Saturday, 18 February 2012 11:06

“ችግራችን ከተቋሙ ሳይሆን ከሃላፊዎቹ ነው”

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ እስልምናዎች ጉዳይ ምክር ቤት ላይ ትችት መሠንዘር ከጀመረ ቆይቷል፡፡ በያዝነው ወር ግን ተቃውሞዎች ቀጥለው በአንዳንድ ቦታዎች ረብሻን አስነስቷል፡፡ የጉዳዮችን መንስኤ ለማወቅና አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት ወደ ዝግጅት ክፍላችን የመጣውን ጋዜጠኛና ፀሐፊ አህመዲን አማልን አነጋግረናል፡፡

ጥያቄያችሁ ምንድነው?

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት መጋቢት 4 ቀን 1968 ዓ.ም ነው በበጐ አድራጐት ድርጅት መልክ የተመሠረተው፡፡ ከዚህ በኋላ ህዝቡ በየአምስት አመቱ የሚያምናቸውን ሰዎች ሲመርጥ ቆይቷል፡፡ በ1983 ዓ.ም የኢህአዴግ መንግስት ሲመጣ የነበሩት አመራሮች እንዲቀየሩ የሚል ህዝቡ ጥያቄ አቅርቦ በ1985 ምርጫ ተካሄደ፡፡ በ1987 ደግሞ አንዋር መስጊድ ረብሻ ተፈጠረ፡፡ በዚህ ምክንያት በ1992 ዓ.ም ምርጫ ተካሄደ፡፡ ይሄኛው ምርጫ ላይ ቅሬታ አለን፡፡ ብዙ ግጭት ነበረበት፡፡ ብዙ ምሁራን የተመረጡበት ቢሆንም ህጋዊ የሆኑትን አስወግደው በራሳቸው መንገድ የገቡበት ነበር፡፡ ህዝቡ እስከ ጠ/ሚኒስትሩ ድረስ በመሄድ እንዲወርዱ ጠይቆ ነበር፡፡

ከዚያም ሙስሊሙን በህግ የሚወክል የሙስሊሞች ጠቅላይ ጉባኤ ተብሎ ተቋቋመና አሁን   ያሉት ሃላፊዎች ተመረጡ፡፡ በየአምስት አመቱ ምርጫ ማካሔድ ነበረባቸው፡፡ ግን  ከ1992 ዓ.ም በኋላ  ህዝቡ  ምርጫ አላደረገም፡፡ በየክልሉና ወረዳ ላይ ቅ/ጽ/ቤት አለ፤ ግን ማንም አያውቅም፡፡ ሼህ ኤልያስን ማን እንደመረጣቸው አይታወቅም፡፡ አሁን ያሉትና ከሳቸው በፊት የነበሩትን ፕሬዚዳንት ማን እንደመረጣቸው አናውቅም፡፡ ወደ ህዝቡ ወርደው አያወያዩም፡፡ ለምሳሌ ጅማ ከተማ እና ናዝሬት ላይ የእስልምና ጉዳዮች ቦታ የላቸውም፡፡ ጅማ ላይ ሙኒር ከሚባል መስጂድ ውጪ ያሉ አርባ መስጂዶች ለእስልምና ጉዳዮች ሃላፊ እውቅና አይሰጡም፡፡ አልመረጥናቸውም ብለዋል፡፡ ናዝሬት ላይ የዛሬ 9 አመት አካባቢ ሁሉም መስጊዶች ም/ቤቱ እኛን አይወክለንም ብለው ተፈራርመው ልከዋል፡፡ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት የሙስሊሙ ተቋም ነው፤ ህዝቡ እስከ ወረዳ ወርዶ የሚፈልገውን ሰው መምረጥ ይችላል እንጂ በጓሮ በር ማን እንዳስቀመጣቸው ባልታወቀ ሁኔታ ተመረጥን እያሉ የሚመረጡት አሰራር መቆም አለበት፡፡ ሁለተኛ እስልምና ጉዳዮች ህዝቡ መርጦናል ብለው የወጡት 2001 ሚያዝያ ላይ ነው፡፡ ግን ከ1992 ዓ.ም በኋላ ምርጫ አልተካሔደም፡፡ ስለዚህ ጥያቄያችን ምርጫ መካሄድ አለበት የሚል ነው፡፡ እስካሁን 120ሺህ ሰዎች ፈርመው አሁን ያሉት ፕሬዚዳንት እኛን አይወክሉም ብለዋል፡፡ ሌላው አህበሽ የሚባል አስተሳሰብ ህዝቡ ላይ ለመጫን ከፍተኛ ስራ እየተሠራ መሆኑ ነው፡፡

አህበሽ ምንድነው?

አህበሽ የሚለው ቃል የመጣው ሀበሻ ከሚለው ነው፡፡ ይህንን አስተሳብ የመሠረቱት አብደላ ሀረር የተባሉ ግለሰብ ናቸው፤ የሀረር ከተማ ተወላጅ ናቸው፡፡ ወደ ሊባኖስ ሄደው ከሊባኖሲያዊያን ጋር ይህንን አስተሳሰብ ሲመሰርቱ፤ መሪው ሀበሻዊ ስለነበር ድርጅቱ አህባሽ ተብሎ ተሰየመ፡፡ አሁን በሁሉም አገራት አለ፡፡ ነገር ግን የሙስሊሙን አቋም አይወክልም በሚል ለምሳሌ አዝሀር ከሚባል የግብጽ እስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስተያየት ተሠጥቶበታል፡፡  ትክክለኛ ቃሉን አይወክልም፤ ከእስልምና ያፈነገጠ ነው በሚልም የሳውዲ አረቢያ ኡላማ ም/ቤትና የአለም የኡላማዎች ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስሊ አብዱራህማን ገልፀውታል፡፡

ሙስሊሞች፤ ቁርአን የአላህ ቃል ነው ብለው ያምናሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡ ሌላው ከኢትዮጵያ  ያፈነገጠ አስተሳሰብ አላቸው፡፡ ሀረር የሱማሌ ናት ብለው ያምናሉ፤ ይጽፋሉ፡፡  ሌላ በአለም ያሉትን ሰዎች በሦስት ይከፍላሉ፡፡ ሙስሊም የሆነ አለ፡፡ ሙስሊም ያልሆነና ከሙስሊሙ ጋር ለመኖር የተስማማ ወገን አለ፡፡ ሦስተኛ ከሙስሊሙ ጋር ጠላትነትን ያወጀ ወገን አለ በማለት በሶስት መንገድ ይከፍሏቸዋል፡፡ እንዲህ ከከፈሉ በኋላ ከሙስሊሙ ጋር በሠላም ለመኖር ከተስማሙት ውጪ ያሉትን በጠላትነት ይፈርጃሉ፡፡

ለምሳሌ በእስልምና አለባበስ ሴቶች ሒጃብ ይለብሳሉ፤ ይሔ በቁርአንም አለ፡፡ እነዚህ ሠዎች ግን አንድ ሴት ሒጃብ አድርጋ ሱሪ ብትለብስ ችግር የለውም ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ም/ቤት አህበሽን አቋሙ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡ እዚህ ላይ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴርም ሆነ መንግስት ሀይማኖት ውስጥ ገብቶ ጫና መፍጠር ይችላል ወይ ብለን እየጠየቅን ነው፡፡ ከሠኔ 2003 አ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችም ምክር ቤት የአህበሽን አስተምህሮ ለማራመድ በሀረር ከተማ አላማያ ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ዘመቻ አድርጓል፡፡

ከ1300 በላይ የእስልምና አባቶችና መሪዎች  ተጠርተው ነበር፡፡ ስምንት መቶ ሠዎች ብቻ ናቸው ፕሮግራሙን ተካፍለው የጨረሱት፡፡ ሁሉም ኢማም እና አባቶች መቀበል አለባቸው በማለት አመራር ላይ ያሉ ሠዎች ጫና አድርገዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ይጠቅማታል ብለው በክልሎች በርካታ ስልጠና ሠጥተዋል፡፡ ሀይማኖቱን በጥልቀት የሚያውቁና የተቃወሙ ሠዎች በርካቶች ቢሆኑም፤ ከእስልምና ጉዳዮችና ከኢማምነት እንደሚወገዱ ማስፈራሪያ ነበር፡፡ ስልጠናውን የተቃወመ አክራሪ ነው ይባላል፡፡ የታሰሩም አሉ፡፡ አስተማሪዎቹ ሊባኖስያዊያን ናቸው፡፡ አንድም ኢትዮጵያዊ የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተሠራ ያለው ስራ ህገ ወጥ ሆኖ ዝም መባሉ ይከብዳል፡፡

አሁን ምርጫ ይካሔዳል ተብሏል!! ይሔንን እንደ መፍትሔ ታዩታላችሁ?

በፍትሀዊና ህጉን ጠብቆ ምርጫ ማካሔድ መፍትሔ ነው ብለን እናስባለን፡፡ የእኛ ችግር ተቋሙ ላይ ሳይሆን ተቋሙ ውስጥ ያሉት ሀላፊዎች ላይ ነው፡፡  እየሔዱበት ያለው አካሔድ ሙስሊሙን የሚበጠብጥ አንድነቱን የሚያናጋና የሚበታትን ነው፡፡ አወሊያ ላይ ችግር ተፈጠረ፡፡ የት/ቤቱ ችግር የሙስሊሙ ማህበረሠብ ችግር ሆነ፡

የአወሊያ ት/ቤት ችግር መፍትሔ አገኘ?

አወሊያ በ1940ዎቹ ኡስታል አሊያህ የተባሉ ግለሠብ ያቋቋሙት የሙስሊሙ ተቋም ነው፡፡ ት/ቤት ሲጀምር የግለሠብ ነበር፡፡ የአረብ የሊግ አባላት ኢትዮጵያን ሲጐበኙ ት/ቤቱንም ጐብኝተው ስለነበር በሳውዲ ኤምባሲ በኩል ድጐማ ተደረገለት፡፡ ት/ቤቱን ያስተዳድሩ የነበሩ አባቶች በ1967 ዓ.ም ሚሽን ይሁን ተብሎ ይመዝገብ ብለው በ1977 ላይ የህዝብ ትምህርት ቤት ተብሎ ቀጠለ፡፡ በዚህም በ1987 ደግሞ የህዝብና የሀይማኖት ት/ቤት በመሆን በቀጣይም 56ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ አስኮ ጋር ተሠጥቶት የተገነባ ኮሌጅ፣ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም አስክሬን ማጠቢያ፣ ማንኛውም ሠው ቢሞት ከቤት ሔደው በማምጣት የሚያጥቡበትና በራሳቸው መኪና ወስደው የሚቀበሩበት… ይሔንን ሁሉ የያዘ ተቋም ሆስፒታል እየተገነባ ነው፡፡ ህፃናት ማሳደጊያና መስጂድ አለው፡፡

ተቋሙ በነፃነት እንደእስካሁኑ ይቀጥል ነበር፡፡ ግን ለም/ቤቱ ተሰጠ፡፡ ከፍተኛ ሙስና እንዳለበት ስለሚታመን ተቃውሞ ተነስቷል፡፡  በዚህ አልቆመም፡፡ መጀመሪያ ያደረጉት አመራሮችን ማባረር ነው፡፡ የአረብ መምህራንን በሙሉ አባረሩ፡፡ ቀጥለው ካሪኩለም ልንቀይር ነው ብለው ሦስት አመት ተምረው ስድስት ወር ለመመረቅ የቀራቸውን ተማሪዎች ወደ ቤታችሁ ሒዱ አሏቸው፡፡ ልጆቹ ለሙስሊሞች ጉዳይ ም/ቤት “ቢያንስ ይቺን ቀን እንጨርስ” ቢሉም አንድ ቀን አንፈቅድላችሁም ተባሉ፡፡ በዚህም ችግሩ ገንፍሎ ወጣና መንግስት ጋር ሊደርስ ቻለ፡፡

ሙስናን በተመለከተ ም/ቤቱ አጣራለሁ፤ ኦዲትም ተደርጓል ብሏል፡፡

የሙስናን እናጣራለን ብለው ያደረጉት ነገር የለም፡፡ ም/ቤቱ ውስጥ የሀጂና ሁምራ ዘርፍ አለ፡፡ ዘንድሮ ወደ 6ሺህ ሠው ሔዷል፡፡ ሲሔዱ ገንዘብ ይከፍላሉ፡፡ የዶላር እጥረት አለ ተብሎ በሀዋላ ነው የሚከፈለው፡፡ አንድ ሠው እዚህ ሲከፍል፤ በሳዑዲ አረቢያ ደግሞ አገልግሎቱን ያገኛሉ፡፡ ከዚህ በፊትም ኮሚቴ አቋቁመው በዚህ ጉዳይ ላይ እናጣራለን ብለዋል፡፡ ግን አንድም የተጠየቀ የለም፡፡

ሀጂና ሀምራ ላይ ህዝቡ ብዙ ጊዜ ነው የሚያማርረው፡፡ ተጓዦች ስቲከር ለመለጠፍ ሦስት መቶ ብር ነው የሚከፍሉት፡፡ ስቲከሯ ግን በ50 ሳንቲም ነው የምትሰራው፡፡ ለምሳሌ እኔ ዘንድሮ ባለቤቴን ይዤ ሀጂና ሁምራ በራሴ ነው የሄድኩት፡፡ ኤምባሲ ቪዛ ስጡኝ ብዬ ሔጃለሁ፡፡ በመጅሊሱ በኩል የሔደ አንድ ሠው 37ሺህ 620 ብር ይከፍላል፤ ከትራንስፖርትና ከሌሎች ጥቅማጥቅም ጭምር፡፡ እኛ ግን ለሁለት ሰው አርባ ሰባት ሺህ ብር ነው የከፈልነው፡፡  መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም ይላል ህገመንግስቱ፡፡ እነዚህን ችግሮች መንግስት መፍታት አለበት ስንል መስጂድ ቢቃጠል መንግስት ቆሞ አያይም፡፡

ሀይማኖት ውስጥ አልገባም ብሎ አይቆምም ማረጋጋት አለበት፡፡ ያለበለዚያ ችግሩ እየተባባሰ ይሄዳል፡፡

ም/ቤቱ በሰጠው መግለጫ ችግር አለ የሚሉት በህገወጥ መለገድ ለመንቀሳቀስ የሚፈልጉና አክራሪዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ህገወጦቹ እነሱ ናቸው፡፡ ጥቂት ወጣት ህገወጥ ሊባል ይችላል፡፡ አብዛኛው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ግን ህገወጥ ሊባል አይችልም፡፡ የአህበሽን ስልጠና በግዳጅ ሲያከናውኑ የተቃወማቸውን ሰው አክራሪ ሊሉ ይችላሉ፡፡ አሁን በሃላፊነት ላይ ያሉት አህመድ አብደላሂ በፊት በኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ነበሩ፡፡

ህዝቡን የሚከፋፍል መተዳደሪያ ደንብ ሲያዘጋጁ ነበሩ፡፡ አሁንም እነሱን ያልተቀበለ አክራሪ ብለው ነው የሚያስቡት፡፡ ፊርማ ፈርመው ም/ቤቱን አናውቀውም ያሉት በሙሉ አክራሪዎች ናቸው፡፡

መፍትሔው ምንድነው?

መንግስት ጣልቃ መግባት ሲችል መፍትሔ አለው፡፡ ለጠየቅነው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ለየካቲት 5 ቀጠሮ ተሠጥቶናል፡፡ ያንን እንጠብቃለን፡፡ ህዝቡ ውክልና ሰጥቶናል፡፡ ማስፈፀም ካልተቻለ መልሰን ወደ ህዝቡ እንወስድና መፍትሔ ከህዝቡ ጋር እንፈልጋለን፡፡

 

 

Read 4208 times Last modified on Saturday, 18 February 2012 13:00