Print this page
Saturday, 20 February 2016 09:36

“እባካችሁ ፀጥታ! ዲሞክራሲ እንቅልፍ ላይ ነው!”

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(22 votes)

· ኃይሌ፤ “ዲሞክራሲ ለአፍሪካውያን ድሎት ነው” ቢልስ?
· ኢህአዴግ፤ “ዲሞክራሲ ለኛ የህልውና ጉዳይ ነው” ብሏል

  ባለፈው ሳምንት በእዚሁ ጋዜጣ፤ “መንግስት በነዳጅ ዋጋ ላይ ተገቢውን ቅናሽ አላደረገም”  በሚል ርዕስ በወጣው ዘገባ ላይ ሁለት ኢኮኖሚስቶች የሰጡት ፍፁም ተቃራኒ ትንተና በእጅጉ አስገርሞኛል፡፡ (የሮኬት ሳይንስ ትንተና እኮ አይደለም!) የነዳጅ ዋጋ ትንተና ነው! በነገራችሁ ላይ ሁለቱም ዶክተሮች ናቸው፡፡ ሁለቱም ኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚስቶች! (ገረመኝ አልኩ እንጂ አጠፉ አልወጣኝም!
አንደኛው ኢኮኖሚስት በሰጡት አስተያየት፤ ምንም እንኳን በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ቢቀንስም የኢትዮጵያ መንግሥት ከነፍስ ወከፍ ገቢ ጋር የተመጣጠነ እንጂ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ማድረግ የለበትም ሲሉ መክረዋል፡፡ (መንግስት እቺን አግኝቶ ነው!) ግን ለምን ይሆን? ምሁሩ እንደሚሉት፤ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ሲደረግ እየተረጋጋ የመጣውን የግብይት ስርዓት ሊያናጋው ይችላል፡፡
 ሁለተኛው ኢኮኖሚስት ግን ይሄን አጥብቀው ይቃወማሉ፡፡ ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ መደረጉ በምንም መመዘኛ የኢኮኖሚ መናጋት አይፈጥርም ብለዋል፤ፍርጥም ብለው፡፡ “እሾህን በእሾህ” ይባል የለ! (ምሁርን በምሁር!) ኢኮኖሚስቱ ይቀጥላሉ፡፡ የዛሬ ዓመት አካባቢ ነዳጅ በዓለም ገበያ በበርሜል ከ110 ወደ 55  ዶላር ሲቀንስ፣ በአገር ውስጥ የነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ከ20 ብር ወደ 9 እና 10 ብር መውረድ ነበረበት ያሉት እኒሁ ባለሙያው፤ አሁንም በዓለም አቀፍ ገበያ ከ30 ዶላር በታች ሲሸጥም በሃገር ውስጥ በሊትር 7 እና 8 ብር መሸጥ ነበረበት ብለዋል፡፡ (በምርጫ ከተወዳደሩ ሁለት ድምጽ አሽራቸዋለሁ!) “ነዳጅ በዓለም ገበያ በከፍተኛ መጠን ሲቀንስ በዚያው ልክ በሀገር ውስጥም መቀነስ ይገባዋል” ባይ ናቸው - (በካላንደርም በዋጋም ከዓለም ወደ ኋላ ቀረን እኮ!)
በነገራችሁ ላይ አንዳንዴ መንግስት ፈጣጣ ነው፡፡ (የየትኛውም አገር ማለቴ ነው!) የኛ አገሩ መንግስት ለምሳሌ፣ አንድ ጊዜ እንዲሁ በዓለም ገበያ ነዳጅ ቀንሶ፣ጭጭ አለ፡፡ ጋዜጠኞች ጠ/ሚኒስትሩን ጠየቋቸው፡፡ እሳቸውም፤ እስከዛሬ ነዳጅ በመንግስት እየተደጎመ ይቀርብልን እንደነበር አስታውሰው፣ይቀነስ የሚባል ከሆነ መንግስት ሌላ ጊዜም መደጎሙን እንደሚያቆም አሳስቀው ነገሩን፡፡ (መንግስት ከኪሱ አውጥቶ የሚደጉመን አይመስልም!)
ወደ ኢኮኖሚስቶቹ ልመልሳችሁ፡፡ ቆይ ግን እንዴት ነው ሁለት ኢኮኖሚስቶች በአንድ ጉዳይ ላይ እንዲህ የሚለያዩት? (“ልማታዊ” እና “ኒዮሊበራል” ኢኮኖሚስቶች ቢኖሩ ነዋ!)  የሆኖ ሆኖ በኢኮኖሚክስ እንኳን አልተስማማንም፡፡ (ፈረንጅ በሰራው ሳይንስ ማለት ነው!)  
ለእኔ መቼም… የነዳጅ ዋጋ ሲቀንስ ኢኮኖሚውን ያናጋዋል ከሚሉት ኢኮኖሚስት ይልቅ መንግስት በደፈናው የሰጠው መግለጫ ይሻለኛል፡፡ አያችሁ … መንግስት ግራ ሳያጋባን በቀላሉ እንዲህ ነው ያለን፡- “በአፍሪካ ዝቅተኛው የነዳጅ ዋጋ የኢትዮጵያ ነው” (ለምን ፔቲሽን ተፈራርመን ለኢራን መንግስት አናስገባም!) የነዳጅ ድጎማ ታድርግልና፤ለመንግስት ሳይሆን ለኛ -ለጭቁኖቹ! “ባለደብል ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት” የሚለው ስማችን ግን ድጎማውን የማግኘት ዕድላችንን ሳያጠበው አይቀርም፡፡ (መሞከሩ ግን አይከፋም!)
በነገራችን ላይ በአሁኑ ሰዓት ነዳጅ በጣም በርካሽ ዋጋ የምትሸጠው አገር ቬኔዝዌላ ስትሆን በሊትር 0.02 ዶላር ብቻ ነው፡፡ መንግስት በነዳጅ ዋጋ ላይ ድጎማ ስለሚያደርግ ቬኔዝዌላውያን መኪናቸውን በነፃ ነው የሚያሽከረክሩት ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ (ድጎማ ይሏል ይሄ ነው!) እስቲ ለጠቅላላ እውቀት ያህል የዓለም አገራትን ወቅታዊ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ እንመልከት፡፡ (መንግስታችንንም ለመታዘብ እኮ ነው!) ኩዌት -0.22 ዶላር፣ ሳኡዲ አረቢያ -0.24 ዶላር፣ አልጀርያ - 0.30 ዶላር፣ ናይጄሪያ - 0.44 ዶላር፣ ናምቢያ - 0.69 ዶላር፣ ሱዳን -0.77 ዶላር፣ ግብፅ -0.80 ዶላር፣ ጋና -0.85 ዶላር፣ ኬንያ -0.87 ዶላር … በሊትር እየሸጡ ነው ተብሏል፡፡
አንድ የፌስቡክ ጸሃፊ ዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ፍጥነት እያሽቆለቆለ፣ የኛ አገር ግን ድንቡሎ እንኳን አለመቀነሱ ቅጥል አድርጎት መሰለኝ፣ እንዲህ የሚል ማስታወሻ ፌስቡኩ ላይ አሰፈረ፡- “የኛ መንግስት ዋጋ የሚቀንሰው ነዳጅ በነፃ ሲታደል ነው” ልማታዊ መንግስታችን ግን ኩም አደረገው፡፡ በነፃ ሳይታደል ዋጋ በመቀነስ፡፡ (80 ሳንቲም ብትሆንም!)
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ ያሳየው ቅናሽ የነፃ ያህል በሉት፡፡ ይልቅስ ዋጋው አልቀመስ ያለው ምን መሰላችሁ? … ዲሞክራሲ!! በተለይ ደግሞ ለኛ ለአፍሪካውን ሰማይ ነክቶብናል፡፡ (በኃይሌ ቋንቋ “ቅንጦት” በሉት!) እናላችሁ … ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ … ሰሞኑን ከዲሞክራሲ ጋር በተያያዘ ለሰነዘረው አስተያየት የትችት ናዳ የወረደበት … ዲሞክራሲ ያለ ቅጥ  በመወደዱ ይሆን? (ጥያቄ ነው!)
ለነገሩ ኃይሌ ሁሌም ነገር ይጠናበታል፡፡ በሩጫ እንዴት 3ኛ ይወጣል ተብሎ ያልወረደበት መዓት የለም፡፡ አንድ የህንድ አትሌት በአገሪቱ ታሪክ ከ20 ምናምን ዓመት በኋላ 3ኛ ወጥቶ ለአገሩ ነሀስ በማስገኘቱ ኤርፖርት ማን እንደተቀበለው  ታውቃላችሁ? የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር! ሃይሌ ገንዘብ ላይ ቆንቋና ነው በሚልም እንደ ጉድ ተወርዶበታል (በገዛ ገንዘቡ እኮ ነው!) ደግነቱ ግን እሱም ጥኑ ነው፡፡
እስቲ አትሌት ኃይሌ “… ዲሞክራሲ ለአፍሪካውያን ቅንጦት … ነው” ሲል ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ የሰጠውን ቃለ ምልልስ ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ የወረደበትን የትችት ናዳ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንቃኘው፡፡ (ትችቶቹ በአብዛኛው ኢ-ዲሞክራሲያዊ ናቸው!) እኔ የምላችሁ … ዲሞክራሲን ለመከላከል ያህል እንኳን እንዴት ዲሞክራሲያዊ መሆን አቃተን፡፡  (ዲሞክራሲያዊነት በአንድ ጀንበር አይፈጠርም!) እናላችሁ --- ትችቶቹ ሃሳብ ላይ ሳይሆን ሰውየው ላይ ነው ያነጣጠሩት፣ ከጨዋና ምክንያታዊ አስተያየት ይልቅ ወደ ስድብና ዘለፋ ያደላሉ፡፡ ብዙዎቹ ዲሞክራሲ ለአፍሪካውያን ቅንጦት ሳይሆን መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብለው አልሞገቱም፡፡ በእርግጥ አንዳንዶቹ ኃይሌ እንዲህ ለማለት ፈልጎ ነው … በማለት ከትችት ናዳ ሊያድኑት ሞክረዋል (ባይሳካላቸውም!)
ለምሳሌ አንድ የፌስቡክ ፀሐፊ፤ “ዲሞክራሲ አፍሪካ ውስጥ አይፈቀድም ማለቱ ነው” ሲል አባባሉን በራሱ መንገድ ተርጉሞታል፡፡ ሌላ የፌስቡክ ፀሐፊ ደግሞ፤ “አፍሪካ ውስጥ ዲሞክራሲ አለ? የለም፤ ያንን ነው እሱ የገለፀው” ብሏል፡፡ (ትርጉም ከራስ ነው!) “በዚህ የግሎባላይዜሽን ዘመን ኃይሌ ይሄንን ማለት አልነበረበትም” ሲል የተቸ የግሎባላይዜሽን አቀንቃኝም ተገኝቷል፡፡  በርከት ያሉ ተቺዎች ግን “ድሮስ እሱን ማን ፖለቲከኛ አደረገው!” የሚል መረን የዘለለ አስተያየት ነው የሰነዘሩት፡፡ (ለምክንያታዊነት አለርጂክ ሆነናል!)
ህይወት የምሻው የተባለች ዝነኛ የፌስቡክ ፀሐፊ ባሰፈረችው ዘለግ ያለ ትችት፤ “እኔ የምልህ ኃይሌ፤ ለመሆኑ ዲሞክራሲን የቅንጦት ዕቃ የሚያደርግ መልካም አስተዳዳሪ እንዴት ያለ ነው? (የሚያስፈልገን መልካም አስተዳዳሪ ወይም መሪ ነው  … ስላለ ነው!) መልካምነቱስ ምኑ ላይ ነው? ነው ወይስ አንተም ያንን ‹ከዲሞክራሲ ዳቦ ይቅደም› የሚል የታከተ ክርክር ልትጀምረን ነው? … ለኮስማናው ህዝባችን ዲሞክራሲ እንደ ቦርቃቃ ልብስ ስለሚሰፋው ‹ሩህሩህ አምባገነን› (ቤኒቮለንት ዲክታተር) ይበቃዋል› ይሉት ዘፈን ልትዘፍንብን ነው … ‹አፍሪካውያን ደግሞ ዳቦ ከበሉ መች አነሳቸው?› እያልክ ልትዘባነንብን ነው?” እያለች እንደ ጉድ ትወርድበታለች፡፡ (ልብ አድርጉ! ትርጉምና ትንታኔ የኃይሌ አይደለም!)
ለዚህም ይመስለኛል … ኃይሌ ሰሞኑን ከ“ታዲያስ አዲስ” ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፤ “ሁሉም በመሰለው ይተርጉመው” የሚል ምላሽ የሰጠው፡፡ (“አደጋ አለው” አለች አዛሉ!) ከጥቂት ዓመታት በፊት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጎት አለኝ ማለቱን በማስታወስም፤ “እኔ መሪ ስሆን እንኳን ዲሞክራሲ ፍርፋሪውን እንዳትጠብቁ” --- ሊለን ፈልጎ ነው ያሉም አልጠፉም፡፡ (ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነኝ ብሎ የተመረጠ መሪ አለ እንዴ?)
በነገራችን ላይ … አትሌት ኃይሌ ከ“ታዲያስ አዲስ” ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ በፌስቡክ የተነሳውን “አቧራ” (በኢህአዴግ ቋንቋ “ብዥታ”) ያጠራዋል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ ተፈጥሮ ነበር፡፡ (እኔን አይጨምርም!) እንዳለመታደል ሆኖ ግን (“ከአያያዝ ይቀደዳል…” እንዲሉ!) ቃለ ምልልሱ ሌላ ተጨማሪ “ብዥታ” ፈጥሮ አረፈው፡፡ ጋዜጠኞቹ፤ ሀሳቡን በቅጡ እንዲያብራራ አልተመቹትም፡፡ ይልቁንም እነሱ ወደፈለጉት አቅጣጫ ሲጎትቱትና የትችት ናዳ ካወረዱበት ወገኖች ጋር ለማስታረቅ (አውቀውም ይሁን ሳያውቁ) ሲሞክሩ ነው የተስተዋለው (“ሽምግልና” በሬዲዮ ተጀመረ እንዴ?) እኔ የምለው --- የፕሮግራሙ አዘጋጆች ኃይሌን ጠየቁት ነው አዋከቡት … የሚባለው?
ደስ አለንም አላለንም ኃይሌ እንግዲህ አንዴ ተናግሮታል - “ዲሞክራሲ ለአፍሪካውያን ቅንጦት ነው” በማለት፡፡ ያ ሁሉ አቧራ የተነሳው ለምን እንደሆነ ግን አሁንም አልገባኝም፡፡ “እባካችሁ ፀጥታ!ዲሞክራሲ እንቅልፍ ላይ ነው” በሚባልበት ዘመን ላይ ነን እኮ!! እናላችሁ … ዲሞክራሲ ለአፍሪካዊው ምኑ ነው? ልንል ሁሉ እንችላለን፡፡ (የቀድሞው ጠ/ሚ፤ “የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ምኑ ነው?” ያሉት ትዝ አለኝ!)
 በነገራችን ላይ ኢህአዴግም ከአትሌት ኃይሌ ሀሳብ ጋር የሚስማማ አይመስለኝም (በመርህ ደረጃ ማለቴ ነው!) ለምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ በተደጋጋሚ፤ “ዲሞክራሲ ለእኛ የምርጫ  ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው” ሲል ሰምተነዋል!! (የሰማነው ሁሉ ግን እውነት ነው ማለት አይደለም!) በእርግጥ ዞር ይልና፤ “ዲሞክራሲ በአንድ ጀንበር የሚመጣ ሳይሆን ሂደት ነው” ይለናል - ኢህአዴግ ነብሴ፡፡ (“ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያውያን ቅንጦት ነው” የሚለው ሃሳብ ግሩም የምርጫ ክርክር አጀንዳ ይወጣዋል!)
በነገራችን ላይ በቅርቡ የሞቱት የሲንጋፖር መሪ ሊ ኩዋን ዩው፤ “ዲሞክራሲ ለታዳጊ አገራት ቅንጦት ነው” በሚል አባባላቸው ይታወቁ ነበር፡፡ በአንደበታቸው ብቻ ሳይሆን በተግባርም፡፡ የእሳቸውን ሃሳብ የሚቃወም ታዲያ እራሱን የሚያገኘው ወህኒ ቤት ነበር፡፡ እንዲያም ሆኖ አገራቸውንና ህዝባቸውን አጃኢብ ለሚያሰኝ የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግና አብቅተዋል ተብለው ይወደሳሉ - የቀድሞው የሲንጋፖር መሪ! በየጎዳናው ላይ የነበሩ ለማኞችንም አጥፍተዋል ይባላል (ሲያስፈልግ ዘብጥያ እያወረዱ ማለት ነው!)
ሰውየው የሞቱ ጊዜ ታዲያ ህዝቡ እንባ ተራጭቶ ነው የቀበራቸው፡፡ (“ሩህሩህ አምባገነን” ናቸዋ!) በቻይናም አንድ ሰሞን “ዲሞክራሲ የበለፀጉ አገራት ድሎት ነው” ማለት ፋሽን ነበር፡፡ አትሌት ኃይሌ ከ“ታዲያስ አዲስ” ጋር በነበረው የአየር ላይ ቆይታ … “30 ዓመት የገዛ መሪ በምርጫ ሲወዳደር…” ብሎ ያቋረጠው ንግግር አለ፡፡ እውነቱን እኮ ነው … አፍሪካ ውስጥ 30 ዓመት አንቀጥቅጦ የገዛ አምባገነን መሪ፣ ከስልጣን መውረድ ሲገባው በምርጫ ይወዳደራል፡፡ ሰሞኑን ራሱ የኡጋንዳው ሙሴቪኒ ከ30 ዓመት ሥልጣን በኋላ፤“ለኡጋንዳ ከእኔ ውጭ የሚሆናት የለም” ብለው የምርጫ ንግግር ሲያደርጉ ነበር፡፡ ተፎካካሪዎቻቸው ከእነ ደጋፊዎቻቸው ግን በፖሊስ እየተዋከቡ ነው፡፡ (ዲሞክራሲ ለአፍሪካ ቅንጦት ነው ድሎት?)
አፍሪካ ውስጥ አምባገነን መሪዎች የአገራቸውን ህገ-መንግስት ሰርዘውና ደልዘው የሥልጣን ዘመናቸውን ሲያራዝሙ በግላጭ አልታዘብንም?! የሱዳኑ … የኡጋንዳው … የዚምባቡዌው … የኤርትራው … የስዊዚላንዱ … መሪዎች ለስንት ዓመት ነው ሥልጣን የሙጥኝ ብለው የተቀመጡት? … 30? … 40?…. ! በአህጉረ አፍሪካ ድህነቱ … ድርቁ --- ረሃቡ … የእርስ በርስ ጦርነቱ … መቼ ፋታ ሰጥተው ያውቃሉ? ይሄ ታዲያ “ዲሞክራሲ ለአፍሪካ ቅንጦት ነው” አያሰኝም!? ወዳጆቼ … ችግሩ ያለው አትሌት ኃይሌ ጋ እንዳይመስላችሁ፡፡ እኛው ዘንድ ነው፡፡ ከተጣላንም መጣላት ያለብን ከኃይሌ ጋር ሳይሆን ከራሳችን ጋር መሆን አለበት ወይም ከአምባገነን መሪዎቻችን ጋር አሊያም ከዲሞክራሲያዊ እሴቶች ጋር ከተጣላው ባህላችን ጋር! (“አህያውን ፈርቶ…” አለ የአገሬ ሰው!) አትሌት ኃይሌ  በማህበራዊ ሚዲያው በወረደበት የትችት ናዳ ትንሽ የተደናገጠ ይመስል ነበር፡፡ ሰሞኑን ከእነሰይፉ ጋር በሬዲዮ ሲያወራ ከድምፀቱ እንደተረዳሁት፡፡ የአንዳንዶቹ ዓላማም ማስደንገጥ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በስተመጨረሻ የተናገው ነገር ግን ያጽናናል፡፡ “ሰው የተናገርኩትን እንደመሰለው ይተርጉመው … እኔም በየጊዜው አዲስ ነገር መልቀቄ አይቀርም” (ጀግና ምንጊዜም ጀግና ነው!) ለነገሩ ዕድሜውን ሙሉ ያመነበትን እየተገበረ፣ ለስኬትና ለዝና የበቃ ሰው፤የትችት ናዳ ወረደብኝ ብሎ ከአቋምና ከእምነቱ ውልፊት ሊል አይችልም!)
እኔ የምላችሁ ----- ኃይሌ ስንት ያወራንለትን ወደ ፖለቲካ የመግባት ህልሙን ከምን አደረሰው? (ሃሳቡን መቀየር መብቱ እንደሆነ አልጠፋኝም!) ለነገሩ ለጦቢያ በፖለቲከኝነቱ ከሚፈይድላት ነገር የበለጠ በኢንቨስተርነቱ ይጠቅማታል ብዬ አስባለሁ፡፡ እሱ … “ዲሞክራሲ ለአፍሪካ ቅንጦት ነው” ብሏል፡፡ እኔ ደግሞ፤ “በአፍሪካ የፖለቲካ ሜዳው ጠባብ ነው፤ናላ ያዞራል፤ጸጉር ያሸብታል፤ዘብጥያ ያስወርዳል” እለዋለሁ፡፡ (ይቅርበት እያልኩ ነው!)

Read 8237 times Last modified on Saturday, 20 February 2016 11:59