Print this page
Saturday, 18 February 2012 11:27

“25 የስኬት ቁልፎች” ምን ይላል?

Written by  ሶፎንያስ
Rate this item
(45 votes)

አንድ ሰው በትርፍ ጊዜው ብዙ ሙታን ወደተቀበሩበት የመቃብር ስፍራ ሄዶ በሰዎች መቃብር ላይ የተጻፉትን ጽሑፎች በማንበብ ሳይ ሳለ፣ በአንድ ሰው መቃብር ላይ አንድ ግር የሚል ጽሑፍ አነበበ፡ ጽሑፉ በ”30 ዓመቱ ሞተ፣ በ60 ዓመቱ ተቀበረ” ይላል፡ ጽሑፉ ግር ብሎት ቆሞ ማሰላሰል ጀመረ፡፡“የስኬት ጥማት ባይኖር መጓጓትና መነሳሳት የተሰኙ አስገራሚ ስሜቶች ትርጉም ያጣሉ፡፡ የምንጓጓውና የምንነሳሳው ለምንድን ነው? ስኬት ነው ብለን ወዳሰብነው ደረጃ ለመድረስ አይደለምን? በተቃራኒውም፤ እንደተስፋ መቁረጥ፤ ጭንቀትና ሀዘን የመሳሰሉትም ጠንካራ አሉታዊ ስሜቶቻችን ከስኬት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ተስፋ መቁረጥ የሚባለው ስሜት እንዲኖር በቅድሚያ ተስፋ ያደረግነው ነገር ሊኖር የግድ ነው፡፡ ተስፋ ያደረግነውን ነገር አጓጊነት የወሰነው ለመድረስ የቃጣንለት ነገር እንደ ስኬት ስለሚቆጠር ነው፡፡”

ከላይ የሰፈረው ሀሳብ የተወሰደው በቅርቡ ከታተመው “25 የስኬት ቁልፎች” ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ራስ አገዝ (Self-help) ወይም አነቃቂ (motivational) ከሚባሉ መጽሐፎች አንዱ ነው፡፡

ራስ አገዝ ከሚባሉት መጻሐፍት አብዛኞቹ በውጪ ደራሲያን የተደረሱ ናቸው፡፡ እነዚሁ መጽሐፍት በተለያዩ ተርጓሚዎች ወደ አማርኛ ተተርጉመው አንብበናል፡፡

በውጪ ፀሐፍት የለመድናቸው እንደዚህ ዓይነት መጽሐፍት በእኛው ጸሐፍት መጻፍ መጀመራቸው አንድ ለውጥ ነው፡፡

መጽሐፉ የተጻፈው በዶ/ር ኢዮብ ማሞ ነው፡፡ ዶ/ር ኢዮብ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን Organizational management የማስትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በEducation እና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በ Leadership እንዳገኙ ከመጽሐፉ ጀርባ የሰፈረው መረጃ ያመለክታል፡፡ ዶ/ሩ “አመራር A to Z” የተባለ ሌላ መጽሐፍ ያላቸው ሲሆን ይሄ ሁለተኛ መጽሐፋቸው ነው፡፡

በዚህ “25 የስኬት ቁልፎች” ሲሉ በሰየሙት መጽሐፋቸው ለስኬት ወሳኝ ናቸው ያሉዋቸውን ነጥቦች በሀያ አምስት ምዕራፎች ከፍለው አቅርበዋል፡፡

“የነፋሱ ግፊያ ወደ ከፍታዬ ያወጣልኛል” በሚለው ምዕራፍ ለስኬት የተግዳሮት አስፈላጊነት ምን ያህል እንደሆነ ጽፈዋል፡፡ ተግዳሮትና ስኬትን በንስርና ንፋስ ንፅፅር አቅርበውልናል፡፡

“ንስር የሚጋፋው አንድ ብቸኛ ተግዳሮት ነፋስ ነው፡፡ የሚያስገርመው ነገር ግን ንስር ወደ ከፍታው እንዲወጣ የሚደግፈውም ያው የሚጋፋው ነፋስ የተሰኘው ነገር ነው፡፡ የንስር አቋም “የሚጋፋኝን ይህንን ነፋስ ተጠቅሜ ወደ ከፍታዬ እበራለሁ፤ የነፋሱ ግፊያ ወደ ከፍታዬ ያወጣኛል፡፡” ንስር ከሚጋፋው ብቸኛ ጠላቱ ከነፋስ ተግዳሮት ውጪ ለመኖር ቢወሰንና ያንን ጥያቄውን ተግባራዊ የሚያደርግለት ኃይል ተገኝቶ ነፋስ ከፍጥረት ክስተት ውስጥ ቢወጣለት የሚጋፋው ብቸኛ ነገር ስለተወገደለት “እፎይ” ይላል፡፡ ታሪኩ ግን እዚያ ላይ ብቻ አያበቃም፡፡ የከፍታ ህይወቱንም እዚያው ያስረክባል፡፡ ከሚጋፋው ከብቸኛ ጠላቱ ከነፋስ ውጪ ንስር ከዶሮ ተለይቶ አይታይም፡፡” (ገፅ 52)

ተግዳሮት በሌለበት ስኬት አይኖርም ነው አዝማሚያው፡፡ ስኬታማ ሰዎች ከፈተና ርቀው የኖሩ ሳይሆኑ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተው፤ በፈተና ተፈትነው ነጥረው የወጡ ወርቆች ናቸው፡፡ ወርቅ እነሱ ዘንድ የሚገኘውና ብርቅና ድንቅ የሚሆኑብንም ለዚህ ነው፡፡

ስኬታማ ሰዎች ችግሮችን እንደ ዕድሎች እንጂ እንደ ችግሮች አያዩዋቸውም፡፡ የተከፈተ በር የተከፈተ ስለሆነ ሌላ እምቅ ዕድል በውስጡ አላዘለ ይሆናል፡፡ የተዘጋ በር ግን የመከፈት ዕድልን የያዘ በረከት ነው፡ በተከፈተው በር መግባት ስኬት ሊሆን አይችልም፡፡ የተዘጋውን በር በብልሀት ከፍቶ መግባት ግን ስኬት ነው፡፡ ስለዚህ ስኬት ያለው ተግዳሮት ባለበት ነው፡፡ የንስሩ ከፍታ በሚፈታተነው ነፋስ መኖር እንደተሳካ ስኬታማነት ከችግሮት ማህፀን ይወለዳል፡፡

“የሰውን ዘር የአምፑልን ብርሃን እንዲፈለስፍ ያነሳሳው የጨለማው ተግዳሮት መሆኑን አትዘንጋ፡የበሽታው ግፊያና የስቃያችን ጥልቀት በህክምና ዛሬ የደረስንበት ደረጃ እንድንደርስ አበረታን፡፡ መራራቃችንና ለመገናኘት ያለን ናፍቆት የጫነብን የመገለል ጫና የበረራን ፈጠራና የስልክን መስመር የመሳሰሉትን ብልሃቶች ከውስጣችን ፈልቅቆ አወጣው፡፡” ይላል መጽሐፉ፡፡

“በ30 ዓመቱ ሞተ፣ በ60 ዓመቱ ተቀበረ” በሚል ርዕስ ስር በቀረበው ክፍል ባለ ራዕይ የመሆንና በዓላማ የመፅናት አስፈላጊነት ቀርቧል፡፡ ከዓላማ ውጪ የሚኖር ህይወት ከህይወት አይቆጠርም፡፡ ዓላማ ቢስ ወይም ከባለራዕይነት ወደ ዓላማ የለሽነት የመጣ ሰው ኖሯል ለማለት ከባድ እንደሆነ ያትታል - ይህ የመጽሐፉ ክፍል፡፡

“አንድ ሰው በትርፍ ጊዜው ብዙ ሙታን ወደተቀበሩበት የመቃብር ስፍራ ሄዶ በሰዎች መቃብር ላይ የተጻፉትን ጽሑፎች በማንበብ ሳይ ሳለ፣ በአንድ ሰው መቃብር ላይ አንድ ግር የሚል ጽሑፍ አነበበ፡ ጽሑፉ በ”30 ዓመቱ ሞተ፣ በ60 ዓመቱ ተቀበረ” ይላል፡ ጽሑፉ ግር ብሎት ቆሞ ማሰላሰል ጀመረ፡፡ “አንድ ሰው በ30 ዓመቱ ሞቶ እንዴት ለ30 ዓመታት ሳይቀበር ሊቆይ ቻለ?” ይህንን እያሰበ የጽሑፉን ትርጉም የሚያውቅ አንድ ሰው ደረሰ፡፡ “ምን እንደምታስብ ገብቶኛል” አለው ሃሳቡን አንብቦ፡፡

ጥያቄውን በግምት ደርሶበት ኖሮ በቀጥታ መልሱን ነገረው፡፡ “ይህ ሰው እጅግ በጣም የሚያስገርም ራእይና ዓላማ የነበረው ሰው ነበር፡፡ ብዙ ነገሮችን የመስራት እቅድ የነበረውና በዚህም ትጋቱ በሕብረተሰቡ ዘንድ እጅግ የታወቀና ለትልቅ ነገር የሚጠበቅ ሰው ነበር፡፡ ልክ 30 ዓመት ሲሞላው በተለያዩ ውጣ ውረዶች በማለፉ ምክንያት ተስፋ በመቁረጥ ዓላማውን ሁሉ ትቶ ከርታታ ሰው ለመሆን በቃ፡፡ የሚቀጥሉትን 30 ዓመታት እንዲሁ በየቦታው ሲንቀዋለል ነው ያሳለፈው፤ ካለምንም ዓላማ፡፡ የጽሑፉ ትርጉም ይህ ነው፡፡ ሰውዬው ሞተ ብለው የሚያምኑት ራእዩን በጣለበትና ጊዜውን በተራ ነገር ማሳለፍ በጀመረበት በ30 ዓመቱ ነው - በአካል ቢኖርም ሞቷል ነው አባባላቸው፡፡ ልክ በ60 ዓመቱ ታምሞ አካላዊ ሞትን ሲሞት ያን ጊዜ ተቀበረ ማለታቸው ነው”

በአካል መኖር ብቻውን ኖሯል አያስብልም ነው ነገሩ፡፡ ህያው የሚያደርገን ራእይና የመኖር ዓላማ እንጂ ቆሞ መሄድ አይደለም፡፡ ቆሞ ለመሄድ በአራት እግር ሆነ እንጂ አህያም ይሄዳል፡፡ አህያ ግን የሰውን ስራ ከማቅለሉ ውጪ የራሱ ራዕይ የለውም፡፡ ስለሌለውም የሌሎች ባሪያ ሆኖ ይኖራል፡፡ በሰው ራእይና ዓላማ የለሽ ህይወት ህይወት ሳይሆን ሞት ነው፡፡ ዓላማ አልባው ሰውም ለመቀበር ነፍሱ ከስጋው እስክትነጠል ይጠበቃል እንጂ ሙትማ ሙት ነው፡፡ ሰውን ህያው የሚያደርገው ህልሙ ነው የሚሉ ይመስላሉ ፀሐፊው፡፡ ልክ ነው! ዓላማ ያለው ሰው መሆንና በዓላማው የሚፀና ሰው መሆን ሁለት የስኬት ቁልፎች ናቸው፡፡

ስኬታማ ሰዎች ባለራዕይ ናቸው፡፡ ለራዕያቸውም ታማኝና ፅኑ ናቸው፡፡ ለፈተናም ሆነ ለየትኛውም ነገር በቀላሉ እጅ አይሰጡም፡፡ እጅ አለመስጠታቸው የህያውነታቸው ምልክት፣ የስኬታቸው ጠቋሚ ነው፡፡

በሌላው ስለ ትኩረት ወሳኝነት በሚያወራው “እንዲያይ ሳይሆን እንዲያተኩር” በሚለው ምዕራፍ ለስኬት የትኩረትን አስፈላጊነት ያትታሉ ዶክተሩ፡፡

“አንዳንድ ሰዎች የሚያስገርምን ብቃት፣ ሌላው ያላገኘውን ታላቅ እድልና የተመቻቸ ሁኔታ ይዘው ሳሉ ሲባክኑና አንድም ነገር ሳያከናውኑ ሲያልፉ የሚታየው ለምንድን ነው? የተበታተነና ትኩረቱን ያጣ ማንነት ስላላቸው ነው፡፡” (ገፅ 64)

ትኩረት ለስኬት ወሳኝ ነው፡፡ አንድን ስራ በትኩረት ካልሰሩት ስራው የተሳካ ስራ ሊሆን አይችልም፡፡

በትኩረት ራስን በየቀኑ ካላሳደጉ ስኬታማ ሰው መሆን አይቻልም፡፡ ትኩረት ቁልፍ ነው፡፡ ትኩረቱ ከተበታተነ አስር ሰው ስራ፣ ትኩረት ያደረገ ያንድ ሰው ስራ የተሻለ ነው፡፡ ትኩረት ለስራ ጥራትና ዕድገት ብቻ ሳይሆን ለራስ ዕድገት ጭምር ወሳኝ የስኬት መሳሪያ ነው፡፡

ትኩረት የሚጐድለው ሰው እንዴት ከስኬት እንደሚርቅ ለማሳየተ አንበሳን በምሳሌነት አንስተዋል - ዶክተር ኢዮብ፡፡ አንበሳ ምንም ኃያልና ብርቱ ቢሆን የእንስሳ አሰልጣኙ የአንበሳውን ኃይል የሚያሳጣበትና እራሱን ከአደጋ የሚከላከልበት መላ አለው፡፡ ባለ አራት እግር ጠረጴዛ ይዞ ወደ አንበሳው ይቀርባል፡፡ የአንበሳው ትኩረት ለምግብነት ከፊቱ ቆሞ ከሚጠብቀው ሰውዬ ይልቅ በጠረጴዛው እግሮች ላይ ይሆንና ከአንዱ እግር ወደሌላው እግር ትኩረቱ ይበታተናል፡፡

የእንስሳት ንጉሡ አንበሳ ምን የመሰለ ቀለብ ከፊቱ ቀርቦ ሳለ ትኩረት በማጣቱ ምክንያት ግዳይ ሳይጥል ይቀራል፡፡ ሰውም ልክ እንደዚህ ነው፡፡ ትኩረት ቢያደርግ ኖሮ ድል ይመታቸው የነበሩ በርካታ ነገሮችን ትኩረት በማጣት የተነሳ ድል ሳያደርግ ይቀርና በተቃራኒው በሁኔታዎች ድል ይመታል፡፡

“ታላላቅ ሰዎች አይወለዱም” በሚለው ምዕራፍ ታላቅነት ከመወለድ እንደማይመጣ እናነባለን፡፡ ታላላቅ ሰዎች አይወለዱም፤ ነገር ግን እራሳቸውን ይወልዳሉ፡፡ ስኬታማ ሰዎች አይታደሉም፤ ነገር ግን በጥረት ዕድልን ይጠራሉ፡፡ ውጤታማ ሰዎች ዕድለኛ አይደሉም፤ ነገር ግን ሰራተኛ ናቸው፡፡

መወለድና እራስን መውለድ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ መወለድ በሌላ ሰው ምጥ ወደ መሆን መምጣት ነው፡፡ ራስን መውለድ ግን ራስን አርግዞ፣ በራስ ምጥ እራስን መፍጠር ነው፡፡ የመጀመሪያው ድካም የለበትም፡፡ ሁለተኛው ግን ጥረትና ትጋትን ይጠይቃል፡፡

“አንዲትን ከብዙዎች እይታ ርቃ የምትገኝን መንደር በመጐብኘት ላይ የነበሩ ሰዎች ገና እንደደረሱ የገረማቸው የዚያች መንደር ርቀት ነው፡፡

ከዚህ በፊት ብዙ ጐብኚዎች የመጡባት አትመስልም፡፡ በዚህች መንደር በመዘዋወር እያሉ በአንድ ሜዳ ላይ የሚጫወቱትን ወጣቶች ቁጭ ብለው የሚያዩ አንድ አዛውንት አገኙና ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ እንዲህ የሚል ጥያቄ ጠየቋቸው፣ “በዚህ መንደር ታላላቅ ሰዎች ተወልደው ያውቃሉ?” ጥያቄው ግልጽ ቢሆንም፣ አዛውንቱ “ምን ዓይነት ጥያቄ ነው” በሚል እይታ ከቃኟቸው በኋላ እጅግ ቀላልና ግልጽ የሆነ መልስ ሰጧቸው፡፡ የእኝህ አዛውንት ፈጣን መልስ ጎብኚዎቹን አስገረማቸው፡፡ መልሳቸው፣ “በዚህች መንደር የሚወለዱት ህጻናት ብቻ ናቸው”፡፡ አስገራሚ መልስ!” (ገፅ 40)

ታላቅ የመሆን ድርሻ ላንተ የተተወ ነው፡፡ “የሚወለዱት ህጻናት ብቻ ናቸው፡፡” የትም መንደር ውስጥ ቢሆን ይህ የማይለወጥ እውነት ነው፡፡ ታላላቆች በታናሽነት ዘመን በትጋት ራሳቸውን ታላላቅ አድርገው ይፈጥራሉ፡፡

“25 የስኬት ቁልፎች” የተሰኘው መጽሐፍ በዚህ መልኩ የተለያዩ 25 ለስኬት አስፈላጊ ያላቸውን ነጥቦች እየዳሰሰ በ160ኛው ገፅ ላይ ያበቃል፡፡ መጽሐፉ በየጽሑፉ መሀል የሀሳቡ መደገፊያና ማጠናከሪያ የሆኑ አባባሎችን በወሽመጥነት እያስገባ ያቀረበ ሲሆን በ30 ብር ለአንባቢያን ቀርቧል፡፡ እንድታነቡት እየጋበዝኩ ነው - እግረመንገዴን፡፡

 

 

Read 18437 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 11:34