Print this page
Saturday, 27 February 2016 12:20

የመጨረሻው ቃለተውኔት

Written by  ደራሲ፡- ፍ ሬድሪክ ብራውን ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(5 votes)

(ካለፈው የቀጠለ)
ልዝብ ፈገግታው ፊቱ ላይ እንዳለ፣ መልሱን አንስቶ ከቡና ቤቱ ፊት ለፊት፣ በሩ አጠገብ ወዳለው የስልክ ቁምሳጥን ሄደ። የዋይን ካምፕቤልን ቁጥር ደወለ።
“ዋይን? ቻርለስ ግሪሻም ነኝ።”
“አቤት?”
“ቢሮህ መጥቼ ላገኝህ ፈልጌ ነበር?”
“ይሄውልህ ግሪሻም ስማኝ፤ ተጨማሪ ገንዘብ ከሆነ የምትፈልገው የለም። ከሶስት ቀናት በኋላ የተወሰነ ገንዘብ ይላክልሀል። ባለፈው ተስማምተሀል፣ ድብን አድርገህ ተስማምተሀል፤ በመደበኛነት ያንን ያህል ገንዘብ የምሰጥህ ከሆነ አንተ …”
“ዋይን፣ ገንዘብ አይደለም። ተቃራኒውን ነው ወዳጄ። እንዲያውም ገንዘብ ከማውጣት ያድንሀል።”
“እንዴት?” ቅዝቅዝ ያለ ድምፅ ነው። ጥርጣሬ በሽ ነው ድምፁ ውስጥ።
“ለአዲሱ ተውኔትህ ተዋናዮች ትመለምላለህ። አውቃለሁ፤ አውቃለሁ፤ ቀጥታ ምልመላውን አንተ እንደማታደርግ አውቃለሁ። ግን አንዲት ቃል ካንተ፣ አንተ አንዲት ቃል ብቻ ብትል ዋይን፣ የሆነች ክፍል እንድጫወት ያደርጉኛል። ወላ ዝም ብሎ፣ አልፎ ሂያጅ ገፀባህሪ እንኳ ለምን አይሆንም። የፈለገው ይሁን። በዚህ ከተባበርከኝ ሁለተኛ አላስቸግርህም።”
“ተውኔቱ እስኪያልቅ ድረስ ብቻ ነው የማታስቸግረኝ?”
ልኡል ቻርለስ ጉሮሮውን አፀዳ። እያዘነ እንዲህ አለ፦
“አዎ። ተውኔቱ እስኪያልቅ ድረስ ብቻ ነው የማላስቸግርህ። ያንተ ተውኔት ግን ለረዥም ጊዜ መድረክ ላይ የመቆየት እድል አለው፣ ዋይን።”
“ቃለተወኔቱን አጥንተህ ሳትጨርስ፣ በስካር ምክንያት እንደማትባረር እርግጠኛ ሁን።”
“በስራ ላይ እያለሁ አልጠጣም። ጨርሶ። የሆነች ቦታ ብትፈልግልኝ ምን ትሆናለህ? በኔ ይሁንብህ አላሳፍርህም። መተወን እንደምችል ታውቃለህ። በብቃቴ ትተማመናለህ አይደል?”
“አዎ።” የቂም ይሁን የቅሬታ ጉርምርመታ ነገር አለው ድምፁ። የፈለገ ይኑረው። ዋናው መልሱ ‘አዎ’ መሆኑ ነው። ቀጠለ ዋይን፦ “መልካም እንግዲህ። ሌላው ቢቀር ላንተ የምሰጠውን ገንዘቤን እንደማተርፍ ነግረኸኛል። እንዴት አይነት ዘናጭ መከራከሪያ መሰለህ፤ እሱ እራሱ አንድ መደራደሪያ ሆኖልሀል። አስራ አራት ተዋናዮች ናቸው የሚመለመሉት። እና እኔ ይመስለኛል …”
“አሁኑኑ መጣሁ፣ ዋይን። እና አመሰግናለሁ። እጅግ አመሰግናለሁ።”
የህዝብ ስልክ ቁምሳጥኑን ለቆ ወጣ። ቅዝቅዝና ጥርት ያለው አየር ተቀበለው። ወደ መድረክ መመለሱን በማስመልከት የፍንጥር ለመጠጣት እንዳይወሰወስ ፈራ። እዚህ ጋ እራሱን አስተካከለ፦ ከጠጣም የሚጠጣው ወደ መድረክ መመለሱን በማስመልከት አይደለም። ‘ምናልባት ወደ መድረክ ሊመለስ መቻሉን’ በማስመልከት ነው መሆን ያለበት። ውሉ አለየም ገና። ቁርጡ አልታወቀም። ዋይን ካምፕቤል ትብብር አድርጎለትም ላይሳካ ይችላል።
ወደ የምድር ውስጥ መተላለፊያው እየሄደ ትንሽ ተንቀጠቀጠ። ጃኬት መግዛት አለበት ። ከሚቀጥለው ወር … ከሚቀጥለው ወር … ከሚቀጥለው ወር … ምንድነው የሚባለው? ዳረጎት። በሚቀጥለው ወር ከዋይን ካምፕቤል ከሚቀበለው ዳረጎት ተበድሮ ጃኬት መግዛት አለበት። ቅዝቃዜው እየከፋ መጣ። በጣም ተንቀጠቀጠ። የምድር ውስጡን መተላለፊያ አቋርጦ ወደ ዋይን ቢሮ አመራ። የዋይን ቢሮ ይሞቃል። የዋይን አቀባበል ግን ቀዝቃዛ ነበር። ዋይን፣ ያለበት  ተጎልቶ ዝም ብሎ አየው።
በመጨረሻም እንዲህ አለ፦
“ገፀባህሪውን አትመስልም፣ ግሪሻም። ኩነኔ ይሉሀል ይሄ ነው፤ ነገርዬውን አትመስልም። አስቂኝ ነገር ነው።”
ልኡል ቻርለስ እንዲህ አለ፦
“ለምን አስቂኝ እንደሆነ አላውቅም። እንዲሁ በተፈጥሮ ሁኔታ፣ ገፀባህሪውን መምሰል አለመምሰል ይህቺን ታህል ለውጥ አያመጣም። ሜክአፕ የሚባል ነገር አለ። መተወን የሚባል ነገር አለ። እውነተኛ ተዋናይ የትኛውንም ገፀባህሪ መምሰል ይችላል።”
ዋይን፣ ትዝብት ላይ በሚጥል ሁኔታ የታፈነ ሳቅ ሳቀ። አንዲህ አለ፦
“አስቂኝ እንደሆነ አልታወቀህም፣ ግሪሻም። ነው ግን። አንተ ልትሞክራቸው ትችላለህ ብዬ ያሰብኳቸው ሁለት ክፍሎች አሉ። አንደኛው በቃ ዝም ብሎ፣ አልፎ ሂያጅ ገፀባህሪ ነው። ሶስት ቦታዎች ላይ ብቻ በጣም አጫጭር ወሬዎች ይኖሩሀል። ሌላኛው …”
“አቤት?”
“አስቂኝ ነገር ነው ግሪሻም። ተውኔቴ ላይ ብላክሜይለር አለ። ኩነኔው እዚህ ጋ ነው፤ አንተ እልል ያልክ ብላክሜይለር ነህ ። ባለፉት አምስት አመታት እኔ ነበርኩ ‘ሳሳድግህ’ የነበርኩት። ኖርክብኝ።”
ልኡል ቻርለስ፦ “ድርጊቴ አግባብና ምክንያታዊ ነው። ፍላጎቶቼ መጠነኛ ናቸው። አንድም ቀን ከፍ አድርጌያቸው አላውቅም።” አለ።
“የብላክሜይለሮች ቀንደኛ ተምሳሌት ነህ፣ ግሪሻም። እንከን አይወጣልህም። የሚያክልህ የለም። በእውኑ አለም አንተን መሳይ ሰው መኖሩን ማወቅ አዝናኝ ነገር ነው ፤ እውነቴን ነው የምነግርህ። ታላቁ ፌዝ ምን መሰለህ ? በኔ ተውኔት ላይ አንተ ብላክሜይለሩን ሆነህ እንድትጫወት መፍቀድና ተውኔቱ መድረክ ላይ እስከሚቆይ ጊዜ እኔ፣ ላንተ ብላክሜይል አለመክፈሌ ነው። ተውኔቱ ይከፍልሀል። ብዙ ድርሻ ያለው፣ ጎልቶ የሚታይ ረዳት ገፀባህሪ ነው። ከኔ ከምታገኘው የሚበልጥ ክፍያ ታገኛለህ። ግን …”
“ግን ምን?”
“አትመስልም። አንተ ብላክሜይለር ከመሰልክ፤ እኔ ድራሼ ይጥፋ። እንደ ብላክሜይለር አሳማኝ ገፀባህሪ አይወጣህም። ሽቁጥቁጥ ነህ። በዚያም ላይ ሰውን ብላክሜይል ስታደርግ ሀፍረት ሊገልህ ነው የሚደርሰው። አትንገረኝ፤ አውቃለሁ፤ አውቃለሁ፤ ሆድህንና መጠጥህን የሚያስችል ስራ ቢኖርህ፤ ወይም ሁለቱን የምትሸፍንበት ምንም አይነት አማራጭ ቢኖርህ ነገርዬውን እንደማታደርግ አምናለሁ። እኔ ተውኔት ውስጥ ያለው ብላክሜይለር ጨካኝና አይበገሬ ነው። እንዲያም ነው መሆን ያለበት። ግድ ነው። የአንተ ቢጤውን ብላክሜይለር ሰዎች አምነው አይቀበሉም፣ ግሪሻም።”
“እድሉን ስጠኝ ፣ ዋይን ። እስኪ እሱን ክፍል ላንብበው።”
“ትንሿን ክፍል እንድትጫወት ብንስማማ ይሻለናል። አልፎ ሂያጅ ገፀባህሪ ቢሆንም እቀበላለሁ ብለሀል። እሱኛው ይሻላል። ተቀባይነት የምታገኘው ልሙጡን ገፀባህሪ ብትጫወት ነው። መሰሪና ጨካኝ አትመስልም።”
“ላንብበው። ቢያንስ ላንብበው።”
ዋይን፣ በምን ቸገረኝ ትከሻውን ነቀነቀ። ጠረጴዛው ጥግ ጋ የተቀመጠ የተጠረዘ ረቂቅ ጠቆመው። ጥራዙ ከዋይን ይልቅ ለልኡል ቻርለስ ይቀርባል። “እሺ እንግዲህ ገፀባህሪው ሪክተር ይባላል። ያንተ ታላቁ ትእይንት፣ ረዥሙና መሳጩ ንግግር ሁለት ገፅ ያህል ይረዝማል። የመጀመሪያው ገቢር፣ ትእይንት አንድ፣ የጀርባ ገፅ ጀምሮ አለልህ። በል ጀምር ፤ አንብብልኝ።”
የልኡል ቻርለስ ጣቶች በጉጉት፣ በስሱ ተንቀጠቀጡ፤ የመጀመሪያውን ገቢር፣ ትእይንት አንድን አገኘው። ገለፀ። “መንፈሱ እንዲገባኝ፣ በመጀመሪያ ለራሴ ላንብበው፣ ዋይን።” ዘለግ ያለ ንግግር ነው። በፍጥነት፣ ሁለት ጊዜ አነበበው። ቀጨም አደረገው። የራሱ አደረገው። አደገኛ ሸምዳጅ ነው። ረቂቁን አስቀመጠ። ውቃቢው እስኪመጣለት ትንሽ አብሰለሰለ።
ፊቱ ቀዝቃዛና የማይበገር ሆነ። አይኖቹ ቆባቸውን ገርበብ አድርገው ለበሱ። ቆመ። ዴስኩን በእጆቹ ተደገፈ  የዋይንን አይኖች በአይኖቹ ቆንጥጦ ያዛቸው። ንግግሩ እንደ ዶፍ ወረደ። ድምጹ ስለት አለው፤ እንደ ብረት ይቀዘቅዛል፤ በድን ያደርጋል።
ዋይን፣ እየሰማው አይኖቹ እየፈጠጡ መጡ። ተዋናይነትን ለምታፈቅረው የልኡል ቻርለስ ነፍስ ይህ ጥዑም የመንፈስ ምግብ ነበር። ዋይን እንዲህ አለ፦ “ድራሼ ይጥፋ ብዬ እምላለሁ፤ መተወን ትችላለህ። መልካም እንግዲህ፣ ይህን ገፀባህሪ እንድትጫወት እተጋለሁ። ውስጥህ ያለ አይመስለኝም ነበረ። አለ። እየጠጣህ ጉድ እንዳትሰራኝ እንጂ …”
“አልጠጣም።”
ልኡል ቻርለስ ተቀመጠ። ንግግሩን ሲያደርግ እርግትና ቅዝቅዝ ብሎ ነበር። በትንሹ ተንቀጠቀጠ። መንቀጥቀጡ እንዲታይበት አልፈለገም። ዋይን፣ የመጠጥ ሱስ ወይም ህመም ነው ብሎ ሊያስብ ይችላል። ጉጉትና ወደር የሌለው ደስታ አንደሆነ ላይገባው ይችላል። አዲሱ ህይወት ‘አሀዱ’ ተብሎ ሊቆጠር ነው። የዳግም ማንሰራራቱ ተስፋ እውን መሆን ሊሆን ይችላል። ይህቺን ቅጽበት ምን ያህል በተስፋ ሲጠብቃት እንደኖረ ማሰቡ ይቀፋል። ምርጥ ረዳት ተዋናይ ሆኖ ሊጫወት ነው፤ ለዚያውም የዋይን ካምፕቤል ተውኔት ላይ፤ የዋይን ተውኔቶች ደግሞ መድረክ ላይ ብዙ የሚቆዩ አይነት ናቸው። የስኬት መንገድ ተጀመረ ማለት አይደል? ጥያቄ የለውም። ፕሮዲዩሰሮች ሊያዩት ይጀምራሉ። ከዚያ በኋላ ሻል ያለ ገፀባህሪ ይጫወታል። ከዚያ በኋላም ሌላ ሻል ያለ ገፀባህሪ ይጫወታል። ከዚያ … እያለ ይቀጥላል።
እራሱን እያሞኘ እንደሆነ ታውቆታል። ተሰፋ ግን የምር ውስጡ አለ። የደስታው መጠን አይነገርም። እንዲህ በሀይለኛው የሚያሰክር መጠጥ የትኛውም መሸታ ቤት ውስጥ የላቸውም። በደስታ ሰክሯል፤ እልል ያለ ስካር።
ኸረ እንዲያውም የሼክስፒር ስራዎች ዳግም ሲመደረኩ የመተወን እድል ሁሉ ይኖረዋል። ሼክስፒር ሁሌም ደግሞ ደጋግሞ እንደተመደረከ ነው። የሼክስፒርን አብዛኛዎቹን ዋነኛ ገፀባህሪያት በደንብ ያውቃቸዋል። ሸምድዶዋቸዋል። የተወነው ግን ጥቃቅንና አነስተኛ ገፀባህሪያቱን ነው። ማክቤዝ፣ አቢይ ገፀባህሪ ቢሉ ማክቤዝ ነው፣ የማክቤዝ ያ ወደር የሌለው ንግግር …
“ሼክስፒርን ብትሆን ምኞቴ ነበር፣ ዋይን። የፃፍከው ተውኔት ደግሞ-ማክቤዝ። ማክቤዝ ውስጥ ብዙ ድንቅ ነገሮች አሉ። እጅግ የተዋቡ ነገሮች አሉልህ ። ይህን ስማማ፦
    የነገ ውሎ ፣ የነገ ውሎ ፣ የነገ ውሎ
    ከቀን ወደ ቀን ይሳባል
    በእድሜ ንፉግ ጀርባ ታዝሎ
    እስከ መጨረሻይቱ የጊዜ ቀነ ቀጠሮ
    ትላንትናን ፣ ትላንት በስቲያን
    ለጅሎች ጥርጊያ አሳምሮ
    ወደ ሞት ትቢያ ይሸኛል
    ዛሬ ፈጥሮ ነገ ቀብሮ ።
    ኸረ ከቶውን ቅሪ …” (******)
ዋይን ተቀበለው፦
“ ‘አንቺ ክፉ የእድሜ ጭላንጭል’ … ወዘተርፈ። ምንም ጥርጥር የለውም፤ ወብ ነገር ነው። እኔም ሼክስፒርን ብሆን ምኞቴ ነው፣ ግሪሻም። ስሰማህ ለመዋል የሚያስችል ጊዜ የለኝም ግን። ሌሎች ብዙ ስራዎች ይጠብቁኛል።”
ልኡል ቻርለስ በረዥሙ ተነፈሰና ቆመ። ማክቤዝ አጀግኖታል። መንቀጥቀጡ አሁን የለም። “አንተ ብቻ አይደለህም፤ ሁሉም ሰዎች ለመስማት የሚሆን ጊዜ የላቸውም። መልካም እንግዲህ፣ ዋይን። እጅግ በጣም አመሰግናለሁ።”
“አንዴ ቆይ። አወራርህ ተዋናዮችን የምመለምላቸው እኔ እንደሆንኩና ኮንትራቱን አስፈርሜህ የጨረሰን አስመሰልከው። እኔ የጀመሪያው መሰናክል ነኝ። የመጀመሪያውን መሰናክል ብቻ ነው ያለፍከው። ዳይሬክተሩ ነው ተዋናዮችን የሚመለምለው። ምልመላው ላይ እኔና ቆርያኖስ ምክር እንለግሳለን። ተስማምተን እናፀድቃለን ። እስካሁን ዳይሬክተር አልቀጠርንም። ዲክሶን የሚሆን ይመስለኛል። መቶ በመቶ እርግጠኛ አልሆንም ገና ።”
“እሱን ላናግረው ? በትንሹ አውቀዋለሁ።”
“እምምም-እስካሁን ቁርጥ ያለ ውሳኔ የለም። አንተን ወደ እሱ ብልክህ ፣ እሱን እንደምንቀጥረው እርግጠኛ ይሆንና ብዙ ገንዘብ ሊጠይቀን ይችላል። ያን ያህል ውድ ዳይሬክተር ነው እያልኩ አይደለም። ኒክን ማናገር ትችላለህ፤ ገንዘብ የመደበው እሱ ስለሆነ የተዋናዮች ምልመላ ላይ ተሰሚነት ይኖረዋል።”
“እሱን አናግረዋለሁ በቃ፣ ዋይን።”  
ዋይን የኪስ ቦርሳውን አወጣ።
“ይኼውልኽ፣ ሃያ ዶላር ነው።” አለ፦ “አቋምህን መላ አበጅለት። ፀጉርህን ተስተካከል። ፂምህን ተላጭ። ፀዳ ያለ ሸሚዝ ልበስ። ሱፍህ ለክፉ አይሰጥም፤ ትንሽ ብትተኩሰው ሸጋ ነው። እና ምን ይሆናል መሰለህ …”
“አቤት?”
“ሀያ ዶላሩ ስጦታ አይደለም። በሚቀጥለው ወር ከምሰጥህ ላይ ይቆረጣል።”
“አሪፍ ውል ነው። ጋሽ ቆርያኖስን እንዴት ልቅረባት? ገፀባህሪውን በደንብ መተውን እንደምችል ላሳያት? ልክ ላንተ እንዳሳየሁኝ?”
ዋይን ካምፕቤል አገጠጠ።
“የገፀባህሪውን ንግግር በለው፤ እባክህ፤ ልክ ለኔ ባልክልኝ ቅላፄ፣ በለው፤ ምላስህ ላይ ነው ጨዋታው፤ ያንተ ቢጤ ተዋናዮች እንደሚያደርጉት እንደ ተራ ወሬ አትድፋው፣ ለዚህ ለዚህ ማንኛውንም ለፍላፊ መንገደኛ ተዋናይ ማድረግ ይቻላል። አየር አታላምጥ። ሼክስፒርን ማነብነብ እኔም እችላለሁ።”
“እንዴት የሚለው ይለፈን።” ልኡል ቻርለስ ሳቅ አለ፦ “እልፍ አእላፍ ምስጋና፣ ዋይን ነብሴ። ደህና ሁን።”
(ይቀጥላል)

Read 2886 times