Saturday, 18 February 2012 11:50

የላሊበላው የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ነቢይ መኰን ነቢይ መኰን
Rate this item
(2 votes)

ይምርሃነ ክርስቶስን ጐበኘን!

ላሊበላ የማር አገር ነው፡፡ ማር ካለ ጠጅ አለ - ብርዝም፣ ደረቅም! ይህንኑ ልናይ አመሻሽ ላይ አራት ሆነን እንወጣለን፡፡ ሁለቱ ወጣቶች አብረውን ናቸው፡፡ ቀጭኑ ወጣት “ምንም ብቀጥን ጠጅ ነኝ” የሚባል ዓይነት ልጅ ነው፡፡ ብዙ አድባራትንና ገዳማትን ከዚህ በፊት እንደጐበኘ ከንግግሩ ለማወቅ ይቻላል፡፡ እንደወጣን፤ “ትላንት ያየነው ጠጅ ቤት (ብርዝ ቤት) እንሂድ እንዴ?” አለ፡፡ “ኧረ መሽቷል!” እዚሁ ግድም እንፈልግ” አለ ሌላው ጐልመስ ያለው ወጣት፡፡ “ታሪካዊ - አመጣጡ ወደ ኢትዮጵያ የሚገርም ዓይነት ልጅ ነው፡፡ ኢራቅ፣ ባግዳድ፣ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የነበረ’ኮ ነው” አለኝ ወጣቱ፤ ጐልማሳውን ሲገልፀው፡ታሪኩን ወደፊት እንመለስበታለን፡፡ አሁን ወደ ጠጅ ቤታችን እንሂድ፡፡ በውይይት ያፀደቅነው፣ “ካረፍንበት ት/ቤት ቅጽር ግቢ አካባቢ ቢሆን ይሻላል፡፡ መሽቷል” የሚለው ነበር፡፡

“ለምን አገሬውን አንጠይቅም?” አለ ቀጭኑ ወጣት፡፡ “አይጠፋም ጠጅ ቤት”

“ይሻላል” አልኩኝ፡፡ ለብርዝ ቤት መንገድ መሪ ያስፈልገዋል፡፡

አንድ ሰው ከመንገድ ዳር አገኘንና፤

“እዚህ አካባቢ ጠጅ ቤት የት ይገኛል?” አልነው፡፡

“ሁለት ቤት አለ፡፡ አንደኛው ስትመለሱ ይጨልምባችኋል፤ መንገዱ ያስፈራል እንጂ ጥሩ ጠጅ አለው፡፡ ሌላው ትንሽ ቁልቁለት (አዘቅት ነው ነገሩ) አለው እንጂ እዚች ጋ ነው፡፡ ኑ ላሳያችሁ” አለና እሺም ሳንለው ቀደመ፡፡ የደግ አገር ነው” አልኩኝ በሆዴ፡፡

መንገዱን አሳየንና መታጠፊያው ጋ ሲደርስ፤

“በዚህች ቆልቆል በሉ፡፡ ቁልቁለቱን ስትጨርሱ፣ የጠጅ ቤቱ በር ላይ ደረሳችሁ ማለት ነው”

“እግዜር ይስጥልን፡፡ እዚሁ አካባቢ አይደለህ?”

“አዎን ነኝ፡፡” አለ፡፡

ዝርዝር ፍራንክ ስለሌለን ስንመለስ ልንሰጠው ነው፡፡ በስንት ሰዓት እንደምንመለስ የሚያውቀው ግን ጠጁ ብቻ ነው!!

ቁልቁለቱ ቁልቁለት አደለም አዘቅት ነው፡፡ በዛ ላይ ያንሸራትታል፡፡

“ዕውነተኛው ገደል ግቡ ይሄ ነው፤ አዲሳባ ስንቀልድ ኖረን” አልኩኝ፡፡

የጠጅ ቤት መግቢያ እንዲህ ካስቆለቆለ ወደገዳማቱ ሲኬድ አለ የሚባለው ዳገት - ቁልቁለትማ እንዴት ሊያደርገን ይሆን?

እየተደጋገፍን ገደሉን ጨርሰን ዕውነትም ጠጅ ቤቱ አፍ ጋ ደረስን፡፡ ትልቅ ግቢ ነው፡፡ ከዋናው በር እስከ ቤቱ ርቀት አለ፡፡ ገባን፡፡

“ቁጭ በሉ፡፡ ቁጭ በሉ፡፡” አሉን ባለጠጅ ቤቱ አፍጋ ደረስን፡፡ ትልቅ ግቢ ነው፡፡ ከዋናው በር እስከ ቤቱ ርቀት አለ፡፡ ገባን፡፡

“ቁጭ በሉ፡፡ ቁጭ በሉ፡፡” አሉን ባለጠጅ ቤቷ፡ እናታችን ነው የመሰሉን፡፡ ሣሎንና ጓዳ ይታያል፡፡ ሳሎኗ ጠባብ ናት፡፡ አስተናጋጇ የእማማ ልጅ ጠይም ቆንጆ ልጅ ናት፡፡ ወጣቶቹ ዐይናቸውን ያሳረፉባት መሰለኝ፡፡ ከዛ እማማ አሉ፡፡ እኛ አራት ነን፡፡ ሌሎች ቀድመውን የገቡ ሦስት ወጣቶች አሉ፡፡ አለቀ፡፡ ሣሎኗ ጢም ብላ ሞልታለች፡፡ ቀድሞ እንደሚተዋወቅ ሰው ነው ጨዋታችን፡፡

“ብርዝ ይሁን ደረቅ?” አሉ እማማ፡፡ ቃናቸው “ጊዮርጊስ ነው ሜታ?” አይነት የአዲሳባ ትዕዛዝ አቀባበል ነው፡፡

“ብርዝ፣ ብርዝ…” አልን፡፡

“ብርዝ ሆድ ይነፋል” አለች አንደኛዋ፡፡

“ግዴለም ሎሚ እንጨምቅበታለን” አሉ እማማ፡፡ ሎሚ ብርዝ ውስጥ እንደሚገባ እንደምናውቅ ነው የገመቱት፡፡

“ይሄ የመጀመሪያ ትምህርታችን ነው” አልኩኝ፡፡

ተቀዳ፡፡ ሎሚ ተጨመቀበት ብርሌው ውስጥ፡፡ በጣም ጣፋጭ የሎሚ ቃና ያለው ብርዝ ሆነ፡፡ መኮምኮም ስንጀምር “ራት ብሉ” አሉን፡፡ “የቆየ ደግነት ከየት መጣ?” አልን፤ መጠጥ የሚሸጥበት ቤት እንደቡና ቁርስ ራት ብሉ የሚባልበት ዘመን እንደ ቀይ ቀበሮና ኒያላ ብዥ ብዥ የሚል ትዝታ ነው፡፡ ወጣቶቹማ ያን ዘመን ሊያስቡትም አይችሉ፡፡

“ኧረ እማማ እራት አያስፈልግም” አለች አንዷ፤ ኪሣራውንም አስባ ነው፤ ይሉኝታም ነው፡፡

“ኧረ ምን ይላችኋል? የላሊበላ በረከት ነው” አሉና መልስም ሳይጠብቁ ለሁላችንም ሳህን አደሉን - እማማ፡፡

ገረመኝ፡፡ በዕውነት፤ እንዲህ ያለ ደግነት ካየን ዘመን አልፎታል!

እንጀራ በፆም ወጥ በላን፡፡ ጠጁን ቀጠልን፡፡

ሲመሻሽ ወጣንና ዳገቱን በድግፍግፍ ወጣነው፡፡ አጭር ነው፤ ግን ቀጥ ያለ በመሆኑ የኋሊት ይጐትታል፡፡ የጠጅ ቤት መንገድ መሪያችን የለም፡፡ ወደ ማደሪያው ሄዷል ማለት ነው፡፡

መኝታችን ዘንድ ስንደርስ፤

“አንድ ቤተ - ክርስቲያን፤ 42 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ያለ ነገ ጠዋት እንጐበኛለንና በ7 ሰዓት ተነሱ” አሉ አባ፡፡

“አይሆንም፡፡ ምን ያጣድፈናል፡፡ በጣም ሌሊት ሆነ” አለ ሰው፡፡ በመጨረሻ ከንጋቱ 10 ሰዓት ተወሰነ፡፡

ሰው ብዙ የተኛ አይመስልም፡፡ በ10 ሰዓት ተሳፍሯል አውቶብሱ ላይ፡፡ ኮረኮንች መንገድ ነው፡፡ በፀሎት ጀመርነው፡፡ በመዝሙር አጀብነው፡፡ መንገድ ቀጠልን፡፡ 11 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ ጐማ ተበላሸ፡ ቆምን፡፡ ቆምን፡፡ ቆምን… ታታሪው ሹፌር ከሌላ አውቶብስ ዕቃ ለምኖ ተውሶ የሚጠብቅና የሚላላውን ይሠራል፡፡ “ጐማ ብቻ አይደለም ሌላም ችግር ነበር፡፡ አሁን እያለቀ ነው ግቡ” አሉ አባ፡፡

12 ሰዓት ከ25 ደቂቃ መኪናችን ተንቀሳቀሰ፡፡ ዕልል ተባለ!

ወደ ይምርሃነ ክርስቶስ ልንገሠግስ ነው ማለት ነው፡፡ ብልብላ የምትባል ትንሽ ከተማ ስንደርስ ወደ ቀኝ ታጠፍንና ቀጠልን፡፡ አሁን መንገዱ ላይ ከሩቅም ከቅርብም የአውቶብሶች ሰልፍ እናይ ጀመር፡፡ ጥቂት እንደሄድን መኪናችን ቆመ፡፡

ሹፌሩ - “ትራፊክ በዝቷል፡፡ በእግር ትሄዳላችሁ? ወይስ ቀለል እስኪል እንጠብቅ?”

ከፊሉ - “በእግር እንጀምረው” አለ፡፡ ከፊሉ “ኧረ በጣም ሩቅ ነው፤ በእግር አይሞከርም” አለ፡፡ የተጣደፈው ከመኪና ወርዶ መቋሚያውን እየያዘ በእግር መንገድ ጀመረ፡፡ ሌላው ቁጭ አለ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ሹፌሩ መጣ፡፡

“መጠጋት ይቻላል፤ ስላሉ እንንቀሳቀስ” አለ፡፡

ደስ አለን፡፡ መኪናው ተንቀሳቀሰ፡፡ በጣም ረዥም መንገድ ነው፡፡ ሰው ያን ሁሉ መንገድ እንዴት ሊዘልቀው ነበር? በእግር መንገድ የጀመሩትን ጫንናቸው፡፡

“ይሄን ሁሉ መንገድ እንዴት ሊወጡት ነበር?” ስል ጠየኩ፡፡

“ዕምነቱ ነዋ” አሉ አንዲት መነኩሲት፡፡ “እምነቱ መቀነት ነው፡፡ ወኔ ነው፡፡ ጉልበት ይሆንሃልኮ!” አሉ፡፡

በመጨረሻ እዋናው ቦታም ባይሆን መኪናችን የሚቆምበት ቦታ ደረስን፡፡ ያም ሆኖ ይምርሃነ ክርስቶስ ገና ነው፡፡ ደክሞናል፡፡ ግን መንገዱን ማሸነፍ ግድ ነው፡፡ ከእኛ ጋር የምትጓዝ አንዲት ከአውስትራሊያ የመጣች ልጅ አለች፡፡ መንገድ አገኘሁዋት፡፡ መንገዱን ጥቂት አብረን ለመጓዝ ጣርን፡፡

“እዚህ ቦታ መጥተሽ ታውቂያለሽ?”

“አላውቅም የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው”

“አያልቅም፤ አይደል?”

“You see it’s visible, but unreachable (ይታያል፣ ግን አይደረስበትም)

“ዋናው ጉዳይ እሱ መሰለኝ፡፡ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው - ይል የለ? ይሄኛው ደግሞ ቢያዩም አይደርሱበትም፤ ነው መሰለኝ” ተሳሳቅን፡፡

“ከየት ነው የመጣሽው - የውጪ ትመስያለሽ?”

“ከአውስትራሊያ”

“እዚያ ብዙ ቆየሽ?”

“4 ዓመት”

“ከመጣሽ ቆየሽ?”

“ሁለት ሣምንቴ ነው”

“የእኛ ሰው ኮሙኒኬሽን አይገርምሽም? እዚች ጋ ነው ይሉሻል - ሁለት ሰዓት ልትጓዢ ትችያለሽ”

“እሱንማ ተወኝ - በጭራሽ ለግምት አይመችም”

እንዴት እንደተለያየን ሳላውቅ ከላይ የሚወርደውም፤ ከታች የሚወጣውም ሰው ዋጠን፡፡ ደክመን ደክመን በድንጋይ ከተሠራውና ወደ ይምራህነ ክርስቶስ ወደሚያደርሰው፣ ቀጭን፣ ጠመዝማዛ የደረጃ መንገድ ደረስኩኝ፡፡

“ሞተን ሞተን ደረስን” አሉ አንድ ሽማግሌ፡፡

“ኧረ ዋናው ገነትም እንደዚህ አይርቅም” አለ አንድ የደከመው ጐረምሣ፡፡

“እዚያ ስትደርስ ደግሞ ዋናው ገነት እንደዚህ ቅርብ አደለም ትላለህ” አሉት መነኩሲቷ፡፡

ወጥተን ወጥተን ከዋሻው ፍልፍል የይምርሃነ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ደረስን፡፡

ስለይምርሃነ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የሰማሁት፣ ያየሁትንና ያነበብኩትን ትንሽ ልተርክላችሁ:-

የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ሕንፃ ቤተክርስቲያን በሰሜን ወሎ፣ በላስታ ወረዳ ከቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት በሰሜን አቅጣጫ የመኪና መንገድ ከመሠራቱ አስቀድሞ በነበረው የእግር መንገድ ከሆነ፤ ከላሊበላ መዳጌ፣ ከመዳጌ ደጐሳይ ይምርሃነ ክርስቶስ ቢያንስ 5 ሰዓት ቢበዛ 6 ሰዓት የሚወስድ ሲሆን ወደ ቤተክርስቲያኑ ሲቀርቡ እስከ ቤተክርስቲያኑ 1.381 ኪ.ሜ በሆነው በሀገር በቀል ፅድና ወይራ የተሸፈነውን የቤተክርስቲያኑን አፀድ መሀል ለመሀል አቋርጠው ከሄዱ በኋላ ይገኛል፡፡

በመኪና ከሆነ ግን 42 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከላሊበላ ወደ ሰቆጣ በሚወስደው የመኪና መንገድ 30 ኪ.ሜ ተጉዘው ቀሪውን 12 ኪ.ሜ ብልብላ ከምትባል አነስተኛ ከተማ ወደ ምሥራቅ (ወደቀኝ) አቅጣጫ ከተጓዙ በኋላ የሚገኝ ታላቅ የቅድስና ሥፍራ ነው፡፡ ወደ ህንፃ ቤተክርስቲያኑ ልንደርስ 6 ኪ.ሜ ሲቀረን ዛዚያ የሚባለውን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስን ልዩ ሥፍራ እናገኛለን፡፡ ደኑንና የአካባቢውን የተፈጥሮ አቀማመጥ በሚገባ ለማየት በሰሜን አቅጣጫ ከሚገኘው “ሴኮ” ጋራ ከሚባለው ተራራማ ቦታ ላይ ለሄደ ከማነፁ በፊት 22 ዓመት ድንኳን ተክሎ የቀደሰበት ቦታ ነው፡፡ ዛዚያ (ዟዟ) ማለት ዟ ብሎ መቀመጥ ወይም ተዝናንቶ መቀመጥ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስና አገልጋዮቹ ከብዙ ድካም በኋላ ዕረፍት ስላገኙባት፤ በሥጋና በነፍስ ዕረፍተ አገኘንባት ዟ ብለን ተቀመጥንባት ሲሉ ዛዚያ (ዟዟ) ብለዋታል፡፡ የአካባቢው ህዝበ ክርስቲያን እስከ ዛሬም ይዘክርበታል፡፡

የቅድዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የአሠራር ጥበቡ በአካባቢው ከሚገኙት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፤ አድባራትና ገዳማት የተለየ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የተንፀባረቀበት ነው፡፡ ከፍታው ከወለሉ እስከ ጣራው 5.9 ሜትር ገደማ ነው፡፡ ከዕፅዋትና ወጥ ከሆኑ ከከበሩ ድንጋዮች በተለያዩ የመስቀል ቅርፃ ቅርፅ የተዋቡ 26 መስኮቶች አሉት፡፡ 22ቱ በውስጥ የሚከፈቱ ናቸው፡፡ 4ቱ የማይከፈቱ ድፍን ናቸው፡፡ ሦስት ወጥ የሆኑ የዕፅዋት (የእንጨት) በሮች አሉት፡፡ አሠራሩ በጭቃ በተያያዙ፣ መጠናቸው በተስተካከለ ደቃቅ ጥቁር የዐለት ድንጋዮች የተገነባ ሲሆን ድንጋዮቹ ከላይና ከታች በጥንቃቄ በተጠረቡ ለስላሳ ሰፋፊ እንጨቶች የተያያዙ ከመሆናቸውም በላይ ኖራ መሰል በሆነ ነገር የተለሰኑ ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያኑ በውስጡ ሶስት ቤተ መቅደሶች አሉት፡፡ የመካከለኛው መንበር ያለበት መቅደስ የሰማዕቱ የቅዱስ ቂርቆስና የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ የመታሰቢያ ታቦታት፤ ከበስተቀኝ ደግም የቅድስት ድንግል ማርያም፤ ከበስተግራ የቅዱስ ጊዮርጊስና የመልዐኩ የቅዱስ ሩፋኤል የመታሰቢያ ታቦታት ያሉባቸው መቅደሶች ይገኛሉ፡፡ ቤተክርስቲያኑ በማዕዘን በማዕዘኑ ላይ በምሥራቅና በምዕራብ 4 ፎቆች አሉት፡፡ ወለሉ ደግሞ ቀላል ነገር ግን ለስላሳና ጠንካራ በሆነ ጥርብ ድንጋይ የተነጠፈ ሲሆን የውስጠኛው ጣራ ከእንጨት፣ በተለያየ የመስቀል ቅርፅ የተሠራ ነው፡፡ ዐምዶቹ (የጣራው ተሸካሚ ምሰሶዎች) በጥንቃቄ በተጠረቡ ጠንካራ፤ ለስላሳና ከባድ በሆኑ የከበሩ ድንጋዮች የተገነቡ ናቸው፡፡ በስተምሥራቅ በኩል ወጣ ያለ ክብ ጉልላት የሚመስል ጣራ አለው፡፡

የመቅደሶቹ ጣራዎች ሳይቆጠሩ የቅድስቱ ውስጣዊ የጣራ ክፍል በስምንት የተከፈለ ሲሆን፤ ሰባቱ የሰባቱ ሰማያት ምሳሌ ነው፡ የመካከለኛው (ስምንተኛው) ለሰባተኛው ሰማይ ለፅርሃ አርያም በድጋሚ ምሳሌ ሆኖ ይነገራል፡፡ በድጋሚ ምሳሌ መሆኑ ከሰባቱ ሰማያት ከፍ ያለውና የመጨረሻው ሰማይ ፅርሐ አርያም ነው፡፡ ሰባቱ ሰማያት የሚባሉት 1. ኤረር 2. ራማ 3. ኢዮር 4. ሰማያዊት ኢየሩሳሌም (መንግስተ ሰማያት) 5. ሰማይ ውዱድ 6. መንበረ መንግሥት 7. ፅርሐ አርያም

በቅዱሳቱ የጣራ ውስጣዊ ገፅታ በመካከለኛው ክፍል ላይ የተንጠለጠሉ ዕንቁዎች ይታያሉ፡፡ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ከሠፋፊ እንጨቶች የተሠሩ ሁለት ጥንታዊ ሣጥኖች ይገኛሉ፡፡ የቤተ መቅደስ መገልገያ ዕቃዎችን በማስቀመጫነት የሚያገለግሉ ናቸው፡፡

በዕቃ ቤትነት ማለትም ንዋየተ ቅድሳትን ለማስቀመጥ ይምርሃነ ክርስቶስ ያነፀው ህንፃም አለ፡፡ ያሠራር ጥበቡ ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስና የአገልጋዩ የክርስቶብነ መቃብሮች ሌሎቹ ዋሻ ውስጥ የሚገኙ ዕይታዎች ናቸው፡፡ በዚሁ ዋሻ የቅዱሳን አፅም ያረፈበት የክብር ቦታ አለ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች የእንኑም መቃብር በማለት ይጠሩታል፡፡ እንኑም ማለት እናንቀላፋ ነው በግዕዝ፡፡ ምነው ቢሉ “ኖመ” ማለት ተኛ፤ አንቀላፋ፤ ሞተ ማለት ነውና፡፡

በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ልዩ ልዩ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ የህንፃውን ያህል ዕድሜ ያላቸው የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ መቋሚያና ካባ፣ ከሰማይ የወረደለት መስቀልና ፅዋ፣ ገድለ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ በዘመነ መንግሥቱ አዋጅ ሲነገርበት የነበረ ነጋሪት፣ የጳጳሳት መቋሚያዎች እንዲሁም የእጅ መስቀሎች፣ በርካታ የብራና መፃህፍት፣ ትንንሽ መንበር መሰል የሆኑ ከአንድ ወጥ እንጨት ድንቅ በሆነ ጥበብ ተቀርፀው የተሠሩ መቀመጫዎችና የንዋየ ቅድሳት ማስቀመጫዎች ከሕንፃ ቤተክርስቲያኑ ግንባታ የተረፉ የእንጨት ቅርፃ ቅርፅ፣ ከታላላቅ የቀድሞ መኳንንት፣ ለምሳሌ ከነራሴ ወሌ የተሰጡ፣ መስቀሎችና በርካታ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ይምርሃነ ክርስቶስ ቅዱሱና ንጉሡ ማን ነበር?

(ይቀጥላል)

 

 

Read 3128 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 11:55