Saturday, 13 February 2016 10:57

መልካም አስተዳደር የወቅቱ ቁልፍ ችግር

Written by  አበበ ተክለሃይማኖት/ጆቤ (ሜ/ጄ)
Rate this item
(9 votes)

“ህዝቡ ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መወሰንና መሳተፍ አለበት ሲባል ቅንና ሳይንሳዊ የሆኑ ሃሳቦችን ብቻ
መስማት አለበት ማለት አይደለም፤ የተሳሳተና ኋላቀር ሃሳብንም በነፃ መስማት አለበት፡፡ ሰምቶ ከተከተለው
መከተል ይችላል፡፡-----”

(የመጨረሻ ክፍል)
-- በህወሓት ጉባኤ ወቅት የተወሰኑ ጄኔራሎች መቐለ አካባቢ ያንዣብቡ ነበር ብለው አንድ ሁለት እዚያ የነበሩ ሰዎች ገለፁልኝ፡፡ ታዲያ ምን አለበት ለራሳቸው ጉዳይ ሄደው ከጉባኤው ጋር ተገጣጥሞ ሊሆን ይችላል ብዬ አልኳቸው። አንደኛው፤ “አይ ማታ ማታ ከፖለቲካ መሪዎች ጋር ይገናኙ ነበር” አለኝ። እኔም የድሮ ጓደኞቻቸውን በአጋጣሚ አግኝተው እየተጫወቱ ይሆናል ስል ግምቴን ተናገርኩ፡፡ “አይ ሰዎች የተለያየ ትርጉም እየሰጡት ነው” አሉኝ። ነገሩ ግራ ገባኝና፤ “በጉባኤዉ ላይ በቀጥታ ተፅእኖ እያሳደሩበት ነው እያላችሁኝ ከሆነ፣ እንዲህ የሚያደርጉ አይመስለኝም፤ህገ መንግስቱን ጠንቅቀው ያዉቁታል፤ በኮርት ማርሻል (ወታደራዊ ፍርድ ቤት) የሚያስቀጣቸዉና በቀጥታ ከሰራዊቱ የሚያባርራቸው መሆኑን በሚገባ ስለሚያውቁት አይሞክሩትም” አልኳቸው፡፡  
 በሌላ በኩል ደግሞ ህወሓት የመከላከያ ጄኔራሎች በፖለቲካው ውስጥ ገብተው እንዲዘባርቁ የምትፈቅድ አይመስለኝም። ፖለቲካዊ ትርጉሙ መሰረታዊ ነው። ብዙ አንፀባራቂ ታሪክ ስርታ እዚህ የደረሰች ድርጅት፣ ይህን ከፈቀደች ሞታለች ወይም አንድ እግሯን ጉድጓድ ውስጥ አስገብታለች ማለት ነው፤ስል ነገርኳቸው። በተጨማሪም የድርጅቱ ሊቀመንበር የጄኔራሎቹን ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት የሚቀበሉ አይመስለኝም አልኩኝ፡፡ አንደኛው ሰውዬ፤የሊቀመንበሩ አፍቃሪ ስለነበር “ይሄስ እዉነትክን ነው” ብሎኝ ነገሩ ለጊዜው ተቋጨ፡፡
 --- ወይን መፅሄት በ50ኛ እትሙ፣ ህገ መንግስቱን በግላጭ የጣሰና የተፈጠረውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ምን ማድረግ እንደሚችሉ የሚያሳይ ደንበኛ ምሳሌ በመሆኑ ሰፋ አድርጌ ለመፈተሽ ተገድጅያለሁ። የወይን ስፖንሰሮች፡- የፌዴራል ሚኒስቴር መስርያ ቤቶች፣ መከላከያ ሚኒስቴር ሳይቀር፣ የአዲስ አበባ ቢሮዎች፣ የዞን ፅህፈት ቤቶች፣ በትግራይም ከክልል ቢሮዎች እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ የመንግስት መዋቅሮች ----- ነበሩ፡፡ አሁን ጥያቄው የመንግስት መስርያ ቤቶች የአንድን ፖለቲካዊ ድርጅት ልሳን መፅሄት ስፖንሰር ማድረግ ይችላሉ ወይ? ነው፡፡ የግል ድርጅቶች ተጨምረውበት በማስታወቂያ የታጨቀ ቢሆንም 50ኛ እትሙ መፅሄት በ50 ብር ሲሸጥ ነበር፡፡
 እነዚህ የመንግስት ተቋሞች፣ የአንድ ፖለቲካዊ ድርጅትን ልሳን እንዲደጉሙ ሕገ መንግስቱ ወይም ሌሎች ህጎች ይፈቅዳሉ ወይ? በተለይ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 87/5 መሰረት፤ ከፖለቲካዊ ወገናዊነት ነፃ በሆነ መንገድ ስራዉን ማከናወን ያለበት መከላከያ፣ የመጽሄቱ ስፖንሰር ሆኖ ማየት አስገራሚ ነው። ዕብሪት ነው!!! መንግስት ከህግ ዉጪ አንድን ፓርቲ መደጎም የለበትም። አይ… ህገ መንግስቱ አይከለክልም ከተባለም፣ በህጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱትን የመድረክ፣ ዓረና እና መኢአድ ልሳኖችን ስፖንሰር ቢያደርጉ የፓርቲዎቹ  የፋይናንስ አቅም ደካማ ከመሆኑ አንጻር፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ድጋፍ እንዳደረጉ በተቆጠረላቸው ነበር። ከዲያስፖራ ጥገኝነትም ያላቅቋቸው ነበር።
  የመፅሄቱን ይዘት በዝርዝር ስመለከት ደግሞ እውነት የህወሓት ልሳን ነው ወይ? የሚል ጥያቄ እንዳነሳ አስገድዶኛል። ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ በኢህአዴግ ውስጥ  መነቃቃት መፈጠሩ ይታወቃል፡፡ የህወሓት ጉባኤ ደግሞ ከሌሎች የግንባሩ ድርጅቶች የሰላ እንደነበር ተነግሯል፡፡ የዚህ የሰላ ጉባኤ ምልክት ተደርገው በህዝቡ ሞገስ ያገኙት ቄስ ገብረገርግስ ገብረማርያም የጉባኤዉን ሂደት ሲገልፁ፤ “ፊት ንፊት ገጢምና እንተወሐደ ንለባም ክርደኦ ገይርና አለና! ቀይናን እዉን ሰንቢዱ አሎ” (ቢያንስ ፊት ለፊት ገጥመን ልባሙን እንዲረዳ አድርገናል! ጠማማው ደግሞ ደንግጥዋል) ነበር ያሉት ከ ዉራይና መፅሄት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፡፡ ነባራዊው ሁኔታ እንዲህ ሆኖ ሳለ፣ ትግራይ ውስጥ የተፈጠረውን ማዕበል በተመለከተ ከወይን ምንም አለማግኘቴ ግርምት ፈጥሮብኛል። በኔ አመለካከት ወይን ቁጥር ሃምሳ (ሌሎች እትሞችን ስላላነበብኩ አስተያየት ለመስጠት ያስቸግረኛል) የዴሞክራሲ ማዕበሉ ያስፈራቸው የድርጅቱ አመራር ወይም ከበስተጀርባቸው የሚደጉሟቸው ሃይል ልሳን እንጂ የህወሓትን 12ኛ ጉባኤ መንፈስ የሚያንፀባርቅ አይደለም።  በተለይ የመከላከያ ጉዳይ አሳሳቢ ነው። ታዳጊ አገር እንደመሆናችንና ዴሞክራቲክ ተቋሞቻችን ደካማ በመሆናቸው የታጠቀው ሃይል ወይ ራሱ ንጉስ (King) ወይም አንጋሽና አፍራሽ (King Maker and breaker) የመሆን አደጋ ሊጋረጥብን ይችላል፡፡ አሁን የታየው ምልክት እንዳይሰፋ ከወዲሁ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ የሲቪልያን ቁጥጥሩም ጠበቅ ማለት ይኖርበታል፡፡ ጠንካራ የሃገር መከላከያ፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ዘብ ቢሆንም፤ ከልክ በላይ ካበጠ ግን የ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች መሳርያ ስለሚሆን በዚህ ረገድ የተሰማሩ ምሁራን፤ ወታደራዊ ክፍሉ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወይም ቅልበሳ (democratization and de-democratization) ላይ የሚኖረውን ሚና እንዲያጠኑት መንግስት ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት፡፡ እኔ በበኩሌ በዚህ ዙርያ ኢትዮጵያን ማእከል አድርጎ የተጠና ጥናት አላገኘሁም።
 ----የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ህገ-መንግስቱንና ሌሎች የአገሪቷን ህጎች ከቁብ እንደማይቆጥሩት በተግባር እያሳዩን ነው፡፡ የህወሓት 40ኛ አመት በትግራይ ቴሌቪዥን የወራት ሙሉ ሽፋን እንዲሁም በኢቢሲ (EBC) ላቅ ያለ ሽፋን የተሰጠው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ትንፋሽ ለመተንፈስ እንኳ የማትበቃ ጥቂት ደቂቃ በተመደበላቸው የምርጫ ወቅት መሆኑን ስንገነዘብ ደግሞ የመንግስት መገናኛ ብዙኃንን ባህሪና ማንነት የበለጠ መረዳት እንችላለን፡፡ ለመሆኑ ህወሓት በትግራይ ቴሌቪዥንና በEBC ላሰራጨው የወራት ፕሮግራም ክፍያ ፈፅሟል? ቢፈፅምስ ይህ ተገቢ ተግባር ነውን?
 ---- ከመንግስት ውጪ የሆነ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ እስካሁን በአገራችን ላይ አለመኖሩ አስገራሚ ነገር ነው። የዚህ ዋና ምክንያት ምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ለመሆኑ  መንግስት፤ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ የተለየ ሃሳብ ለሚያቀነቅኑ ወገኖች የቴሌቪዥን ፍቃድ ለመስጠት ድፍረት ይኖረዋል? ወይስ ለመንግስት የማያጎበድድ ከሆነ ፍቃድ አያገኝም?
  የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊ፤ የካቲት 11 መከበር ያለበት፣ በዚህች አገር ታሪክ የዴሞክራሲና የልማት የማዕዘን ድንጋይ የተቀመጠበት ቀን ነው ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ ሆኖም ቀኑ ለርካሽ ጊዜያዊ ፕሮፓጋንዳና ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን በመጣስ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ለማፈን መዋል የለበትም ብሎ ያምናል፡፡ የምንወደውና የምናከበርው በዓል፤ ህገ መንግስትን ባከበረና ለዴሞክራሲያዊ ስርኣት ግንባታ አስተዋፅኦ በሚያደርግ መልኩ መከበር አለበት፡፡ የካቲት 11 ሁሌም መከበርና መዘከር ያለበት በዓል ነው። ይህን ስል ግን በሰማእታት ደም እየነገዱ ለመኖር ባለመ ሁኔታ መከበር እንደሌለበትም በማሳሰብ ነው። አንዳንዴ ለበዓሉ የሚወጣውን ገንዘብ ሳስተውል፣ ምናለ ለጥናትና ምርምር ፈሰስ ቢደረግበት እላለሁ፡፡
 በተመሳሳይ መንፈስ ህዳር 11 መከበርና መዘከር ያለበት ታሪካዊ ቀን ነው፤ ነገር ግን የክብረ በዓሉ አጀማመር ልክ የህወሓትን ይመስላል። ጋዜጠኞች ወደ ትግል ቦታ ተወስደዋል፤ በማን በጀት? የክልል ፓርላማ ግልፅ በሆነ መንገድ ከወሰነም፣ የክልሉ መንግስት ይህን ለማድረግ ህገ መንግስቱ ይፈቅድለታል ወይ? በጀቱስ ስንት ነው? ብአዴን በአማራ ክልል ቴሌቪዥንና በ EBC ለሚያሰራጨው ፕሮግራም ይከፍላል ወይ ? አሁንም የበዓሉ አከባበር ህገ መንግስቱንና ሌሎች ህጎችን የተከተለ ነው? እስከ ምን ድረስ አሳታፊ፣ ግልፅና ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መልኩ እየተሰራ ነው? እስከ ምን ድረስ ሚዛናዊ መረጃስ ለህዝብ ያቀርባል? የሚሉት ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው። ይህ ሃቅ ኦህዴድንም ደኢህድንንም የሚመለከት ነው፡፡ በቅርቡ ከኢቢሲ ዜና አንባቢ ጀርባ እናየው የነበረው የኢህአዴግ 10ኛ ጉባኤ መፈክርን ነበር፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ብዙ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ዓረና/መድረክ ወይም አብኮ ድርጅታዊ ጉባኤ ቢያካሂዱ ኢቢሲ ተመሳሳይ ሽፋን ይሰጣል? ከእነአካቴውስ በቅጡ ይዘግበዋል? መምቻ ይሆናል ብሎ ካሰበ፣ “አዎ በደንብ ነው እንጂ” ይሆናል መልሱ፡፡ ይህ በግላጭ የሚታይ ፀረ ህገ መንግስትነት በጊዜ መታረም አለበት።
 ---- መሬት ላይ ያለው እውነታ ከላይ እንደተገለፀው ቢሆንም፤ ኢህአዴግ በ1992 ለውይይት ያቀረበው ሰነድ ግን እንደሚከተለው ይላል፡ “ህዝቡ ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መወሰንና መሳተፍ አለበት ሲባል ቅንና ሳይንሳዊ የሆኑ ሃሳቦችን ብቻ መስማት አለበት ማለት አይደለም፤ የተሳሳተና ኋላቀር ሃሳብንም በነፃ መስማት አለበት፡፡ ሰምቶ ከተከተለው መከተል ይችላል፡፡ በሂደት በተግባር ከስህተቱ ተምሮ ወደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ይመለሳል፡፡ ካልተቀበለው ደግሞ ይበልጥ በነፃ ፍላጎቱና በሚያስተማምን አግባብ ቅን ወደሆነው ሃሳብ ይገባል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ የአስተሳሰብ ልዕልናውን የሚያረጋግጠው የተሳሳቱ ሃሳቦችን በማፈን አይደለም፡፡ የተሳሳቱ ሃሳቦችን ማፈን ማለት የሚያጋልጣቸውና የሚታገላቸው ሳይኖር ውስጥ ለውስጥ እንዲጎለብቱና እንዲጠነክሩ በር መክፈት ማለት ነው” ይላል በገፅ 65 ላይ፡፡
 ይህ የተጠቀሰው ዶክመንት በገፅ 123 ላይም እንዲህ ይላል፤ “መላውን ህዝብ /አብዛኛው ክፍል/ ለአመታት ለአንድ ፓርቲ አመለካከት በማጋለጥ፣ ሌሎችን በመከላከል የሚደረግ አሰራር መከተል በሃሳቦች መካከል ነፃ ውድድር እንዳይኖር የሚያደርግ ነው፤ የኃይለስላሴና የደርግ መንግስታት ይህን ማድረጋቸው የሚያመላክተው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ባህርያቸውን ነው” (ኢህአዴግ፣ 1992 ዓ.ም ገጽ 123) ። ምን ዋጋ አለው? ሰነድ ሌላ እውነታው ሌላ፡፡
---ሚዲያዎች ተገቢ ሚናቸዉን በተገቢ አዃሃን ከተጫወቱ የዴሞክራታይዜሽን ሃይል ሆነው የላቀ ጥቅም ይኖራቸዋል፤ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን አጥፊና የኢ-ዴሞክራታይዜሽን ሃይል መሆናቸው አይቀርም።
  የአንድ ለአምስት ተቋም
 ---- አንድ ለአምስት አደረጃጀትም ለህዝቡ የቀረበና የሚወስዱት እርምጃዎችም ቀጥተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ሊጠኑና በጥልቀት ሊዳሰሱ ይገባቸዋል፡፡ ይህ አደረጃጀት እታች ወርዶ የተፈጠረ ተቋም ሲሆን አጠቃላይ ህዝቡን ለልማት አነቃንቆ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ በጎ ለውጦችን በማስመዝገብ፣ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ሊያግዝ የሚችል ፈጠራ የታከለበት አደረጃጀት ነው፡፡ በአግባቡ ካልተያዘ ግን የደህንነት ተቋም ተቀጥያ ሊሆን ይችላል፡፡ ለጠባብ የፓርቲ ፖለቲካዊ መሳርያነት ከተጠቀምንበትም ጉዳቱ የከፋ ይሆናል፡፡
በቤተሰብ ውስጥ ስለላንና ጥራጣሬን ሊተክል ይችላል፤ አለን የምንለውን የቆየ ማህበራዊ እሴትንም ድምጥማጡን ሊያጠፋው ይችላል።
 ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ወደ ህዝቡ ወርዶ ለማገልገልና ድህነትን ለመቅረፍ የሚያደርገው ትግል ላቅ ያለ ምስጋና ይገባዋል፡፡ በማዳበርያ፣ በምርጥ ዘር፣ በእርሻ ቴክኖሎጂዎችና አስተምህሮዎች የሚያደርገው ድጋፍ እንዲሁም ውሃ፣ የጤና እና የትራንስፖርት አገልግሎት ወደ ገበሬው ለማድረስ የሚደረገው ጥረትም ይበል የሚያሰኝ  ነው፡፡ በስመ ነፃ ገበያና ሊበራል ዴሞክራሲ ከላይ የተጠቀሱት አገልግሎቶችና ግብአቶች  አይመለከተኝም፣ በገበያ ህግ ይመራ ቢል፣ ምን ሊከሰት እንደሚችል ማሰብ አያዳግትም፡፡
 ሆኖም ይህ ዘላቂ ነውን? ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ዘላቂነት የሚረጋገጠው መሰረታዊ የተቋሙን (አንድ ለአምስት) ችግር ሲፈታ ነው፤ መሰረታዊ ችግሩ ደግሞ ሌላ ሳይሆን የዴሞክራሲ እጥረት (democratic deficiency) ነው:: በዚህ ዙርያ ብዙ ነገሮች ይነሳሉ፡፡ ጥልቅ ጥናት የሚፈልግና ከቦታ ቦታ ሊለያይ የሚችል ነገር መሆኑን ሳንዘነጋ ከአጠቃላይ ከባቢው (General environment) እና ከምታዘባቸው ነገሮች ተነስቼ ስለ ጉዳዩ ጥያቄ ማንሳት  ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ በትንሹ የገጠርን እንኳን ብንወስድ ከኢትዮጵያ ህዝብ ከ80% የሚሆነውን ህዝብ የሚያንቀሳቅስ አደረጃጀት መሆኑን ስንገነዘብ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ መፃፉ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሚሆን እንረዳለን፡፡
 አንድ ለአምስት የሚባለው ተቋም /አደረጃጀት/ ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት የሚመሰርቱት ተቋም ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡
የተቋሙ አባላት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የተደራጁ ናቸው ብንል እንኳ ከውጭ የሚሰጥ አመራርም ቁልፉ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ከዴሞክራሲ አኳያ ግን መመለስ ያለብን ጥያቄዎች አሉ፤ መሬት ላይ ያለውን ሃቅን መሰረት አድርገን በመነሳት፡፡
 እውን አሁን ያለን አንድ ለአምስት አደረጃጀት በአባላት በጎ ፍቃድ የተመሰረቱ ናቸው? ፍላጎታቸውን መሰረት አድርገው በነፃነት ራሳቸው ይወስናሉ? የቀረበላቸው ግብአት መርጠው የመቀበልና እምቢ የማለት መብት አላቸው? “ህዝብ ከራሱ ተሞክሮ ይማራል” የሚለው ዴሞክራሲያዊ መፈክር በተግባር ላይ እየዋለ ነው? ግምገማውስ ምን ይመስላል? አንድ ሰው በተለያየ ምክንያት ማዳበርያ ወይም ምርጥ ዘር አልገዛም ቢል ሰውዬው ላይ ምን ይከተላል? ይሄስ እንዴት ነው ሪፖርት የሚደረገው? ባለስልጣናት በቅጣት ሊታጀብ የሚችል ማስገደድን እያከናወኑ አይደለምን? እኔ በጣም አሉታዊና የተፈጠረውን በጎ ውጤት ሊያቀጭጭ ይችላል የሚል ድምዳሜ ነው ያለኝ፡፡ ዘላቂነቱ መረጋገጥ ካለበት የተቋሙ በዲሞክራሲ ዙሪያ የሚታዩ እጥረቶች መታከም መቻል አለባቸው፡፡
ይህ አገር ሙሉ የሚያንቀሳቅስ ተቋም፣ በፀረ ዴሞክራሲ አሰራርና ባህል ከተተበተበ፣ ኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ኪሳራ ለመገመት የሚያስቸግር ቀውስ የሚፈጥር ነው፡፡
 ባጭሩ ተቋሙ ቀና ለሆነ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ተግባር እንዲውል ከተደረገ የዴሞክራታይዜሽን ሂደቱ ዋና መዋቅራዊ መሰረት ይሆናል፤ ምክንያቱም ከ80 ፐርሰንት በላይ የሚሆነው ህዝባችንን የሚያንቀሳቅስ ተቋም በመሆኑ ነው። በተቃራኒው ይህ ተቋም ወይም አደረጃጀት ከታለመለት አላማ አፈትልኮ፣ የጠባብ ፖለቲካዊ ፍላጎትና የቁጥጥርና ስለላ መዋቅር ተቀጥያ ከሆነ ግን የኢ-ዴሞክራታይዜሽን ሃይል ሆኖ ያርፈዋል፡፡
 ከአዘጋጁ፡- ይሄ የመጨረሻው የጽሁፉ ክፍል ለጋዜጣው በሚያመች መልኩ ኤዲት ተደርጎ የቀረበ ሲሆን በቦታ እጥረት ምክንያትም አንዳንድ ሃሳቦች መቀነሳቸውን ለውድ አንባቢያን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡
 








Read 6222 times