Saturday, 05 March 2016 11:11

የመጨረሻው ቃለተውኔት

Written by  ደራሲ፡- ፍ ሬድሪክ ብራውን ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(7 votes)

(የመጨረሻው ክፍል)
    ፀጉሩን ተስተካከለ፤ መስተካከል ነበረበት። ፂሙን ተላጨ፤ አስፈላጊ አልነበረም፤ ጠዋት ተላጭቷል። አዲስ ነጭ ሸሚዝ ገዛ። ጫማውን አስጠረገ። ሱፉን አስተኮሰ። ሳሎኑን ለማሳመር ይህን ያህል ይበቃል። ጓዳውስ? ውስጡስ? ነፍሱን ለማስደሰት እራሱን ጋበዘ። ምን? ማንሀታን ቢራ። የት? የጨዋዎች መጠጥ ቤት። ስንት ጠጣ? ሶስት ብቻ። አጠጣጡ እንዴት ነበር? የጨዋ አጠጣጥ ነዋ፤ ቀስ ብሎ እያጣጣመ፤ ቢራውን እያኘከ ጠጣ። ምግብስ? ከማንሀታኑ ጋር የቀረቡለትን ሶስት ቼሪዎች በላ። (cherry፦ የፍራፍሬ አይነት ነው-ተርጓሚው)  
መስታወቱ ቆሻሻ አይደለም። ንፁህ ነው። ሰማያዊ መስታወት ነው ግን። ከይሲ አስመሰለው። መስታወቱ ውስጥ ላለው የራሱ ከይሲ ምስል፣ ከይሲ የሆነ ፈገግታ ፈገግ አለለት። እሺ ባክህ የኛ … የኛ … የኛ ምን ? ብላክሜይለር። ገፀባህሪውን እስከ ሞት ጥግ ድረስ ተጫወተው። ተዘፈቅበት። አንድ ቀን ማክቤዝን ሆነህ ትጫወታለህ።
አስተናጋጁ ላይ ይሞክረው? ይለማመድበት? አይሆንም። ከዚህ በፊት አስተናጋጆች ላይ ተለማምዶባቸዋል። መስታወቱ ውስጥ ያለው ሰማያዊ ሰውዬ ፈገግ አለለት። ፊትለፊት ባሉት መስታወቶች ውስጥም አየው። ፊትለፊት ያሉት መስታወቶችም በአመሻሹ ብርሃን ስስ ሰማያዊ ሆነዋል። ይህ ማለት ሰዓት ደርሷል ማለት ነው። ይኼኔ ቆርያኖስ የምሽት ክለቡ አናት ላይ ያለው ቢሮ ውስጥ ተሰይሞ ይሆናል።
ከቡና ቤቱ ወጣ። ሰማያዊው አመሻሽ ተቀበለው። ታክሲ ያዘ፤ ታክሲ የሚያስይዝ ተጨባጭ ምክንያት አልነበረም። የቆርያኖስ ክለብ ግፋ ቢል አስር ህንፃ ያህል ቢርቅ ነው። ፉት ቢላት ጭልጥ የምትል ርቀት ነበረች። ታክሲ ተጨባጭ ባይሆንም ሌላ ጥቅም ነበረው፣ የስነልቦና ጥቅም። ለባለ ታክሲው ያልተጠበቀ፣ ጠቀም ያለ ጉርሻ መስጠትም የስነልቡና ጥቅም ነበረው። ሰጠው። ብሉ ፍላሚንጎ፣ የቆርያኖስ አዲሱ ክለብ ገና አልተከፈተም። ሰውየው ቆርያኖስ ነዋ። ምንም የሚያስቸኩል ነገር የለም። እንግዳ መቀበያው በር ግን ክፍት ነው። ልኡል ቻርለስ ወደ ውስጥ ዘለቀ። አንድ አስተናጋጅ ጠረጴዛዎቹን እያለበሰ ነው።
“ወደ አቶ ቆርያኖስ ቢሮ ትወስደኛለህ?”
“ሶስተኛ ፎቅ ። እዚያ ጋ ሊፍት አለ።”
አቅጣጫውን ጠቆመው። ዳግም ልኡል ቻርለስን አየውና፦ “ክቡርነትዎ ።” የሚል ነገር አከለ።
“አመሰግናለሁ።” አለ ልኡል ቻርለስ ።
ሊፍቱን ተሳፈረ። ሊፍቱ ሶስተኛ ፎቅ አድርሶ፣ ጨለምለም ያለ ኮሪደር ላይ አራገፈው። ብዙ በሮች አሉ። በአንደኛው ውስጥ ብቻ መብራት ይታያል። በሩ ላይ “የግል” የሚል ፅሁፍ አለ። በቀስታ አንኳኳ። “ይግቡ” ገባ። ሁለት ግዙፍ ሰዎች አሉ፤ ካርታ እየተጫወቱ ነው። አንዳቸው፦
“እህስ?” አለ።
“ማንኛችሁ ነው ቆርያኖስ?”
“ለምን ፈለከው?”
“ይኸው ካርዴ።” ላናገረው ሰው ካርዱን አቀበለ። ልኡል ቻርለስ ሰዎቹን አያቸው፤ ሁለቱም ኒክ ቆርያኖስ ነገር አይመስሉም። ቀልቡም በእርግጠኝነት ነግሮታል። “አቶ ቆርያኖስን የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርግለት ተውኔት ጋር በተያያዘ ላናግረው እንደምፈልግ ትነግርልኛለህ?”
ያናገረው ሰውዬ ካርዱን ተመለከተ። “እሺ።” የያዛቸውን መቆመሪያ ካርዶች አስቀመጣቸው። የውስጠኛውን ቢሮ በር ከፍቶ፣ ወደ ሌላ ክፍል ዘለቀ። ከአፍታ ቆይታ በኋላ ተመልሶ መጣ። “ግባ።” አለው። ልኡል ቻርለስ ገባ። ኒክ ቆርያኖስ፣ ከጥቁር እንጨት የተሰራውና በጌጣጌጦች የተዋበው ጠረጴዛ ላይ ፣ የተቀመጠውን ካርድ እያየ ነበር ። ቀና አለ፦
“ፉገራ ነው?” ጠየቀ።
“ምኑ ነው ፉገራ?”
“ተቀመጥ። ፉገራ ነው ወይስ የምር ሰር ቻርለስ ሀኖቨር ግሪሻም ነህ ? ማለቴ፣ ያ ማለት ልኡል ማለት ይሆናል፤ እንዲያ አይደል አንዴ? የምር ልኡል ነህ?”
ልኡል ቻርለስ ፈገግ አለ።
“ከዚህ በፊት እንዳልሆንኩኝ ለማመን ቃላት አባክኜ አላውቅም ነበር። አሁን ለማመን ሳይረፍድ ይቀራል? ሞኝነትስ አይሆንም? ለማንኛውም ግን ብዙ ሰዎችን በቀላሉ ለማግኘት አግዞኛል።”
ኒክ ቆርያኖስ ሳቀ።
“ምን እንዳልክ ገብቶኛል። ምን እንደምትፈልግም መገመት እችላለሁ። ጀማሪ ተዋናይ ነህ። ልክ ነኝ?”
“ተዋናይ ነኝ። አንድ ተውኔት በገንዘብ እንደምትደግፍ ወሬ ደርሶኛል። ወላ የተውኔቱን ረቂቅ  አንብቤያለሁ። ሪክተርን ሆኜ መጫወት እፈልጋለሁ።”
ኒክ ቆርያኖስ ደበረው።
“ሪክተር- ተውኔቱ ላይ ያለው ብላክሜይለር ነው አይደል?”
“ነው።” ልኡል ቻርለስ እጆቹን ከፍ አደረጋቸው። “እባክህ ገና ካሁኑ ገፀባህሪውን አትመስልም እንዳትለኝ። እውነተኛ ተዋናይ ማንኛውንም ነገር መምሰል፣ ማንኛውንም ነገር መሆን ይችላል። ብላክሜይለር መሆን እችላለሁ።”
“ትችል ይሆናል። ግን ተዋናይ የምመለምለው እኔ አይደለሁም።”
ልኡል ቻርለስ ሳቀ። ቀስ እያለ ፈገግታውን ፊቱ ላይ አስረጀው። አስረጅቶ ገደለው። ቆመ። በሁለት እጆቹ የኒክን ከጥቁር እንጨት የተሰራ ጠረጴዛ ተደገፈ። ሳቀ። ይኸኛው ሳቅ ሌላ ሳቅ ነው። ድምፁ ቀዝቃዛ ፣ ክርር ያለ እና እንከንየለሽ ነው። እንዲህ አለ፦
“ስማ ወዳጄ ፣ እንዲሁ ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ ወደ ጎን ልትገፋኝ ፣ ገሸሽ ልታደርገኝ አትችልም። ከምትገምተው በላይ ብዙ አውቃለሁ። ማስረጃ ማቅረብ አልችል ይሆናል። ፖሊሶቹ ግን ይችላሉ። የት ግድም መመልከት እንዳለባቸው መጠቆም ብቻ ነው ከኔ የሚጠበቀው። ዎልተር ደኖቫን። ወዳጄ ይህ ስም ምን ያስታውስሀል? ወይም ሴፕቴምበር አንድ የሚሉት ቀን? ወይም ወደ ብሪጅፖርት ከሚወስደው መንገድ መቶ ሜትር ያህል ወጣ ብላ፣ በስታንፎርድና በብሪጅፖርት አማካይ ላይ ያለች ቦታ? እንዴት ነው?”
“ይበቃል። ይበቃል።” አለ ኒክ። በቀኝ እጁ አውቶማቲክ ሽጉጥ አለ። በጣም ጥቁር ነው። በጣም ያስጠላል። በግራ እጁ ዴስኩ ላይ ያለውን መጥሪያ እየደወለ ነው። ልኡል ቻርለስ ሀኖቨር ግሪሻም አውቶማቲኩን አየው። አውቶማቲክ ሽጉጡ ብቻ አይደለም፤ ሁሉም ነገር ታየው። ሞትን አየው። ለአፍታ ተሸበረ። ሽብሩ በኖ ጠፋ። አሁን ለጉድ ተገረመ። ለጉድ። እንከንየለሽ ስራ ነው። እስከ መጨረሻዋ ዐረፍተነገር ድረስ በድንቅ ሁኔታ የታቀደ ነው። “እንከንየለሹ ወንጀል” ወላ በግልፅ ነው ማስታወቂያ የተሰራለት።
ሰው መገመት ያቅተዋል? አንዲትም ክፉ ነገር አልገመተም ነበር። ሰው ትንሽ እንኳን አይጠራጠርም? ይህቺን ታህል ጥርጣሬ አልመጣለትም። ዋይን ካምፕቤል እንዴት አይመረው? እንዴት አያንገሸግሸው? እስከ መቼ ነው የማንንም ብላክሜይለር ተሸክሞ የሚኖረው? እስከ መቼ ነው ደም የሚታለበው? ትንሽ ናት እኮ? ትንሽስ ብትሆን ስንት አመታት ሙሉ? በአለም ላይ ካሉት ምርጥ ፀሀፊተውኔቶች አንዱ በእንዲህ አይነት ድንቅ ድርሰት ከችግሮቹ አንዱን ቢያስወግድ ብዙ ይገርማል? አይገርምም። እጅግ ረቂቅ ።እጅግ ቀላል።
እንዲህ ነው የሆነው፦ ዋይን የኒክን የወንጀል ድርጊት በሆነ መንገድ አውቋል። ከዛ ለልኡል ቻርለስ ብቻ ባዘጋጀው የተውኔቱ ረቂቅ የኒክን ወንጀል ፅፎ አስገብቷል። ምን ነበር ያለው ዋይን? “የገፀባህሪውን ንግግር በለው፤ እባክህ … ”
ዋይን ሌላም ነገር አውቋል፤ ልኡል ቻርለስ አሳልፎ እንደማይሰጠው አውቋል። አሁን፣ ቃታ ከመሳቡ በፊት ባለችው ቅፅበት እንኳ፣ ልኡል ቻርለስ፦ “ዋይን ይህንን ነገር ያውቃል። ይህ ሁሉ የሱ ሴራ ነው። የኔ አይደለም።” ማለት ይችላል።
ያን በመናገር ግን ምንም አያተርፍም፤ ህይወቱን ማዳን አይችልም። አሁን አውቶማቲክ ሽጉጡ ልብወለዱን፣ ወደ እውን ወለድነት ይቀይረዋል። እውነቱን ተናግሮ ካምፕቤልን ይዞ ወደ መቃብር መግባት ይችላል። የራሱን ህይወት ግን ማትረፍ አይችልም። ጠፍቶ ማጥፋት ብቻ ነው የሚችለው። ይህ ዋይን የሚባለው ሰውዬ፣ እጅግ በጣም ጠንቅቆ ነው የሚያውቀው። ልኡል ቻርለስ እውነቱን በመናገር ምንም የማያተርፍ ከሆነ አሳልፎ እንደማይሰጠው አውቋል። ለጉድ ይገርማል። ማንም፣ ማንንም እንዲህ አብጠርጥሮ አውቆ አያውቅም። እጆቹን ከዴስኩ ላይ አነሳ እና ቀጥ ብሎ ቆመ። እጆቹን በጥንቃቄ በጎኖቹ አሳርፎዋቸዋል። ሁለቱ ወጠምሻዎች መጥተዋል።
ኒክ እንዲህ አለ፦
“ፔት፣ ከሸራ የተሰራውን የፖስታ ማስቀመጫ ጆንያ ከመሳቢያው ውስጥ አምጣ። እና ደግሞ መኪናው በእንግዶች መግቢያ በር ፊትለፊት በኩል ነው የቆመው?”
“አዎ፤ አለቃዬ።” ለአንዳቸው እጅ ነስቶ ከበሩ ጀርባ ሄደ።
ኒክ አይኑንም ሆነ ቀዝቃዛውን አፈ ሙዝ ከልኡል ቻርለስ ላይ አልነቀለም። ልኡል ቻርለስ ፈገግ አለለት።
“ውለታ ልጠይቅ?” ብሎ ጠየቀ።
“ምን?”
“ሚጢጢ ውለታ። ሊደረግልኝ ከታቀደው በተጨማሪ አነስ ያለ ውለታ ነው የምጠይቀው። ሰላሳ አምስት ሰከንድ ይሰጠኝ።”
“እ?”
“ብዙ ጊዜ ሰዓት እየያዝኩ አረጋግጬያለሁ። ያን ያህል ነው ርዝመቱ። አብዛኞቹ ተዋናዮች በሰላሳ ሰከንድ ይሉታል፤ በጣም ያፈጥኑታል። እያወራሁ ያለሁት፣ ምንም ጥርጥር የለውም፣ ዘመን አይሽሬ ስለሆነው የማክቤዝ ንግግር ነው። አሁኑኑ ከምትገድለኝ ከሰላሳ አምስት ሰከንድ በኋላ ልትገድለኝ ትፈቅዳለህ ? ሰላሳ አምስት ሰከንድ ብቻ?”
የኒክ አይኖች የበለጠ ጠበቡ።
“ያልከው አልገባኝም። እጆችህን ፊትለፊት አድርጋቸውና ይታዩኝ እንጂ ለሰላሳ አምስት ሰከንድ ጣጣ የለም።”
ልኡል ቻርለስ እንዲህ አለ፦
“የነገ ውሎ፣ የነገ ውሎ፣ የነገ ውሎ …”
ከወጠምሾቹ አንዳቸው ተመልሶ መጣ። ከሸራ የተሰራ ነገር ይዟል።
“ሰውየው አስቸጋሪ ነው እንዴ?” ብሎ ጠየቀ።
“ዝም በል።” አለ ኒክ።
አንዳቸውም አላቋረጡትም። ሁሉም በትእግስት ነበር የሚያደምጡት። ሰላሳ አምስት ሰከንድ በጣም ብዙ ነው።
“…ኸረ ከቶውን ቅሪ
አንች ንፉግ የእድሜ ጭላንጭል፣
የምትንቀሳቀሽ ጥላ
የሰው ሕይወት፣ የሰው እድል …
ቅሪ፣ ከቶውን ቅሪ፣
ሞያ እንዳነሰው ተዋናይ
ተታትሮ፣ ተፍጨርጭሮ፣
ተርበትብቶ መድረኩ ላይ
ለብልጭታ ብቻ እሚታይ
ወዲያው በቅፅበት ለመጥፋት
እንደማያዛልቅ ሲሳይ …
አዬ የሰው ልጅ ሕይወት
ጅል የተረተሸ ተረብ ነሽ፣
ከንቱ ጫጫታና ሁከት
ቋሚ ትርጉም የሌለበት።” (*******)
ጨረሰ ። ረዥም ፀጥታ ሆ ።
በአክብሮት፣ በትንሹ ጎንበስ ብሎ እጅ ነሳ። ለተመልካቾች የቀረ ነገር እንደሌለ ማሳወቁ ነበር። የኒክ ጣት ቃታውን አጠበቀ። የአድናቆት ጭብጨባው ጆሮ ያደነቁራል።
(የእንግሊዝኛው ርዕስ፦ Good Night, Good Knight)
 (***)    Ah, with the Grape my fading life provide... (ኦማር ኸያም)
(****)    A Hair perhaps divides the False and True (ኦማር ኸያም)
በመጀመሪያ ለጋሽ ተስፋዬ ገሠሠ ያለኝን አክብሮትና አድናቆት መግለፅ እወዳለሁ። ለጥቆም ምስጋናዬን ማቅረብ እሻለሁ። ከዚህ በታች ያለችውን የኦመር ኻያም ሩባያት የጋሽ ተስፋዬን ትርጉም ለልቦለዱ ለመጠቀም ስጠይቃቸው መልካም ፈቃዳቸውን ለግሰውኛል። አመሰግናለሁ አቦይ ተስፋዬ ። እድሜ ከጤና ጋር ይስጥልኝ ብያለሁ።
(*****) After a momentary silence spake
Some Vessel of a more ungainly Make:
‘They sneer at me from leaning all awry:
What! Did the Hand then of the Potter Shake?
(የዚህ ትርጉም የተወሰደው፦ መልከአ ዑመር፤ የዑመር ኻያም ሩብ አያቶች፤ በተስፋዬ ገሠሠ፤ 1987 ዓ.ም፤ ኢትዮጽያ መጻሕፍት ድርጅት።)
(******)Tomorrow, and tomorrow, and tomorrow,
Creeps in this petty pace from day to day,
To the last syllable of recorded time;
And all our yesterdays have lighted fools
The way to dusty death. Out, out-
(የዚህ ትርጉም የተወሰደው፦ ማክቤዝ፤ ፀጋዬ ገብረ መድህን፤ ፲ ፱ ፶ ፬ ዓ.ም. ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ)
(*******)…Out, out brief candle!
Life’s but a walking shadow, a poor player
That struts and frets his hour upon the stage
And then is heard no more; it is a tale
Told by an idiot, full of sound and fury,
Signifying nothing.
(የዚህ ትርጉም የተወሰደው፦ ማክቤዝ፤ ፀጋዬ ገብረ መድህን፤ ፲ ፱ ፶ ፬ ዓ.ም. ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ)



Read 2792 times