Saturday, 13 February 2016 11:59

ሀበሻ ዊክሊ ----- ከየት ወዴት?

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ለቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ከ3 ሚ. ብር በላይ በጀት ተይዟል

    አዲስ አበባ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኮከበ ፅባህ፣ የመሰናዶ ትምህርቱን ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ተከታትሏል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ፣ በኮምፒዩተር ሳይንስ በድግሪ ተመርቋል፡፡ በልጅነቱ ነፍሱ ወደ ኪነ-ጥበቡ ታደላ ስለነበር ፊልም ፕሮዱዩስ የማድረግና የመተወን ህልም ነበረው፡፡ ፓይለት ለመሆን ሁለት ጊዜ ጥረት ቢያደርግም በአንድ ሴንቲ ሜትር የቁመት ማነስ ምክንያት ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡
የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለ በተደጋጋሚ ስኮላርሺፕ ሞክሮ አሜሪካና ካናዳ ያሉ ሁለት ዩኒቨርስቲዎች ቢቀበሉትም ኤምባሲዎቹ ቪዛ አልፈቀዱለትም፡፡ በዚህ ተስፋ የቆረጠው የ28 ዓመቱ ወጣት አዶኒክ ወርቁ ፊቱንና ልቡን ሙሉ በሙሉ ወደ አገሩ መልሶ በትጋት መስራት ጀመረ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አዶኒክ ወርቁ ጋር በህይወቱና በቢዝነስ ሥራው፣ በህልሙና ራዕዩ ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ ዝነኛው ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ የሚያቀነቅንበት ኮንሰርት በጊዮን ሆቴል እንደሚያዘጋጅም አውግቷታል፡፡ እነሆ፡-  
   
    እንዴት ነው በቀጥታ ወደ ሁነት አዘጋጅነትና ወደ ቢዝነስ ስራ የገባኸው?
እኔ ኤቨንት ኦርጋናይዝ ማድረግ የጀመርኩት በ1997 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነው፡፡ ያኔ ስኩል ካርኒቫል በማዘጋጀት እና፣ ዲጄ ሆኜ እሰራ ነበር፡፡ እነዚህ በዋናነትም ባይሆን ፍላጐቶቼ ነበሩ፡፡ ቢዝነስን በተመለከተ አብዛኛው ቤተሰቤ በንግድ ስራ ላይ የተሰማራ ስለነበር ተማሪም ሆኜ ቤተሰቤን በስራ አግዝ ነበር፡፡ ሆኖም ብዙ ወደ ኪነ ጥበቡ ስለማደላ ፊልሞችን እመለከት ነበር፡፡  
ወደ ውጭ አገር የመሄድ ጉጉት እንደነበረህ ሰምቻለሁ -----
ጉጉቴ ውጭ ሄዶ ለመኖር ሳይሆን ለመማርና ቶሎ ለመለወጥ ነበር፡፡ እንደነገርኩሽ ሆሊውድ የሚሰሩ ፊልሞችን በዲሽ ላይ አያለሁ፡፡ እያንዳንዱ ዲሽ ላይ የማየውን ነገር እመኛለሁ፤ያንን ነገር ለማግኘት የግድ እዛው ቦታው መገኘትና መማር አለብኝ ብዬ አስብ ነበር፡፡ በጣም ልቤ ተሰቅሎ ነበር፡፡ ሆኖም ከአንዴም ሁለት ሶስቴ አልተሳካም፤በዚህ ምክንያት ውጭ የመሄዱን ነገር እርግፍ አድርጌ ተውኩት፡፡
ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀህ እንደወጣህ ሥራ የጀመርከው የት ነው?
ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቅሁ ወደ ቤተሰቤ የቢዝነስ ስራዎች ገባሁ፡፡ እንደ ነገርኩሽ ተማሪም ሆኜ ከቤተሰቤ ጋር በትርፍ ሰዓቴ እሰራ ስለነበር ስራውን አውቀዋለሁ፤ስለዚህ ቤተሰቤን እየወከልኩ በተለያዩ የስራ ቦታዎች ላይ ማገዝ ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያም ካሉን በርካታ እህት ኩባንያዎች “ሻካይና” በተባለው ውስጥ ማርኬቲንግ ማናጀር ሆኜ መስራት ቀጠልኩ ማለት ነው፡፡
የራስህን ኮምፒዩተር ቤት የከፈትከው መቼ ነው?
በዚያው ዓመት የ“ሻካይና” ማርኬቲንግ ማናጀር ሆኜ እየሰራሁ “አዶኒክ ኮምፒዩተር ሶሉሽን” የተባለ የራሴን ድርጅት ከፈትኩት፡፡ እንደነገርኩሽ በኮምፒዩተር ሳይንስ ነው የተመረቅሁት፡፡ እውቀቱና ክህሎቱ አለኝ፤ስለዚህ እውቀቴን ወደ ቢዝነስ መለወጥና ራሴን ማሳደግ ስለምፈልግ አብረውኝ የተማሩና ደህና ውጤት የነበራቸውን ልጆች አሰባስቤ፣ የራሴንም እውቀት ጨምሬበት ጥሩ ጥሩ ስራዎችን መስራት ጀመርን፡፡ ለምሳሌ ድርጅቱ ገና እንደተከፈተ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤትን ዌብሳይት ዴቨሎፕ አደረግን፡፡ በጣም የሚገርምሽ ብዙ ልምድ ከነበራቸው በርካታ ድርጅቶች ጋር ተወዳድረን፣ የሥራ ልምድ ሳይኖረን የከንቲባውን ጽ/ቤት ዌብሳይት መስራት ለእኔ ትልቅ ስኬት ነበር፡፡
በመቀጠል “አዶኒክ ጆብስ” የተሰኘ ብዙ ወጪ የወጣበት፣ ሥራንና ሥራ ፈላጊዎችን የሚያገናኝ ዌብሳይት ሰራን፡፡ ሥራ ፈላጊዎች ሲቪ ይዘው ገና ማስታወቂያ አንብበው ነው ስራ የሚፈልጉት፡፡ ይህን ድካም የሚቀንስ ነው፤ አዶኒክ ጆብስ ዌብሳይት፡፡ ሆኖም በወቅቱ እንዲህ አይነት ዌብሳይቶች ስላልተለመዱ እንዲታወቁ ለማድረግ ብዙ ጣርን፤ ነገር ግን አለማምደን ገቢ ለማግኘት በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ ለአንድ ዓመት በዚህ መልኩ ከሰራሁ በኋላ ፊቴን ወደ ኪነጥበብ ማዞር ፈለግሁኝ፡፡
ኢቢኤስ ላይ ሀበሻ ዊክሊ የተሰኘ የቴሌቪዥን ፕሮግራም እንደነበረህ አስታውሳለሁ፡፡ ለምን ቆመ?
ዌብሳይት የሚሰራው የኮምፒዩተር ድርጅት እንዳለ ሆኖ፣ ወደ አርቱ የመግባት ፍላጎት ቀድሞም ስለነበረኝ አመቺ ሁኔታዎችን እየጠበቅኩኝ ነበር፡፡ ኢቢኤስ መከፈቱ ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረልኝና ጥሩ ፕሮፖዛል ሰርቼ አስገባሁ፤ተቀባይነትም አገኘሁ፡፡ ሁሌም የውጭዎቹን የፊልምና የሙዚቃ ቦክስ ኦፊስ ስመለከት፣ ለምን የእኛ አገር ፊልሞችስ ቦክስ ኦፊስ አይኖራቸውም እላለሁ፡፡ በወቅቱ በእኛ አገር ቴሌቪዥንም ሆነ ሬዲዮ በስፋት የሚያወራው ስለ ውጭ ፊልሞች፣ ስለ ውጭ አክተሮች፣ ስለ ውጭ ሙዚቃ ነበር፡፡ ለምን የሀገራችን ዝነኞች (ሰለብሪቲዎች) አይወራላቸውም የሚል ቁጭት ነበረብኝ፡፡ ይህንን ለመስራት ካለኝ ጉጉት ተነስቼ ነው የፕሮግራሙን ስም ራሱ “ሀበሻ ዊክሊ” ብዬ የሰየምኩት፡፡ በፕሮግራሙ ኢትዮጵያ ውስጥ በሳምንት ውስጥ ምን ምን ኪነጥበባዊ ክንውኖች እንደነበሩ የሚጠቁሙ መረጃዎችና መዝናኛዎች ይቀርቡበት ነበር፡፡ አዳዲስ ፊልሞች፣ አዳዲስ ሙዚቃዎች፣ አዳዲስ የአገራችን ሁነቶች፣ በፕሮግራማችን ይስተናገዱ ነበር፡፡ ወቅቱ ደግሞ አሪፍ አሪፍ ፊልሞች መውጣት የጀመሩበት ነበር፡፡ እነ ፔንዱለም፣ ሂሮሺማ፣ አባይ ወይስ ቬጋስ  መውጣት ስለጀመሩ ለፕሮግራማችን ጥሩ ግብአቶች እያገኘን መጣን፡፡
ታዲያ ለምን አቆማችሁት?
እንግዲህ “ሀበሻ ዊክሊ” አቅማችንን የፈተንንበት፣ወደ መዝናኛው ኢንዱስትሪ ይበልጥ የገባንበትና ከብዙ ሰዎች ጋር የተዋወቅንበት ፕሮግራም ነው፡፡ አንደኛ እኛ የመጀመሪያዎቹ አውት ሶርስ አድራጊዎች ነን፤ ሁለተኛ ኢቢኤስ ያን ጊዜ በ2003 ዓ.ም ማለት ነው በደንብ አይታወቅም ነበር፡
እነዚህ ነገሮች ስፖንሰር ለማግኘትም ሆነ ብዙ ነገር ለመስራት ፈትነውን ነበር፡፡ የቢሮ ኪራይ ነበረብን፣ ካሜራም ተከራይተን ነበር የምንሰራው፡፡ ኤዲተርም አስቸጋሪ ነበር፡፡ በዚያ ፈተና ውስጥ የአንድ የአንድ ሰዓት 50 ፕሮግራሞችን ለአንድ ዓመት ሰራን፡፡ ስራችን ደግሞ ቲቪ ሾው አይደለም፤ ሰባት አይነት የተለያዩ ፕሮግራሞች ይቀርቡበት ነበር፡፡ የተለያዩ ፈጠራዎችን በማከል ፕሮግራሙን ለየት ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ያንን ከባድ ፈተና እየተጋፈጠን ነው የቆየነው፡፡ ቦክስ ኦፊስ ለማውጣት ሲኒማ ቤቶችን ማሳመን፣ የፕሮዲዩሰሮች ማህበራትን ማግባባት -----ስንቱ ነገር አሳልፈን መሰለሽ ቦክስ ኦፊስ የጀመርነው፡፡ ዱባይ ሳይቀር ሄደን የአመት በዓል ፕሮግራም ሰርተናል፡፡
ጥሩ እየሆንን፣ ገቢያችንም ደህና እየሆነ ሲመጣ የአንድ ዓመት ኮንትራታችን አልቆ እንቀጥላለን ብለን ስናስብ፣ኮንትራቱ ሳይታደስ ቀረ፡፡ እኛም ትንሽ ተቀይመን ስለነበር በዚያው ቆመ፡፡
አሁንም ሀበሻ ዊክሊ በሚለው ስም ነው ብዙ ስራ እየሰራችሁ ያላችሁት?
ልክ ነው፡፡ የቲቪ ፕሮግራማችን ሲቆም ስሙ በጣም ጥሩ ስለሆነ “አዶኒክ ግሎባል ኢንተርቴይንመንት” የሚለውን ወደ ሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ቀየርነውና ቀጠለ፡፡ የኩባንያው ባለድርሻዎችም እኔና ባለቤቴ ሀና ሆንን ማለት ነው፡፡
ዘንድሮ በ15 ሚ. ብር ለአዲስ ዓመት ባዘጋጃችሁት ኤክስፖ፣ “በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ” ላይ ለማስመዝገብ በሂደት ላይ የነበሩ ሁለት የፈጠራ ሥራዎችን ለእይታ አቅርባችሁ ነበር፡፡ ሂደቱ ምን ላይ ደረሰ?
አዎ፤ትልቁን ፖስት ካርድ በ50 የበሬ ቆዳ ሰርተናል፡፡ በብራና ለመስራት ስለፈለግን ነው፡፡  በሻማ ትልቁን 15 ሜትር የገና ዛፍ ሰርተናል፡፡ እኛ አዳዲስ ፈጠራዎችን የምንሰራው ስለ አካባቢ ጥበቃ፣ ስለ አየር ንብረት ለውጥ ሰዎችን ለማስተማር ነው፡፡
በላቪሲን ኤክስፖ ትልቁን የገና ዛፍ ከወዳደቁ በርካታ የውሃ ላስቲኮች ሰርተን፣ አካባቢን ከማቆሸሽ በፈጠራ ስራ ላስቲኮችን ስራ ላይ ማዋል እንደሚቻል አስተምረናል፡፡ ብዙ የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎችም ሽፋን ሰጥተውት ነበር ብዙ የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች ሽፋን ሰጥተውት ነበር፡፡ ረጅሙም ዛፍ ከሻማ የተሰራው ፀሐይ እየመታው ሲቀልጥ የዓለምን የሙቀት መጨመር ለማሳየት ነው፡፡ ፖስት ካርዱንና የሻማ ዛፉን ጊነስ ላይ ለማስመዝገብ ሂደት ላይ ነን፤ ሌሎች አሟሉ የተባልነውን ለማሟላት እየጣርን ነው፡፡
በዚህ ወር መጨረሻ ላይ በጊዮን ትልቅ የሙዚቃ ኮንሰርት ለማቅረብ ቴዲ አፍሮን አስፈርማችኋል፡፡ እስቲ ዝርዝሩን ንገረኝ ?
እንደ ሁነት አዘጋጅነታችን ትልልቅ ሥራዎችን ሰርተን ተሳክቶልናል፤እየተሳካልንም ነው፡፡ ከቴዲም ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በስራ የምንገናኝባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ እውነት ለመናገር ከቴዲ ጋር ኮንሰርት እንስራ ብለን ብዙም እቅድ ይዘንበት አናውቅም፡፡ ነገር ግን አጋጣሚው ከተፈጠረ ለምን አናደርገውም፣ ለምንስ አንሞክረውም? አልን፡፡ ምክንያቱም ጥሩ ስራ እንደምንሰራ እንተማመናለን፡፡ መጀመሪያ እርሱ አሜሪካ ስለነበረ ብዙ ጉዳዮችን ተወያይተን የጨረስነው ከባለቤቱ ከአምለሰት ሙጬ ጋር ነበር፡፡ ከዚያም ከእርሱ ጋር ተገናኘንና ተወያየን፡፡ አጋጣሚዎቹ ጥሩ ሆኑና ስምምነት ላይ ደረስን፡፡ ኮንሰርቱ የካቲት 26 ቀን የአብይ ፆም ከመግባቱ በፊት ባለው የመጨረሻው ቅዳሜ  ይካሄዳል፡፡ እንግዲህ ሶስት ሳምንት ነው የሚቀረን፡፡
በምን ያህል ክፍያ ተስማማችሁ?
ለቴዲ የምንከፍለውን ለመናገር የእሱን ይሁንታ ማግኘት አለብን፡፡ እኛ ለአጠቃላይ ፕሮግራሙ ግን ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ይዘንለታል፡፡
ዝግጅቱ እንዴት ነው ታዲያ ?
አሁን ሩጫ ላይ ነን፡፡ ምክንያቱም ጥሩ ስራ መስራት አለብን፡፡ አንዳንድ ማሟላት ያለብንን ሁኔታዎች እያሟላን ነው፡፡ እነዚህን ጥንቅቅ አድርገን ስንጨርስ ስለ መግቢያ ዋጋው፣ ስለ ክፍያው  ወዘተ----በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ እናደርጋለን፡፡
ከዚህ ቀደም የቴዲ የተለያዩ ኮንሰርቶች በተለያዩ ምክንያቶች ተሰርዘዋል፡፡ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር የወሰዳችሁት የተለየ ጥንቃቄ አለ?
እኛ እንደ ሀበሻ ዊክሊ የምንናገረው፤ቴዲ ትልቅና ተወዳጅ ድምፃዊ መሆኑን ነው፤ገበያው እንደሚፈልገው እናውቃለን፡፡ ከዚህ በፊት ስለተሰረዙት ኮንሰርቶች እያሰብን፣ ስራችንን ከመስራት ወደ ኋላ አንልም፡፡ አሁንም በተወዳጅነቱ ከአድናቂዎቹ ጋር እንዲገናኝ በእኛም በእሱም በኩል ማድረግ ያለበንን እያደረግን ነው፡፡ እስካሁን ባለውም ሂደት የገጠመን እንቅፋት የለም፡፡ ተፈራርመናል፡፡ ለአዲስ አበባ አስተዳደርም የማሳወቂያ ደብዳቤ አስገብተናል፡፡
የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ባለቤት ለመሆን መወዳደራችሁን ሰምቻለሁ፡፡ እንዴት ሆነ?
እንግዲህ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት በጣም ጥሩ የሆነ ፕሮፖዛል ቀርፀን አስገብተናል፡፡ ተፎካካሪ ከሆኑት ውስጥ እኛም አለንበት፡፡ ሀበሻ ዊክሊ ወደፊት እንደ ግብ ያስቀመጣቸው ትልልቅ ራዕዮች አሉት፡፡ አንዱና ትልቁ ራዕያችን፤ የራሳችን የቴሌቪዥን ጣቢያ መክፈት ነው፡፡ ሆሊዉድ ውስጥ ያለው የፊልም ደረጃ ወደ አገራችን እንዲመጣም እናስባለን፡፡ ከቴሌቪዥኑ ጣቢያ ሬዲዮው ስለቀደመ እድሉን ለመጠቀም ወደ ሬዲዮው ገብተናል፡፡ ብዙ ዝግጅት አድርገን ነው በውድድሩ የተሳተፍነው፡፡ ከፋይናንሱ ይበልጥ የሬዲዮ ፋይዳና ቴክኒክ ላይ ሰፊ ዝግጅት አድርገናል፡፡
ኤፍኤም ሬዲዮ ሲከፈት ያማከሩ፣ በሬዲዮ ኢንስታሌሽን ስራም ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን አዋቅረንበታል፡፡ ትልቅ ሬዲዮ ጣቢያን ያቋቋሙ ትልቅ ሰው በፕሮፖዛሉ ስራ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ የተለየ የሬዲዮ ሀሳብ ይዘናል፤አሁን ያለውን የሬዲዮ ትሬንድ በዜናም፣ በዜና ሰዓትም፣ በአቀራረብም---- በተለይ ከውጭው ጉዳይ ይልቅ በአገራችን ጉዳይ ላይ አተኩረን ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት አለን፡፡
እዚህ አገር ባለሀብቱ ራሱ ስፖንሰር የሚያደርገው በብዛት የሚደመጠውን እንጂ የሚዘገበው ነገር ምንም ይሁን ምን ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ይሄ የተበላሸ አስተሳሰብ ነው፤ ይሄን አስተሳሰብ እንቀይራለን ብለናል፡፡ በኦዲዮም በቪዲዮም በደንብ የተደራጀ ስቱዲዮ አለን፡፡ ወደፊት ደግሞ ወደ ቴሌቪዥን ባለቤትነቱ እንሄዳለን፡፡
ባለፈው ያሸነፈ ድርጅት አለ ተብሎ በስም ተጠቅሶ በማህበራዊ ሚዲያው ሲናፈስ ነበር፡፡ መጨረሻው ምን ሆነ?
ጨረታው ሲወጣ 40 ድርጅቶች ለመሳተፍ ሰነድ ወስደዋል፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ አራት ድርጅቶች ናቸው ጨረታውን ያስገቡት፡፡ ከአራቱ አንዱ የእኛ ሀበሻ ዊክሊ ነው፡፡ ቴክኒካሊ ጥሩ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ ጨረታው የተሰረዘው በፋይናንስ አቅም የተሻለ ድርጅት አልተገኘም በሚል ነው፡፡ አሁን ጨረታው በድጋሚ ወጥቷል፡፡ ማንም እንዳላሸነፈ ባለስልጣኑ በጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል፡፡ ስለዚህ ለሁለተኛ ጊዜ ጨረታውን ከ15 ቀን በኋላ እናስገባለን፡፡
ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነህ፡፡ ትዳር ምን ይመስላል?
ባለቤቴ በጣም ጐበዝ፤ቀልጣፋና ጠንካራ ሴት ናት፡፡ ስራውን ከእኔ እኩል ትሰራለች፡፡ በስራ ላይ ጭቅጭቁ፣ የሀሳብ ፍጭቱ አለ፡፡ ቤታችን ስንገባ የምንዋደድ ባልና ሚስቶች ነን፡፡ ኤንጂል አዶኒክ የተባለች ቆንጆ ሴት ልጅ ወልደናል፤በጣም ደስተኞች ነን፡፡ እንደ ጓደኞችም እንደ ሥራ ባልደረቦችም ነን፡፡

Read 3216 times