Saturday, 13 February 2016 11:12

ጎንደር “ወቀሳዬ” ናት!

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(6 votes)

“ዓይን ማየት ነው የሚያቅ
የብርሃን ዕድሜ አዚሙ እስኪያልቅ …
ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ዳግም አዘቦን አየኋት
ዙሪያ ቅፅሯን አስተዋልኳት
አጠናኋት አዳመጥኋት ….”
ባለቅኔው ፀጋዬ ገብረመድኅን፣ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ “አዘቦን” ዳግም ሲያያት ተፀፀተባት፡፡ “ሰው እንደ አይጥ በየጥሻው ሲጥ ሲል” ያየባት፡፡ “መሬቷ እንደ ሞረድ ስለት፤ ጥርሷ ሲፋጭ እንደ ደወል ሰቆቃ እንጂ እኮ ድምፅ አደል!” ያለባት፡፡ አዘቦ የአመታት አቀበት ጅስሟን፣ ቅስሟን አስገብሯት፣ ያወጣት ጉልላት ላይ ሆና ፀጋዬ አገኛት፡፡ “እሰይ አልኳት” ይላል፡፡ እኔስ?
… እኔም ከአስራ አራት ዓመት በኋላ ጎንደርን ላያት ታጨሁባት፡፡ ከእንባዬ ወይም ከፈገግታዬ ላጣቅስባት፤ ከስሜቴ አምስት አውታር አንድም ዘለሰኛ እንደ ላስቲክ ልጎትትባት፤ ወይም እንደ ትዊስት ባለ ቅብጠት ላናጥርባት ታጨሁባት፡፡
ጎንደርን ካየኋት አሥራ አራት አመት ሞላት፤ ቢሆንም ውስጤ፣ ደማቅ ቀለም አላት፡፡ አመት እንደ ዓለት ቢነባበርባት የማይቀብራት ከተማ ናት፡፡ ሁልጊዜም ከታች ሆኜ ወደ ላይ የማያት ደብርነት አላት፡፡ እንደ ብዙ ከተሞች ክፍት አፍ “አሁን” የማይጮህባት፣ ጥንታዊ አስተዋይነት የረበበባት ናት፡፡ ሁልጊዜም … ጎንደር ስሄድ ላለፈው ማንነቴ የአሁን እኔነቴ ይሰግዳል፤ ይገብራል፣ ይጎናበሳል … እንዴትስ እንዲህ ላያደርግ ይችላል? የአሁን ማንነቴ ምን ይዟል? ብቻውን የት ደርሷል?
… ጎንደር ሄዶ፣ የፋሲል ግንብን አይቶ፣ በራሱ ቀርቶ ከቅድመ አያቶቹ ዝቅ ብሎ የሚኮራ ማነው? ፋሲለደስ ጎንደርን እስከቆረቆረበት 1623 ዓ.ም ድረስ ያለው ዘመን፤ “ምንም” እንደሆነው ሁሉ ከዚያ ወዲህም ከአፄ ቴዎድሮስ በኋላ እንዲሁ ታላቅነት በኪነ-ህንፃ የመግዘፉ ነገር “ምንም” ይሆናል፡፡ ዛሬን የሚወቅሰው ጥንታዊ ግንባታ፣ በፋሲል ቤተ መንግስት ቅርፅ አይወሰንም፤ ወደ ይዘቶቹም ይማትራል፡፡ የመታጠቢያ ገንዳው፣ የፋሲለደስ ልጅ (የቀዳማዊ ዮሐንስ) ቤተ - መፃህፍት እና ለቆንስላዎች የተዘጋጁት ቢሮዎች - መኖሪያ ቤት፣ ምሽት ማሳለፊያ መጠለያ ብቻ ለሆነብን ለእኛ መተዛዘቢያዎቻችን ናቸው፡፡ አሁን ከአራት መቶ አመት በኋላ እንኳን ቤቶቻችንን ከመዋኛ ገንዳ ጋር ከማዳበል ይልቅ ሳሎን ማስፋትና መኝታ ክፍሎች ማብዛት ከመጠለያ ሰቀቀን ያለመገላገላችን ምልክቶች ናቸው፡፡ የመኖሪያ ቤት፣ ቢሮና ቤተ - መፃህፍትማ “ከቀበጡ አይዘሉ”ን የሚያስተርት የመሰበር ምልክ ተደርጎ ይታያል፡፡
… ትርፍ ማከል ሲያቅተን “ጥሪያችንን” በላን፡፡ መኖራችን ዕዳ፣ በህይወት መገኘታችን ወቀሳ ሆነብን፡፡ ያለፈውን ያላስቀመጥን፣ የዘር እህል ያልቆጠብን፣ የ“ባዶ” መተላለፊያ ድልድይ ሆንን፡፡ ጎንደር ወቀሳዬ ናት፡፡ እዚያ ሄጄ ስመለስ ቀና ማለት ያቅተኛል፤ መንፈሴ ይጎብጣል፤ ነፍሴ በመፃጉነት ትቃትታለች …
… ዛሬስ?
“ግጥም በመሰንቆ”ዎች ሲጋብዙኝ “ላስብበት” አልኩ፡፡ እንደ አቡነ ጴጥሮስ ፅዋ ግብዣው መራር ሆኖ ታየኝ፡፡ “አዎ፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ” እንዳሉ አቡኑ፤
“እሸሸግበት ጥግ አጣሁ፣
እምፀናበት ልብ አጣሁ” ማለት አሰኘኝ፡፡ ግን ደግሞ መሸከም መፍትሔ አይደለምና “ይቺ ጽዋ ከእኔ ትለፍ” ለማለት አልደፈርኩም፡፡
“መቼ ነው?”
“የካቲት አራት፣ አርብ ዕለት” አሉኝ፡፡
“ጥሩ፤ አርብ ጠዋት እመጣለሁ፣ ቅዳሜ ጠዋት እመለሳለሁ፡፡”
“ትችላለህ”
ይቺ ናት ስልታዊ ማፈግፈግ፡፡ “መጣሁም” “ቀረሁም” ለማለት የሚያመች ውሳኔ፡-
አርብ (በጋዜጣ አቆጣጠር - ትናንት) የጎንደርን ግጥም በጎንደር መሰንቆ አፈጣጥሜ አደምጣለሁ፡፡ ግሩም እንደሚሆን እተማመናለሁ፡፡ ኪነ - ህንፃ ባይሆንልንም ኪነ - ጥበብን አስቀጥለን፣ እዚህ መድረስ አላዳገተንም፡፡
 በጥንቲቱ ጎንደር፣ በቀዳማዊ ኢያሱ ዘመን “ግጥም በመሰንቆ”ን የመሰለ ልማድ በቤተ መንግስት አካባቢ እንደነበር አንዳንድ የታሪክ መዛግብት ይገልፃሉ፡፡ በዘመኑ ያልተለመደ ስለነበርም ነቀፌታና ውግዘት ይደርስበት የነበረው በአለማዊ አይን ተዳኝቶ ሳይሆን ከቀኖና አንፃር ተገምቶ እንደነበር መጠርጠር አያዳግተንም፡፡
ጎንደር በቀዳማዊ ኢያሱ ዘመን (ከ1675-1699 ዓ.ም) በጥበብ ምሽትነት የማይቀነበብ ምናልባትም “የጥበብ ፌስቲቫል” ሊባል የሚችል ድግስ የማዘጋጀት ልማድ ነበራት፡፡ ካህናቱ ከመንፈሳዊው ባሻገር ዓለማዊ ቅኔ የሚያቀርቡበት መድረክ “የፌስቲቫሉ” አንዱ አካል ነበር፡፡ መኳንንቱ የእርስ በእርስ የበገና ጨዋታ ፉክክር ያካሂዱ ነበር፡፡ የሰንጠረዥና የገበጣ ውድድር በወንድ መኮንንኖችና በሴት ወይዘሮዎች መካከል ይደረግ ነበር፡፡
ይሄንን “የጥበብ ፌስቲቫል” ከአለማዊና ከመንፈሳዊ አንፃር አይቶ መዳኘት ሁለት ፅንፍ ድምዳሜ ላይ እንደሚያደርስ ግልፅ ነው፡፡ እንደ እኔ ያለው ዓለማዊ ዘጋቢ፣ ጥበብ በምን ያህል ሁኔታ ማበብ እንደጀመረች አስረግጦ ወጉን ሊያፍታታ ይሞክር ይሆናል፡፡ መንፈሳዊው በይበልጥ አክራሪው መንፈሳዊ ግን እንደ አለም ፍፃሜ መዳረሻ እርከን ሊመለከተው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ከመንፈሳዊ ወገን የሆኑት አለቃ አፅመጊዮርጊስ እንዲህ በማለት ከግሳፄ ጋር ይገልፁታል፡፡
“(በአፄ ኢያሱ) በዚያ ዘመን በዚያ ወራት የቀልድ የቧልት የጨዋታ ዘመን ነበረ ካህናቱ በቅኔ እርስ በርሳቸው ይሳደቡ ነበር፣ መኳንንቱ በበገና ይጫወቱ ነበር፣ ወታደሩ በክራር አዝማሪውም በመሰንቆ ሲያዘምር የሚናገረውን በማድነቅ የወንድ መኮንን፣የሴት ወይዘሮ በሰንጠረዥና በገበጣ፣ ሲጫወቱ ሲያቧልቱ በፍቅር በጋብቻ ተቀላቀሏቸው፡፡ በዘመኑ ዝሙት፣ በስካርና ዘፈን እጅግ በዛ፡፡ ጎንደር ያለልክ ሰማች፣ ገረረች፡፡”
በዚህ ዘመን አንድ መንፈሳዊ ሰው፤ “ግጥም በመሰንቆ”ን ቢጋበዝ ሊሰጥ የሚችለውን አስተያየት ተንተርሶ ከአራት መቶ ዓመት በፊት የነበረውን መገመት ይበቃል፡፡ አለቃ አፅሜ የጎንደር በጥበብ መላቅ ለእሳቸው አልታያቸውም፡፡ ቅኔን ወደ አለማዊ ጉዳይ አውርዶ የእለት ተዕለት ህይወት ማስተንተኛ ማድረጉ ጎፍንኗቸዋል፡፡
ምናልባትም ይሄ “የጥበብ ፌስቲቫል” በጎንደር እንዳይቀጥልና እንዲዳፈን የመደረጉ ውሳኔ ላይ የእንዲህ ያሉ ሰዎች አስተያየት ትልቁን ድርሻ ሳይወስድ አይቀርም፡፡ ያኔ “የጥበብ ፌስቲቫሉ” ቀጥሎ ተስፋፍቶና ተንሰራፍቶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ በሙዚቃ፣ በስፖርት፣ በግጥም፣ በልቦለድ፣ በሥነ ስዕል … የት እንስፈነጠር ነበር? …
…. ጎንደር ወቀሳዬ ናት፡፡    


Read 3510 times