶች በዳሸን ባንክ የተለያዩ ቅርንጫፎች ሥራ የተቀጠሩ ሲሆን ወዲያው ትዳር መስርተው ሴት ልጅ ወልደዋል፡፡ ትዳር ከመሰረቱ በኋላ ጭቅጭቁና ማስፈራሪያው መባባሱን የገለፀችው ወጣቷ፤ የምለብሰውን ልብስ የሚመርጠው እንኳን እሱ ነበር - ትላለች፡፡ ወደ ስራ ስትሄድም መተጣጠብና መቀባባት እንደማይፈቅድላት እንዲሁም ፀጉሯን እንደነገሩ እንድታስይዝ ብቻ እንደሚያስገድዳት ተናግራለች፡፡ ፀዳለች በጐፋ ዳሸን ባንክ፣ ባለቤቷ መሰለ ደግሞ በቄራ ዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ መ/ቤቶች እንደሚሰሩ የተናገረችው ወጣቷ፤ መ/ቤት ስትሄድ የምትለብሳቸውን ልብሶች በተመለከተ “አለባበስሽን አስተካክይ” የሚል  ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ይሰጣት እንደነበር ጠቁማለች፡፡   “አንቺ ብትለይኝ የእህትና የወንድሞችሽን ልጆች ት/ቤታቸው ሄጄ እገድላለሁ፤ አይንሽን ጐልጉዬ አወጣለሁ” በሚል ዘወትር ያስፈራራት እንደነበርም  ፀዳለች ተናግራለች፡፡ በየወሩ የምታገኘውን ደሞዝ አንድም ሳታስቀር ለባሏ ታስረክብ የነበረችው ወጣቷ፤ የትራንስፖርት ብቻ ቆርጦ ይሰጠኝ ነበር ብላለች፡፡ የቤት አስቤዛ ሸምታ እንደማታውቅ ገልፃ፤ ሸመታውን የሚያከናውነው ባለቤቷ እንደነበር ተናግራለች፡፡

የዘወትር ፀባቸው መነሻ ቅናት እንደነበር የምትናገረው ፀዳለች፤ ሞባይል ቢኖረኝም ከእሱ ስልክ ውጪ ማንሳትም ሆነ መደወል እንደትችል ገልፃለች፡፡ በምትሰራበት የዳሸን ባንክ ጐዳ ቅርንጫፍ በየወሩ የስራ ልውውጥ እንደሚደረግ የምትናገረው ፀዳለች፤ ጥር 28 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀድሞው ዳታ ወደ ኮምፒውተር የማስገባት ሥራዋ ተቀይራ ካውንተር ላይ በቴለርነት እንድትሰራ ከአለቃዋ ትዕዛዝ እንደደረሳት ጠቁማ ጉዳዩን ለባለቤቷ ስታማክረው ግን መብሸቁን ገልፃለች፡፡ “በመስታወት ውስጥ ሆነሽ ለመታየት ነው“ በሚል የቅናት ስሜት ተቃውሞውን በመግለጽ ካውንተር ላይ አልሰራም ብላ ለአለቆቿ እንድትነግራቸው ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ሰጣት፡፡በነጋታው ከስራ ወጥታ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ ቤቷ የደረሰችው ፀዳለች፤ መጀመሪያ ያገኘችው ባለቤቷን ነበር፡፡ የሁለት አመት ልጃቸውን አቅፎ የነበረው መሰለ፤ ልጁን ለሠራተኛው ይሰጥና ልጅቷን እንደያዘች አቮካዶ ገዝታ እንድትመጣ ሠራተኛዋን ያዛታል፡፡ የቤት ሠራተኛዋም ህፃኗን አቅፋ ትወጣለች፡፡ ሠራተኛዋ እግሯ እንደወጣ መሰለ ለሚስቱ ጥያቄ ያቀርባል “ያልኩሽን ለአለቃሽ ነገርሽ? ፀዳለችም፤ “ዋናው አለቃዬ ባለጉዳይ ስለበዛበት ለምክትሉ ነግሬው በተመደብሽበት ቦታ መስራት አለብሽ ብሎኛል” በማለት መልስ ሰጠች፡፡ ባለቤቷም በቁጣ ስሜት “እንዴት በዛሬ ቀን ባለጉዳይ በዛ!” ይልና በቦክስ ይላታል፡፡ የተለመደው ድብደባ ነው ብላ አስባ ነበር፡፡ ድብደባው እያየለ ሲመጣ ግን ከወትሮው የከፋ መሆኑን ተገነዘብኩ ትላለች፡፡ በሰነዘረባት ተደጋጋሚ ቦክሱ አይኖቿ እንዳበጡ የምትናገረው ወጣቷ፤ ስለት ይዞ እንደተጠጋት ገልፃለች፡፡ ራሷን ለመከላከል መታገል ጀመረች፡፡ የሷ ትግል ግን ባለቤቷ ያሰበውን ከመፈፀም አላገደውም፡፡ ጡቷንና እጇን ከነከሳትና ደጋግሞ በቦክስ ከመታት በኋላ አይኗን በስለቱ ወግቷታል፡፡ በደረሰባት ጥቃት ብዙ ደም እንደፈሰሳት የገለፀችው ፀዳለች፤ ራሷን ስታ እንደነበርና የነቃችው በላንድማርክ ሆስፒታል ውስጥ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ባሏ ጉዳቱን ካደረሰ በኋላ የሞተች መስሎት ጥሏት ጠፍቷል፡፡ እስከትላንት ድረስም አልተያዘም ብላለች - ተጐጂዋ፡፡ በተሰነዘረባት ተደጋጋሚ ቦክስ የአፍንጫዋ አጥንት በመሰበሩ ከፍተኛ ደም በአፍና በአፍንጫዋ እየፈሰሰ ሲሆን የህክምና ባለሙያዎች ሊረዷት እንዳልቻሉ ተናግራለች፡፡

ዓይኗ ከፍተኛ እብጠት ስላለው ሃኪሞች የጉዳት መጠኑን ለማወቅ እንዳልቻሉም ጠቁማ፤ ከአንድ ሳምንት በኋላ እንድትመለስ ተነግሯት ወደ ቤቷ መመለሷን ገልፃለች፡፡ በወንድሟ ቤት ተኝታ ጉዳትዋን ስታስታምም የቆየችው ፀዳለች፤  በአፍንጫዋ የሚፈሰው ደም ባለመቆሙ ትላንት ገርጂ ወደሚገኘው ካዲስኮ ጠቅላላ ሆስፒታል መወሰዷን ቤተሰቦቿ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የተጐጂዋ ሁለቱም ዓይኖች ማየት እንደማይችሉ ታውቋል፡፡ “ነጭ ነገር ብቻ ነው የሚታየኝ” ብላለች - ፀዳለች፡፡

 

 

Read 23218 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 12:36